የተራበችው ነፍሴ!
ጥቅምት ፬፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም
ቀንና ሌት ዙሪያዬን ከቦ ሲያስጨንቀኝ፣ ሲያሠቃየኝ የኖረው ባዕድ ከእኔ ባልሆነ መንፈስ ሊገዛኝና ከበታቹ ሊያደርገኝ ሲጥር በዘመኔ ኖሯል፡፡ ሥቃይና ውጥረት በተቀላቀለበት መከራ ውስጥ ብኖርም ሁል ጊዜ ተስፋን ማድረግ አላቆምኩም፤ ሆኖም ተፈጥሮዬ የሆነውን ሰላም ስናፍቅ የሰማይን ያህል ራቀብኝ፡፡
ምሬትና ጥላቻ በፈጠረው የባዶነት ስሜት መኖር ሲሰለቸኝም ነጻነቴን ሽቼ እጅጉን አዘንኩ፤ አለቀስኩም፤ ተከፍቼ ያሳለፍኳቸው ወቅቶች ሲታወሱኝ መቋቋም የማልችለው ይሆንብኝና ማንም ወደማይኖርበት ስፍራ መሰደድን አስባለሁ፡፡አልሆልኝ ሲል መልሼ እተወዋለሁ፤እሾህ ውስጥ እንደተተከለች ጽጌሬዳ በችግርና በአረንቋ በመከበቤ ሰላምን እጅጉን እናፍቃለሁ፤እራባለሁ፡፡
ሰላም የተራበችውም ነፍሴ ብቸኛ ስትሆን ፍቅርንም ተራበች፤ ያለ ፍቅር መኖር እስኪሳናትም ተዝለፈለፈች፤ በቅዱስ መንፈሱ ሕይወትን የሰጣት ጌታዋ ፍቅር በመሆኑ እርሱን ያጣች ጊዜ መኖር ተሳናት፤ ህልውናዋ አደጋ ላይ ሆነ፡፡ እርሱ ቅዱስ ሆኖ እርሷን ሲቀድሳት ንጽሕት ነፍስ ስለ ቅድስናዋ አመስጋኝ ብትሆንም ለእርሷ ባዕድ የሆነው ሊገዛት ሲጥር የማትቀበለው ሆነባት፤ ርኩስነቱ የማይስማማት በመሆኑ በእኩይነቱ ዕረፍት አሳጣት፡፡
ዓለሟ ሲጨልም፣ መሄጃ መድረሻ ሲጠፋባት ወደ ውስጧ ተመልክታ ልቧ መሐል እንደ ሻማ መብራት የሚንቦገቦገውን፣ እንደ ወራጅ ውኃ የሚፈሰውን የፍቅር ጥማት አሰበችና በዚያች በተስፈኛይቱ ቀን ጌታዋ ሲመጣ የምታገኘውን ነጻነትና ፍጹም ሰላም አስባም ተጽናናች፡፡
አሁን ግን የተራበችው ነፍሴ የፍቅር ባለቤት እግዚአብሔርን መሻቴ ወደ እርሱ እንድቀርብ የሚያደርገኝ በጎውን ጊዜ አጥብቄ በመፈለጌም ተደሰተች፡፡ እራሴን እንድመረምርም ትወተውተኝ ጀመር፡፡ ይህን ጊዜ ልጅነቴ ትዝ አለኝ፤ በአባትና በእናቴ ቤት ስኖር ጨዋታን እንጂ የመኖር ትርጕሙ ምን እንደሆነ ለማገናዘብ የአእምሮ ብስለቴ ባይፈቅድልኝም የንጽሕና ተምሳሌት ነበረና ወደዚያ ለመመለስ እጅጉን ተመኘሁ፤ በዚያን ጊዜ የቤተ ሰብ ፍቅር ላሳወቀኝ ፈጣሪዬን አመሰግነዋለሁ፤ ምንም እንኳን እኔነቴን ለማግኘት ብቸገርም ስለ ልጅነቴ አውስቼ እጽናናለሁና፡፡
የአሁኑ ማንነቴ መሠረት ልጅነቴ ቅንነት፣ ታዛዥነት እና በጎነት የበዛበት ዓለም ነበር፤ ሆኖም በዚህ ወቅት በዙሪያዬ የማየው ነገር ሁሉ ልጅነቴን የሚያወሳ አልሆን ቢለኝ ሕሊናዬ ተረበሸ፤ የማየውን ክፋትም ለመርሳት ዓይኔን ጨፈንኩ፤ ሐሳቤን ወደ በጎው ጊዜም ለመመለስ ጣርኩ፡፡ ይህ ዓለም ጥላቻና ማስመሰል ወደ በዛበት የሐሰት መንደር ተለውጧልና ይታክታል፡፡ በዚህም አዘቅት ወስጥ መሆኔን ተረድቼ እጅጉን አዘንኩ፡፡
በዙሪያዬ የከበቡኝ አስመሳዮች ክፋት በወለደው ስሜት ለጥፋት ሲዳረጉ፣ ማንነታቸው ተቀይሮ እንደ እንስሳ ሆነው ማየት “በእውን ነው ወይስ በሕልም” ያስብላል፡፡ “ይህ ሁሉ ለምን ሆነ?” ብዬም በአእምሮዬ አሰላሰልኩ፤ “እኔስ አምላኬን እንዲህ አስከፍቼውስ ይሆን?” ብዬ እራሴን ጠየኩ፤ ጥፋትን እንደ ጀብድ ክፋትንም እንደ ቀልድ ከሚያዩ ሰዎች መካከል መኖር ምንኛ ያስከፋል! “ግፍና በደል የሚፈጽሙ ሰዎች በሠሩት ኃጢአት የተነሣ ይህ ሁሉ እልቂት መድረሱ በእርሱ ቁጣ ይሆን?” ብዬም ደግሜ ጠየኩ፡፡ እርሱን ማስከፋትና ሕጉን መተላለፍ መቅሠፍት እንደሚያመጣ በቅዱሳት መጻሕፍቱ ውስጥ ያነበብኩበትን ጊዜ ለማሰብ ትንሽ ፋታ ወሰድኩ፡፡
እርስ በርስ ፍቅር አጥተው በጥላቻ መንፈስ ሲሰዳደቡ፣ ሲነቋቆሩ፣ ሲገዳደሉ፣ እውነትን ክደው፣ ፈጣሪን ረስተውና ሰውነታቸውን አርክሰው በእርኩስ መንፈስ እንደ እንስሳ የሚነዱ ሰዎችን ማየት በጎ ባይሆንም “እስከ መቼ?”ን መመለስ እስካሁን አልቻልኩምና ወደ ልጅነቴ ተመመልሼ ነፍሴን ከጭንቀት ልታደጋት አሰብኩ፡፡
የተራበችው ነፍሴ ልጅነቴን እንዳስብ አደረገችኝ፤ የልጅነቴ መገኛ ፈጣሪዬንም አስቤ በሕይወት ዘመኔ ሁሉ በትግዕሥቱና በቸርነቱ ስላኖረኝ አመሰገንኩት፤ የሚያስፈልገኝን ሳይነግፈኝ አኑሮኛልና፡፡ ለእርሱ መገዛትም የልቤ መሻት ሆነ፤ ወደዚያ ወደ ናፈኩት ልጅነቴ መመለስን ተመኘሁ፡፡ በዚያን ጊዜ በነበረኝ ንጹሕ ልብ ስለፈጠረኝ አምላክ ተገንዝቤ እንደነበረ ለማወቅ በመፈለጌ መመርምር ጀመርኩ፤ የነበረኝን ቅንነት አስታውሼ አሁን እርሱን አጥብቄ ፈለኩት፡፡
በንጽሕና ሕይወት መኖር መታደል በመሆኑ ስለ ንጹሐን መኖር አስቤ ፈጣሪን ደግሜ አመሰገንኩት፡፡ ተስፋችን ናቸውና፤ እነርሱን ባሰብኩ ቁጥር እንደ እነርሱ መሆንን ልቤ ተመኘ፡፡ ‹‹ልበ ንጹሐን ብፁዓን ናቸው፤ እግዚእብሔርን ያዩታል›› የሚለውን ቃል ሳስታውስ “ምንኛ ታደሉ!” ብዬ ተገረምኩ፤ አደነቁም፤ (ማቴ.፭፥፰) እነርሱን የቀደሰ አምላክ እኔንም በሕይወት መንገድ እንደሚመራኝ ተስፋ አደረኩ፡፡
የመኖሬን ትርጉም በማሰላሰል የመፈጠሬ ምክንያት ለታላቅ ክብር መሆኑን አመንኩ፤ ስለዚህም ጥያቄዬን ለመመለስ ወደሚችልና ለነፍሴ ዕረፍትን ወደሚሰጥ ወደአንድ የማውቀው መምህር፣ አዳኝ፣ ቤዛም ወደ ሆነው ጌታ ልቤ ተጓዘ፤ እግሬም ወደ ተቀደሰችው የእግዚአብሔር ቤት ወደ ቤተ ክርስቲያን አመራ፤ ጆሮዎቼ ስለ ፈጣሪ ደጋግመው ሰሙ፤ ዓይኖቼ የእርሱን ምስል ዳግመኛ ተመለከቱ፤ ጉልበቶቼም ሰገዱለት፤ ሕሊናዬ ስለ እርሱ ማሰብ አዘወተረ፡፡ በዚህም ለፈጠረኝ መገዛትን ጭምር ተመኘሁ፤ የእኔ መኖር በእርሱ መሆኑን ተረዳሁ፤ እርሱም በእኔ ውስጥ ይኖራልና!
የተራበችው ነፍሴም በቅዱስ ቃሉ ጠገበች፤ ጥሟንም አረካች፤ መልካም በሆነው እና ስክነት በሞላበት ቅጹሩ ውስጥ በመገኘቴ ሰላምን አገኘች፤ ዘወትርም ወደ እርሱ በመገሥገስ፣ ስለ እርሱ እያሰብኩ በጥላው ሥር መኖር በመጀመሬ ፍቅርን አገኘች፤ በክበቡ ውስጥ አድርጎም እስከ ሕልፈተ ሕይወቴ ድረስ እንዲያኖረኝ ምኞቴ በመሆኑ እርሱን እርሱን ስል እውላሉ፤ አድራለሁ፤ አንድ ቀንም ነፍሴን በእጁ አድርጎ በእቅፉ እንደሚያቀኖረኝ አምናለሁና ያን ዕለት እናፍቃለሁ!
የተራበችው ነፍሴ አንተን ትናፍቃለችና ጌታ ሆይ ቶሎ ና! ማራናታ!