የአባ ማሩ ተረት /ለሕፃናት/

ግንቦት 7/2004 ዓ.ም.

በልያ አበበ

እንደምን አላችሁ ልጆች! እግዚአብሔር ይመስገን ደኅና ነን እንደምትሉ አልጠራጠርም፡፡ ዛሬ የምነግራችሁ ተረት ስለ አንበሳ፣ ጥንቸልና አሳማ ነው እሺ በጣም ጥሩ ልጆች ተረቱን ልንገራችሁ?  ግን እኮ ስለራሴ አላስተዋወኳችሁም፡፡ ስሜ አባ ማሩ ዘነበ ይባላል፡፡ ቁመቴ በጣም አጭር ነው፡፡ ፊቴ ደግሞ ልክ እንደ ብርቱካን ክብ ሆኖ ዓይኖቼ ትናንሽ ናቸው፡፡ ሁል ጊዜ የምለብሰው ነጭ ሱሪና ነጭ ሸሚዝ ነው፡፡ ከእጄ ነጭ ጭራ አይለይም፡፡ ለምን ነጭ ጭራ እንደምይዝ ታውቃላችሁ? በሰፈሬ የሚኖሩ እንደ እናንተ ያሉ ሕፃናት ወደ 12፡00 ሰዓት አካባቢ ፀሐይ ስትገባ ተሰብስበው ይመጡና “አባ ማሩ ዘነበ ተረት ይንገሩን?” እያሉ በዙሪያዬ ስብስብ ይላሉ፡፡ እኔም ልጆችን በጣም ስለምወዳቸው ትንሸን ወንበሬን ይዤ ከቤቴ እወጣና ከግቢያችን ካለው ሰፊ ሜዳ ቁጭ እላለሁ፡፡ ልጆችም በዙሪያዬ ይሰበሰባሉ እሳት እየሞቅን ተረቱን አጫውታቸዋለሁ ታዲያ ያን ጊዜ ትንኞች በአፌ ውስጥ እንዳይገቡ በነጩ ጭራዬ እከላከላቸዋለሁ፡፡ ስለራሴ ይኸን ያኽል ከነገርኳችሁ ወደ ተረቴ ልመለስ፡፡ ዝግጁ ናችሁ ልጆች? ጎበዞች፡፡

 

ተረት ተረት፤ “የመሠረት” አላችሁ፤ በአንድ ሰፊ ደን ውስጥ አንበሳ፣ ጥንቸልና አሳማ ይኖሩ ነበር፡፡ ከዕለታት በአንደኛው ቀን አንበሳው በጣም ስለራበው ምግብ ፍለጋ ከዋሻዋ ሲወጣ “እግዚአብሔር ሆይ ዛሬ በጣም ስለራበኝ እባክህን ምግብ ስጠኝ?” ብሎ ጸለየ፡፡ ጸሎቱን እንደጨረሰ ከፊት ለፊቱ ጥንቸልን ተመለከታት አንበሳውም “አምላኬ ሆይ ጸሎቴን ሰምተህ ምግብ እንድትሆነኝ ጥንቸልን ስላዘጋጀህልኝ አመሰግንሃለሁ” ብሎ አፉን ከፍቶ ዐይኑን አፍጥጦ ቆመ… ጥንቸልም አንበሳውን ስታይ በጣም ደነገጠችና “ወይኔ አምላኬ ይኼ አንበሳ በጣም ያስፈራል እባክህን የዛሬን ብቻ ከዚህ አንበሳ አፍ አውጣኝ” ብላ ጸለየች፡፡

 

አንበሳው፡- “እግዚአብሔር ሆይ አብላኝ” በማለት እየ ጸለየ ጥንቸሏም “እግዚአብሔር ሆይ ከዚህ አንበሳ አድነኝ” እያለች እየጸለየች ሁለቱም መሮጥ ጀመሩ፡፡ አንበሳው ከኋላ ሲያባርራት ጥንቸሏም ስትሮጥ አንድ ወንዝ አገኘች፡፡ ወንዙን ዘላ ስትሔድ ከወንዙ አጠገብ አንድ አሳማ በልቶ ጠጥቶ ጸሎት ሳያደርግ ተኝቶ ነበር፡፡ አንበሳውም ዞር ሲል የተኛ አሳማ ተመለከተ ወዲያው አንበሳው የተኛ አሳማ ከአጠገቤ እያለ ከጥንቸል ጋር ምን አሯሯጠኝ አለና ጥንቸሏን ትቶ አሳማውን በላ፡፡ ከዚያ በኋላ የጥንቸሏን መዳን የአንበሳውን መብላት የአሳማውን መበላት ያዩ አንድ ሽማግሌ

 

“ልብላም ያለ በላ፤ ልውጣም ያለ ወጣ ከመሐል የተኛ አሳማ ተበላ” ብለው ግጥም ገጠሙ ይባላል፡፡

 

ልጆች ከዚህ ታሪክ ምን ተማራችሁ? ጸሎት ከመጥፎ ነገር ያድናል ካላችሁ ትክክል ናችሁ፡፡ ስለዚህ እናንተም ምግብ ስትበሉ ማታ ስትተኙ ጠዋት ስትነሡ አባታችን ሆይ የሚለውን ጸሎት ከጸለያችሁ ከመጥፎ ነገር ትድናላችሁ እሺ፡፡

 

ለዛሬው ተረቴን ከዚህ አቆማለሁ በሌላ ጊዜ በሌላ ተረት እስክንገናኝ ድረስ ደኅና ሁኑ ልጆች፡፡