የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ቢያደርገው የምንላቸው ነጥቦች

ጥቅምት 12 ቀን 2005 ዓ.ም.

 

ቅዱስ ሲኖዶስ ኤጲስ ቆጶሳት የያዘውን፣ የታወቀ ሕጋዊ መንበር፣ ታሪካዊና ሕጋዊ መሠረት እንዲኖረው ሆኖ የተደራጀውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምልዐተ ጉባኤ ነው፡፡ ይህ ምልዐተ ጉባኤ ለአንዲቷ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አንድነትና ልዕልና እጅግ አስፈላጊና አንድ ነው፡፡

 

አስፈላጊነቱም የሚመነጨውና የሚረጋገጠው በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ፣ የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ በመሆኑና ውሳኔዎች ሁሉ ይግባኝ የሌለባቸው ከመሆኑ ላይ ነው፡፡ ሐዋርያት ከክርስቶስ፤ ሐዋርያነ አበውና ሊቃውንት ከሐዋርያት፣ እኛም ከእነዚህ ሁሉ የወረስናቸውን መሠረተ እምነት፣ ሥርዐተ አምልኮና ትውፊት የሚጠብቅና የሚያስጠብቅ ዐቃቤ ሃይማኖት ነው፡፡

 

በዚህ መነሻነት የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ የሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት በዓመት ሁለት ጊዜ ይሰበሰባል፡፡ በጥቅምትና በግንቦት ርክበ ካህናት፡፡ በሁለቱም ጉባኤያት በመንፈስ ቅዱስ መመራቱንና የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ መሆኑን የሚያረጋግጡ ውሳኔዎች እንዲያሳልፍ ይጠበቃል፡፡ የሚወሰነውም ውሳኔ እንከን እንዳይኖርበት በፍጹም መንፈሳዊነት ተገቢ ጥንቃቄም እንዲያደርግ ይጠበቃል፡፡

 

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ መደበኛ ስብሰባ እንዲሁም እንደ አስፈላጊነቱ ልዩ ስብሰባ በማካሄድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና፣ አመራር፣ አስተዳደር፣ እርምጃና ፖሊሲ ሁሉ የሚወሰን የመጨረሻው አካል እንደመሆኑ ምልዐተ ጉባኤው ፍሬያማና ውጤታማ ተግባራት የሚከናወኑበት ሊሆን እንደሚገባም ይታመናል፡፡

 

በዚሁ መሠረት ቤተ ክርስቲያናችን በምልዐተ ጉባኤው ውሳኔና የውሳኔ አፈጻጸም ተጠቃሚ መሆኗ እንዲረጋገጥ አጥብቀን እንሻለን፡፡ በተነጻጻሪም ከጥቅምት 12 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚካሔድ የሚጠበቀው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ይህን እውን ሆኖ እንዲያሳየን ይጠበቃል፡፡ አጀንዳውም ከዚህ አንጻር ቢቃኝ ተገቢ ነው፡፡

 

በዚህ የአጀንዳ ቅኝት ተገቢነትና ወቅታዊነት አግባብ በአጀንዳነት ተወያይቶበት ውሳኔ እንዲያሳልፍባቸው እንደ ልጅነት የምንሻቸው አጀንዳዊ ውሳኔዎች ውስጥ ዐበይቶቹ በአምስት ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡ እርቀ ሰላምና የስድስተኛው ፓትርያርክ ሹመት አጠቃላይ አፈጻጸም፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያን የሚሻሻልበትንና ቤተ ክርስቲያናችን ቋሚ የምርጫ ሕግ ባለቤት የምትሆነበትን አገባብ መወሰን፤ ተግባሩና ሓላፊነቱ በግልጽ የተቀመጠለት የቴክኒክ አካል መሰየምና በአምስተኛ ዘመነ ፕትርክና በይደር በተያዙ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ እንዲወሰን የቤተ ክርስቲያን ልጅነት አሳባችንን እናቀርባለን፡፡

 

ከእነዚህም በተጨማሪ ከአምስተኛው ፓትርያርክ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዕረፍት በኋላ በዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክነት የተሾሙት ብፁዕ አቡነ ናትናኤልም ሆኑ የቋሚ ሲኖዶሱን አፈጻጸም መገምገምና ውሳኔ ሊሰጥባቸው የሚገቡ ክስተቶች ላይም ውሳኔ ከመስጠትም በላይ ቀጣዩን የአተገባበር ፍኖተ ካርታ /Roadmap/ ተጠያቂነት በሚያጎናጽፍ አግባብ ቢያስቀምጥ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት ገንቢ ሚና ይኖረዋል ብለን እናምናለን፡፡

 

ምእመኑም ትናንት የቅዱስ ሲኖዶስን የምሕላ ዓዋጅ ተቀበሎ እንደመፈጸሙ ቀጣዩንም ውሳኔዎቹን መፈጸም ይገባዋል፡፡ ከአባቶቻችን ጎን በመሆን የልጅነት ድርሻውን ቢወጣ እንላለን፡፡

 

ቤተ ክርስቲያናችን በኲለንታዋ ወደቀደመ ክብሯና ልዕልናዋ እንድትመለስ የምልዐተ ጉባኤው ድርሻ በሙቀተ መንፈስ ቅዱስ ዘመኑን የዋጀ ውሳኔ መወሰንና አተገባበሩን መከታተል፤ የቤተ ክህነቱ መዋቅር ድርሻ ውሳኔዎቹን ማስፈጸምና ምቹ መደላድል መፍጠር ሲሆን የምእመኑ ድርሻ ደግሞ ለውሳኔው ተፈጻሚነት ምልዐተ ጉባኤውንም ሆነ የቤተ ክህነቱን መዋቅር በሁሉም መደገፍ ያስፈልጋል፡፡

 

ስለዚህ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ውሳኔን መቀበል የቤተ ክርስቲያናችን የአንዲትነት፣ ሐዋርያነት፣ ቅድስትነትና ኲላዊነት መገለጫ ነውና ውሳኔዎቹን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ ሁላችንም የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁ እንድንሆን ያስፈልጋል፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር


  • ምንጭ፡- ጽምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 20ኛ ዓመት ቁጥር 3 ከጥቅምት 16-30 2005 ዓ.ም.