የቅዱስ ያሬድ ድርሰት በሆነው ምዕራፍ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀረበ
ሚያዝያ 13 ቀን 2004 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
ምዕራፍ የዘወትርና የጾም ተብሎ በሁለት እንደሚከፈል የገለጹት ዶክተር ውቤ ካሣዬ፤ የዘወትር የሚባለው አመቱን ሳይጠብቅ በየአመቱ ባሉት ሳምንታትና በዓላት በአገልግሎት ላይ የሚውል ሲሆን፤ የጾም ምዕራፍ ደግሞ በጾመ አርባና በአንዳድ የምህላ ቀናት እንደሚዜም፤ የሁለቱም መሠረታቸው የዳዊት መዝሙርና ድጓ ወይም ጾመ ድጓ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
በአገልግሎት ላይ ምዕራፍ ሦስት አካላት ማለትም መሪና ተመሪ እንዲሁም አንሺ ያስፈልጉታል፡፡በግራና በቀኝ በመከፋፈልና በመቀባበል ይቀርባል፡፡ ምዕራፍ በዋናነት የሚያካትታቸው ሰባት ክፍሎች አሉት፡፡ እነሱም ውዳሴ ማርያም፤ መስተጋብእ፤ አርባዕት፤ አርያም፤ ሠለስት፤ ክስተትና መወድስ በመባል ይታወቃሉ፡፡ የየራሳቸው ባህርያትና መጠን እንዳላቸውም በጥናቱ ላይ የቀረበ ሲሆን እያንዳንዱ ክፍል ከሰኞ እስከ እሁድ በመከፋፈል አቅርበውታል፡፡የድጓ መምህር በሆኑት በመምህር መንግሰቱ መላኩ/ የጥናቱ አቅራቢ የአብነት መምህር / አማካኝነት ከእያንዳንዱ ክፍል በዜማ እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡
ምዕራፍ ማለት ማረፊያ ማለት ሲሆን በዜማ ቤት ሲሆን ደግሞ ከሰላም ለኪ ጀምሮ የጾም ምዕራፍ እስኪፈጸም ድረስ ያለው ትምህርት ሁሉ ምዕራፍ ይባላል፡፡ የሚጠናው በቃል ነው፡፡ በቃል ትምህርት ጊዜ የተለየ አቀማመጥ ሲኖረው በመጽሐፉ ደግሞ የተለየ ተራ እንዳለው በጥናታቸው አቅርበዋል፡፡
የቅዱስ ያሬድ ዜማ እጅግ የመጠቀና ሰማያዊ ምስጋና መሆኑን፤ እግዚአብሔርም ለቅዱስ ያሬድ የሰጠው የተለየ ሰማያዊ ምስጢር እንደሆነ፤ ቅዱስ ያሬድ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም አባቶች አስተዋጽኦ እንዳደረጉ፤ ከእነዚህም መካከከል አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫና ሌሎችም እንደሚጠቀሱ በጥናቱ ላይ ተብራርቷል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ከሌላው አለም የዜማ አቀራረብ ጋር ሲነጻጸር ቀደምት የሚያደርገው ሲሆን የኖታ አጠቃቀምን በተመለከተ በአለም ላይ እየተሰራበት ካለው የሙዚቃ ኖታ ፍጹም የተለየ ያደርገዋል፡፡ የቅዱስ ያሬድን የኖታ አጠቃቀም አውሮፓውያን በራሳቸው የኖታ ሥርዓት ለመቀየር ጥረት ቢያደርጉም እንዳልተሳካላቸው በጥናቱ ላይ ተገልጸል፡፡
የቅዱስ ያሬድን መንፈሳዊ ድርሰቶች እጅግ እንደሚመስጣቸውና ልዩ ትኩረት እንዲሰጡት እንዳደረጋቸው የገለጹት ዶክተር ካሣዬ የቅድስት ቤተክርስቲያንን የአብነት ትምህርት ለመማር ካላቸው ፍላጎት የተነሳ የቅዱስ ያሬድን ዜማ በመማር ላይ እንደሚገኙና አራት አመታትን እንዳስቆጠሩ፤ ለጥናቱም እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የውጭ ሃገር ጸሐፍት የቅዱስ ያሬድ መንፈሳዊ ሥራዎች ላይ ጥናቶች የተደረጉ ቢሆንም ስራዎቻቸው በአብዛኛው የተዛቡ አቀራረቦች እንዳሏቸውና ለአንዳንዶቹም ማስተካከያ እንዲያደርጉ ጭምር እንደጻፉላቸውና ይህ ጉዳይ እጅግ ያስጨንቃቸው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ከውጭ ጸሐፍት በተጨማሪ በጣት የሚቆጠሩ የቤተክርስቲያን አባቶችና ምሁራን በቅዱስ ያሬድ ሥራዎች ላይ ጥናቶችን ያደረጉ ሲሆን፤ በአንዳንድ አባቶች ጥናት መሠረት ያሬዳዊ ዜማ በአጠቃላይ እስከ አሥራ አራት ሺህ የሚደርሱ ዜማዎች እንዳሉት ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን በእለቱ በመድረክ ላይ ከተጋበዙት ሊቃውንት መካከል የድጓ ሊቅ የሆኑት ሊቀ ህሩያን በላይ መኮንን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በመሥራት ላይ የሚገኙ ሲሆን ያሬዳዊ ዜማን አስመልክቶ ባጠኑት ጥናት መሰረት ዜማዎቹ እስከ ሃያ ሺህ እንደሚደርሱ መስክረዋል፡፡
በዶክተር ውቤ ካሣዬ ትኩረት ሊሰጥባቸው ይገባል ተብለው ከቀረቡ ሃሳቦች መካከል፤ የቅዱስ ያሬድ መንፈሳዊ ሥራዎች ለአለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረት ቢደረግ፤ ትውልዱን በመንፈሳዊ እውቀት ለመቅረጽ እንዲቻል በየሰ/ት/ቤቶች ትምህርቱ ቢሰጥ፤ ጥናትና ምርምር መደረግ ስለሚገባው ቤተክርስቲያን ከፍተኛ የእውቀት ክምችት ያላትና የበለጸገች ስለሆነች ይህንንም በጥናትና ምርምር በመደገፍ ማኅበረ ቅዱሳን አጠናክሮ እንዲገፋበት አሳስበዋል፡፡
እስከአሁንም በቤተ ክርስቲያናችን በቅዱስ ያሬድ ላይ ከጻፉ ሊቃውንት መካከል “የኢትዮጵያ ጥንታዊ ትምህርት” በሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ፣ “ያሬድና ዜማው” በሊቀ ካህናት/ርዕሰ ደብር ጥዑመ ልሳን ካሳ፣ “ጥንታዊ ሥርዐተ ማኅሌተ ዘአቡነ ያሬድ ሊቅ” በመሪጌታ ልሣነ ወርቅ ገ/ጊዮርጊስ ይጠቀሳሉ፡፡
መርሃ ግብሩን በመምራት ቀሲስ ዶክተር ሙሉጌታ ስዩም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትየጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች ት/ክፍል ረዳት ፕሮፌሰርና የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር ሰብሳቢ የተሳተፉ ሲሆን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ሰሙነ ሕማመትን አስመልክቶ ከቅዱስ ያሬድ ዝማሬዎች በመርሐ ግብሩ መጀመሪያና መዝጊያ ላይ አቅርበዋል፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ መምህራን፤ ከተለያዩ ተቋማትና መሥሪያ ቤቶች ጥሪ የተደረገላቸው ኃላፊዎችና ምዕመናን የተገኙ ሲሆን በቀረበው ጥናት ላይ ከታዳሚዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች በጥናቱ አቅራቢ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡