የአሰቦት ገዳም ደን ቃጠሎ ሪፖርታዥ

መጋቢት 1/2004 ዓ.ም.


በእንዳለ ደምስስ

አይቴ ሀሎከ አምላከ አበዊነ? /የአባቶቻችን አምላክ ወዴት አለህ?/

የአሰቦት ቅድስት ሥላሴና የአባ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ ገዳም ደን በእሳት የተቃጠለ ሲሆን  ለማጥፋት በማኅበረ መነኮሳቱና ምዕመናን እንዲሁም በፌደራል ፖሊስና በኦሮሚያ ፖሊስ ከፍተኛ ጥረት ከአምስት ቀናት በኋላ ሊጠፋ ችሏል፡፡

 

የአሰቦት ገዳም በ13ኛው መቶ ክ/ዘመን በአባ ሳሙኤል ዘወገግ የተመሠረተ ሲሆን በ15ኛው መቶ ክ/ዘመን አህመድ ግራኝ አጠፋው፡፡ የገዳሙ መነኮሳትም ከሞት የተረፉት ተበታተኑ፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ለረጅም ዘመናት አገልግሎት መስጠት ያልቻለ ቢሆንም አንዳንድ መናንያን ወደቦታው በመሔድ በጸሎት ተወስነው ይኖሩ እንደነበር ይነገራል፡፡ በ1911 ዓ.ም. ንግስት ዘውዲቱ እንደገና ገዳሙ እንዲመሰረት አደረጉ፡፡

 

በ1928 ዓ.ም. የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን በመውረሩ ገዳሙን ለማጥፋት ጥረት አድርጎ ነበር፡፡ አፄ ኃ/ሥላሴ በ1936 ዓ.ም. በተጠናከረ ሁኔታ ገድመው፣ መተዳደሪያ፣ ርስት ጉልት ሰጥተውና ለመነኮሳት መኖሪያ አሰርተው በሥርዓት እንዲጠበቅ አደረጉ፡፡ ሣራ ማርያም አካባቢ / ከአሰቦት ገዳም በስተምዕራብ/ እስከ 300 ወታደሮች ተመድበው ገዳሙንና ደኑን ሲጠብቁ እንደነበር አበመኔቱ የታሪክ ማኅደርን ጠቅሰው ይገልጻሉ፡፡ በ1969 ዓ.ም. የሶማሊያ ጦር ኢትዮጵያን ለመውረር ያደረገውን ጥረት ተከትሎ ወታደሮቹ በመወሰዳቸው ገዳሙ አደጋ ስላንዣበበበት ከገዳሙ የተውጣጡ አራት መነኮሳት ብቻ በየቀኑ መጠበቅ ጀመሩ፡፡ አሁንም በዚህ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡

 

ለመሆኑ የእሳት ቃጠሎው መነሻው ምንድነው? እንዴትስ አለፈ?

 

የካቲት 20 ቀን

እንደ ገዳሙ አባቶች ገለጻ አራት የሚሆኑ ሰዎች የአሰቦት ቅድስት ሥላሴና የአባ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ ገዳም ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ሲሆን ማንነታቸው ያልታወቀ ዘራፊዎች ጥቅጥቅ ያለውን ጫካ ሰንጥቀው በመገሥገስ ላይ ናቸው፡፡ ከሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ጀርባ የገዳሙ 62 ከብቶችና 25 አህዮች ለግጦሽ ተሰማርተዋል፡፡ ወደ ገዳሙ እየቀረቡ የመጡት ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች ከብቶቹን ፍለጋ ጥቅጥቅ ያለው ደን ውስጥ ተሸጎጡ፡፡ ከዚያም ደኑ ሳይበግራቸው ከብቶቹን አግኝተው መንዳት ጀመሩ፡፡ የገዳሙ መነኮሳት እንዳይደርሱባቸውም በተጠንቀቅ ግራ ቀኝ እየተገላመጡ የሚመጣውን ኀይል ለመመከት በመዘጋጀት በጥድፊያ ከብቶቹን ነዷቸው፡፡

 

የገዳሙ ጥበቃ አባላት የእለቱ ተረኞች ሁለት ብቻ ሲሆኑ ከብቶቹ መነዳታቸውን በመረዳታቸው እየጮሁ ተከተሏቸው፡፡ ማኅበረ መነኮሳቱም ተሰባስበው ከብቶቹን ለማስጣል ተረባረቡ፡፡ ከብቶቹን ለመውሰድ የቋመጡት ዘራፊዎች እንዳልተሳካላቸው ሲረዱ ከብቶቹን ጥለው ፈረጠጡ፡፡ መነኮሳቱ ከብቶቻቸውን ይዘው ወደ ገዳማቸው በመመለስ አገር ሰላም ነው ብለው ጸሎት ላይ ተጠምደዋል፡፡

 

ድንገት ከአሰቦት ሥላሴ ገዳም በስተጀርባ ከሚገኘው ደን የተወሰኑ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የእሳት ጭላንጭል መታየት ጀመረ፡፡  ከብቶቹን ለመዝረፍ ያደረጉት ጥረት ያልተሳካላቸው  ደኑን በእሳት አያይዘው ጠፍተዋል፡፡ የደኑን መያያዝ ያስተዋሉት ማኅበረ መነኮሳት እሳቱን ለማጥፋት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀረ፡፡ እሳቱ ደኑን እየበላ ወደፊት ለፊት ወዳለው የተራራው ክፍል መቅረቡን ቀጠለ፡፡ ሌሊቱን ሙሉ መነኮሳቱና መነኮሳይያት ለማጥፋት ሳይቻላቸው ንጋቱ ተተካ፡፡ የደረሰላቸው ግን አልነበረም፡፡

 

የካቲት 21 ቀን

የገዳሙ ዋና መጋቢና ምክትል አበመኔት በሆኑት አባ ዘወልደ ማርያም አስተባባሪነት ለሚመለከታቸው ለሐገረ ስብከቱና ለወረዳው ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ፤ እንዲሁም ለማኅበረ ቅዱሳን የሜኤሶ ወረዳ ማዕከል አባላት ህዝበ ክርስቲያኑን እንዲቀሰቅሱ በመደወል አሳወቁ፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን የሜኤሶ ወረዳ ማእከል አባላት ከወረዳው ቤተ ክህነት ሓላፊዎች ጋር በመሆን ለሚመለከታቸው አካላት ለሐገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ፤ ለአሰበ ተፈሪ፣ ለድሬዳዋ፣ ለሐረር፣ ለአለማያ፤ ለበዴሳ፤ ለናዝሬትና ሌሎችም የማኅበረ ቅዱሳን ማእከላት በማሳወቅ ምእመናንን አስተባብረው እንዲመጡ ለማድረግ ጥረት ተደረገ፡፡ በሜኤሶ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያንና አጎራባች አብያተ ክርስቲያናት የአደጋ ጊዜ ጥሪ ደወል በማሰማት ለምእመናን ስለ ጉዳዩ ተገለጸ፡፡ ለፌዴራል ፖሊስ፤ ለኦሮሚያ ፓሊስ፣ ለሐገረስብከት ጽ/ቤት፣ ለወረዳ አስተዳደሮች ሁሉ ለማሳወቅ ጥረቶች ተደረጉ፡፡

 

የገዳሙ አበምኔት ከአሰቦት ከተማ እስከ ገዳሙ ያለውን የ18 ኪሎ ሜትር የመኪና መንገድ ለመሥራት የተቋቋመው የመንገድ ሥራ ኮሚቴ ለውይይት ባቀረበላቸው ጥሪ መሠረት አዲስ አበባ ነው የሚገኙት፡፡ የገዳሙ ደን በእሳት መያያዝ የሰሙት በ21/6/2004 ዓ.ም. ጠዋት ነው፡፡፡ ገዳሙ በዋና መጋቢና ም/አበምኔቱ አባ ዘወልደ ማርያም በመመራት ላይ ነው፡፡

 

ምእመናን ጀሪካን ከየቤታቸው በማሰባሰብ ውኃ ሞልተው ወንዶች በጭንቅላታቸው፤ ሴቶች በወገባቸው አዝለው የቤተ ክርስቲያንን ጥሪ ተቀብለው በእንባ እየተራጩ ከአሰቦት ከተማ እስከ ገዳሙ ያለውን የ18 ኪሎ ሜትር መንገድ መጓጓዣ ስለሌለ በእግር ጉዞ ተያያዙት፡፡

 

የሜኤሶ ከተማ ግብርና ጽ/ቤት የመኪና እርዳታ እንዲያደርጉ በመጠየቃቸው አንድ ፒክ አፕ መኪና በመስጠት ውኃዎቹ በጀሪካን እየተሞሉ ተጫኑ፡፡ 30 የሚደርሱ የመጀመሪያዎቹ ግብረ ኃይሎች በመኪናው ተሳፍረው ቦታው  ደርሰው በጀሪካን ውኃ እያፈሰሱ በቅጠል ለማጥፋት ጥረት አደረጉ፡፡ ከእሳቱ ፍጥነትና ከእሳት አጥፊው ማነስ ጋር ተዳምሮ የማይመጣጠን ሆነ፡፡ አካባቢዉ የሃዘን ቀጠና ሆነ፡፡ አቅመ ደካሞች መነኮሳትና መነኮሳይያት የአገር ሽማግሌዎች አንገታቸውን ቀና አድርገው ወደ ሰማይ በማንጋጠጥ በእንባ የታገዘ ጸሎት ከማድረስ ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡ እሳቱ እየገሰገሰ ነው፡፡

 

የሀገረ ስብከትና የየወረዳዎቹ ቤተ ክህነት ሓላፊዎች፤ የኦሮሚያ ፓሊስ ኃይል፤ የፌደራል ፖሊስ ልዩ ኃይል፤ በተለይም ወጣቶች፤ የየቤተ ክርስቲያኑ ሰ/ት/ቤቶች አባላት፤ ማኅበራትና ምእመናን እየገሰገሱ ነው፡፡ ገዳሙ ከተገደመ ጀምሮ ለ800 ዓመታት በግርማ ሞገሳቸው የሚታወቁት የዝግባ፣ የጥድ፣ የዋርካ፣ የወይራ ሰማይ ጠቀስ ዛፎች የእሳቱን ቃጠሎ መቋቋም ተስኗቸው በመገንደስ ላይ ናቸው፡፡

 

ሕዝበ ክርስቲያኑ እየወደቀ እየተነሣ ማጥፋቱን ተያይዞታል፡፡ እሳቱ በነፋሱ ታግዞ ይምዘገዘጋል፡፡ የዱር እንስሳትና አዕዋፍ የሚደርሱበት ጠፍቷቸው ይተራመሳሉ፡፡ ምእመናን ለማጥፋት ይሯሯጣሉ፡፡ የእሳቱ ነበልባል ከ10 ሜትር በላይ ከፍ ብሏል፡፡ እንደ ዘንዶ እየተጥመለመለ እየተወረወረ የሚወጣውን ፍለጋ ይወነጨፋል፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ የሚተመውን እሳት እያዩ  “አንቺ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከምትቃጠይ እግዚአብሔር እኛን ያስቀድመን፡፡ ጥፋትሽን አያሳየን” የሚሉ ምእመናን ያለ የሌለ ጉልበታቸውን በመጠቀም ጦርነት ከእሳቱ ጋር ገጥመዋል፡፡ እሳቱ ፍጥነቱን ጨመረ፡፡ ብርሃንም ለጨለማ እጇን ሰጠች፡፡ ክርሰቲያን ተስፋ አይቆርጥም አይደል? እሳቱ ቢያንስ ቤተ ክርስቲያኑንና የልማት ተቋማቱን እንዳይበላ ለመከላከል እየተፍጨረጨሩ ነው፡፡

 

አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከሦስት ጊዜ በላይ የእሳት አደጋ ተከስቷል፡፡ በራሳቸው ጥረት እሳቱን በቁጥጥር ስር አውለውት ነበር፡፡ የዛሬው ግን  የሚቻል አልሆነም፡፡

ምእመናን በጨለማው እየተሯሯጡ ጀሪካኖቻቸውን ተሸክመውና አዝለው የቻለ ለመነኮሳቱና ለምእመናን የሚሆን ስንቅ እየያዘ 18 ኪሎ ሜትሩን እየወደቁ እየተነሱ፣ ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እያነቡ ይከንፋሉ፡፡

 

እግዚአብሔር በአውሎና በወጀብ መካከል መንገድ አለው

እሳቱን በማጥፋት ሂደት ውስጥ እያሉ የካቲት 21 በግምት ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት አካባቢ አንድ አሳዛኝ ክስተት ተፈጠረ፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን የሜኤሶ ወረዳ ማእከል ሰብሳቢ ዲያቆን ዘውገ በቀለ እንደገለጹት እሳቱ 10 ሜትር ያህል ተምዘግዝጎ እየነጎደ በንፋሱ ታግዞ በቡድን በማጥፋት የነበሩ ወንድሞችና እኅቶችን ለሁለት ከፈላቸው፡፡ በመካከላቸው ታላቅ የእሳት ባሕር ተከሰተ፡፡ ነበልባሉ ገረፋቸው ራሳቸውን ለመከላከል ትግል ገጠሙ፡፡ ወደላይ የተከፈለው ቡድን እንደምንም አመለጠ፡፡ የታችኛው ቡድን 18 ወጣቶች ግን ዙሪያቸውን በእሳት ተከበቡ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ የሜኤሶ ወረዳ ማኅበረ ቅዱሳን አባላትና የሰ/ት/ቤት አባላት ነበሩ፡፡ ከእነሱም ውስጥ ደግሞ ሁለቱ ሴቶች ናቸው፡፡ ከላይ ያሉ ምእመናን ከለቅሶና ዋይታ ውጪ ምንም ማድረግ አልቻሉም፡፡ እሳቱ ጥርሱን አግጦ አፉን ከፍቶ እነሱንም ሊበላ በመጣደፍ ላይ ነው፡፡ “አይቴ ሀሎከ አምላከ አበዊነ?” የአባቶቻችን አምላክ ወዴት ነህ?  ከዚህ መዓት አውጣን?! በማለት ወደ እግዚአብሔር ጮሁ፣ ያድናቸው ዘንድ መማጸን ወይም በእሳቱ መበላት፡፡ እንደ ንሥር ክንፍ ኖሯቸው በረው አይወጡ ነገር እሳቱ አያስጠጋም፡፡ ተሰባስበው አንድ ነገር አደረጉ፡፡ የኅብረት ጸሎት ማድረግ፡፡ እንባና ለቅሶ ተደባለቀ፡፡ውዳሴ ማርያም ተጀመረ፡፡ በጸሎት ይተጋሉ፡፡ እሳቱ እየተምዘገዘገ ሊውጣቸው በመቅረብ ላይ ነው፡፡ ከላይ ዋይታና ለቅሶ ይሰማቸዋል፡፡ እነሱ ደግሞ ውዳሴ ማርያም በመድገም ላይ ተጠምደዋል፡፡ በዚህ ቅጽበት አሁንም አንድ እፎይታን የሚፈጥር ክስተት ተፈጠረ፡፡ ዞር ብለው ሲመለከቱ አጠገባቸው አነስተኛ ዋሻ አገኙ፡፡ ሁሉም ዘለው ዋሻው ውስጥ ገቡ፡፡ እሳቱ በአምስት ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ዋሻው እላዩ ላይ የእሳት ዝናብ እየወረደበት ነው፡፡ እሳቱን አመለጥን ሲሉ በጪሱ ደግሞ ታፈኑ፡፡

 

ውዳሴ ማርያም ጸሎቱ ቀጥሏል፡፡ እኩለ ሌሊት እየተቃረበ ቢሆንም እሳቱ እያየለ ወንድሞችና እኅቶችም በእሳቱ እንደተከበቡ ነው፡፡ ከላይ ነበልባል ከስር ፍምና ጪስ ብቻ፡፡ ከላይ ካሉትና እሳቱን በማጥፋት ላይ ከሚገኙት መካከል በትርፍ ጊዜያቸው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙ ሁለት የፌደራል ፖሊስ አባላት ከዚህ በላይ መታገስ አልቻሉም፡፡ በፌስታል የታሰረ ዳቦ ይዘው ብንሞትም ስለ ሃይማኖታችን እንሙት፡፡ እነዚህ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ሲሞቱ ዝም ብለን አንመለከትም” በማለት አንድ ወንድም አስከትለው ከሞቱ አጽማቸውን እንሰበስባለን፡፡ ካልሞቱም በሕይወት አብረን እንድናለን፡፡ ከሞትንም አብረን እንሞታለን፡፡ በማለት አፉን ከፍቶ ወደሚጠብቃቻው እሳት ውስጥ ተወርውረው ገቡ፡፡

assebot2

የእግዚአብሔር ተአምር ሆነና እየተንሸራተቱ እሳቱ ላይ እየተረማመዱ እየተለበለቡ ከወንድሞቻቸውና እኅቶቻቸው ጋር ዋሻው ውስጥ ተቀላቀሉ፡፡ አልሞቱም ተቃቅፈው በእንባ ተራጩ፡፡ በድካምና በረሃብ የደከመ ሰውነታቸውን ያጠነክሩ ዘንድ የያዙትን ዳቦ ሰጧቸው፡፡ መዝሙር ይዘመራል፣ እሳቱ ደግሞ ይቀርባል፡፡ መውጫ ቀዳዳ ሁሉ ተደፍኗል፡፡ ከሞት ጋር ተፋጠዋል፡፡ ራሳቸውን ለአምላካቸው ከመስጠት ውጪ ምንም ምርጫ አልነበራቸውም፡፡ ሰለስቱ ደቂቅን ያዳነ አምላክ እንዲያድናቸው ይማጸናሉ፡፡ ባያድናቸውም ስለ ሐይማኖታቸውም እንኳን ለመሞት ቆርጠዋል፡፡ ዝማሬው ግን ቀጥሏል፡፡ “አድኝኝ እናቴ ከስጋ ፈተና….” በዝማሬው መካከል አንዱ በጭንቀት እንደ ተዋጠ አንድ ነገር ትዝ አለው፡፡ ከነኀጢያቴ ልሞት ነው ማለት ነው? ከመሞቴ በፊት የንስሐ አባቴ ጋር መደወል አለብኝ” በማለት ስልኩን ደወለ፡፡ “አባቴ በእሳት ተከበናል፤ እኔና ጓደኞቼ መሞታችን ነው፤ እባክዎ ከመሞታችን በፊት ይፍቱን!” ያቀረበው ጥያቄ ነበር፡፡ የተደናገጡት አባት፡፡” “አይዟችሁ፡፡ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን፤ ሁላችሁንም እግዚአብሔር ይፍታችሁ!” አሏቸው የመረጋጋ ስሜት ውስጡ ተፈጠረ፡፡ በእሳት ውስጥ ከተከበቡት መካካል አንዱ የማኅበረ ቅዱሳን የሜኤሶ ወረዳ ማእከል ሰብሳቢ ዲ/ን ዘውገ በቀለ ሲሆን ስለሁኔታው ሲገልጽ ” በሕይወትና በሞት መካከል ሆነን ምንም ማድረግ ሳንችል ቀርተን በጣም ያዘንኩት የእኛ መሞት ሳይሆን በዝምታ ተውጠን ተራራው በእሳት ሲበላ ፤ከአባቶቻችን  ለትውልድ የተላለፈ ማንነትና ቅርስ ሲናድ ማየቴ ነበር ያስለቀሰኝ” በማለት ነበር የገለጸው፡፡ ሊነጋ ሲል ደግሞ እግዚአብሔር ከንጋቱ ጋር ተገለጠ፡፡ እሳቱ በአንደኛው አቅጣጫ ነፋስ ወደታች ገፍቶት ጠፋ፡፡ ነገር ግን ፍሙን መርገጥ ስለማይችሉ ጥቂት መጠበቅ ነበረባቸው ታግሰው ቆዩ፡፡ ምንም እንዳልተፈጠረ በመቁጠር፤ ከሞት ጋር ግብግብ የፈጠሩበትን ሁሉ ረስተው የሚቃጠለውን ደን ለማጥፋት ፈጠኑ፡፡

 

የካቲት 22 ቀን

የገዳሙ አበምኔት አዲስ አበባ የሔዱበትን ጉዳይ ሳይጨርሱ ወደ ገዳሙ ተመለሱ፡፡ እሳቱን የማጥፋት ተግባር ቀጥሏል፡፡ ከሐረር፣ ከድሬዳዋ፣ ከአለማያና ከናዝሬት ምእመናን እየጎረፉ ነው፡፡  እሳቱን ለማጥፋት ውኃው በእጅ ይረጫል በቅጠል ይቀጠቀጣል፡፡  እሳቱ ተራራውን ጨርሶ ጫፍ ላይ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ እየገሰገሰ ነው፡፡ ከመነኮሳት መኖሪያ የ50 ሜትር ርቀት ብቻ ቀርቶታል፡፡ ባሕታዊ መርአዊ /መነኮሳቱ አይዋ መርኣዊ ይሏቸዋል/ የ80 ዓመት አዛውንት ናቸው፡፡ ከዐርባ ዓመታት በላይ በገዳሙ ውስጥ ኖረዋል፡፡ እሳቱ ከበአታቸው ጋር ፊት ለፊት ተፋጠዋል፡፡ የ50 ሜትር ርቀት ላይ አባ ዘወልደ ማርያም እቃቸውን እንዲወጣ ቢጠይቋቸው አሻፈረኝ አሉ፡፡ “የኔን በአት እግዚአብሔር አያቃጥለውም” በማለት ጸኑ፡፡ በጀሪካን ጸበል ይዘው በመሔድ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ በማለት ሦስት ጊዜ ረጩት፡፡ እሳቱ ተጥመልምሎ ወደ ምዕራብ ዞረ፡፡ እግዚአብሔር ተአምራቱን ገለጠ፡፡ የመነኮሳቱ ቤቶችም ከመቃጠል ዳኑ፡፡

 

assebot3እሳቱ ተራራውን አገባዶታል፡፡ በልምላሜ ግርማ ሞገስ ተውቦ የሀገር ሀብት፣ የብርቅዬ የዲር እንስሳት አእዋፍ የመናንያንና የተሰወሩ አባቶች መኖሪያ ያ አሰቦት ተራራ እርቃኑን ቀርቷል፡፡ ድንጋዩ ገጦ ባዶውን ተጋልጧል፡፡ ጥቁር የሃዘን ልብስ ለብሷል፡፡ ከሰዓት በኋላ ጋብ ለማለት ሞከረ፡፡ ምእመናን ዝለዋል፤ አቅማቸው ተሟጧል፡፡ እሳቱም አብሮ ተዳከመ፡፡ ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ሲሆን እሳቱም ምእመናንና ማኅበረ መነኮሳቱ የእፎይታን አየር ተነፈሱ፡፡ እሳቱ ቢጠፋም ፍሙ ሙሉ ለሙሉ ባለመጥፋቱ ደግሞ ሊቀሰቀስ ይችላል የሚለው ሥጋት የሁሉም ቢሆንም ምእመናን በተከሰተው ነገር እያዘኑና እያለቀሱ ወደ መጡበት መመለስ ግድ ሆነ፡፡ የሜኤሶ ወረዳ የማኅበረ ቅዱሳን አባላትና የወረዳው ቤተ ክህነት ጸሓፊና ሌሎችም ከመነኮሳቱ ጋር በመነጋገር ለማደር ወሰኑ፡፡

 

የካቲት 23 ቀን

እሳቱ በመጥፋቱ ቀኑን ሙሉ ለሚመለከታቸው አካላት በስልክ በማሳወቅ የጥበቃው ሁኔታ እንዲጠናከር ለማድረግ አቤቱታ በማቅረብ ተዋለ፡፡ መነኮሳቱም በመሰባሰብ ወደፊት በገዳሙ ሕልውና ዙሪያ ምን ማድረግ እንዳለባቸው በመመካከር ነው ያለፈው፡፡ የገዳሙ ግርማ ሞገስ የነበረው በሺዎች ሄክታር የሚገመተው ደን ወድሟል፡፡ የቀረው በአባ ሳሙኤል ገዳም በኩል ያለው ደን ብቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በመጋቢት 2000 ዓ.ም. ደግሞ 11,000 /አስራ አንድ ሺህ/ ሄክታር ደን መቃጠሉ ይታወሳል፡፡

 

አመሻሽ ላይ የማኅበረ ቅዱሳን አባላትና የወረዳው ቤተ ክህነት ጸሓፊን ጨምሮ ሁላችንም ከአባቶች ቡራኬ ተቀብለን ጉዟችንን ወደ ሜኤሶ ለማድረግ ወስነን ተሰናብተን፡፡ 6 ኪሎ ሜትር ቁልቁለቱን ተያያዝነው ከምሽቱ አንድ ሰዓት ሲሆን ቁልቁለቱን እንደጨረስን ቀና ብለን ወደ ተራራው ተመለከትን፡፡ በልምላሜና በሰንሰለታማነት የሚታወቀው ሰማይ ጠቀሱ ተራራ፤ የገዳማውያን አባቶች መኖሪያ ፤ ጤዛ ልሰው ድንጋይ ተንተርሰው ዳዋ ለብሰው ግርማ ለሊቱን ድምጸ አራዊቱን ጸበ አጋንንቱን ታግሰው ለሃገር ለወገን  የሚጸልዩበት ደንና ዋሻ በከፊል ወድሟል፡፡

 

አንገታችንን ወደ ላይ እንዳቀናን እንባችን ፈሰሰ፡፡  መልሰን ደግሞ ወደ አባ ሳሙኤል ገዳም ተመለከትን፡፡ ከተወሰኑ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ አዲስ የደን ቃጠሎ መከሰቱን ተመለከትን፡፡ በዚያች ቅጽበትና ሰዓት የተለኮሰ ነው፡፡ እሳቱ ገና መጀመሩ ነው፡፡ እኛ ካለንበት ቢያንስ የ3 ሰዓት መንገድ ሊያስኬድ የሚችል ነው፡፡ በስልክ ለአበምኔቱ አሳውቀን ሕዝቡን የመቀስቀስ ሥራ ተጀመረ፡፡ በምሽት መሔዱ አደጋ ስለሚያስከትል ያለው ምርጫ እስኪነጋ መጠበቅ ነው፡፡ እሳቱም ባለበት ቆሞ አይጠብቅ ያገኘውን እያጨደ እየሰለቀጠ መጓዙን ይቀጥላል፡፡ ምን ምርጫ አለን?! እሳቱ ወደ ለአባ ሳሙኤል ገዳም  መነኮሳይያት መንደር ተምዘገዘገ፡፡

 

የካቲት 24 ቀን

መረጃው የደረሳቸው ምእመናን፣ የፌዴራል ፖሊስና የኦሮሚያ ፖሊስ በመሰብሰብ በሌሊት ጉዞ ተጀመረ፡፡ ቦታው ሲደረስ ግን ያጋጠመው ችግር የከፋ ነበር፡፡  ማንነታቸው ያልታወቀ ግለሰቦች በምእመናንና በፌደራል ፖሊስ ላይ የተኩስ እሩምታ ከፈቱ፡፡ በቦታውም ብፁዕ አቡነ ዳንኤል የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ከቅዱስ ፓትርያርኩ የተላኩ ልኡካን በተገኙበት የፌደራል ፖሊስ በወሰደው እርምጃ ተኩስ የከፈቱ ታጣቂዎችን ከአካባቢው ማራቅ በመቻሉ እሳቱን ለማጥፋት ጥረቱ ቀጠለ፡፡ ወደ የቤቱ ተበታትኖ የነበረው ማኅበረ ምእመናን ጀሪካናቸውን ውኃ ሞልተው ለማጥፋት ተፋጠኑ፡፡ አመሻሽ ላይ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡

 

ማኅበረ መነኮሳቱ ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ከፌደራል ፖሊስ ተወካዮችና ባለሥልጣናት ጋር በጥበቃ ዙሪያ ውይይት የተካሔደ ሲሆን በፌደራል ደረጀ መፍትሔ እንደሚሰጥ ለመነኮሳቱ ተገልጾላቸዋል፡፡

 

ብፁዕ አቡነ ዳንኤል የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመነኮሳቱ ከመንግሥት የጥበቃ ኀይል እንዲመደብላቸው ለጠየቁት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ “በተከሰተው ቃጠሎ አዝኛለሁ ለቅዱስ ፖትርያርኩ ስለ ጉዳዩ አሳውቃለሁ፡፡ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሔ ይሰጥበታል” በማለት ማኅበረ መነኮሳቱንና ምእመናንን አጽናንተዋል፡፡

 

assebot1የገዳሙ አበምኔት ከዚህ በፊት ስለተከሰተው የደን ቃጠሎ ሲገልጹም በ2000 ዓ.ም. በተመሳሳይ ሁኔታ ከፍተኛ መጠን ያለው ደን በእሳት ቃጠሎ እንደወደመ በማስታወስ “ደኑን ለመጠበቅ ከመንግሥት ጥበቃ እንዲመደብልን በተደጋጋሚ አሳውቀናል፡፡ ደኑ የገዳሙ ብቻ ሳይሆን የሐገር ሀብት ነው፡፡ በረሃማነትን ለመከላከል መንግሥት ጥረት እያደረገ ባለበት ሁኔታ ውስጥ እንዲህ አስከፊ የደን ውድመት መድረሱ አሳዝኖኛል” ብለዋል፡፡ ስጋቱ ግን አሁንም ቀጥሏል፡፡

 

በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው ቃጠሎ መንስኤዎች ሁለት እንደሆኑ ማኅበረ መነኮሳቱ ይገልጻሉ፡፡ አንደኛው በዋነኛነት አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ከብቶቻቸውን ሳር ለማብላት በሚል የገዳሙን ክልል ጥሰው መግባትና የገዳሙን ከብቶች በየጊዜው ለመዝረፍ መሞከራቸው ነው፡፡ ካልተሳካላቸው ደኑ ላይ እሳት ለቀውበት ይጠፋሉ፡፡ በተደጋጋሚ ከብቶችን የዘረፉ ሲሆን ጉዳዩ በሽምግልና እየተያዘ ለመስተዳደር አካላት አቤቱታ በማቅረብ የማስመለስ ሒደት ነው ያለው፡፡ አልፎ አልፎም እያስቀሩባቸው እንደሆነ በሃዘን ተውጠው መነኮሳቱ ይገለጻሉ፡፡ አሁንም በስጋት ውስጥ ይገኛሉ፡፡

 

ሁለተኛው ደግሞ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ በምሽት ተደብቀው ዛፍ እየቆረጡ በመውሰድ መተዳደሪያ ያደረጉ ሕገ ወጥ ዛፍ ቆራጮች ከጊዜ ወደጊዜ ቁጥራቸው መጨመሩ ሌላው ስጋታቸው ነው፡፡ ቀን ስለሚደርስባቸው ጨለማን ተገን በማድረግ በቡድን ወደገዳሙ ክልል በመግባት፣ እንዲታያቸው እሳት በማቀጣጠል ዛፎችን ይጨፈጭፋሉ፡፡ እሳቱን ሳያጠፉት ይሔዳሉ፡፡ ቃጠሎም ይቀሰቀሳል፡፡

 

በገዳሙ ውስጥ የመነኮሳት መኖሪያ በቅድስት ሥላሴ ገዳም ዙሪያ ሲሆን የመነኮሳይያት መኖሪያ ደግሞ ገዳሙን በመሠረቱት በአባ ሳሙኤል ዘወገግ ገዳም ዙሪያ ነው፡፡ 50 መነኮሳት፣ 25 መነኮሳይያት፣ መናንያን ባህታውያን የአብነት ተማሪዎችን ጨምሮ 170 የሚሆኑት በገዳሙ ውስጥ ይኖራሉ፡፡

 

የገዳሙ አበምኔት አባ ተክለ ማርያምና የገዳሙ ማኅበረ መነኮሳት እሳቱን በማጥፋት የተባበሩትን ሁሉ በእግዚአብሔር ስም አመስግነዋል፡፡ ለመሆኑ ለገዳሙ ደህንነት ማነው ኃላፊነቱን የሚወስደው? “ ዲያብሎስ ቀስቱን ጨረሰ ዝናሩንም አራገፈ ቤተ ክርስቲያንን ግን ሊያጠፋት አልቻለም” እንዳለው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቅድስት ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ደም ላይ ተመስርታለችና ከቶ የሲኦል ደጆች ሊያነዋውጧት አይችሉም!!!