«የተራቡትን ከበረከቱ አጠገባቸው» /ሉቃ. ፩፥፶፫/
በረቂቅ መቻል
በፍጡራን አንደበት ተነግሮ ስለማያልቅ ክብሯና ልዕልናዋ ክብር ምስጋና ይድረሳትና ይህንን ኀይለ ቃል የተናገረችው አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ክብርት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። ወንጌላዊው ሉቃስ በወንጌሉ ጸሎተ እግዝእትነ ማርያምን እንደ ጻፈልን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ብዙ ኀይለ ቃላት ያላቸውን ምሥጢራት በዚህ ክፍል ተናግራለች። ይህ የተናገረችው ኀይለ ቃል በውስጡ ብዙ መንፈሳዊ፣ ሰማያዊ ትርጉም አለው። ምልእተ ጸጋ፣ምልእተ ውዳሴ፣ምልእተ ክብር የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ የጸሎት ክፍል ከተናገረችው ብዙ ወርቃማ ቃላት መካከል ለትምህርታችን «የተራቡትን ከበረከቱ አጠገባቸው» የሚለውን ኃይለ ቃል እንመለከታለን። ይህንን ኀይለ ቃል እመቤታችን ስለ ሦስት ነገር ተናግራዋለች፤ እነርሱም የሚከተሉት ናቸው።
፩. በረከተ ሥጋ/ምግበ ሥጋ ስጣቸው/
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የነቢያትን ጌታ የወለደች በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል አንደበትም የጎደላት ጸጋ የሌለ መሆኑ የተመሰከረላት ስለሆነች፤ ጌታችን ሰውን ሁሉ ጥቂቱን አበርክቶ የሚመግብ የበረከት አምላክ እንደሆነ ተናገረች። ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ብዙ ሕዝብ የቃሉን ትምህርት ሰምተው፣የእጁን ተአምራት አይተው ሲከተሉት። ምንም በሌለበት ምድረ በዳ ሙሉ ቀን ሲያስተምራቸው ከዋለ በኋላ ሊመሽ ባለ ጊዜ አባቶቻችን ሐዋርያት ወደ ጌታችን ቀርበው ጊዜው መሽቷልና ሕዝቡን አሰናብት አሉት። እርሱም የሚበሉትን ስጧቸው ሳይበሉ እንዳይሔዱ አላቸው። ሐዋርያው እንድርያስም በእኛ ዘንድ ከአምስት እንጀራ እና ከሁለት ዓሣ በስተቀር የለም። ይህ ጥቂት ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ሕዝብ እንዴት ይበቃል አለ? ጌታም ሁሉን በሥርዐት እንዲቀመጡ ከአዘዘ በኋላ ያንን ባርኮ በሚፈልጉት መጠን እንዲሰጡአቸው አዘዘ። እነርሱም እንደታዘዙት አደረጉ። አምስት ሺሕ ሰዎች ሴቶችና ሕፃናት ሳይቆጠሩ ተመግበውት ዐሥራ ሁለት መሶብ ፍርፋሪ ተርፎ ተነሥቷል። ዮሐ ፮፥፭-፲፫
ይህ እንግዲህ በእምነት ሁነን ያለንን ጥቂት ነገር ይዘን ወደ እግዚአብሔር ብንቀርብ እንደ ሚያበረክትልን ያሳያል። «ለሚያምን ሁሉ ይቻላል» (ማር.፱፥፳፫) እንዲል። ሰው የሚሰጠው ስጦታ ላያጠግብ ፣ላያረካ ይችላል ሲሰጥም ሰጠሁ ብሎ ያማል እግዚአብሔር የሚሰጠው ስጦታ ግን ጥቂቱ ብዙ ነው። ሲሰጥም ሰጠሁ ብሎ አይናገርም ዛሬ በረከተ ሥጋ እየራቀን ባለበት በዚህ ዘመን በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ቀርበን እንዲሰጠን መለመን ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል፤ «ለምኑ ይሰጣችኋል» ብሏልና። አንዳንዶቻችን ግን የምንበላውን እና የምንጠጣውን እንዲሁም የምንለብሰውን በአጠቃላይ ለቁመተ ሥጋ የሚያስፈልገንን ስለ ማግኘት አጥብቀን ስንጨነቅ ይታያል። ግን ጌታችን በቅዱስ ወንጌል «ስለዚህ እላችኋለሁ ለነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት ለሥጋችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ. . . የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ ሰማያዊ አባታችሁ ይመግባቸዋል እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡም?» /ማቴ.፮፥፳፭-፳፤ ማቴ.፯፥፰/
በእውነት ጌታችን የተናገረው ይህ አምላካዊ ቃል ሰው ሥራ ፈትቶ ከሰማይ መና እንዲጠብቅ አይደለም። የሰማይ አዕዋፍም ካልበረሩ አይመገቡም፤ ልዩነቱ ግን ምን እንበላ ይሆን? ብለው አለመጨነቃቸው ነው። እኛም በተሰለፍንበት ሥራ በትጋት ልንሠራ ይገባል። ገበሬ እርሻውን፣ ተማሪ ትምህርቱን፣ ነጋዴ ንግዱን ወዘተ በፍጹም ትጋት መሥራት ያስፈልጋል። ለምግበ ሥጋ ወይም በዚህ ዓለም ስንኖር ለሚያስፈልገን ነገር ስንሠራ በሥራችን ሁሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማስቀደም እና ፈቃዱን በጸሎት መጠየቅ ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል። ይህ ሲሆን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጸሎቷ እንደተናገረችው «የተራቡትን ከበረከቱ አጠገባቸው» ያለችው ኀይለ ቃል በሕይወታችን ይሠራል ማለት ነው። እግዚአብሔር አምላክ የምንሠራውን ሥራ ሁሉ በቸርነቱ ይባርክልን።
፪. ቃለ እግዚአብሔር ነው
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም «የተራቡትን ከበረከቱ አጠገባቸው »ብላ ስትናገር ከላይ እንደተመለከትነው ምግበ ሥጋን ብቻ አይደለም፤ ምግበ ነፍስ ሆነውን ቃለ እግዚአብሔርን ጭምር እንጂ። ጌታችን በቅዱስ ወንጌል እንደተናገረ «ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ጭምር እንጂ» ሰው በምግበ ሥጋ ብቻ የሚኖር ከሆነ የነፍስ ምግብ ከሆነው የእግዚአብሔር ቃል ከተለየ ከፈጣሪው ይለያል። ልብላ፣ ልጠጣ፣ ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ ነገ እሞታለሁ የሚል ይሆናል። ይህ ደግሞ ሰው የተፈጠረበትን ዓላማ ያስዘነጋዋል፡፡ /ማተ.፬፥፬/
ሰው የተፈጠረው እግዚአብሔርን እንዲያመሰግን፣ክብሩን እንዲወርስ ነው። ለዚህ ደግሞ ትልቁ የሰው ሕይወት መሠረት ቃለ እግዚአብሔር ነው። አባታችን ቅዱስ ጴጥሮስ የእግዚአብሔርን ቃል ለሕፃናት ማደግ መሠረት በሆናቸው በወተት መስሎ ተናግሯል። እንዲህ ሲል «ዛሬ እንደተወለዱ ሕፃናትም ሁኑ፤ ለመዳን በእርሱ ታድጉ ዘንድ ቅልቅል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ» ። ይህ የእግዚአብሔር ቃል የርኩስ መንፈስ የዲያብሎስን አሠራር ከእኛ የሚያርቅ በትክክለኛይቱ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት የሚያጸና ከክሕደት፣ ከጥርጥር/ኑፋቄ/ የሚለይ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ የሚያስገዛ ነው። /፩ኛጰጥ፪፥፪/ ሁለት ስለት ባለው ሰይፍም መስሎ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም ተናግሯል። «. . . የመንፈስ ቅዱስን ሰይፍ ያዙ ይኸውም የእግዚአብሔር ቃል ነው።» እንዲል። በሌላም ስፍራ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኤርምያስ ስለ እግዚአብሔር ቃል ኃያልነት ሲናገር እንዲህ አለ። «በውኑ ቃሌ እንደ እሳት ድንጋዩም እንደ ሚያደቅቅ መዶሻ አይደለምን? ይላል እግዚአብሔር።» /ኤር፳፫፥፳፱/፤ ኤፌ.፮፥፲፭-፲፯/
እንግዲህ የእግዚአብሔር ቃል የነፍስ በረከት ከሥጋ እና ከነፍስ መከራ መዳኛ ነው። በተለይ በወጣትነት ዕድሜ መንገዳችንን የምናቀናበት ማለትም ሕይወታችን መስመር የምናስይዝበት ነው። ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት «ጎልማሳ መንገዱን በምን ያቀናል? ቃልህን በመጠበቅ አይደለምን?» ይላል። ይህ ከእግዚአብሔር በረከት ሁኖ የተሰጠን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጸሎቷ እንደተናገረችው ነፍስ ልትጠግበው የሚገባ የእግዚአብሔር ቃል በረከት እንደሰማነው ልንሠራው ያስፈልጋል። /መዝ፩፻፲፰፥፱ ምግበ ሥጋ የሚስፈልገን ጤንነታችን ለመጠበቅ በሕይወት ለመኖር እንደሆነ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተነው በሥራ ልንተገብረው ያስፈልጋል። ስለ ጾም ስንማር የምንጾም፣ስለ ጸሎት ስንማር በጸሎት የምንጠመድ፣ስለ ምጽዋት ስንማር የምንመጸውት፣ስለ ንስሓ ስንማር ንስሓ የምንገባ ስለ ሥጋ ወደሙ መቀበል ስንማር የምንቆርብ ልንሆን ያስፈልጋል። ጌታ በቅዱስ ወንጌል እንደተናገረ «ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርግ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል» እንዲል /ማቴ.፯፥፳፬/። ቃሉን መስማት ብቻ ሳይሆን የሰማነውን ቃል የተማርነውን ትምህርት በተግባር ልንገልጸው ይገባል፡፡
፫.ሥጋ ወደሙ ነው
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም «የተራቡትን ከበረከቱ አጠገባቸው» ስትል ዋነኛው ምሥጢር በአዳም በደል ምክንያት በሰው ልጆች ሁሉ ላይ ነግሶ የነበረውን ረኀበ ነፍስ አስወገዳላቸው። የነፍስ ጥቅም የሆነ ለመንግሥተ ሰማያት የሚያበቃ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ሰጣቸው ማለት ነው። የሰው ጠባዩ ብዙ ጊዜ ባለመታዘዝ የተገለጠ ነው። አታድርግ የተባልውን ለማድረግ የሚፋጠን አድርግ የተባለውን ለማድረግ ዳተኛ የሆነ ነው። አባታችን አዳም «ዕፅ በለስን አትብላ በበላህ ጊዜ ትሞታለህ» ተባለ ዘፍ ፪፥፲፯።
አዳምም በነፃ ፈቃዱ ተጠቅሞ አትብላ የተባለውን በላ ጸጋው ተገፈፈ፣ረኀበ ነፍስ ጸናበት እግዚአብሔር አምላክም በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ሊያድነው ወዶ በድንግል ማርያም ሥጋ ተገልጾ ፍጹም ፍቅሩን በገለጸ ጊዜ ረኀበ ነፍስ ከሁላችንም እንዲያርቅልን ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው ብሎ ሰጠን ዮሐ፮፥፶፬። ነገር ግን ዛሬም ቢሆን የሰው ልጅ ተቃራኒ በመሆኑ መንገድ ሕይወት የሚገኝበትን ከፈጣሪው ጋር የሚወዳጅበትን የክብር ትንሣኤ የሚነሣበትን ሥጋውን እና ደሙን ከመቀበል ሲያፈገፍግ ይታያል። ለዚህም ብዙ የሚያቀርባቸው የየራሱ የሆነ ምክንያቶችንም ሲደረድር ይሰማል፡፡ ግን ምክንያት አያድንምና ወደዚህ ሕይወት ንስሓ በመግባት በምክረ ካህን፣በፈቃደ ካህን በመሆን ልንቀርብ ያስፈልጋል።
አምላካችን መንፈሳዊውን ሰማያዊውን ማዕድ/ሥጋውንና ደሙን/ በቤቱ በቅድስት ቤተክርስቲያን አዘጋጅቶ «ወደ ሰርጌ ኑ» ይላልና ጥሪውን ሰምተን ወደዚህ ሕይወት ልንመጣ ይገባናል። ችላ ብለን ብንተወው እኛም በሕይወታችን እንቸገራለን፣እንራባለን ለነፍስ ሞት ተላልፈን እንሰጣለን ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ የጠፋው ልጅ ወደ ልቡ እንደተመለሰ የአባቱ ቤት ትዝ ብሎት በዚህ በረኀብ ከምሞት ልነሣና ወደ አባቴ ቤት ልሂድ በዚያ በአባቴ ቤት ባሪያ ሆኜ እየበላሁ ብኖር ይሻለኛል። አባቴን በእግዚአብሔርና በአንተ ፊት በድያለሁና ማረኝ ልበል ብሎ በማሰብ እንዳልቀረ ወደ አባቱ ቤት እንደተመለሰ አባቱም ይቅርታ እንዳደረገለት እንደ ባሪያ ያይደለ በልጅነት ክብር እንዳኖረው ፍሪዳውን እንዳረደለት ልብሱን እንዳለበሰው ጫማ እንዳጫማው ቀለበት እንዳደረገለት፤ ስለ ልጁም ሲመሰክር ልጄ ጠፍቶ ነበር ተገኘ ሙቶም ነበር ተነሣ ደስ ይበለን እንዳለ ሁሉ እኛም በረኀበ ነፍስ እንዳንሞት በእግረ ንስሓ ተነሥተን ወደ አባታችን ቤት ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን እንምጣ፤ ስለ ኃጢአታችን ንስሓ እንግባ እግዚአብሔር አባታችን ይቅር ይለናል፤ በልጅነት ክብር ይቀበለናል፤ በኃጢአት የጠፋን በንስሓ እንመለስ፤ በበደል የሞትን በጽድቅ እንነሣ፤ የቅድስናን ሸማ/ካባ/ ወደሚደርቡ አገልጋዮች/ካህናት/ እንቅረብ ከዚያም ስለእኛ የተሰዋውን ፍሪዳ ሥጋውን ደሙን ያቀብሉናል ወደ ዘለዓለም ሕይወት ወደ መንግሥተ ሰማያት ያደርሱናል። (ሉቃ. ፲፭፥፲፩)
ስለዚህ ለምን በረኀበ ነፍስ እንሞታለን? «የተራቡትን አጠገባቸው» ብላ ድንግል ማርያም እመቤታችን እንደተናገረች ይህንን ጸጋ ለማግኘት እንሽቀዳደም ሥጋውን ደሙን የተቀበልን ደግሞ ወደ ኋላችን እንዳንመለስ በጽድቅ ሥራ እንድንጸና በረኀበ ነፍስ እንዳንያዝ እንጠንቀቅ ። ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት የወላዲተ አምላክ የድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን ጸሎት የመላእክት ተራዳኢነት አይለየ፤ አሜን።