የአብነት ትምህርት ቤቶች ችግር አሳሳቢ መኾኑ ተገለጠ
ነሐሴ ፲፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
በይብረሁ ይጥና
ኹሉም ሕዝበ ክርስቲያን የድርሻውን ተወጥቶ የአብነት ትምህርት ቤቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማድረግ ካልተቻለ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለማስቀጠል አሳሳቢ መኾኑ ተገለጠ፡፡
በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት የሚገኙ የአብነት ት/ቤቶችን ጉዳይ በሚመለከት ሐምሌ ፳፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በዮድ አቢሲኒያ የምግብ አዳራሽ በተካሔደው ውይይት የአብነት ትምህርት ቤቶች ችግር ካልተቀረፈ ወደፊት የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን ማግኘት አስቸጋሪ ነው ተብሏል፡፡
በዕለቱ የሰሜንና ደቡብ ጎንደር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ እና የምዕራብና ደቡብ ምዕራብ አውሮፓ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሙሴ የአብነት ትምህርት ቤቶችን መከባከብ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ማስቀጠል መኾኑን በማስረዳት በመላው ዓለም የሚኖሩ ምእመናን በአንድነት ኾነው ለአብነት ት/ቤቶች መጠናከር የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የአብነት ትምህርት ቤቶችን ኹኔታ የሚዳስስ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ዶ/ር አበባው ምናዬ የአብነት ትምህርት ቤቶችን ምንነትና ያሉባቸውን የምግብ፣ የቁሳቁስና የአልባሳት እጥረት፣ ወዘተ. የመሳሰሉ ችግሮች በመጥቀስ ችግሮቹ በዚህ ከቀጠሉ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት እንደሚያደናቅፉ በጥናታቸው ጠቁመው የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብራትን ማዘጋጀትና የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን ማከናወን ከችግሮቹ መፍትሔዎች መካከል የሚጠቀሱ ተግባራት መኾናቸውን አመላክተዋል፡፡
የጥናቱ አወያይ ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ በበኩላቸው ‹‹ቤተ ክርስቲያን የምትጠበቀው ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ቀጣይነት ሲኖራቸው ነው፡፡ እስካሁን የት ነበርን ብሎ ወደ ኋላ ከማሰብ ይልቅ ዛሬም ጊዜው ገና ነውና በመላው የአገራችን ክፍሎች ለሚገኙ የአብነት ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ የኾነ ሥራ በመሥራት ዘለቄታዊ መፍትሔ ማምጣት ይኖርብናል›› ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የአብነት ትምህርት ቤቶች የሚረዱበትን ኹኔታ የሚያመቻች ሰባት አባላት የተካተቱበት ዐቢይ ኰሚቴ ከተዋቀረ በኋላ የውይይት መርሐ ግብሩ በበብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ጸሎት ተፈጽሟል፡፡