የኅዳር ጽዮን በዓል አከባበር ዛሬም ቀጥሎ በድምቀት ተከብሯል።
ዲ/ን አሉላ መብራቱና በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ
ኅዳር 20 ቀን ከዋዜማው ጀምሮ መከበር የጀመረው የኅዳር ጽዮን በዓል ዛሬም ቀጥሎ በድምቀት ተከብሮ ውሏል።
ከትናንትና ማታ 2፡00 ደወል ከተደወለበት ጀምሮ፥ ሊቃውንት ካህናትና ዲያቆናት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በስብሐተ ማኅሌት በማድረስ ሌሊቱን አሳልፈዋል።
ሥርዓተ ማኅሌት እንዳለቀ ዛሬ ጠዋት 1፡00 ዑደተ ታቦት ተጀምሯል። ሁለት ዓይነት ዑደት የተካሄደ ሲሆን የመጀመሪያው ዑደት በሐውልት አደባባይ ተደርጓል። በዚያም የአክሱም ሊቃውንትና የሰ/ት/ቤት መዘምራን የክብረ በዓሉን ዝማሬ አቅርበዋል። በቦታው ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፥ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል።
ሁለተኛው ዑደት ቅዱስ ያሬድ የአርያም ዜማውን ባሰማበት በሙራደ ቃል ተከናውኗል። በዚህኛው ዑደት፥ ቅዱስነታቸው አቡነ ጳውሎስ ሠፋ ያለ ትምህርተ ወንጌል በሁለት ቋንቋ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ሰጥተዋል። የማዕከላዊ ትግራይ አክሱም ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሰላማ በዓሉን በተመለከተ አጠር ያለ መግለጫ ሠጥተዋል። በቅዱስነታቸው ጋባዥነት ብፁዕ አቡነ ኤልሣዕ ተጨማሪ ትምህርት ያስተማሩ ሲሆን የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ በበኩላቸው እለቱን አስመልክተው በንባብ ንግግር አሰምተዋል።
ሥርዓተ ቅዳሴ የተጀመረው ከቀኑ 6፡20 ነበር። በእለቱ ሠራየ ዲያቆን ሆኖ የቀደሱትና ከማኅበረ ቅዱሳን የአማርኛ መካነ ድር ጋር የስልክ ቆይታ ያደረጉት መ/ር ፍስሐ ጽዮን ደሞዝ እንደገለጹልን፥ በብፁዕ አቡነ ገሪማ፥ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስና በብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስ የተመራው የቅዳሴ ሥርዓት በ3 መንበር የተከናወነ ሲሆን፥ ሥርዓተ ቁርባኑ በእያንዳንዳቸው በ3 አቅጣጫ በአጠቃላይ በ9 ሙሉ ቀዳሽ ተከናውኗል። የቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የጠጠር መጣያ ቦታ እስከሚታጣ ሙሉ ነበር።
እንደ መ/ር ፍስሐ ጽዮን ገለጻ፥ እርሳቸው በቀደሱበት በዋናው የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበሩት መላው ምእመናን የቅዱስ ሥጋውና የክቡር ደሙ ተሳታፊ መሆናቸው ልዩ ድባብ ፈጥሯል። በአጠቃላይ ለምእመናን ቅዱስ ቁርባን ለማቀበል ብቻ ወደ አንድ ሰአት የሚጠጋ ክፍለ ጊዜ እንደወሰደ አያይዘው ገልጸውልናል።
ከዋዜማው ጀምሮ በ100,000ዎች ለሚገመቱ ምእመናን በአራቱም አቅጣጫ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሲስጥ ውሏል።
/ከትናንት ጀምሮ መረጃዎችን ሲያደርሱን ለነበሩና ለተባበሩን ለንቡረ እድ በላይ መረሳ፣ ለመ/ር ፍስሐ ጽዮን ደሞዝና ለመ/ር ዲበኩሉ ልሳነ ወርቅ በእግዚአብሔር ስም ምስጋናችንን እያቀረብን ጥንቅራችን በዚህ እንቋጫለን/