የባሕር ዳር ማእከል የጽ/ቤት ግንባታ በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ
ኅዳር 16 ቀን 2007 ዓ.ም.
ግዛቸው መንግሥቱ /ከባሕር ዳር ማእከል/
በማኅበረ ቅዱሳን የባሕር ዳር ማእከል በደብረ ጽዮን ሰላም አድርጊው ማርያም ገዳም በተሠጠው ቦታ በመገንባት ላይ የሚገኘው ጽሕፈት ቤት በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ የጽ/ቤት ግንባታ ኮሚቴ የቴክኒክ ክፍል አስተባባሪ አቶ አስናቀ ለወየ አስታወቁ፡፡
የሕንፃ ግንባታ ኮሚቴው ኅዳር 7 ቀን 2007 ዓ.ም እየተገነባ ያለውን ጽሕፈት ቤት በተያዘለት እቅድ መሠረት እየተጠናቀቀ መሆኑን ለአባላቱ ለማብሠርና ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ በተዘጋጀው መርሐ ግብር ላይ የኮሚቴው አስተባባሪ አቶ አስናቀ ለጽሕፈት ቤት ግንባታ የሚሆን ቦታ ለሰጠውና በዐሳብና ልዩ ልዩ ድጋፍ በማድረግ ላይ ለሚገኘው ለደብረ ጽዮን ሰላም አድርጊው ማርያም ገዳም ሰበካ ጉባኤ፣ እንዲሁም የግንባታውን ወጪ ወርሃዊ ደመወዛቸውን በመለገስ ሙሉ በሙሉ ለሚሸፈኑት የማኅበሩ አባላትን አመስግነዋል፡፡ እየተገነባ ያለው ጽሕፈት ቤት የመጀመሪያ ምእራፍ ሲሆን፤ የጣራ ሥራውና ቆርቆሮ ማልበሱ በኅዳር ወር፤ ሙሉ ግንባታው ደግሞ እስከ ጥር 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ተጠናቆ አገልግልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ገልጸዋል፡፡
ኮሚቴው ባቀረበው ሪፖርት እየተገነባ ያለው ጽሕፈት ቤት በቋሚነት የሚያገለግለው ለአዳራሽነት ሲሆን፤ ለቢሮ የሚያገለግሉ ክፍሎች በሁለተኛው የግንባታ ምእራፍ ከገዳሙ በተገኘው ክፍት ቦታ ላይ እንደሚገነቡ ተጠቅሷል፡፡ የጽሕፈት ቤቱ የመጀመሪያ ምእራፍ ግንባታ ልዩ ልዩ የሙያ ድጋፎችን ሳይጨምር እስከ 600,000 ብር የሚፈጅ በመሆኑ አባላት በሙያና በገንዘብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ኮሚቴው ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
ግንባታው ሲጠናቀቅ የባሕር ዳር ማእከል፣ የሰሜን ምእራብ ማእከላት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት፣ የጣና ወረዳ ማእከልና ግቢ ጉባኤያት እንደሚገለገሉበት የተጠቀሰ ሲሆን፤ የጽሕፈት ቤቱ መገንባት ለማእከሉና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ ለሚፈጽሟቸው የቤተክርስቲያን አገልግሎት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተገልጿል፡፡
የማእከሉ ሥራ አስፈጻሚ በ2003 ዓ.ም ጽሕፈት ቤት መገንባት እንዳለበት ለአባላቱ ዐሳብ በማቅረብ፤ የጽሕፈት ቤት ግንባታ ኮሚቴ በማቋቋም አባላት ገንዘባቸውን አሰባስበው ግንባታውን ለመጀመር ጥረት ተደርጓል፡፡ ነገር ግን በተለየዩ ችግሮች ምክንያት የዘገየ ቢሆንም በጥቅምት 2005 ዓ.ም አሁን የሚያገለግልበትን ጊዜያዊ ጽ/ቤትና የግንባታ ቦታ በደብረ ጽዮን ሰላም አድርጊው ማርያም ገዳም ለማግኘት በመቻሉ ማእከሉ አገልግሎቱን ለማጠናከርና በርካታ ሥራዎችን እንዲሠራ አስችሎታል፡፡
ግንቦት 29 ቀን 2006 ዓ.ም. ለጊዜው ተቋርጦ የነበረውን የጽሕፈት ቤት ግንባታ ፕሮጀክት አዲስ ኮሚቴ በማዋቀር ወደ ተግባር ለመሸጋገር እንቅስቀሴ ተጀመረ፡፡ ኮሚቴው ለግንባታ በሀብትነት ይዞት የተነሳው የባሕር ዳር ማእከል አባላትን ብቻ በመሆኑ አባላትን በማወያየት የወር ደመወዛቸውን በዐራት ጊዜያት ከፍለው እንዲያጠናቅቁ በማስወሰን ገንዘባቸውን በመለገስ፤ በሙያ በመደገፍ ባደረጉት ብርቱ ጥረት አሁን የጽሕፈት ቤት ግንባታው በተያዘለት እቅድ መሠረት እየተከናወነ መሆኑን ኮሚቴው አስታውቋል፡፡
የባሕር ዳር ማእከል በማእከልነት የተቋቋመውና አገልግሎቱን የጀመረው በ1985 ዓ.ም ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በማእከልነት ተደራጅተው ሰፊ አገልግሎት እየፈጸሙ ያሉትን ዘጠኝ ማእከላት አቅፎ ነበር፡፡ ማእከሉ እንደተመሰረተ አገልግሎቱን ይፈጽም የነበረው በምእራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት በተሰጠችው አነስተኛ አንድ ክፍል ጽሕፈት ቤትና በግለሰብ ቤት እንደነበረ የጽሕፈት ቤት ግንባታ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡ የባሕር ዳር ማእከል ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር አገልግሎቱን ለመፈጸም እንዲችል ከ1985 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 2005 ዓ.ም ድረስ በባሕር ዳር ከተማ በተለያዩ ቦታዎች ዘጠኝ ጽ/ቤቶችን በመከራየት ሰፊ አገልግሎት የፈጸመ ቢሆንም ለከፍተኛ የቢሮ ኪራይ ወጭ ሲዳረግ የቆየ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ማእከሉ አገልግሎት ይፈጽምባቸው የነበሩ ጽ/ቤቶች የነበሩበት አካባቢ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የማይመቹ አስቸጋሪና ከቤተክርስቲያን ቅጽር የራቁ በመሆናቸው ማእከሉም ሆነ አባላቱ የማይረሱ ፈተናዎችና ችግሮችን እንዳሳለፉ የቀደሙ የማእከሉ አባላት ይገልጻሉ፡፡ ለረጅም ዓመታት ጽሕፈት ቤት ባለመኖሩ የደረሰበት ፈተናና በአገልግሎቱ ላይ የተፈጠረበት ጫና የማእከሉ ሥራ አስፈጻሚ ዓላማውን ለማሳካትና ለአገልግሎቱን በአግባቡ ለመፈጸም የሚያስችለውን ምቹ ጽሕፈት ቤት መገንባት እንዲያስብና አባላቱም በቆራጥነት ለግንባታው እንዲነቃቁ እንዳደረጋቸው የጽሕፈት ቤት ግንባታ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡
በተያዘ ዜና በማኅበረ ቅዱሳን በባሕር ዳር ማእከል የደብረ ሰላም ወረዳ ማእከል ከወረዳ ማእከሉ አባላት ገንዘብ በማሰባሰብ ከደብረ ሰላም በዓለ እግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ባገኘው ቦታ ላይ ባለ 4 ክፍል ጽ/ቤት ገንብቶ የጣሪያ ማልበስና የግድግዳ ግርፍ ስራውን ማጠናቀቁና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለአገልግሎት እንደሚያበቃ የወረዳው ማእከል አስታውቋል፡፡