የአብነት መምህራን የምክክር ጉባኤ ሊካሄድ ነው፡፡
ጥር 29 ቀን 2006 ዓ.ም.
በታመነ ተ/ዮሐንስ
የማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የአብነት መምህራን የምክክር ጉባኤን ለሦስተኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሊያካሂድ ነው፡፡ መርሐ ግብሩ ከየካቲት 6 እስከ 9 ቀን 2006 ዓ.ም ለሦስት ተከታታይ ቀናት ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በመርሐ ግብሩ ይዳሰሳሉ ተብለው ከተያዙ አጀንዳዎች መካከል የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ነጻ የትምህርትና ሥልጠና ዕድል፣ የአብነት ት/ቤቶች የጤና ግንዛቤን ባካተተ እና ትርጓሜ መጻሕፍትን በተመለከተ በዋነኝነት የሚነሡ ርዕሰ ጉዳዮች ሲሆኑ፤ የአብነት ት/ቤቶች የምስክር አሰጣጥና የአገልግሎት ሁኔታ እና ሌሎች ተዛማጅ ርዕሰ ጉዳዮችም ይወሳሉ፡፡
ይህ ጉባኤ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት መርሐ ግብራት ለየት የሚያደርገውን የዋና ክፍሉ ዳይሬክተር ዲ/ን አእምሮ ሲገልጹ “የአሁኑ የምክክር ጉባኤ ለየት ባለመልኩ የሚያጠነጥነው ከሀገሪቷ የትምህርትና የጤና ፖሊሲ ጋር ተደጋጋፊነት ባለው መልኩ ሲሆን፤ ይህም በሀገር ልማት ላይ ያለንን ተሳትፎ የሚጨምር ነው፡፡” ብለዋል፡፡ አያይዘውም በዚህ በተያዘው ዕቅድ መሠረት መጓዝ ከተቻለ የአብነት ተማሪዎችን መደበኛ ትምህርት የመደገፍ ትልም ተጠናክሮ በመቀጠል የአንድ ለአንድ የትምህርት አሰጣጥን ከአንደኛ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ እስኪደርሱ ተግባራዊ ለማድረግ ያስችላል፤ በዚህም የአብነት ተማሪዎቹ በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ እንዲሆኑ እንደሚያግዛቸው አውስተዋል፡፡ በዚህም መሠረት የነገ የቤተ ክርስቲያን ተረካቢ የሆኑትን የአብነት ተማሪዎች መደገፍ አስፈላጊ መሆኑን አክለዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ከተለያዩ አኅጉረ ስብከቶች የተውጣጡ ከ200 በላይ የአብነት መምህራን የሚገኙ ሲሆን ለሦስት ተከታታይ ቀናት በግዮን ሆቴል፣ በቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣንና በስብሰባ ማእከል(6ኪሎ) ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ይካሂዷል፡፡ በዚህም መሠረት በስብሰባ ማእከል(6ኪሎ) የካቲት 9 ቀን 2006 ዓ.ም ከቀኑ ከ7፡30 ጀምሮ በሚከናወነው የመዝጊያ መርሐ ግብር ላይ ምእመናን በመታደም የበረከቱ ተሳታፊ ይሆኑ ዘንድ ሓላፊው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡