የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ አምላክ /ለሕፃናት/

ኅዳር 7 ቀን 2005 ዓ.ም.

በኪዳነማርያም


አባታችን አብርሃም እግዚአብሔርን በማያውቁ፣ ጣዖት በሚያመልኩ መንደር ውስጥ ይኖር ነበር፡፡ አባቱ ጣዖት እየቀረጸ የሚሸጥ ነበር፡፡ አንድ ቀን አባቱ ሸጠህ ና! ያለውን ጣዖት ከረሀቡ ያስታግሰው ዘንድ አብላኝ ብሎ ቢጠይቀው አልሰማህ አለው፡፡ የጠየቀውን አልመልስልህ ሲለው ሰባብሮ ጣለው፡፡ ወደ ሰማይ አንጋጦ ጨረቃን ጠየቃት አልመለሰችም፣ ፀሐይን ጠየቀ አልመለሰችም፡፡ ተስፋው ሲሟጠጥ አምላከ ፀሐይ ተናበበኒ (የፀሐይ አምላክ አናገረኝ) አለ፡፡ እግዚአብሔርም ሰማው ከዘመዶችህ ተለይተህ እኔ ወደ ማሳይህ ስፍራ ውጣ አለው፡፡ አባታችን አብርሃምም እንደታዘዘው በመፈጸሙ እግዚአብሔር ቃልኪዳን ገባለት፡፡ ዘርህን እንደ ምድር አሸዋ አበዛዋለሁ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ አለው፡፡ አብርሃምም ከሣራ ይስሐቅን ወለደ፣ ይስሐቅም ታዛዥ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አብርሃምን አንድያ ልጅህን ሠዋልኝ ባለው ጊዜ አብርሃም ታዘዘ፡፡ ልጁ ይስሐቅም አባቱን ታዘዘ፡፡ አምላክህን ከምታሳዝነው እኔንም ዓይን ዓይኔን እያየህ ከምትራራ በጀርባዬ ሠዋኝ ብሎ አባቱን አበረታው፡፡ እግዚአብሔርም የአብርሃምን እምነት የልጁን ታዛዥነት ዓይቶ በይስሐቅ ፋንታ ነጭ በግ በዕፀ ሳቤቅ አዘጋጅቶ እንዲሠዋ አደረገ፡፡ የበጉም ምሳሌ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

 

ይስሐቅም ለእግዚአብሔር ታማኝ ነበር ካደገ በኋላ ርብቃን አግብቶ መንታ ልጆችን ወለደ፡፡ የልጆቹ ስም ዔሳው እና ያዕቆብ ይባላሉ፡፡ እነዚህ ልጆች ገና በእናታቸው ማኅፀን እያሉ ይገፋፉ ነበር፡፡ ነገር ግን የበኩር (የመጀመሪያ) ልጅ ሆኖ የተወለደው ኤሳው ነበር፡፡ በሀገራቸው ልማድ የበኩር ልጅ መሆን የአባትን በረከት ምርቃት የሚያሰጥ ነበር፡፡ እነዚህ ልጆች ካደጉ በኋላ ዝንባሌአቸው የተለያየ ነበር፡፡ ዔሳው አደን የሚወድ ያዕቆብም በቤት ውስጥ እናቱን የሚላላክ ሆነው አደጉ፡፡ አንድ ቀን ኤሳው ከአደን ሲመለስ ምንም አልቀናውም ነበር፡፡ በጣም ተርቦ ወንድሙ ያዕቆብን ከሠራኸው የምስር ወጥ አብላኝ አለው፡፡ ያዕቆብም ብኩርናህን ስጠኝና ከሠራሁት አበላሀለው ብሎ ነፈገው፡፡ ዔሳውም ብኲርናዬ ረኀቤን ካላስታገሰችልኝ ለችግሬ ካልሆነችኝ ለኔ ምኔ ናት ብሎ አቃለላት፣ በምስር ወጥ ሸጣት፡፡ አባታቸው ይስሐቅ ስላረጀ ምርቃቱን፣ በረከቱን ሊያስተላልፍ የበኩር ልጁ ዔሳውን ጠርቶ እነሆ እኔ አረጀሁ የምሞትበትንም ቀን አላውቅም፤ ሳልሞት ነፍሴ እንድትባርክህ የምወደውን ምግብ ሠርተህ አብላኝ አለው፡፡ ይህን ሁሉ እናታቸው ርብቃ ተደብቃ ትሰማ ነበር፡፡  አብልጣ የምትወደው ያዕቆብን ነበርና የአባቱ ምርቃት እንዳያመልጠው የሰማችውን ሁሉ ነገረችው፡፡ አባትህ የሚወደውን ምግብ እኔ አዘጋጅልሀለው አለችው፤ አባቱ እርሱ ዔሳው እንዳልሆነ ቢያውቅበት በበረከት ፈንታ መርገም እንዳይደርስበት ያዕቆብ ፈራ፡፡ አባታችሁ በእርጅና ምክንያት ዓይኑ ስለተያዘ አንተንም በመዳበስ እንዳይለይህ እንደወንድምህ ሰውነት ጠጉራም እንድትመስል በበግ ለምድ ሸፍኜ መልካሙን የዔሳው ልብስ አለብስሀለው መርገሙም በእኔ ላይ ይሁን ብላ መከረችው፣  አደፋፈረችው፡፡ ያዕቆብ እናቱ ያዘጋጀችውን ምግብ ይዞ ገባ አባዬ ያልከኝን አዘጋጅቻለሁ፤ ብላ ነፍስህም ትባርከኝ አለው፡፡ አባቱም አንተ ማነህ? ብሎ ጠየቀ፡፡ እኔ የበኩር ልጅህ ዔሳው ነኝ ብሎ ዋሸ፡፡ እንዴት ፈጥነህ አገኘህ? አለው፡፡እርሱም እግዚአብሔር አምላክህ ወደ እኔ ስላቀረበው ነው፤ አለው፡፡

 

እጁንም ዳሰሰና ድምፅህ የያዕቆብን ጠረንህ ደግሞ የዔሳውን ይመስላል ብሎ ልጁ ያዕቆብ ካቀረበለት መአድ ተመግቦ ሲጨርስ የልጁን ጠረን አሸተተ፣ እግዚአብሔር ፈቅዷልና  “እግዚአብሔርም ከሰማይ ጠል ከምድርም ስብ የእህልንም የወይንንም ብዛት ይስጥኽ፤ አሕዛብ ይገዙልህ ሕዝብም ይስገዱልህ፤ ለወንድሞችህ ጌታ ኹን የእናትህም ልጆች ይስገዱልህ፤ የሚረግምህ እርሱ ርጉም ይሁን የሚባርክህም ቡሩክ ይሁን፡፡” ብሎባረከው፡፡ ዔሳው ከአደን ደክሞ ውሎ ለአባቱ የሚሆን ምግብ አዘጋጅቶ አባዬ ያልከኝን አዘጋጅቻለሁ፤ ብላ ነፍስህም ትባርከኝ ብሎ አገባለት፡፡ አባቱም አንተ ማነህ? አለው፡፡ እኔ የበኩር ልጅህ ዔሳው ነኝ አለ፡፡ አባቱም አሁን በረከቱን የወሰደው ዔሳው አይደለምን? ወይስ ምርቃትህን ታናሽህ ያዕቆብ አታሎ ወሰደብህ? አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ዔሳው በኀይል ጮኸ! መጀመሪያ ብኩርናዬን ቀጥሎ በረከቴን አታሎ ወሰደብኝ እያለ በጣም አዘነ፡፡ አባቱንም እንዲህ ብሎ ጠየቀው በረከትህ አንዲት ብቻ ናት? አባቱ ይሥሐቅም “እንሆ መኖሪያኽ ከምድር ስብ ከላይ ከሚገኝ ከሰማይም ጠል ይሆናል፤ በሰይፍህም ትኖራለህ ለወንድምህም ትገዛለህ፤  ነገር ግን በተቃወምኸው ጊዜ ቀንበሩን ከአንገትህ ትጥላለኽ።” አለው ዔሳውም ለእርሱ የተረፈችውን በረከት ተቀበለ፡፡ በያዕቆብም ቂም ይዞ በልቡ “ለአባቴ የልቅሶ ቀን ቀርቧል፣ ከዚያም በኋላ ወንድሜን ያዕቆብን እገድለዋለሁ!” አለ፡፡  ዔሳው የያዕቆብን ሕይወት ለማጥፋት እንደተነሳሳ እናታቸው ርብቃ በማወቋ ያዕቆብን ካደገበት ከኖረበት ቤት ወደ ካራን ምድር ወደ አጎቱ ላባ እንዲሰደድ መክራ ሸኘችው፡፡

 

በመጽሐፍ ቅዱስ በኦሪት ዘፍጥረት ላይ እንደምናነበው ያዕቆብም በእርጅናው ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ልጆቹ አብልጦ ይወደው የነበረውን ዮሴፍን ወንድሞቹ ሸጠውት ሳለ ነገር ግን ክፉ አውሬ በልቶታል ብለው ዋሹት፤ በዚህም ምክንያት ለልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ፡፡ ነገር ግን ዮሴፍ በተሰደደበት ቦታ ሁሉ እግዚአብሔር አብሮት ነበርና ኋላ ላይ ቤተሰቡ በረሀብ ምክንያት ተሰደው ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ ለቤተሰቡ መልካም አድርጓል፡፡

 

ልጆች ከዚህ ሁሉ የምንማረው፡-

  1. ለቤተሰቦቻችን በመታዘዛችን የበለጠ እንደሚወዱን፤

  2. እናትና አባትን ማክበር እንዳለብን፤

  3. የእግዚአብሔርን በረከት ለማግኘት መጣር እንዳለብን፤

  4. የተሰጠንን ብኩርና(ሃይማኖት) ማቃለል መናቅ እንደሌለብን፤

  5. መዋሸት የሚያመጣብን መከራ ሥጋ መከራ ነፍስ እንዳለ፤

  6. እግዚአብሔር የገባውን ቃል ኪዳን እንደማያጥፍ እንደማያስቀርብን፤

  7. እግዚአብሔር የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ አምላክ ተብሎ እንዲጠራ አላፈረባቸውምና በእነዚህ ደጋግ ቅዱሳን አባቶች ምልጃ መጠቀም እንዳለብን እንማራለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን፡፡