የነነዌ ህዝቦች (ለህጻናት)
በአንድ ወቅት ስሙ ዮናስ የተባለ ሰው ነበር፡፡ ከእለታት አንድ ቀን እግዚአብሔር አምላክ ለዮናስ እንዲህ አለው፡፡ «ወደ ነነዌ ከተማ ሂድ ለሕዝቡም በምትሰሩት የኃጢዓት ሥራ በጣም አዘኜባችኋለሁ፡፡ ይኼንን የምትሠሩትን ሥራ ካላቆማችሁ ከተማዋን አጠፋታለሁ» ብለህ ንገራቸው አለው፡፡ ነገር ግን ዮናስ እግዚአብሔር ያዘዘውን ማድረግ አልፈለገም፤ እየሮጠ ማምለጥ እና ከእግዚአብሔር መደበቅ ፈለገ ስለዚህም ዮናስ ከነነዌ ከተማ በተቃራኒው ወደ ምትገኘው አገር በመርከብ መሔድ ጀመረ፡፡
እግዚአብሔርም በባሕሩ ላይ ኃይለኛ ነፋስን አመጣ መርከቧም ከአንድ ጎን ወደ ሌላ ጎን፤ ከላይ ወደ ታች እያለች አቅጣጫዋን ጠብቃ መሔድ አቃታት፤ ውኃውም ወደ መርከቧ ውስጥ መግባት ጀመረ፡፡
በመርከቧ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ሁሉ በጣም ፈሩ፤ መርከቧም ትሰጥማለች ብለው በጣም ተጨነቁ ሁሉም ሰዎች በከባድ ጭንቀት ላይ ሆነው እግዚአብሔር አምላክ ይኸንን ታላቅ ንፋስ የላከብን ምን መጥፎ ነገር ሰርተን ነው ብለው መጨነቅ ጀመሩ፡፡
ይኼ ሁሉ ነገር ሲሆን ግን ዮናስ እንቅልፍ ወስዶት ነበር፡፡ የመርከቧም አለቃ ወደ ዮናስ ሔዶ ቀሰቀሰው፡፡ «ይህን ከባድ የሆነ ንፋስ ያቆምልን ዘንድ ለአምላክህ ፀልይልን» አለው፡፡
ዮናስም ይህን ሲሠማ ለመርከቧ አለቃ ይህ ነገር የመጣው በእኔ ይሆናል ከአምላክ ለመደበቅ እየሞከርኩ ነበር እኔን አንስታችሁ ወደ ውኃው ብትጥሉኝ ንፋሱ እና የመርከቧ መናወጥ ሊያቆም ይችላል አላቸው፡፡ በመርከቧም የነበሩ ሰዎች ዮናስ እንደነገራቸው አደረጉ፡፡ ወደ ባህሩ ወረወሩት፡፡ ወዲያውም ባህሩ ፀጥ አለ፡፡ ንፋሱም ቆመ፡፡
እግዚአብሔር አምላክም ዮናስን የሚውጠው ትልቅ አሳን አዘጋጀ፡፡ ዮናስም በአሳው ሆድ ውስጥ ሦስት ቀን ቆየ፡፡ በአሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ሆኖ ፀለየ እግዚአብሔርን እንዲረዳው ለመነ፡፡ እግዚአብሔርም የለመኑትን መልካም ነገር ቶሎ የሚሰማ ስለሆነ ፀሎቱን ሰማውና አሳውን ደረቅ መሬት ላይ እንዲተፋው አዘዘው፡፡ ትልቁም አሣ በፍጥነት ትዕዛዙን ተቀብሎ በመሬት ላይ ተፋው፡፡
ዮናስም ምንም ሳይሆን ከትልቁ አሳ ውስጥ ስለወጣ አምላኩን አመሠገነ ወደ ተላከበትም አገር ወደ ነነዌ ወዲያውኑ ሄደ፡፡ ወደከተማዋ እንደገባ ድመፁን ከፍ አድርጎ ለህዝቡ «እግዚአብሔር በናንተ በጣም ተከፈቶባችኋል ምክንያቱም ከክፋ ሥራችሁ የተነሣ ነው፡፡» የነነዌ ህዝቦች ይዋሻሉ፣ ይምላሉ፣ ይሰርቃሉ፣ ሌላም ብዙ መጥፎ ነገር ያደርጉ ነበር፡፡ ዮናስም ከዚህ መጥፎ ሥራችሁ ካልተመለሳችሁ አገራችሁ ይጠፋል ብሏል እግዚአብሔር ብሎ ነገራቸው፡፡ የነነዌ ሰዎችም ይህንን ሲሰሙ በጣም ተጨነቁ፤ የሚሠሩትንም ክፋ ሥራ ትተው እግዚአብሔርን የሚያስደስት ነገር በመስራት ጥሩ ሰው መሆን ፈለጉ፡፡ ስለዚህም ምንም ምግብ ሳይበሉ እና ሳይጠጡ ለሦስት ቀናት ያህል ፆሙ፡፡ ሁሉንም መጥፎ ነገር መሥራት አቆሙ፡፡ መጥፎ ሥራቸውንም ሰውን በመውደድ፣ ታዛዥ በመሆን በመልካም ሥራ ቀየሩት፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ጥሩ ሰዎች መሆናቸውን ሲያይ እጅግ በጣም ተደሰተባቸው ከተማቸውንም አላጠፋባቸውም ብሎ ወሰነ፡፡
አያችሁ ልጆች እግዚአብሔር አድርጉ ያለንን ሁሉ ማድረግ አለብን በአደጋና በአስቸጋሪ ቦታ ላይ ስንሆንም ፀሎት ማድረግ አለብን ይሔን ካደረግን እግዚአብሔር ይጠብቀናል፡፡
ልጆች እግዚአብሔር አምላካችን እኛ ከመጥፎ ሥራችን ተቀይረን ጥሩ ሰዎች እንድንሆን ሁል ጊዜ ይፈልጋል እና ጥሩ ሰዎች ለመሆን ጥረት እናድርግ እሺ ልጆች፡፡
ደህና ሰንብቱ!!