የሰባክያነ ወንጌል እና የግቢ ጉባኤያት ሥራ አስፈጻሚዎች ሥልጠና ተጠናቀቀ

ሐምሌ ፳፯ ቀን፣ ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

በማኅበረ ቅዱሳን ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል በስብከተ ወንጌልና ሥልጠና ክፍል፣ እንደዚሁም በስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር ከልዩ ልዩ ጠረፋማ አህጉረ ስብከት የተውጣጡ ከሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ወር ሲሠለጥኑ የቆዩ ፻፶፪ አዳዲስ ሰባክያነ ወንጌልና የዓቅም ማጎልበቻ ሠልጠኞች ብፁዕ አቡነ ዮናስ የአፋር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ የማኅበሩ አባላት፤ በጎ አድራጊ ምእመናንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች  በተገኙበት ሐምሌ ፳፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በማኅበሩ ሕንፃ ፫ኛ ፎቅ አዳራሽ በብፁዕ አቡነ ዮናስ  ጸሎተ ቡራኬ ተመርቀዋል፡፡

 

ብፁዕነታቸው “ማዕረሩሰ ብዙኅ ወገባሩ ኅዳጥ፤ መከሩስ ብዙ ነው፤ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤” በሚል ኃይለ ቃል መነሻነት “ቅኑት እንደ ገበሬ፤ ጽሙድ እንደ በሬ ኾናችሁ እግዚአብሔርን ለማገልገል ተጠርታችኋልና ቅዱስ ጳውሎስ ‹… መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫዬን ጨርሼአለሁ፤ ሃይማኖቴን ጠብቄአለሁ፡፡ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል …› በማለት እንደ ተናገረው በተማራችሁት ትምህርት መሠረት ወንጌልን እየተዘዋወራችሁ በመስበክ አገልግሎታችሁን በትጋት ተወጥታችሁ እናንተንም ምእመናንንም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለማድረስ ተፋጠኑ፤” ሲሉ ለምሩቃኑ አባታዊ ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋል፡፡

 

የአገር ውስጥ ማእከላት ማደራጃ ማስተባበሪያ ዋና ክፍል ሓላፊ፣ የማኅበረ ቅዱሳን ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ ሰይፈ ዓለማየሁም ምሩቃኑን “እናንተ ለእኛ አለኝታዎቻችን ናችሁ፡፡ ችግሮችን ተቋቁማችሁ በየጠረፋማው የአገራችን ክፍል እየተዘዋወራችሁ የምትሰጡትን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ስናስብ እንበረታለን፡፡ እናንተን የሰጠን ልዑል እግዚአብሔር የተመሰገነ ይኹን፡፡ ወደፊትም ወንጌልን በመስበክ ብዙዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዲወርሱ የማድረግ ሓላፊነታችሁን በትጋት እንድትወጡ ይኹን፤” በማለት የማኅበሩን መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ አቶ ሰይፈ በማያያዝም የሥልጠናውን ሙሉ ወጪ በመሸፈንና በልዩ ልዩ መልኩ አስተዋጽኦ ያበረከቱ በጎ አድራጊ ምእመናንን በማኅበሩ ስም አመስግነዋል፡፡

 

“ይህ የምረቃ መርሐ ግብር አገልግሎት የምትጀምሩበትና መንፈሳዊ አደራ በመቀበል ብዙ ምእመናንን አስተምራችሁ ለማስጠመቅ ቃል የምትገቡበት ዕለት መኾኑን ተገንዝባችሁ የተቀበላችሁትን አደራ በመወጣት ሰፊ አገልግሎት ለመስጠት መትጋት ይጠበቅባችኋል” የሚል ምክር ለምሩቃኑ የለገሱት ደግሞ የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ሓላፊው ቀሲስ ዶ/ር ደረጀ ሽፈራው ናቸው፡፡

 

ከ፬፻ ሺሕ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ሥልጠናውን የደገፉት ስማቸው እንዲጠቀስ የማይፈልጉት በጎ አድራጊ ምእመን ደግሞ “ከኹሉም በላይ በሕይወት መስበክ ይበልጣልና ምሩቃኑ ቃለ እግዚአብሔርን ከማስተማር ባሻገር ለምእመናን መልካም አርአያ ልትኾኑ፤ በአገልግሎታችሁም ብዙ ፍሬ ልታፈሩ ይገባል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

 

እኒህ ወንድም ለዝግጅት ክፍላችን ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡም ከልጅነታቸው ጀምሮ በሰንበት ት/ቤት ማደጋቸውንና ለባዕለ ጠግነት የበቁትም በእግዚአብሔር ቸርነት መኾኑን ጠቅሰው “የቤተ ክርስቲያን ትልቁ የአገልግሎት መሣሪያዋ ስብከተ ወንጌል ነው ብለን ስለምናምን እኔና ባለቤቴ ተመካክረን እግዚአብሔር ከሰጠን ብዙ ሀብት ጥቂቱን በመለገስ ለዚህ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲውል አድርገናል፡፡ ይህንን በማድረጋችንም ትልቅ መንፈሳዊ እርካታን አግኝተናል፡፡ ባለ ሀብት ምእመናንም በሥጋችሁም በነፍሳችሁም መንፈሳዊ በረከትን እንድታገኙ ከማኅበሩ ጋር በመኾን የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት በመደገፍ እንደ እኛ የድርሻችሁን እንድትወጡ፤” ብለዋል፡፡

 

ምሩቃኑ በምረቃ ሥርዓቱ ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል፡፡ በመቀጠልም ማኅበሩ ያዘጋጀላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ፣ የአደራ መስቀልና የምስክር ወረቀት ስጦታ በብፁዕ አቡነ ዮናስ ቡራኬ ተቀብለዋል፡፡

 

ከምሩቃኑ መካከል ከጅንካ ሀገረ ስብከት የመጡት ዲያቆን ሀብታሙ ግዛውና ሰባኬ ወንጌል ዳንኤል ኢላ የሚገኙ ሲኾን ዲያቆን ሀብታሙ አንድ ዓይኑና አንድ ኵላሊቱ አገልግሎት አይሰጡም፡፡ አንድ እግሩም በብረት የተጠገነ ነው፡፡ በተጨማሪም የደም ግፊትና ስኳር ሕመም አለበት፡፡ ሰባኬ ወንጌል ዳንኤል ኢላ ደግሞ በተፈጥሮ የሁለቱም እግሮቹ ዕድገታቸው ያልተሟላ በመኾኑ በእጆቹና በጕልበቱ እየዳኸ ነው የሚጓዘው፡፡

 

እነዚህ ሁለቱ ሰባክያነ ወንጌል በረኀውን፣ ረኀቡንና ጥሙን ታግሠው በጠረፋማ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ወንጌልን በመስበክ ብዙ ሺሕ አዳዲስ አማንያንን አስጠምቀው የቤተ ክርስቲያናችን አባል ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ በዓቅም ማጎልበቻ ሥልጠናውም በልዩ ልዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ግንዛቤ መጨበጣቸውንና ባገኙት ዕውቀት በመታገዝ ከቀድሞው የበለጠ አገልግሎት ለመስጠት መነሣሣታቸውን ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቀዋል፡፡

 

እስከ ሁለት ቀናት ድረስ የሚወስድ መንገድ እየተጓዙ እንደሚያስተምሩ የሚናገሩት ሰባክያኑ በአካባቢያቸው ያለው የመጓጓዣ ችግር ለአገልግሎታቸው መሰናክል እንደ ኾነባቸው፤ እንደዚሁም ቤተ ክርስቲያንና መጠለያ ቤት አለመኖሩ አማንያኑን እንዲበታተኑ እንዳደረጋቸው ይገልጻሉ፡፡

 

አስተያየታቸውን ሲያጠቃልሉም “በጠረፋማ አካባቢዎች የሚኖሩ ወገኖቻችን ተምረው ከተጠመቁ በኋላ ካለባቸው የካህን እጦት ባሻገር ሥጋውን ደሙን የሚቀበሉባቸው፤ ልጆቻቸውን ክርስትና የሚያስነሡባቸው ጸሎት የሚያደርሱባቸው አብያተ ክርስቲያናት ባለመታነፃቸው ተመልሰው በተኵላዎች እየተነጠቁ መኾናቸውንና በመጠለያ ችግር ምክንያት መንገላታታቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት በመላው ዓለም የሚገኙ ምእመናን ለእነዚህ ወገኖቻችን ቤተ ክርስቲያንና መጠለያ ቤት በመሥራት፤ እንደዚሁም ለሰባክያኑ መጓጓዣ የሚኾኑ ተሸከርካሪዎችን በመግዛትየድርሻቸውን እንዲወጡ እንማጸናለን” ሲሉ ጥሪያቸውን ያስተላልፋሉ፡፡

በመጨረሻም በብፁዕ አቡነ ዮናስ ቃለ ምዕ   ዳንና ጸሎተ ቡራኬ የምረቃ ሥርዓቱ ፍጻሜ ኾኗል፡፡

 

በተያያዘ ዜና በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት ማስተባበሪያና ማደራጃ ዋና ክፍል ለሁለት ሳምንታት በሥራ አመራር ያሠለጠናቸው ከልዩ ልዩ የአገር ውስጥ ግቢ ጉባኤያት የተውጣጡ ፻፱ ሥራ አስፈጻሚዎች የማኅበረ ቅዱሳን አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ሐምሌ ፳፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በማኅበረ ቅዱሳን ሕንፃ ሦስተኛ ፎቅ አዳራሽ ተመርቀዋል፡፡

 

በመርሐ ግብሩ ላይ “የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቷል” በሚል ኃይለ ቃል በአገልግሎት መትጋት እንደሚገባ የሚያስረዳ ትምህርተ ወንጌል በቀሲስ ዶክተር ሙሉጌታ ሥዩም የውጭ ማእከላት ማስተባበሪያ ዋና ክፍል ሓላፊ ተሰጥቷል፡፡ ከምሩቃኑ መካከልም ወንድሞች ዲያቆናት ያሬዳዊ ወረብና ቅኔ አቅርበዋል፡፡

 

ለምሩቃኑም “የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራትና ሥርዓት” በሚል ርእስ የተዘጋጀው መጽሐፍ በስጦታ መልክ ተበርክቶላቸዋል፡፡

 

የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝ፣ የአገር ውስጥ ማእከላት ማደራጃ ማስተባበሪያ ዋና ክፍል ሓላፊ፣ የማኅበሩ ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ ሰይፈ ዓለማየሁና የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ መሠረት የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች የቤተ ክርስቲያን ተስፋዎች መኾናቸውን በመጥቀስ “ለወደፊት የማኅበሩ ሥራ አመራር ተረካቢዎች እናንተ ናችሁና በሥልጠናው ባዳበራችሁት ክህሎት በግቢ ጉባኤ ቆይታችሁም ኾነ ከግቢ ስትወጡ በማኅበሩ አገልግሎት ውስጥ በመሳተፍ የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ለማስፈጸም እንድትተጉና በመንፈሳዊ ሕይወታችሁም ለወጣቱ ትውልድ አርአያ እንድትኾኑ” ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

የሥልጠናው ዓላማ በማኅበረ ቅዱሳን ልዩ ልዩ መዋቅሮች ተተክተው ሊያገለግሉ የሚችሉ ሥራ አስፈጻሚዎችን ማፍራት መኾኑን ለዝግጅት ክፍላችን የገለጹት የግቢ ጉባኤያት ማስተባበሪያና ማደራጃ ዋና ክፍል ሓላፊ፣ የማኅበረ ቅዱሳን ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ እስጢፋኖስ ታፈሰ፤ እንደዚሁም ከ፻፱ኙ ሠልጣኞች መካከል ፲፮ቱ እኅቶች መኾናቸውን ያስታወቁት የማብቂያና ማሰማሪያ ክፍል ተጠሪው አቶ ደረሰ ታደሰ የሥልጠናው ወጪ “መሰባሰባችንን አንተው” በሚል መሪ ቃል ከታኅሣሥ ፳-፳፮ ቀን፣ ፳፻፰ ዓ.ም በተዘጋጀው የገቢ ማሰባበሰቢያ መርሐ ግብር በተገኘው ገንዘብ መሸፈኑን አስታውቀዋል፡፡

 

በተጨማሪም ለሥልጠናው መሳካት ልዩ ልዩ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ለኤስድሮስ ኮንስትራክሽንና ንግድ አክስዮን ማኅበር፣ ለሐይመት ንግድ ሥራዎች ድርጅት፣ ለከራድዖን ካፌና ሬስቶራንት፣ ለሌሎችም በጎ አድራጊ ተቋማትና ግለሰቦች በማኅበሩና በሥልጠናው አስተባባሪ ኰሚቴ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ለወደፊቱ ማኅበሩ በግቢ ጉባኤያት ላይ ብዙ ሥራዎችን ለማከናወን ማቀዱን ጠቅሰው “ለዚህም የምእመናን ድጋፍ እንዳይለየን” ሲሉ ጥሪያቸውን ያስተላልፋሉ፡፡

 

በዚህ ሥልጠና የቤተ ክርስቲያንን ማንነት፣ የመንፈሳዊ ሕይወትን ትርጕም፣ ፍቅርን፣ ትሕትናን፣ ፈተናዎችን የማለፍ ጥበብንና ሌላም በርካታ ዕውቀትን እንደ ቀሰሙበት፤ እንደዚሁም የማኅበረ ቅዱሳንን ማንነት በስፋት እንደ ተረዱበትና ለወደፊቱም ቤተ ክርስቲያንን በትጋት ለማገልገል የሚያስችል ዓቅም እንዳጎለበቱበት በዕለቱ አስተያየት የሰጡት ከደብረ ማርቆስ፣ ከጎንደር፣ ከመቱ፣ ከሠመራና ከአዲስ አበባ አልካን ኪያሜድ ግቢ ጉባኤያት የመጡ ሠልጣኞች ተናግረዋል፡፡

መርሐ ግብሩም በአባቶች ጸሎት ተፈጽሟል፡፡