የቅዱስ ያሬድን ፲፭፻፫ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የቅኔ ውድድር ተካሔደ፡፡
ግንቦት ፳፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
በጎንደር ማእከል
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ት/ቤተፐች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በጎንደር ማእከል አዘጋጅነት ግንቦት ፲፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም የቅዱስ ያሬድን ፲፭፻፫ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በጎንደር ከተማ በርእሰ አድባራት ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የቅኔ ውድድር ተካሔደ፡፡
የውድድሩ ተሳታፊ ጉባኤ ቤቶች፡- የደብረ ፀሐይ ቍስቋም ማርያም፣ የደብረ ምሕረት አቡን ቤት ቅዱስ ገብርኤል፣ የቀዳሜ አድባራት አበራ ጊዮርጊስ፣ የመካነ ሕይወት ፊት አቦ እና የደብረ ገነት አዘዞ ቅዱስ ሚካኤል ቅኔ ጉባኤ ቤቶች ሲኾኑ፣ መምህራኑ የመረጧቸው ደቀ መዛሙርትም ጉባኤ ቤቶቹን ወክለው ለውድድር ቀርበዋል፡፡
ውድድሩን በዳኝነት የመሩትም መምህር ፍቅረ ማርያም የመንበረ መንግሥት መድኃኔ ዓለም የ፬ቱ ጉባኤያት ምክትል መምህር፣ ሊቀ ብርሃናት ኤልያስ አድማሴ በዐቢየ እግዚእ ኪዳነ ምሕረት የብሉይ ኪዳን መምህር እና መምህር ቃለ ሕይወት በመካነ ነገሥት ግምጃ ቤት የሐዲስ ኪዳን መምህር ሲኾኑ የውድድሩ መሥፈርቶችም አንደኛ የቅኔው ምሥጢር፣ ሁለተኛ የዜማው ልክ፣ ሦስተኛ ገቢር ተገብሮ አገባብ፣ አራተኛ የቃላት አመራረጥ እና አምስተኛ የጊዜ አጠቃቀም ናቸው፡፡ እያንዳንዱ መሥፈርት ፳፣ ባጠቃላይም ፻ ነጥቦችን የያዘ ሲኾን ለእያንዳንዱ ተወዳዳሪም የ፲፭ ደቂቃ የማቅረቢያ ጊዜ ተሰጥቶታል፡፡
በውድድሩ ከአንደኛ አስከ ሦስተኛ ደረጃ የያዙት የወንጌል አንድምታ ትርጓሜ መጻሕፍትን፤ አራተኛና አምስተኛ የወጡት ደግሞ የትንቢተ ኢሳይያስን አንድምታ ትርጓሜ መጽሐፍ ተሸልመዋል፡፡ ይኸውም ቅኔ ተምረናል በቃን ብለው እንዳያቆሙ እና ቀጣይ መጻሕፍትን እንዲማሩ ለማሳሰብ ነው፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የማእከሉ ሰብሳቢ መምህር ዓለማየሁ ይደግ እንደተናገሩት የውድድር መርሐ ግብሩ የተዘጋጀበት ዓላማ በጉባኤ ቤቶች መካከል መልካም የሆነ የውድድር መንፈስ እንዲኖር፣ ተማሪዎቹ ራሳቸውን እንዲፈትሹ ለማድረግ፣ የቅኔ ትምህርት በማኅበረሰቡ ዘንድ እንዲታወቅ፣ የበታቾቻቸውን ለማነሣሣት እና በዋናነት ቅዱስ ያሬድን ለመዘከር ነው፡፡
የጎንደር ከተማ ወረዳ ቤተ ክህነት ሊቀ ካህናት ሊቀ አእላፍ ጥበበ አወቀ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው እንደዚህ ዓይነቱ መርሐ ግብር እየቀዘቀዘ የመጣውን የአብነት ትምህርት በተለይ የቅኔ ትምህርት እንደሚያጠናክር ጠቅሰው ይህም ማኅበረ ቅዱሳንን እንደሚያስመሰግነው ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ለደቀ መዛሙርቱ አባቶቻችን ይህን ትምህርት በእግዚአብሔር ኃይል ጸንተው፣ ኮቸሮ በልተው፣ በውሻ ተበልተው አቆይተውናል፤ እኛም ጠብቀን ለትውልድ ማቆየት ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ በስድስቱም ጉባኤ ቤቶች የሚገኙ በርካታ የአብነት ተማሪዎች እና በርካታ ምእመናን የተገኙ ሲኾን፣ ከምእመናኑም ይህ የቅኔ ትምህርት እንዲስፋፋ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራ እንደሚገባው አስተያየት ተሰጥቷል፡፡
የጎንደር ማእከል መዘምራንም ቅዱስ ያሬድን የሚዘክሩ የሰማይ ምስጋና የሚል የንስሐ መዝሙር እና ያሬድ ማኅሌታይ ለእግዚአብሔር ካህኑ የሚል ወረብ አቅርበዋል፡፡
የመርሐ ግብሩ መምህር በጽሐ ዓለሙ በመንበረ መንግሥት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የ፬ቱ ጉባኤያት ምክትል መምህር በአብነት ትምህርት ቤት ሦስት ዓይነት ተማሪ አለ፤ እነሱም፡- እግረ ተማሪ፣ ልብሰ ተማሪ እና ልበ ተማሪ ናቸው ካሉ በኋላ ኹላችንም ልበ ተማሪን ኾነን ትምህርታችንን በሚገባ መማር አለብን ብለዋል፡፡
በመጨረሻም በአባቶች ጸሎት መርሐ ግብሩ ተጠናቋል፡፡ ይህ መርሐ ግብር በፋና ኤፍ ኤም 98.1 የሬድዮ ጣቢያም የሚዲያ ሽፋን ማግኘቱ የሚታወስ ነው፡፡