የምእመናን ድርሻ በቤተ ክርስቲያን

ክፍል አንድ

ዲያቆን ዳዊት አየለ
መስከረም ፳፪፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ቤተ ክርስቲያን የምንላት እግዚአብሔር ወልድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከፍጹምና ከማይነገር ፍቅሩ የተነሣ “በእርሱ ፈቃድ በአባቱ ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ መጥቶ…” ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ፣ በተዋሕዶ ሰው ሆኖ፣ ከኃጢአት በቀር በምድር ሁሉን ፈጽሞ፣ በቀራንዮ አደባባይ በመልዕለተ መስቀል ላይ ቅዱስ ሥጋውን ቆርሶ ክቡር ደሙን አፍስሶ የመሠረታት የክርስቶስ አካሉ የሆነች እርሱ ራሷ የሆነላት የምእመናን (በወልደ እግዚአብሔር የባሕርይ አምላክነት አምነው የታመኑለት) ስብስብ (ጉባኤ) ናት። ለዚህም ነው ሠለስቱ ምዕት ቅዱሳን ሊቃውንት በሠሩልን በሃይማኖት ጸሎታችን “ሐዋርያት በሠሯት በአንዲት ክብርት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን” እያልን ዘወትር የምንጸልየው። (ውዳሴ ማርያም ዘሠሉስ፣ ጸሎተ ሃይማኖት፣ ተንከተም በሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክ)

ቤተ ክርስቲያን ስንል ሐዋርያዊት፣ ኩላዊት፣ ቅድስት፣ አንዲት፣ በሰማይ ያሉ የዚህን ዓለም ተጋድሏቸውን በድል አጠናቀው ወደ እግዚአብሔር የሄዱ ቅዱሳን (ሐዋርያት፣ ሰማዕታት፣ ሊቃውንት) እና ገና በዚህ ምድር በተጋድሎ ላይ ያሉ አማንያን (ምእመናን) አንድነት ማለታችን ነው።

በክቡር ደሙ በዋጃትና በሠራት የእግዚአብሔር ማደሪያው በሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስንኖር ሁሉም እንደየድርሻው የሚፈጽመውን፣ የሚጠብቀውንና የሚወጣውን ሥርዓትና ኃላፊነት አበው ቅዱሳን ሐዋርያትም ሐዋርያነ አበው ቅዱሳን ኢቃውንትም በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው አበጅተውልናል፤ በዚህች ምንም እንከን በሌለባት አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለቅዱሳን በተሰጠች በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አንደበት ስንዱ እመቤት በምትሰኝ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እቅፍ ውስጥ ስንኖር ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣና ሥርዓቱን ልንጠብቅ ይገባል። አምላካችን እግዚአብሔር ወልድ በመዋዕለ ሥጋዌው ሲያስተምር የእርሱ የሆንነውን (ምእመናንን) “ከወደዳችሁኝስ ትእዛዜን ጠብቁ” በማለት የእርሱ መሆናችንን የምንገልጥበት አንደኛውና ዋነኛው መንገድ ትእዛዙን በመጠበቅ የድርሻችንን ስንወጣ እንደሆነ በቅዱስ ወንጌል ነግሮናል። (ዮሐ.፲፬፥፲፭)

በክርስቶስ ክርስቲያን ተሰኝቶ ክርስቶሳዊ የሆነ ሁሉ የድርሻውን የሚወጣና ሥርዓቱን የሚጠብቅ ከሆነ በዚህ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ክብሯ ልዕልናዋ ተጠብቆ ትኖራለች፣ ረድኤተ እግዚአብሔርና በረከቱ ዘወትር አይለየንም፤ ሀገር ጽኑ ሰላም ትሆናለች፣ በወዲያኛው ዓለምም የዘለዓለምን ርስት መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን፤ የድርሻችንን የማንወጣና ቸልተኞች የምንሆን ከሆነ ግን የቤተ ክርስቲያንንም የሀገርንም ክብርም ልዕልናም ማስጠበቅ አንችልም፤ በላይ በሰማይም መንግሥተ እግዚአብሔርን እናጣለን፤ ስለዚህ ድርሻውን የሚያውቅ ምእመን(ክርስቲያን) እራሱንም ቤተ ክርስቲያንንም ይጠቅማል። የምእመናን ድርሻ በቤተ ክርስቲያን እጅግ ዘርፈ ብዙ ሲሆን መሠረታዊ የሚባሉትን እንደሚከተለው ዘርዝረን እንመለከታለን፦

 የምእመናን ድርሻ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን (መጠበቅና ማስጠበቅ)

ሥርዓት “ሠርዐ” “ሠራ” ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም “ደንብ፣ አሠራር፣ አካሄድ፣ መርሐ ግብር፣ ውሳኔ፣ የሕግና የትእዛዝ መጠበቂያ ድንብ” ማለት ሲሆን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ስንልም የቤተ ክርስቲያን ሕግ፣ ደንብ፣ መርሓ ግብር፣ አካሄድ፣ የሥርዓቶች አፈጻጸምና አተገባበር ማለታችን ነው። (ደስታ ተክለ ወልድ ገጽ ፰፻፺፬) ቤተ ክርስቲያንም ሥራን ወጥ በሆነ መልኩ ለመፈጸም፣ አንድ ሐሳብና አንድ ልብ ለመሆን እንዲሁም የሃይማኖትን ምሥጢራት ለመጠበቅ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ሠርታለች። ቤተ ክርስቲያን ለመሄድ ከምናስብባት ቅጽበት ጀምሮ አካሄዳችን እንዲሁ እንደመጣልንና በቸልተኝነት እንዳይሆን ለእያንዳንዱ ድርጊቶቻችን የየራሳቸው ሥርዓትና አካሄድ አላቸው፤ ሁላችንም በተሠራው ሥርዓት መሠረት እንድንመላለስ ሲያሳስበን ብርሃነ ዓለም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ወንድሞቻችን ሆይ፥ በሠራንላችሁ ሥርዐት ሳይሆን በተንኮል ከሚሄዱት ወንድሞች ሁሉ፥ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዝዛችኋለን” በማለት ያዘናል። (፪ኛተሰ.፫÷፮፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታየ)

ቤተ ክርስቲያን ለመሄድ (ለመግባት) የሚደረግ ጥንቃቄ፦ አንድ ክርስቲያን እንደ ሳዊሮስ ዘእስሙናይን አገላለጽ በቀን ሦስት ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ሊሄድ ይገባዋል። “እግዚአብሔር ከ፳፬ ሰዓታት መካከል ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄዱባቸው ዘንድ ሦስት ሰዓታትን አደረገ፤ እሊህም ነግህ፣ ጊዜ ቅዳሴና ሠርክ ናቸው።” (ድርሳነ ሳዊሮስ ዘእስሙናይ ገጽ ፻፵፱) በዚህም መሠረት ነግህ ለጸሎትና ለቅዳሴ ሠርክ ለጉባኤ ወደ ቤተ ክርስቲያን በምንሄድባቸው ጊዜያቶች ልንጠነቀቅና ልናስተውል ይገባል፤ የምንሄደው ወደ አምላካችን ቤት ነውና ልባችንን ንጹሕ አድርገን፣ የት እንደምንሄድ አውቀን፣ ራሳችንን አዘጋጅተን፣ ልቦናችንን ከክፉ ሐሳብና ምኞት አርቀን፣ መልካም በሆነው በእግዚአብሔር ሐሳብ አዘጋጅተን፣ ንጹሐ ባሕርይ ለሆነው አምላክ ማደሪያው ወደ ሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነውና የምንሄደው ንጹሕ ሆነን፣ ንጹሕ ልብስ ለብሰንና ነጭ ነጠላ አመሳቅለን (አደግድገን)፣ ሴቶች ራሳችንን ተከናንበን (ፀጉራችንን ሸፍነን) ልንለብስ ይገባል።

በቅዱስ ጋብቻ ተወስነው የሚኖሩ ባልና ሚስት ለቅዳሴ ወደ ቤተ ክርስቲያን ወደ ውስጥ በሚገቡባቸው ዕለቶች እንዲሁም በጾምና በሰንበት በበዓላት ቀኖችም መገናኘት (ሩካቤ መፈጸም) የተከለከለ ነው። በመኝታ የተገናኘ በዕለቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባት አይገባውም፤ እንዲሁም ወደ ቤተ ክርስቲያን ባይሄዱም በዓላትንና አጽዋማትን ሊጠብቁ ይገባል። ርስሐተ አፉንና ርስሐተ ክንፈሩን የማዝረብረብ ነውር ያለበት በዚሁ ነውር ላይ እያለ ወደ ቤተ ክርስቲያን አይገባም፤ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙንም ሊቀበል አይገባውም። (ፍት.ነገ.አን.፲፫)

ሴቶች በደመ ጽጌ ወቅት ላይ (በወር አበባ ወቅት) ሆነው እስከ ፯ ቀን ድረስ፣ ወልደው በአራስነት ወቅት የተወለደው ወንድ ከሆነ እስከ ፵ ቀን ድረስ ሴት ከሆነች እስከ ፹ ቀን ድረስ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳይገቡ ክልክል ነው። ከእነዚያ ቀናቶች በኋላ ግን ገላን ታጥቦ ንጹሕ ሆኖ መግባት ይቻላል። ወንድ ልጅ ሕልመ ሌሊት (ዝንየት) ከመታው በዕለቱ መግባት አይችልም፤ በማግሥቱ ገላውን ታጥቦ ይገባል። (ዘፀ.፲፱÷፲፭፣ ፩ኛቆሮ.፯÷፭-፯፣ ኩፋ.፴፬÷፲፪፣ ዘሌ.፲፪፥፩- ፍ.፣ ፍት.መን.አን. ፮፣ ዘኒቂያ ፳፱፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታየ)

ቤተ ክርስቲያን የመሳለም ሥርዓትና በቅጽሩ የሚደረግ ጥንቃቄ፦ ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን በምሳሌ መጽሐፉ “…ዕለት ዕለት በቤቴ መግቢያ የሚተጋ… እንዳለው እኛ ክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያንን ዕለት ዕለት ጠዋትና ማታ ልንሳለም ልንተጋ ይገባል። ”(ምሳ.፰÷፴፬) ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “…በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ…” እንዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንገባ ከቅጽረ ቤተ ክርስቲያኑ በር ላይ ስንደርስ ጣቶቻችንን አመሳቅለን (የመስቀል ምልክት ሠርተን)፣ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አማትበን፣ ሰግደን ልንሳለም ይገባል፤ (መዝ.፳፰፥፪) ወደ ውስጥ ስንዘልቅም ጫማ አውልቀን፣ ወገባችንን ታጥቀንና አደግድገን እንገባለን፤ ጫማ አድርጎ ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባት ክልክል ነው። ሐሳብን በመንፈሳዊ ነገር ወስኖ ወደ ውጪ ወደ ዓለማዊ ነገር እንዳይሄድ መግታትና መቆጣጠርና ያስፈልጋል፤ ያስቀየሙትን ይቅርታ መጠየቅ፣ የተቀየሙትን ይቅር ብሎ ቅሬታ ማውረድ እንዲሁም በስርቆት በቅሚያ የወሰዱትን የሰው ገንዘብ ለባለቤቱ መመለስ ይገባል፤ መጠጥ ጠጥቶ ሰክሮ ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባት ክልክል ነው፤ በቤተ ክርስቲያን ቅጽረ ግቢ ውስጥ መሸጥ መለወጥ (ገበያ)፣ ግብዣ ማድረግ መብላት፣ መጠጣት፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን የገባውንና የተቀደሰውን ንዋያተ ቅድሳት እንደገና ለሥጋዊ ነገር አውጥቶ መጠቀምና መሸጥ ክልክል ነው። (ፊል.፪÷፱-፲፣ መዝ.፺፭÷፱፣ ዘፀ.፫÷፭-፮፣ማቴ.፳፩÷፲፪-፲፫፣ ፍት. መን አን ፩፣ ፍት. መን አን ፲፪፣ ረስጣ ፳፰)

ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ስንገባም ከካህን ቀርቦ መስቀል መሳለምና በረከት መቀበል ይገባል፤ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ተሥለው የሚገኙ ቅዱሳት ሥዕላትን እጅ መንሳትና የአክብሮት ስግደት መስገድ ይገባል። ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን (ቤተ መቅደስ) ውስጥ ምግብና መጠጥ ይዞ መግባት እንዲሁም አጭርና ያደፈ ልብስ ለብሶ መግባት አይቻልም። ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሳቅ፣ ስለ ዓለማዊ ሥራ መነጋገር ክልክል ነው። ከገቡ በኋላ ዝምታ፣ ጸጥታ፣ ፍርሃት፣ የእግዚአብሔርን ምሕረት በጥብዐት መፈለግ ይገባል፤ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን የመዘምራንን ማሕሌት፣ የቅዱሳን መላእክትን ምስጋና፣ የነቢያትን ትንቢት፣ የሐዋርያትን ስብከት መስሚያና የልዑል እግዚአብሔርን ነገር መማሪያ ቦታ ስለሆነች ነው። (ዮሐ.አፈ.አን ፵፰፣ ቀኖና አቡሊዲስ አን.፯፣ ዮሐ.አፈ.አን.፮፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታየ)

ይቀጥላል…

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!