የቅዱስ ያሬድ መታሰቢያ ዐውደ ርዕይ ተከፈተ
ግንቦት 8/2004 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
ቅዱስ ያሬድ የተሠወረበትን መታሰቢያ ዓመት ምክንያት በማድረግ ከግንቦት 5-12 ቀን 2004 ዓ.ም. የሚቆይ ዐውደ ርዕይ አዲስ አበባ በሚገኘው ደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ተዘጋጀ፡፡ የቅዱስ ያሬድ 1500ኛ ዓመት የልደት በዓል በተለያዩ መንፈሳዊ መርሐ ግብሮች በደማቅ ሁኔታ በሚቀጥለው ዓመት ለማክበር የደብሩ አስተደደር የደብሩ ስብከተ ወንጌል ጽ/ቤት ሰበካ ጉባኤውና ሰንበት ትምህርት ቤቱ ተቀናጅተው እየሠሩ የሚገኙ ሲሆን ይህ አውደ ርዕይ የመርሐ ግብሩ አንድ አካል መሆኑን አዘጋጆቹ ገልጸዋል፡፡
ዓውደ ርዕዩ ካካተታቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል
- የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልዕኮ
- ቅዱሳት ስዕላት
- ዝክረ ቅዱስ የሬድ
- የሰንበት ትምህርት ቤት አገልግሎት በቤተ ክርስትያን የሚሉ ይገኙበታል፡፡
ግንቦት 5 ቀን 2004 ዓ.ም. ከቅዳሴ በኋላ በተከናወነው የአውደ ርዕይ መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ የደብሩ አስተዳደር፤ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ፣ የስብከተ ወንጌል ጽ/ቤትና የደብሩ ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት እንዲሁም ምዕመናን በተገኙበት በድምቀት ተከፍቷል፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አባቶችና የሰንበት ትምህርት ቤቱ አባላት ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም የአውደ ርእዩ አዘጋጆች የሆኑት የሰንበት ት/ቤቱና የስብከተ ወንጌል ጽ/ቤቶች ምእመናን በቤተክርስቲያኑ ተገኝተው ለአንድ ሳምንት የሚቆየውን አውደ ርእይ እንዲመለከቱ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡