የቤተ መጻሕፍቱን የመረጃ ክምችት በዘመናዊ ለማሳደግ ማእከሉ ጥሪ አቀረበ

ጥር 20 ቀን 2006 ዓ.ም.  

በእንዳለ ደምስስ

“ስትመጣ ….መጻሕፍቱን ይልቁንም በብራና የተጻፉትን አምጣልኝ ” 2ኛ ጢሞ4፡13

የማኅበረ ቅዱሳንን ቤተ መጻሕፍት የመረጃ ክምችት ለማሣደግና በዘመናዊ መልኩ ለማደራጀት የ3ኛ ዙር ልዩ የመጻሕፍትና ቤተ መጻሕፍቱን የሚገለግሉ ቁሳቁሶችን ለማሰባሰብ መርሐ ግብር ማዘጋጀቱን የማኅበሩ ጥናትና ምርምር ማእከል ገለጸ፡፡ ከጥር 2 እስከ ጥር 30/ 2006 ዓ.ም የሚቆየው የመጻሕፍትና የቁሳቁስ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሩ በማኅበረ ቅዱሳን ሕንፃ እና በማኅበሩ የንዋያተ ቅዱሳት መሸጫ ሱቆች ከጧቱ 3፡00 እስከ ምሽቱ 1፡00 ሰዓት ይካሔዳል፡፡

በዚሁ መሠረት ቤተ መጻሕፍቱን ለሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ ለተመራማሪዎች፤ ነገ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለሚረከቡ ወጣቶችና ተማሪዎች ትልቅ እገዛ ማድረግ የሚችል በመሆኑ፤ መጻሕፍትን በመለገስ በሥጋም በነፍስም ተጠቃሚ የሚሆን ትውልድ ለመፍጠር የበኩልዎን ድርሻ ይወጡ ዘንድ ተጋብዘዋል፡፡

ቤተ መጻሕፍቱ ከ1996ዓ.ም – 1999 ዓ.ም በጎ ሐሳብ ባላቸዉ አገልጋዮች በለገሱት መጻሕፍት፤ በትንሽ ኮንቴነር ውስጥ ለማኅበሩ አገልጋዮች ብቻ የውሰት አገልግሎት በመስጠት የተቋቋመ ሲሆን፤ የመረጃ ሀብቶቹ ከ500 የማይበልጡ ነበሩ፤ ተገልጋዮችም ውስን ነበሩ፡፡

 

ከ2000 ዓ.ም-2003 ዓ.ም ቤተ መጻሕፍቱ በዲ.ዲ.ሲ. /Dewey Decimal Classification/ ሕግ መሠረት በዕውቀት ዘርፍ ተለይተው እንዲደራጁ በማድረግ ግንባታው ባልተጠናቀቀ የማኅበሩ ሕንፃ ውስጥ የንባብ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ የመረጃ ሀብት ክምችቱም በዓይነትና በብዛት ጨምሮ 3000 በማድረስ፤ ጥናታዊ ጽሑፎች ተሰብስበዉ ለአገልግሎት ዉለዋል፡፡

 

በዚህ ወቅት ብዙ መጻሕፍትን በስጦታ ለመሰብሰብ የተቻለ ሲሆን ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ ከ 400 በላይ መጻሕፍትን አበርክተዋል፡፡ ከ2004 ዓ.ም – 2006 ዓ.ም ባሉት ዓመታትም፤ የመረጃ ሀብቶች ለአያያዝና ለአጠቃቀም በሚያመች ሁኔታ በማደራጀት በምቹ የአገልግሎት ክፍል ውስጥ የንባብ እና የውሰት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ክምችቱም 5000 የታተመ ቅጅ፤ 5000 ያልታተመ ቅጂ ላይ ደርሷል፡፡ አገልግሎቱ በኮምፒውተር የታገዘ በማድረግ በመካነ ድር እና በሶፍትዌር አገልግሎት ለመስጠት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ በቀን በአማካይ ከ50 ለሚበልጡ ሰዎች አገልግሎት ይሰጣል፤ የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ፖሊሲ እና መመሪያም ተዘጋጅቷል፡፡

 

ከ2007 ዓ.ም – 2009 ዓ.ም ድረስ ክምችቱ ወደ 40,000 /አርባ ሺሕ/ በማሳደግ በሶፍትዌር የታገዘና ቀልጣፋ የE-Library፤ የኢንተርኔት እና የዲጂታል አገልግሎት መስጠት የሚያስችለው ተደርጎ እንዲደራጅ የታቀደ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለጥናትና ምርምር የሚሆን ማዕከላዊ የመረጃ ተቋም ይሆናል፡፡

 

ምእመናን ሙያዊ አገልግሎት ከመስጠት ጀምሮ የመረጃ ምንጮችን (መጻሕፍት፣መጽሔት፣ ጋዜጦች) እና የቤተ መጻሕፍት መገልገያዎችን (ኮምፒዉተር፣ ስካነር፣ ፎቶ ኮፒ ማሽን፣ ሲዲ፣ ወንበር እና ጠረጴዛ) በመለገስ፤ የቤተ መጻሕፍቱን ደረጃ በማሳደግ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል አቅማቸው የፈቀደውን ልገሳ እንዲያደርጉ የማኅበሩ ጥናትና ምርምር ማእከል ጥሪ አቅርቧል፡፡