የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከቤተ ክርስቲያን በውግዘት ተለይተው የነበሩትን የዐሥራ ሰባቱ አባቶች ውግዘት ማንሳቱን በመግለጫው አሳወቀ።

ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ ቀደም ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ክህነት ውጭ በሆነ መንገድ በራሳቸው ሥልጣንና በይገባናል ስሞታ የኦሮሚያ ሲኖዶስ መሥርተናል በሚል ተልእኮ ሲንቀሳቀሱ ቢቆዮም በይቅርታ መመለሳቸውን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ይህን ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል፡፡

በዚህም መሠረት ከመጋቢት ፳፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. ጀምሮ የሦስቱን አባቶችና የሃያዎቹን መነኮሳት ውግዘት ቅዱስ ሲኖዶሱ ማንሣቱ የታወቀ ሲሆን ውግዘቱ የተነሳላቸውም አባቶች ቀድሞ ቤተ ክርስቲያን በሰጠቻቸው ማዕረግ እንደሚጠሩም ገልጿል።

በመሆኑም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ተብለው እንደሚጠሩ እንዲሁም ወደ ነበሩበት አገልሎታቸው እንደሚመለሱ ታውቋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሃያዎቹ መነኮሳትም አስቀድሞ ቤተ ክርስቲያን በሰጠቻቸው ስም እና አገልግሎት እንዲያገለግሉ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል።

የቅዱስ ሲኖዶሱ መግለጫ እንደሚከተለው ነው፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

 ጥር ፲፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሐሮ ባለወልድ ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመውን ሕገወጥ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመትን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጥር ፲፰ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የተከናወነው ድርጊት የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማ፣ ቀኖና አስተዳደራዊ መዋቅር የጣሰ ሕገወጥ አድራጎት መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶ በመወያየት ሕገወጡን ሹመት ያከናወኑትና ተሿሚዎችን በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖናዊ ሥርዓት ከዲቁና ጀምሮ የነበራቸውን ማዕረገ ክህነት በሙሉ በመሻር ከቤተ ክርስቲያኒቱ አባልነት አውግዞ መለየቱ የሚታወስ ነው፡፡

ምንም እንኳን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በውሳኔው ውግዘቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በድርጊታቸው ተጸጽተው እና ከስህተታቸው ተመልሰው በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት መሠረት የሚሰጣቸውን ቀኖና ተቀብሎ ለመመለስ ዝግጁ ከሆኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ የይቅርታ በር ክፍት መሆኑን በማሳወቅ መግለጫ የሰጠ ቢሆንም ግለሰቦቹ ከስህተታቸው ተምረው በይቅርታ እድሉ ከመጠቀም ይልቅ በሕገወጥ መንገዱ ቀጥለውና ውግዘቱን ጥሰው በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ መዋቅራዊ አደረጃጀት መሠረት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ሲኖዶስ ተመድበው በሚያገለግሉባቸው አህጉረ ስብከት ላይ እርስ በርሳቸው በመመዳደብ እያደረጉት የነበረውን ሕገወጥ እንቅስቃሴ መንግስት በሕግ የተጠላበትን ሕግን የማስከበር ኃላፊነት በመወጣት የቤተ ክርስቲያናችንን ተቋማዊ ልዕልና እንዲያስከብርልን ከመግለጫም አልፎ በደብዳቤ ያቀረብነው ጥያቄ ተቀባይነት አጥቶ በሕገወጥ መንገድ የተሾሙት ግለሰቦች በመንግሥታዊ የፀጥታ አካላት ታጅበው በኦሮምያ ክልል የሚገኙትን አህጉረ ስብከት፣ ወረዳ ቤተ ክህነት፣ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን በኃይል ሰብረው ተቋማቱን በመውረር ሀብትና ንብረት የተዘረፈ ሲሆን ይህም ሕገወጥ ድርጊት በሚከናወንበት ወቅት ሕገ ቤተ ክርስቲያናችን አይጣስም፣ ሲኖዶሳችን አይከፈልም፣ ቀኖናችን አይደፈርም በማለት በጽናትና በአንድነት ድርጊቱን የተቃወሙት ምዕመናን፣ ወጣቶችና አገልጋይ ካህናት እንዲሁም በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልዩ ልዩ የሥራ ኃፊዎች በተለይም የሻሸመኔና አካባቢው ምእመናንና አገልጋይ ካህናት ለሞት፣ ለአካልና የሞራል ጉዳት፣ ለእስራትና እንግልት ተዳርገዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ቅዱስ ሲኖዶስ ችግሩን እና ፈተናውን የማሳለፍ ሥልጣን ሁሉ ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን በምሕረት አይኑ ተመልክቶ የመጣውን ፈተና ያስወግድልን ዘንድ በጾመ ነነዌ ለሦስት ቀናት ሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ እምነት ተከታዮች ማቅ ለብሰው በጸሎትና በምህላ ወደ እግዚአብሔር እንዲያመለክቱ በወሰነው መሠረት በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ተፈጽሞ በማያውቅ ሁኔታ እንኳንስ ልጆቿ ምእመናን ይቅርና እራሷ እናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም የሀዘን መገለጫ የሆነውን ጥቁር ማቅ ለብሳ ከሀገር አቀፍም አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀዘኗን ገልጣለች፡፡

የእናት ቤተ ክርስቲያንና የልጆቿ ምዕመናን እንባና ጸሎት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ ለውይይት ዝግ የነበረው የመንግስታችን በር ለውይይት ተከፍቷል፡፡ የደረሠብን የጉዳት ከፍተኛነት በሀገራችን መንግሥታዊ ሚዲያዎች ዘንድ ቦታ ቢያጣም አለም አቀፍ ሚዲያዎችና የቤተ ክርስቲያናችን የሚዲያ ተቋማት ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ እንዲደርስ በማድረጋቸው ችግሩን ከእኛም አልፎ በሁሉም አኃት አብያተ ክርስቲያናት፣ የአለም አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት፣ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት እና ሌሎች ሲቢክ ማህበራት ድርጊቱን በማውገዝ ለእናት ቤተ ክርስቲያናችን ያላቸውን አጋርነት ገልጸዋል፡፡ በዚህም በችግራችን ወቅት ከጎናችን ለቆሙት አካላት በሙሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አሁንም በድጋሚ ከፍ ያለ ምስጋናዋን ታቀርባለች፡፡

በመጠቀልም ክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ባመቻቹት የውይይት መድረክ በተወከሉ ብፁዓን አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በኩል በተደረገው መጠነ ሰፊ ውይይት መሠረት ባለ ዐሥር ነጥቦች ላይ የጋራ ስምምነት በተደረሰው መሠረት ሦስቱ የቀድሞ አባቶች የካቲት ፰ ቀን  ፳፻፲፭ ዓ.ም. ወደ ጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ መጥተው በቀድሞ በዓታቸው ተወስነው እስካሁን የቆዩ ሲሆን ሃያዎቹ ተሿሟዎች ደግሞ በስምምነቱ መሠረት ለውሳኔው ተገዥ መሆናቸውን በመግለጽ መጋቢት ፲፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. እያንዳንዳቸው በጽሑፍ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት ባቀረቡት መሠረት ውግዘቱ እንዴት ሊፈታ እንደሚገባ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ጉባኤ የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርብ በታዘዘው መሠረት የቤተ ክርስቲያኒቱን የቀኖና ቅዱሳት መጻሕፍት ዋቢ በማድረግ የውሳኔ ሐሳቡን ያቀረበ ሲሆን እንደሚከተለው በአጭሩ ተገልጿል፡፡

ሀ. “ኢይክል ሰብእ ነሢአ ፀጋ ለሊሁ ወኢምንተኒ እመ ኢተውህበ ሎቱ እምሰማይ” ሰው ከእግዚአብሔር ካልተሰጠው በስተቀር እርሱ ራሱ ጸጋን ገንዘብ ማድረግ አይችልም” (ዮሐ.፫፥፳፯) በማለት በቅዱስ ወንጌል እንደተነገረው የእግዚአብሔር ጸጋ ከላይ የሚሰጠው በቅንነት፣ በትሕትና፣ በትዕግሥትና በጸሎት በመሳሰለው እንጅ በሥርዓተ አልበኝነትና በሕገወጥ የድፍረት መንገድ የሚገኝ የእግዚአብሔር ጸጋ የለም፤ አልኖርም፤ አልነበረም፤ ወደፊትም አይኖርም፡፡

ለ. ብርሃና ለቤተ ክርስቲያን የተባለው ደጉ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስም “ወአልቦ ዘይነሥእ ክብረ ለርእሱ ዘእንበለ ዘጸውዖ እግዚአብሔር በከመ አሮን” እንደ አሮን በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር ማንም ክብርን ለራሱ የሚወስድ የለም ሲል ክብረ ክህነትን በሚገባ ገልጿል፡፡ (ዕብ.፭፥፬) እንዲህም በመሆኑ በአሁኑ ሰዓት ከቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ውጭና ቅዱስ ፓትርያርኩ በሌሉበት በድብቅ የተፈጸመው ሕገወጥ ሢመተ ክህነት ለሿሚውም ሆነ ለተሿሚው የእግዚአብሔርን ጸጋ በራስ ፈቃድ እንደመውሰድ ስለሚቆጠር ከፍተኛ የሆነ የዶግማ ጥሰት ተግባር ነው፡፡

ሐ. ከቅዱስ ቃሉ እንደተማርነው “ቀዳሚሃ ለጥበብ ፈሪሀ እግዚአብሔር፤ የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” (መዝ.፻፱፥፲፣ ምሳ.፩፥፯) ይህንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል መሠረት በማድረግ “ስግዱ ለእግዚአብሔር በፍርሃት፤ ለእግዚአብሔር በፍርሃት ስገዱ” (መዝ.፳፰፥፪)፣ ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት፤ ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ” (መዝ.፪፥፲፩)፣ “ንትነሣእ በፍርሃተ እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔርን በመፍራት እንነሣ (ቅዳ.ማ)” በማለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እስከ እስትንፋሰ ደኃሪት መልእክቷን ዘወትር ታስተላልፋለች፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ይህ ሆኖ እያለ አሁን የተፈጸመው ድርጊት ግን በከፍተኛ ድፍረትና በሕገወጥ መንገድ ከመፈጸሙና የሥልጣነ ክህነትን ክብር ከማጉደፉም በላይ ከውግዘትም በኋላ ከጥፋቱ ባለመማር ሕገወጥነትን እንደ ሕጋዊነት፣ ጥፋትን እንደ ልማት፣ ሐሰትን እንደ እውነት፣ የነፍስ ጥፋትን እንደ ነፍስ ማዳን ተቆጥሮ በልበሙሉነት የአህጉረ ስብከትና የአጥቢያ አበያተ ክርስቲያናት በር በኃይል ተሰብሮ የመውረር ሕገወጥ ተግባር ተፈጽሟል፡፡ ይህም ድርጊት ከውግዘት በኋላ በመሆኑ ሕገ እግዚአብሔርን እያወቁ ወደጎን በመተው የተፈጸመ ድርጊት በመሆኑ የዶግማ ጥሰት ነው፡፡

መ. ቅዱሳን ሐዋርያት ከወሰኗቸው የሕግጋት መጻሕፍት መካከል አንዱ በሆነው በመጽሐፈ ዲድስቅልያ አንቀጽ አንድ ንዑስ አንቀጽ ሁለት ላይ “ወአዘዝነ ከመዝ መዓርገ ሢመታት ለቤተ ክርስቲያን በአርአያ ዘበሰማያት የቤተ ክርስቲያናችን የሹመቶች መዓርግ በሰማያት ባለው አምሳል እንዲሆን አዘዝን” በማለት በንዑስ አንቀጽ ሦስት ላይ “ወንሕነ ንጌሥጽክሙ ከመ ይንበር ኲሉ ለለ አሐዱ አሐዱ እምኔክሙ ውስተ ዘተጸውዐ እምኀበ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ – ከእናንተ ሁሉ እያንዳንዱ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ በተጠራበት ተልእኮ ጸንቶ ይኖር ዘንድ እኛ እንመክራችኋለን በማለት እያንዳንዱ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን በተሰጠው ፀጋና ተልእኮ ጸንቶ ከሚኖር በቀር ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ ባልተሰጠውና ባልተፈቀደለት በሕገወጥ መንገድ ሊሾምም ሆነ ሊሾም እንደማይገባው የሚያስተምረን አምላካዊ ቃል ነው፡፡

ሠ. ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በመጽሐፈ ዲድስቅልያ አንቀጽ ፳ ላይ “በእንተ ዘይሰየም በህልያን እመሂ ኤጲስ ቆጶስ አው ቀሲስ አው ዲያቆን ዘይእኀዝ መዓርገ ሢመት በሕልያን ይሰአር፤ ወይሰዐር ዘሤሞሂ ወይትመተር ለዝሉፉ እምሥርዐተ ክህነት፤ ወኢይሳተፍዎ ወኢበምንትኒ በከመ ረሰይክዎ ለሲሞን መሠርይ እምኀቤየ አነ ጴጥሮስ – መማለጃ በመስጠት ስለሚሾም ኤጲስ ቆጶስ ወይም ቄስ ወይም ዲያቆን ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ የሹመት መዓርግ ቢይዝ ይሻር፣ የሾመውም ይሻር ከክህነት ሥርዓትም እስከ መጨረሻው ይባረር፡፡ እኔ ጴጥሮስ ጠንቋዩ ሊሞንን እንዳደረግሁት በምንም ነገር አያሳትፉት (ሲኖ.ዘሐዋ.ክፍል ሦስት ቁጥር ፳) በማለት ቅዱስ ጴጥሮስ ሥልጣነ ክህነትን ያለአግባብ የሰጠም ሆነ የተቀበለ አካል እስከመጨረሻው ድረስ ከሥርዓተ ክህነት ውጭ እንዲሆን አውግዟል፡፡ በማለትና ሌሎችንም ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ዋቢ በማድረግ በሊቃውንት ጉባኤ የቀረበውን የውሳኔ ምክረ ሐሳብ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በአድናቆትና በአክብሮት ተቀብሎ ተወያይቶበታል፡፡

በመሆኑም ከላይ ቀኖና ሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት አድርጎ ከቀረበው ምክረ ሐሳብና በቤተ ክርስቲያኒቱና በምዕመናን ላይ ከደረሰው ሞት፣ የአካልና የሞራል ጉዳት፣ እስራትና እንግልት አንጻር ውግዘቱ ሊነሣ የማይገባውና በሕግም የሚያስጠይቅ ሕገወጥ አድራጎት ቢሆንም አሁን በተከሰተው ድርጊት በአጭር ጊዜ ውስጥ በእናት ቤተ ክርስቲያን ላይ እና በተከታዮቿ ምዕመናንና አገልጋዮቿ ላይ ከደረሰው ከፍተኛ ጉዳት አንጻር ችግሩን በሆደ ሰፊነትና በይቅርባይነት መፍታት ካልተቻለ አሁን ያለው መከራና ችግር ይቀጥል ቢባል በቀጣይ በቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነትና ሐዋርያዊ ተልዕኮ እንዲሁም በምዕመናንና አገልጋዮቿ ሰላማዊ ጉሮ ላይ የሚያደርሰውን ከፍተኛ የሆነ አደጋ ከግምት ውስጥ በማስገባት እና ካሁን ቀደም ክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በተገኙበትና በመቀጠልም ክቡር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት በተገኙበት በተደረገው ውይይት በተደረሰው ዐሥሩ የስምምነት ነጥቦች መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ በስፋት ከተወያየ በኋላ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡

፩.የካቲት ፰ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. በክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ መሪነት ወደ ጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ በመምጣት እስካሁን ድረስ በበዓታቸው ጸንተው የቆዩት ሦስቱም የቀድሞ ሊቃነ ጳጳሳት ማለትም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ እና ብፁዕ አቡነ ዜናማርቆስ ላይ አስቀድሞ ጥር ፲፰ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተላለፈው ውግዘት ከዛሬ መጋቢት ፳፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. ጀምሮ ተነሥቷል፡፡

፪. ውግዘቱ የተነሣላቸው ሦስቱም ሊቃነ ጳጳሳት ከዛሬ መጋቢት ፳፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. ጀምሮ በቀድሞ የሊቀ ጳጳስነት ማዕረጋቸውና ስማቸው ማለትም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ሊቀጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሊቀጳጳስ እና ብፁዕ አቡነ ዜናማርቆስ ሊቀጳጳስ ተብለው እንዲጠሩና አስቀድሞ ተመድበው ይሰሩበት በነበረው የሥራ ኃላፊነታቸው ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

፫. ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት በተደረገው ውይይት በተደረሰው ስምምነት መሠረት ጥሪውን ተቀብለው ለስምምነቱ ተገዥ በመሆን በጽሑፍ ጥያቄያቸውን ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት ያቀረቡት ሃያዎቹ የቀድሞ መነኮሳት ጥር ፲፰ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ የተላለፈው ውግዘት ከዛሬ መጋቢት ፳፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. ጀምሮ ተነሥቷል፡፡ ቀሪዎቹ አምስቱ ባለው ጊዜ ተጠቅመው ወደቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመለሱ ቅዱስ ሲኖዶስ በድጋሚ እያሳሰበ ውግዘቱን በሚመለከት በቋሚ ሲኖዶስ በኩል ታይቶ እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

፬. ውግዘቱ የተነሣላቸው ሃያዎቹም የቀድሞ መነኮሳት አስቀድሞ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ከዲቁና እስከ ቁምስና ባለው ማዕረገ ክህነታቸው እንዲያገለግሉ እና በምንኩስና ስማቸውም እንዲጠሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

፭. ሃያዎቹ የቀድሞ መነኮሳት የሥራ ምደባን በተመለከተ በተደረሰው ስምምነት መሠረት በቀድሞው የሥራ መደብ ደረጃቸው እንዲመደቡ ቅዱስ ሲኖዶስ በመወሰን ዝርዝር ጉዳዩ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በኩል እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ አዟል፡

፮.በተከሰተው ሕገወጥ ድርጊት መነሻነት ለቤተ ክርስቲያናችን ክብርና ልዕልና ሲሉ ለሞት፣ ለአካልና የሞራል ጉዳት፣ ለእስራትና እንግልት እንዲሁም ለስደት የተዳረጉትን ምዕመናን፣ ወጣቶች፣ አገልጋይ ካህትና ከሀገረ ስብከት እስከ አጥቢያ ያሉ የሥራ ኃላፊዎችን ጉዳትና  መከራ እንዲሁም ችግሩን በሕግ አግባብ እንዲፈታና የቤተ ክርስቲያኒቱ መብትና ጥቅም እንዲከበር ሌሊት ከቀን በማገልገል ላይ የሚገኙትን የሕግ ባለሙያዎች ማህበር የሰጡትን ሙያዊ አገልግሎት ቅዱስ ሲኖዶስ ዘወትር በከባድ ሐዘንና ጸሎት ሲያስታውሰው የሚኖርና በቀጣይ በቤተ ክርስቲያኒቱ የታሪክ መዛግብት ተመዘግቦ ለቀጣዩ ትውልድ መማሪያነት እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

፯. ውግዘቱ የተነሣላችሁ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋይ አባቶችም በቀጣይ በፈጸማችሁት ድርጊት የተጎዳውን መላው ሕዝበ ክርስቲያን እና ክብሯ የተደፈረውን እናት ቤተ ክርስቲያናችሁን ሊክስ በሚችል የትሕትና መንፈስ በማገልገልና ዳግመኛ ከእንዲህ ዓይነቱ ሕገወጥ አድራጎት በመራቅ የተጣለባችሁን ከፍተኛ ኃላፊነት በታማኝነት እንድትወጡ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ያሳስባል፡፡

፰. በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የደረሰውን ፈተና እንዲወገድና የቤተ ክርስቲያኒቱ መብትና ክብር እንዲጠበቅ ቤተ ክርስቲያኒቱን ወክላችሁ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሩት የውይይት መድረክ ላይ በመሳተፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከታችሁ ሦስቱ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ እና ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል እና አቀራራቢ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም በፍትሕ አደባባይ ክስ በመመስረት የደከማችሁ የሕግ ባለሙያዎች ማህበር እና ችግሩን ለመላው ዓለም በማዳረስ ሰፊ ሥራ የሠራችሁ የሚዲያ ተቋማትን ቅዱስ ሲኖዶስ ለሰጣችሁት ታሪክ የማይረሳው አገልግሎት በእጅጉ ያመሰግናል፡፡

፱. ምንም እንኳን አስቀድሞ ከክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ እና ክቡር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት ጋር በተደረገው ውይይትና ስምምነት መሠረት የታሰሩት ግለሰቦች በሙሉ እንደሚፈቱ ቃል የተገባ ቢሆንም እስካሁን ድረስ በርካታ ሰዎች በእስር ላይ የሚገኙ ስለሆነ መንግስት አስቀድሞ በገባው ቃል መሠረት ሁሉንም እስረኞች እንዲፈታልን ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ያሳስባል፡፡

፲. በተከሰተው ችግር ከሀገረ ስብከት እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ባሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ላይ በኃላፊነት ተመድበው ሲሰሩ ቆይተው በችግሩ ምክንያት ተፈናቅለው የቆዩት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሀገረ ስብከትና የወረዳ ቤተ ክህነት ሠራተኞች ያለምንም የፀጥታ ስጋት በምድብ ሥራቸው ላይ እንዲቀጥሉ ከፌዴራል ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የመንግስት አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡

መጋቢት ፳፩ ቀን ፳፻፲፭ ..

አዲስ አበባ

ኢትዮጵያ