የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የመልካም ምግባር መሠረት!
ሰኔ ፳፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል ሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በማኅበሩ ሕንፃ ሦስተኛ ፎቅ አዳራሽ የጥናት ጉባኤ አዘጋጅቶ ነበር፡፡
በዕለቱ *ሥነ ምግባርና ግብረ ገብነት* በሚል ርእስ በአቶ ዓለማየሁ ተክለ ማርያም (በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርትና ሥነ ባሕርይ ጥናት ኮሌጅ ተባባሪ ፕሮፌሰር) በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ በአሁኑ ጊዜ በተለይ በከተማ አካባቢዎች በአብዛኞቹ ወጣቶች ዘንድ የሥነ ምግባር ጉድለት ማለትም ሰውን አለማክበር፣ ወላጆችንና መምህራንን መሳደብ፣ ከውጪው ዓለም የተወሰዱ ኢ-ግብረገባዊ የኾኑ ተግባራትን መፈጸም ወዘተ ዓይነት ጎጂ ባህሎች እየተለመዱ መምጣታቸው፤ ይህም የአገራችንን መልካም ገጽታ እያጠፋ እንደሚገኝ፤ ወጣቱ ትውልድ ቃለ እግዚአብሔርን ቢማርና ቅዱሳት መጻሕፍትን ቢመረምር የጠባይ ለውጥ እንደሚያመጣና የመልካም ምግባር ባለቤት መኾን እንደሚችል ተገልጿል፡፡
የአቶ ዓለማየሁ ጥናት ከዓለም ዐቀፋዊው ግብረ ገብነት አንጻር ስትቃኝ አገራችን ኢትዮጵያ የተሻለች ብትኾንም፣ ከጊዜ ወደጊዜ ግን የዜጎቿ መልካም ባህል ማለትም መተሳሰብ፣ መከባበር፣ መጠያየቅ፣ መቻቻል፣ የአገር ፍቅር፣ ወዘተ የመሳሰለው ጥሩ ልምድ እየቀነሰ መምጣቱን፤ እንደዚሁም አብዛኛው ወጣት በተለይ በከተማዎች ኢ-ገብረገባዊ ባልኾኑ እንደ ሱስ፣ ስካር፣ ዝሙት፣ ትዕቢት፣ ሥርዓት አልባ አለባበስ፣ ወዘተ የመሳሰሉ ተግባራት መያዙን በማስረጃ አቅርቦ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት በትውልዱ አእምሮ ውሰጥ የሥነ ምግባር ትምህርት አለመሥረጹና በተጨማሪም ወጣቱ ትውልድ በዘመናዊ አስተሳሰብ መማረኩ፤ እንደዚሁም አስነዋሪ መረጃዎችንና ምስሎችን በሚያስተላልፉ ሚድያዎች ተፅዕኖ ሥር መውደቅ መኾኑን አትቷል፡፡
ጥናቱ ግብረ ገብነት፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር፣ ዐሥርቱ ትእዛዛት፣ ከክፉ ምግባር መራቅ፣ ሰውን መውደድና ማክበር፣ የአገር ፍቅር፣ ወዘተ የሚያስረዱ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች በዘመናዊው ሥርዓተ ትምህርት ተካተው ለተማሪዎች ይሰጡ በነበሩበት ዘመን የማኅበረሰቡ የመከባበር፣ የመፈቃቀርና የመተሳሰብ ባህሉ ከፍተኛ እንደነበረና ይህ ባህል እየቀነሰ መምጣቱን አውስቶ በአሁኑ ሥርዓተ ትምህርትም ምንም እንኳን ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ እስከ ዐሥራ ሁለተኛ ክፍል ድረስ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ተዘጋጅቶ መሰጠቱ ቢበረታታም በተማሪዎች ዘንድ የሚታየው መምህራንን አለማክበር፣ ፈተና ከሌሎች ተማሪዎች መስረቅ፣ ሥርዓት የሌለው አነጋገርና አለባበስ፣ ወዘተ የመሰሳሰለውን ኢ-ግብረገባዊ ድርጊት ለማስተካከልና ትውልዱን የመልካም ሥነ ምግባር ባለቤት ለማድረግ ግን ከዚህ የበለጠ መሥራት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
ወጣቱ ትውልድ ቃለ እግዚአብሔር ቢማር እንደሚለወጥ ሲመሰክሩ *ዛሬ የተማራችሁት መጽሐፍ ቅዱስ የነገ ሕይወታችሁ ስንቅ ነው* ያሉት የጥናቱ ባለቤት አቶ ዓለማየሁ በመጨረሻም *ምን እናድርግ?* በሚለው የጥናታቸው መደምደሚያ የሰው ልጅ ሦስት የጠባይ መገለጫዎች እንዳሉት፣ እነዚህም አንደኛ የሚያደርገውን የማያውቅ፤ ሁለተኛ የሚያደርገውን የሚያውቅና ሕግን የሚፈራ ነገር ግን ኢ-ግብረገባዊ፤ ሦስተኛ ግብረ ገባዊ ሰው መኾናቸውን ጠቅሰው ኹሉም ሰው *በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአት አልሠራም* እንዳለው እንደ ዮሴፍ ሦስተኛውን ጠባይ ገንዘብ ካደረገ የሥነ ምግባር ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ገልጸው የቤተ ክርስቲያን ትምህርት መማር፤ ግብረ ገባዊ ሕይወትን ማጠናከር፤ ታማኝትን፣ እውነትንና ፍቅርን ማሥረጽ፤ አእምሮን ከክፉ አስተሳሰብ ማጽዳትና የመሳሰሉ ተግባራት ለመልካም ምግባር መሠረቶች መኾናቸውን ጠቁመዋል፡፡