የአትናቴዎስ ትምህርት ስለ መንፈስ ቅዱስ
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ
አባ ጎርጎርዮስ የሸዋ ሊቀ ጳጳስ /M.A/
አትናቴዎስ ስለ መንፈስ ቅዱስም በተናገረበት ባስተማረበት አንቀጽ መንፈስ ቅዱስ እንደ አብ እንደ ወልድ ከአብ ከወልድ ጋር ፍጹም አካል መኾኑን፣ በባሕርይ በህልውና አንድ መኾኑን ይናገራል፡፡ ከቅድስት ሥላሴ ሦስተኛው አካል መንፈስ ቅዱስ ሕጹጽ ፍጡር አይደለም፡፡ በብሉይ ኪዳን፣ በሐዲስ ኪዳን እንደ አብና እንደ ወልድ አምላካዊ ክብሩ ተነግሮለታልና፡፡ እነ አርዮስ እንደሚሉት መንፈስ ቅዱስ ፍጡር ቢኾን ኑሮ የፍጡራን ሕይወት ባልኾነም ነበር፤ እንዴትስ የእግዚአብሔርን ምሥጢር ለማወቅ ቻለ? /1ኛቆሮ.2÷10/ ወልድ ከአብ ጋር አንድ ባሕርይ እንደሆነ መንፈስ ቅዱስም ከአብና ከወልድ ጋር አንድ ባሕርይ ነው፡፡ ሦስቱ አካላት /ገጻት/ ባንድ ባሕርይ ባንድ ህላዌ ይኖራሉ፤ አብ በወልድ ቃልነት ዓለምን ፈጠረ፡፡ ሦስቱ አካላት አንድ አምላክ ነው፡፡ በምሥጢረ ሥላሴ ወይም በሦስቱ መካከል ባዕድ ባሕርይ የለምና፡፡
ወልድ ከአብ እንደ ተወለደ መንፈስ ቅዱስም ከአብ የሠረጸ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት ምሥጢር ገልጧል፤ ቋንቋ አናግሯል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ከበዓለ ጰንጠቆስጤ ጀምሮ የሚመራ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ በአትናቴዎስ ትምህርት የባሕርይና የህላዌ እንዲሁም የአካላት ልዩነት፣ በምሥጢረ ሥላሴ የሚነገሩ ባሕርይ፣ ህላዌ፣ ከዊን በእስክንድርያ ትምህርት ቤት ከአትናቴዎስ በኋላ ትክክለኛ ፍቻቸው እንደሚከተለው ነው፡፡ /ኡሲያ/ ህላዌ የሚለው ቃል በእስክንድርያ ትምህርት ቤት በነበረው የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት አካል ከባሕርይ ሳይለይ አንዱ ከሌላው ተለይቶ የሚታወቅበት ከዊን ማለት ነው፡፡ በአንጾኪያ ግን ይልቁንም ጳውሎስ ሳምሳጢና ተከታዮቹ «ህላዌ» የሚለውን ቃል በተሳሳተ አተረጓጐም በመተርጎም፤ ብዙዎቹን አሳስተዋል፡፡
ለምሳሌ «ዋሕደ ህላዌ» ማለት ሦስቱ አካላት አንዱ በአንዱ አድሮ የሚኖር ማለት ነው፤ ብለው ያስተምራሉ፡፡ እዚህ ላይ ወልድና መንፈስ ቅዱስ አካላዊና በከዊን የተለየ ህላዌ አልነበራቸውም ለማለት ጳውሎስ ሳምሳጢ ይመቸዋል፡፡ በሱ አስተሳሰብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በአብ ህልዋን ኹነው የሚያገለግሉ ዝርዋን እንጂ አካላውያን አይደሉምና፡፡ ስለዚህም በ260 ዓ.ም እሱን ለማውገዝ የተሰበሰቡ ሊቃውንት «ዋሕደ ህላዌ ምስለ አብ» ብሎ አትናቴዎስ ረትቶበታል፡፡ /አሞኡሲዮን ቶ፣ -ትረ/ ይህም የአትናቴዎስ አባባል ከጳውሎስ ሳምሳጢ ጋር ዝምድና የለውም፡፡ «ዋሕደ ባሕርይ» በማለት የባሕርዩን አንድነት «ምስለ አብ» አብ ማለት የአካልን ልዩነት ያሳያልና «ዋሕደ ህላዌ ምስለ አብ» በአንቀጸ ሃይማኖት «ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ» የምንለው ነው፡፡ እንግዲህ ህላዌ የሚለው ቃል፤ በምሥጢረ ሥላሴ አንዱ አካል በሌላው አድሮ ወይም ጥገኛ ኹኖ የማይኖር፣ ከሥላሴ አንዱም አንዱ፣ እያንዳንዱ አካል በአካሉ፣ በመልኩ፣ በገጹ ፍጹም መኾኑን ያሳያል፣ ያመለክታል፡፡ «ህቡረ ህላዌ ምስለ አበመለኮቱ፣ ኅቡረ ህላዌ ምስሌነ በትስብእቱ» /ተረፈ ቄርሎስ/
በሌላም ቦታ «ህላዌ» ከግብርና ከአካል ስም ጋር ተጣምሮ ይገኛል፤ ለአብ የወላዲነት ለወልድ የተወላዲነት፣ ለመንፈስ ቅዱስ የሠራጺነት ስሙ ነው፡፡ «እስመ አበዊነ ስመይዎን በዝንቱ ገጸ መካን ለህላዌያት አካላተ፤ አትናቴዎስኒ ረሰየ ህላዌ አሐደ አካለ ዘእግዚአብሔር ቃል ዘተሠገወ» እንዲል፡፡
ዳግመኛም ህላዌ አካልና ባሕርይ አንድ ኹነው የቆሙበት አስተጋባኢ ስም ስለሆነ ለአካልም ለባሕርይም ይነገራል፡፡ በአንቀጸ ተዋሕዶ ማለት የሦስቱን አንድነት በምንናገርበት ጊዜ አሐዱ ህላዌ እንላለን፡፡ መውለድና ማሥረጽ፣ መወለድና መሥረጽ በዚያው ባንድ ባሕርይ ውስጥ ነውና፡፡
ስለዚህ በምሥጢረ ሥላሴ ባሕርይ አይከፈልም፡፡ አካል አይቀላቀልምና፡፡ ህላዌ ግን ለአካልም ለባሕርይም መነገሩን ገልጠናል፡፡ ባሕርይ ምንጊዜም ቢኾን ለአካል አይነገርም፤ አካልም ለባሕርይ ስም አይኾነውም፣ አለዚያ ግን ባሕርይን መክፈል ስምና ግብርን ማፋለስ ይኾናል፡፡ ወላዲ ባሕርይ፣ ተወላዲ ባሕርይ፣ ሠራጺ ባሕርይ የማይባለውም ስለዚህ ነው፡፡ ከተባለ ግን ሦስት መለኮት፣ ዘጠኝ አካላት ወደ ማለት ይሸነሸናል፤ የምሥጢረ ሥላሴው የግብር ስም ለምሥጢረ ተዋሕዶው የባሕርይ ስም አይሰጥም፡፡ የሦስቱም አካላት መለኮት ወይም ባሕርይ አንድ ነው፡፡ «ሠለስቱ ገጻተ አሐዱ አምላክ» ብሎ ለማመንና ለማሳመን ይህን ኹሉ ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በላይ እንዳየነው በእስክንድርያ የትርጓሜ ትምህርት ቤት እነ አትናቴዎስ «ህላዌን» /ኡሲያን/ ለአካልም ለባሕርይም ሰጥተው ይናገራል፡፡ /ኩነት/ ከዊን ግን ለአካል ብቻ ነው /ኢስታሲስ/ በአንጾኪያ ግን «ህላዌን» /አሲያን/ ለባሕርይ ብቻ /ኩነትን/ ከዊንን /ኢስታሲስን/ ለአካል ብቻ ሰጥተው ይናገራሉ፤ በዚህኛው ልዩነት የለም፡፡