የቃና ዘገሊላ ሰርግ

ጥር፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

ዲያቆን ወልዳይ መረሳ

በአዲስ ኪዳን የዮሐንስ ወንጌል ላይ እንደተጠቀሰው ዶኪማስ ሰርግ ባደረገበት ወቅት ድንግል ማርያምና ጌታ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የታደሙባት (ዮሐ ፪፥፩-፲፩ )፣ እንዲሁም የሐዋርያው ናትናኤል የትውልድ ሀገር ገሊላ ናት (ዮሐ ፳፩፥፪ )። ጌታ በዚሁ ስፍራ ሆኖ በመናገር በቅፍርናሆም ታሞ የነበረውን የሹሙን ልጅ ከሕመሙ ፈውሶታል። (ዮሐ ፬፥፵፫-፶፬ )

ቤተ ክርስቲያን በዓላትን በቅዱሳን ስም፣ በዕለቱ በተፈጸመው ድርጊት ወይም በቦታ ስም ትሰይማለች። ይህም “በአዳሪው ስም ማደሪያው ይሰየማል” እንደሚባለው እንጂ፣ ተአምራቱን የፈጸመው ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

ቤተ ክርስቲያንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረትን ተከትላ ጌታ ለገለጠበት ስፍራ ክብርና ቅድስና በመስጠት በዓሉን በቦታው ስም “ቃና ዘገሊላ” ብላ ታከብራለች። (ዘጸ.፫፥፭፣ ፪ ጴጥ. ፩፥፲፰) ምንም እንኳን በቃና የተደረገው ተአምር ጌታ ተጠምቆ በቆሮንቶስ ገዳም ከተፈተነ በኋላ በየካቲት ወር የተፈጸመ ቢሆንም የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ግን “የውኃውን በዓል ከውኃ በዓል ጋር” በማዛመድ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ከጥምቀት ማግስት እንዲከበር አድርገዋል።

በዚህም መሠረት የቃና ዘገሊላ በዓል ከዘጠኙ የጌታ ንኡሳን በዓላት አንዱ ሆኖ ከዋዜማው ጀምሮ በዝማሬና በቅዳሴ በድምቀት ይከበራል። በዕለቱ የሚቀርቡት ንባባትና ዜማዎችም በቃና ዘገሊላ የተደረገውን ተአምርና ምሥጢር የሚዘክሩ ናቸው። ቤተ ክርስቲያናችን በዛሬው ዕለት የምታቀርባቸው ዝማሬዎችና የቅዱስ መጽሐፍ ንባባት በአንድ ዋና ነጥብ ላይ ያተኩራሉ፤ ይህም በቃና ዘገሊላ የተከናወነው የመጀመሪያው ተአምርና በውስጡ የያዘው ጥልቅ ምሥጢር ነው። ይህ ታሪክ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፪ ከቁጥር ፩-፲፩ ላይ በስፋት ተመዝግቦ ይገኛል። ምንም እንኳን የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የዚህን ወንጌል ትርጓሜ እጅግ ረቂቅና ሰፊ በሆነ ምሥጢር ቢተነትኑትም፣ እኛ ግን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድና እንደ አቅማችን መጠን እነርሱ ካስተማሩት ጥቂቱን እንደሚከተለው በአጭሩ እንመለከታለን።

 የቃና ዘገሊላ ሰርግ

በሦስተኛው ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበር፤ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ። የወይን ጠጅ ባለቀ ጊዜ እናቱ “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” አለችው። እርሱም “አንቺ ሴት፣ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም” አላት። እናቱም አገልጋዮቹን “እርሱ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” አለቻቸው። በዚያም እንደ አይሁድ ሥርዓት ለመንጻት የሚሆኑ ስድስት የድንጋይ ጋኖች ነበሩ። ኢየሱስም “ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው” አላቸው፤ እስከ አፋቸውም ሞሏቸው። “አሁን ቀድታችሁ ለሰርግ አዘጋጁ (ለአሳላፊው) ስጡት” አላቸው።አሳላፊውም ወደ ወይን የተለወጠውን ውኃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደመጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር። አሳላፊውም ሙሽራውን ጠርቶ “ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን ወይን ያቀርባል፣ ከጠጡ በኋላ ግን የተለወጠውን (መካከለኛውን) ያቀርባል፤ አንተ ግን መልካሙን ወይን እስከ አሁን አቆይተሃል” አለው።

ኢየሱስ ይህን የመጀመርያ ተአምር በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ። (ዮሐ ፪፥፩-፲፩) በዚህ ቅዱስ ሰርግ ላይ የጌታ ትሕትና ተገልጦበታል፤ ክብሩ ታውቋል፤ የድንግል ማርያም ርኅራኄና አማላጅነት ታይቷል፤ የጋብቻ (የምሥጢረ ተክሊል) ክብርም በተግባር ትምህርቱ ተሰጥቶበታል።

የጌታ ትሕትና መገለጥ

ክርስቶስ በቤተልሔም በከብቶች ግርግም ተወልዶ፣ በዮርዳኖስም በባሪያውና በአገልጋዩ በዮሐንስ እጅ ተጠምቆ የትሕትና አባት መሆኑ በሁሉ ዘንድ የታወቀ ነው። አሁን ደግሞ “ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ (ድሀ አደረገ)” ተብሎ እንደተጻፈው፤ (ፊል ፪፥፯) በፍጥረታቱና በባሪያዎቹ ሠርግ ላይ እንደ ዋና የክብር እንግዳ ሳይሆን እንደ ማንኛውም እንግዳ ተገኘ። ያውም የወይን ጠጅ እንኳ ለታዳሚዎቻቸው በማያበቃቸው በድሆች የሰርግ ቤት ተገኘ።

ማንንም ሳይንቅ ከባሪያዎቹ ጋር እንደ አንዱ ታዳሚ ተቀመጠ። ያንን ታላቅ ተአምርም “እዩልኝ ስሙልኝ” ሳይል፣ ወይን በሚቀመጥበት በዚያ በጓዳ ጋኖቹ ዘንድ አደረገው። ይህም በሉቃስ ወንጌል (፲፬፥፯-፲፩) ላይ “አንድ ሰው ለሰርግ ቢጠራህ ከሁሉ በላይ ባለው የክብር ቦታ አትቀመጥ፤ ምናልባት ከአንተ ይልቅ የሚከበር ሰው ተጠርቶ ከሆነ፣ አንተንና እርሱን የጠራው መጥቶ ‘ለዚህ ሰው ስፍራ ልቀቅለት’ ይልሃል፤ ያን ጊዜም እያፈርህ ወደ መጨረሻው ስፍራ ትወርዳለህ። ነገር ግን በተጠራህ ጊዜ ሄደህ በዝቅተኛው ስፍራ ተቀመጥ፤ የጠራህ ሰው መጥቶ ‘ወዳጄ ሆይ፣ ወደ ላይ ከፍ በል’ ባለው ጊዜ፣ አብረውህ በተቀመጡት ፊት ክብር ይሆንልሃል። ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፤ ራሱንም ዝቅ የሚያደርግ ከፍ ይላል” ብሎ ራሱ ያስተማረውን ትምህርት በተግባር የፈጸመበት አርአያነት ነው። በዚህም እኛ እንዴት በትሕትና፣ ለሰው ታይታ ሳይሆን ከልብ ማገልገል እንዳለብን አስተማረን።

ክርስቶስ ማንነቱን መግለጡ

በቃና ሰርግ ቤት የተደረገው ተአምር የአዳዲስ አማኞችንና የሐዋርያትን እምነት ለማጽናትም የተደረገ በመሆኑ፣ ወንጌላዊው ዮሐንስ “ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ” ይለናል። እመቤታችን ድንግል ማርያምም ጌታችን ማንነቱ የሚገለጥበት ጊዜ መድረሱን አውቃ “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” አለችው። ጌታችንም “ጊዜዬ ገና አልደረሰም” ማለቱ፣ በወቅቱ ያልነበረው ይሁዳ መጥቶ ተአምሩን እንዲያይና ለወደፊት “እኔ በሌለሁበት ተአምር አድርጎ ለየኝ” የሚል ምክንያት እንዳይኖረው ለማድረግ እንደሆነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ተርጒሞታል።

የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ ክብርና ርኅራኄ ወንጌላዊው ሲገለጽ ቅዱስ ዮሐንስ ታሪኩን ሲጀምር “የኢየሱስ እናት በዚያ ነበረች” በማለት ክብሯን ይገልጻል። ወንጌላዊው በየትኛውም ስፍራ ስሟን በቀጥታ ከመጥራት ይልቅ “እናቱ” ወይም “የኢየሱስ እናት” እያለ ይጠራታል፤ ይህም ሐዋርያት ለእመቤታችን ያላቸውን ታላቅ አክብሮትና ድንግል ማርያም ያላትን የአምላክ እናትነት ጸጋ የሚያስረዳ ነው። ጌታችንም እናቱን “አንቺ ሴት” ማለቱ፣ አዳም ሔዋንን “ከአጥንቴ አጥንት ከሥጋዬ ሥጋ ናት” (ዘፍ ፪፥፳፫) እንዳላት ሁሉ፣ እርሷም የጌታ የሥጋዌው (የሰው የመሆኑ) ምክንያት መሆኗን ለማረጋገጥ ነው።

ድንግል ማርያም የወይኑ ማለቅ በሰርገኞቹ ላይ የሚያመጣውን ኃፍረት ተረድታ፣ እነርሱ ሳይጨነቁና ሳይጠይቋት ቀድማ በመለመን ርኅራኄዋን ገልጻለች። ጌታችንም የእናቱን ልመና ሰምቶ ውኃውን ወደ ወይን በመለወጥ ተአምሩን ፈጸመ።

ምሥጢረ ተክሊል

ጋብቻ ቅዱስ መሆኑ ይታወቅ ዘንድ ክርስቶስ ከእናቱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በሰርጉ ላይ ተገኝቷል። ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ የታነጸች ናት። ይህ ምሥጢርም በእግዚአብሔር ፊት፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ የሚፈጸም መሆኑን ያስረዳል። ጌታችን በሰርግ ቤት እመቤታችንን “አንቺ ሴት” ብሎ መጥራቱ አዳም ሔዋንን “ከአጥንቴ አጥንት፣ ከሥጋዬ ሥጋ ናት” (ዘፍ ፪፥፳፫) እንዳላት ሁሉ፣ ስለ ሥጋዌው (ሰው ስለመሆኑ) የሚጠቁም ነው። ውኃውን ወደ ወይን መለወጡም የከበረ ደሙ ምሳሌ ነው። ስለሆነም ምሥጢረ ተክሊል በሥጋውና በደሙ የሚከብርና አንድ ጊዜ ብቻ የሚፈጸም ቅዱስ ሥርዓት ነው።

የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር በረከቱንና ረድኤቱን ያብዛልን። የአምላክ እናት ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ አትለየን።

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!