የአስቦት ገዳም በተረጋጋ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡
መጋቢት 20 ቀን 2004 ዓ.ም
በኢዮብ ሥዩም
በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት የማገኘው የአሰቦት ቅድስት ሥላሴና የአባ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ ገዳም ደን በአሁኑ ጊዜ በተረጋጋ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተገለጠ፡፡
ያነጋገርናቸው የገዳሙ አበምኔት አባ ተክለ ማርያም እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም የካቲት 20/2004 በገዳሙ ጥብቅ ደን ላይ የተነሣው እሳት ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል፡፡ እሳቱን አስነስተውታል ተብለው በሚጠረጠሩ ግለሰቦች ዳግሞ እንዳይነሣ ማስተማመኛ ባይኖርም ለአሁኑ ምንም ዓይነት የእሳት ሥጋት የለም ብለዋል፡፡
በቅርቡ በተለያዩ አካባቢዎች በሞባይል ስልክ የጽሑፍ መልእክት “የአሰቦት ሥላሴ አካባቢ ደን በድጋሚ ተቃጠለ ምን ይሻለናል” በሚል ርእስ እየተሰራጨ ያለው መልእክትም ሐሰት እንደሆነና ገዳሙን እንደማይመለከትም አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡
በገዳሙ ይዞታ የነበረውና በእሳት አደጋ የወደመውን ደን መልሶ ወደነበረበት ለመመለስና ገዳማውያኑን ለመርዳት በተለይ በማኅበረ ቅዱሳን በኩል እየተደረገ ያለውን ጥረት ያደነቁት አስተዳዳሪው በተለያየ ቦታ ያሉ ምእመናን ለገዳሙ እርዳታ እጃቸውን እንዲዘረጉም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የጽሑፍ መልእክቶችን መሰራጨት ተከትሎ ያነጋገርናቸው ምእመናንም እንደነዚህ ዓይነት የአሉባልታ ወሬዎችና ያልተጣሩ መረጃዎች በገዳማት ላይ እየተከሠቱ ላሉ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፉ ናቸው ብለዋል፡፡
በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአባ ሳሙኤል ዘወገግ የተመሠረተው የአሰቦት ገዳም በተደጋጋሚ እየደረሰበት ያለውን ችግር ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ ለማድረግ ማኅበረ ቅዱሳን ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ጥናት እያደረገ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡