የተምሮ ማስተማር ሰንበት ትምህርት ቤት ልዩ ዐውደ ጥናት አካሔደ
በደመላሽ ኃይለማርያም
የካቲት ፳፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤት የምሥረታ ታሪክ በመጀመሪያ ደረጃ ላይ የሚነሣው አንጋፋው የ‹‹ተምሮ ማስተማር›› ሰንበት ትምህርት ቤት በሚያዝያ ወር ፳፻፱ ዓ.ም የሚከበረውን ስድሳኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም የሰንበት ትምህርት ቤቱ አዳራሽ የካቲት ፳፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ልዩ ዐውደ ጥናት አካሔደ፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም መለሰ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ፤ መጋቤ ኅሩያን አባ ኤልያስ በልሁ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም ምክትል አስተዳዳሪ እና የሰንበት ትምህርት ቤቱ ሰብሳቢ፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ ጥሪ የተደረገላቸው ምሁራንና እንግዶች፤ የልዩ ልዩ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች፤ የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች ተወካዮች፤ ቀደምት የሰንበት ትምህርት ቤቱ አባላት እና በርካታ ምእመናን ታድመዋል፡፡ በዐውደ ጥናቱም ‹‹የተምሮ ማስተማር ሰንበት ትምህርት ቤት አመሠራረትና አገልግሎት›› እና ‹‹የአማርኛ መዝሙራት ታሪካዊ ዕድገትና ተግዳሮቶች›› በሚሉ አርእስት የተዘጋጁ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡ በጥናቶቹ ዙሪያ ከተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎችም በአቅራቢዎቹ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
‹‹የተምሮ ማስተማር ሰንበት ትምህርት ቤት አመሠራረትና አገልግሎት›› የሚለው ጥናት አቅራቢ ኢንጂነር ከፈለኝ ኃይሉ የተምሮ ማስተማርን የአመሠራረት ታሪክ እና አገልግሎት በተለይ ከ፲፱፻፴፱ — ፲፱፻፵፱ ዓ.ም የነበረውን የሰንበት ት/ቤቱን እንቅስቃሴ በጥናታቸው ዳሰዋል፡፡ በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በተፈሪ መኮንን የወንዶች ትምህርት ቤት ተማሪዎች በመነጨ ‹‹ሰዎችን ለማስታረቅ›› የሚል በጎ ሐሳብ የ‹‹ተምሮ ማስተማር›› ሰንበት ት/ቤት እንደተመሠረተ ኢንጂነር ከፈለኝ ገልጸው ለምሥረታውም ዐሥራ ሁለት ወንድሞች ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህ ሰዎች በተጨማሪ በቀድሞ ስማቸው አባ መዓዛ ይባሉ የነበሩት በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ድርሻ የላቀ እንደነበርም ኢንጂነሩ በጥናታቸው አብራርተዋል፡፡
ከዅሉም በተለየ በንጉሡ ዘመን በቤተ ክርስቲያንና በማኅበራዊ አገልግሎት ላይ ከፍተኛ ድጋፍ ሲሰጡ የነበሩትና በ፲፱፻፷፮ ዓ.ም ያለ በቂ ምክንያት በደርግ ባለሥልጣናት በግፍ የተገደሉት አቶ አበበ ከበደ ለሰንበት ት/ቤቱ መመሥረትና መጽናት ግንባር ቀደሙን ቦታ እንደሚወስዱ ጥናት አቅራቢው አስገንዝበዋል፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቱ በ፲፱፻፵፱ ዓ.ም ገብረ ጊዮርጊስ አጋሼ በተባሉ አባት የተሰጠው ‹‹የተምሮ ማስተማር ማኅበር›› የሚለው ስያሜ በ፲፱፻፶ ዓ.ም በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንደጸደቀና ከጊዜ በኋላም ‹‹የተምሮ ማስተማር ሰንበት ት/ቤት›› የሚለው ስሙ በቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና እንዳገኘ ያስታወሱት የጥናቱ አቅራቢ የሰንበት ት/ቤቱ መመሥረት ወጣቶች ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ በር ከመክፈቱ ባሻገር ሰባክያነ ወንጌል እንዲበራከቱና ምእመናን በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡ በጥናታቸው ማጠቃለያም ሰንበት ት/ቤቱ እንዲመሠረት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከቱትን እንደ አቶ አበበ ከበደ ያሉ ባለውለታዎችን በጸሎት መዘከርና በስማቸው መታሰቢያዎችን ማዘጋጀት እንደሚገባ ኢንጂነር ከፈለኝ አሳስበዋል፡፡
‹‹የአማርኛ መዝሙራት ታሪካዊ ዕድገትና ተግዳሮቶች›› የሚለው ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢ ቀሲስ ሰሎሞን ወንድሙ በበኩላቸው የ‹‹ተምሮ ማስተማር›› ሰንበት ት/ቤት የምሥረታ እንቅስቃሴ ከተጀመረበት ፲፱፻፴፭ ዓ.ም አንሥቶ ለሰባ ዓመታት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መስጠቱን በጥናታቸው ጠቅሰዋል፡፡ የአማርኛ መዝሙራት መዘጋጀት የጀመሩት ሰንበት ት/ቤቱ በተመሠረተበት ወቅት አካባቢ መኾኑን ያስታወሱት ጥናት አቅራቢው በወቅቱ መዝሙራቱ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ ቋንቋ በቀጥታ ተተርጕመው ዜማቸውም ሳይቀየር ይቀርቡ እንደነበር እና ይህም ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ የኾኑ መዝሙራት እንዲበራከቱ በር መክፈቱን በጥናታቸው አመላክተዋል፡፡
ያሬዳዊ ይዘታቸውን የጠበቁ የአማርኛ መዝሙራት እንደ ተምሮ ማስተማር ባሉ ሰንበት ትምህርት ቤቶች በየዘመናቱ በጥራዝ መልክ እየታተሙ ለዛሬው ትውልድ መድረሳችውንም አስገንዝበዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የሚዘመሩ ጥቂት የማይባሉ መዝሙራት በሥርዓት ስለማይዘጋጁ ካሉባቸው የዘይቤ፣ የቃላት አጠቃቀም፣ የቀለም እና ሐረግ ምጣኔ ጉድለቶች ባሻገር ምሥጢርን እና ይዘትን፣ እንደዚሁም ያሬዳዊ ዜማን ከመጠበቅ አኳያም ብዙ መሥፈርቶችን እንደማያሟሉ የገለጹት ቀሲስ ሰሎሞን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም የሚቀርቡ መዝሙራት ዅሉ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ተመዝነውና ተገምግመው በተገቢው ዅኔታና በትክክለኛው መሥፈርት ሊዘጋጁ ይገባል በማለት ጥናታዊ ጽሑፋቸውን አጠቃለዋል፡፡
በዚህ ዐውደ ጥናት ሊስተናገዱ መርሐ ግብር ከተያዘላቸው ጥናታዊ ጽሑፎች መካከል በሰዓት እጥረት ምክንያት ያልቀረበው ‹‹መገናኛ ብዙኃንና የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት›› የሚለው የዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ (በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የጥንታውያት መዛግብት ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር) ጥናት በሌላ ጊዜ በተመሳሳይ መርሐ ግብር እንደሚቀርብ የሰንበት ት/ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ ዲ/ን ዘውዱ በላይ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ቃል ገብተዋል፡፡
ከዚህ መርሐ ግብር በተጨማሪም ከሚያዝያ ፲፭ — ፳፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በዐውደ ርዕይ እና በልዩ ልዩ መንፈሳውያን መርሐ ግብራት የሰንበት ት/ቤቱ ስድሳኛ ዓመት ምሥረታ በዓል እንደሚዘከር ከሰንበት ት/ቤቱ ጽ/ቤት ለመረዳት ተችሏል፡፡ ለብዙ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ ለማኅበረ ቅዱሳንና ጽርሐ ጽዮን የአንድነት ኑሮ ማኅበር መመሥረት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያለው ይህ አንጋፋ ሰንበት ትምህርት ቤት በስልሳ ዓመት የአገልግሎት ጉዞው ውስጥ ያበረከተውን መንፈሳዊ አገልግሎት የሚያሳዩ ተጨማሪ የዳሰሳ ጥናቶች መደረግ እንደሚገባቸው በዐውደ ጥናቱ የተገኙ አባቶችና ምሁራን ጠቁመዋል፡፡ በመጨረሻም በአባቶች ጸሎት ጠዋት የተከፈተው ይህ የዐውደ ጥናት መርሐ ግብር በአባቶች ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ አመሻሽ ላይ ተፈጽሟል፡፡