የአውሮፓ ማእከል ፲፮ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሔደ
ሐምሌ ፲፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
በአውሮፓ ማእከል
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል ፲፮ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ከሐምሌ ፩-፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በስዊድን አገር ስቶክሆልም ከተማ ተካሔደ።
በጠቅላላ ጉባኤው በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የሚኖሩ ከሰባ በላይ የማእከሉ አባላት፤ የዋናው ማእከልና የሰሜን አሜሪካ ማእከል ተወካዮች፤ እንደዚሁም ጥሪ የተደረገላቸው ካህናትና ምእመናን ተሳትፈዋል።
በስቶክሆልም መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በመልአከ ብርሃን አባ ገብረ ጊዮርጊስ ካሣዬና በአውሮፓ ማእከል ሰብሳቢ በቀሲስ ዶ/ር ያብባል ሙሉዓለም የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ተላልፏል።
“እስክመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ” /ራእ.፪፥፳፭/ በሚል ኃይለ ቃል በመምህር ፍቃዱ ሣህሌ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል።
የዋናው ማእከል መልእክትም በተወካዩ በአቶ ታምሩ ለጋ አማካይነት ለጉባኤው ቀርቧል።
በጉባኤው የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀምንና መንፈሳዊ ሕይወትን የሚዳስሱ ጥናቶች የቀረቡ ሲኾን፣ እንደዚህ ዓይነት ጥናቶች ለመንፈሳዊ ሕይወት መጠንከር ጠቃሚ በመኾናቸው ለወደፊቱም በተሻለና በተጠናከረ መልኩ እንዲቀርቡ የሚል አስተያየት በጉባኤው ተሳታፊዎች ተሰጥቷል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ “ልጆችን በቤተ ክርስቲያን በተቀናጀ መልኩ ለማስተማር የእኛ ድርሻ” በሚል ርእስ አጭር የግንዛቤ ማስጨበጫ ጽሑፍ በተተኪ ትውልድ ሥልጠና አገልግሎት ክፍል ቀርቧል።
በተጨማሪም የሰሜን አሜሪካ ማእከል ተወካይ አቶ ትእዛዙ ካሣ “የውጭ አገር የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት ተግዳሮቶችና ዕድሎች” በሚል ርእስ በውጭ አገር ያለውን የአገልግሎት ኹኔታና የማእከሉን ተሞክሮ የሚያስገነዝብ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡
የማእከሉ የ፳፻፰ ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ዘገባ ቀርቦ በጉባኤው ተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
የቀጣይ ስድስት ዓመት ስልታዊ ዕቅድ አቅጣጫዎችም በዋናው ማእከል ተወካይ በአቶ ታምሩ ለጋና በአውሮፓ ማእከል ምክትል ሰብሳቢ በዶ/ር ታጠቅ ፈቃዱ አማካይነት ለጉባኤው ቀርበዋል፡፡
ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ማእከሉን በሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩ አባላትም በአባቶች ጸሎት በዕጣ ተመርጠዋል፡፡ የኦዲት እና ኢንስፔክሽን ክፍል ሓላፊም በጉባኤው ተሰይሟል።
የ፳፻፱ ዓ.ም የማእከሉ እና ኦዲትና ኢንስፔክሽን ክፍል የአገልግሎት ዕቅድም ለጉባኤው ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ በምልዓተ ጉባኤው ጸድቋል፡፡
በመጨረሻም ለጉባኤው መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ ለመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ካህናት፣ ለስዊድን ንዑስ ማእከል አባላት፣ ለሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና ለአካባቢው ምእመናን የማእከሉ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ያብባል ሙሉዓለምና የጉባኤው አዘጋጅ ኰሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሳምሶን መለሰ ምስጋና ካቀረቡ በኋላ ጠቅላላ ጉባኤው በአባቶች ጸሎት ተጠናቋል።