የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ በርባናስ አረፉ
በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ
ግንቦት 21/2003 ዓ.ም.
ከሃያ ዓመታት በላይ ቤተ ክርስቲያንን በጵጵስና በቅንነት ያገለገሉት የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ በርናባስ አረፉ፡፡
ርክበ ካህናትን ተከትሎ የሚደረገውን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ለመካፈል ወደ አዲስ አበባ መጥተው በነበሩበት ወቅት ታመው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህም ሳቢያ የምልዐተ ጉባኤውን የመጨረሻውን ቀን ማለትም የማክሰኞ ዕለት ስብስባ አልተካፈሉም፡፡ በዚህም ሁኔታ አርብ ግንቦት 19 ቀን 2003 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ተነስተው የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከሆኑት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ጋር ደብረ ማርቆስ ገብተው ያደሩ ሲሆን ወደ ሀገረ ስብከታቸው መቀመጫ ባሕር ዳር ቅዳሜ 8፡00 ሰዓት ገብተው በመዋል ማታ 1፡30 ላይ እንዳረፉ ታውቋል፡፡
እረፍታቸው ከተሠማ በኋላ በዛሬው ዕለት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አያሌው ጎበዜ ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር በሀገረ ስብከቱ ግቢ ውስጥ በሚገኘው የብፁዕነታቸው መኖሪያ ቤት ሀዘንተኛውን አጽናንተዋል፡፡
የቀብር ሥነ ሥርዓቱም ሰኞ ግንቦት 22 ቀን 2003 ዓ.ም በባሕር ዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም የሚፈፀም ሲሆን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመንግስት ባለስልጣናትና ምዕመናን በሚገኙበት ይፈጸማል፡፡

ብፁዕ አቡነ በርባናስ የተወለዱት በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ወረዳ ልዩ ስሙ ፉቢ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በ1911 ዓ.ም. ሲሆን፥ በ1983 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ አንብሮተ እድ ጵጵስና ተሹመው በተለያዩ ኃላፊነቶች እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አገልግለዋል፡፡