የምእመናን ድርሻ በቤተ ክርስቲያን

ክፍል ሦስት

ዲያቆን ዳዊት አየለ

ጥቅምት ፳፰፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

የንስሓ ሥርዓትና በንስሓ ወቅት ልንፈጽማቸው የሚገቡ ነገሮች

ንስሓ “ነስሐ” “ተጸጸተ፣ በክፉ ሥራው አዘነ፣ በደሉን ገለጠ፣ ኃጢአቱን ተናገረ አመነ” ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን “ጸጸት፣ በተሠራ ኃጢአት ምክንያት የሚደረግ ኀዘን፣ ቁጭት፣ ቅጣት፣ ቀኖና” ማለት ነው። (ደስታ ተክለ ወልድ ገጽ ፰፻፸፰)

በንስሓ ተጸጽቶ ወደ እግዚአብሔር የተመለሰና ቸርነቱን የለመነ ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት መውረሱ አይቀርም። እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሰጣቸው ትልልቅ ስጦታዎች መካከል ዋነኛው የንስሓ መንገድ ሲሆን የእግዚአብሔር ቸርነቱ በሰፊው የሚገለጥበት የሕይወት መንገድ ነው። ንስሓ ዘማዊውን ድንግል የምታደርግ ቅድስት መድኃኒት ነች። እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ከፈጠረ በኋላ በገነት የሚሻውን ሁሉ እያረገ እንዲኖርና ከዕፀ በለስ በቀር ሁሉን እንዲበላ እንዲሁም እንዲጠጣ ሰጥቶት ሳለ ነገር ግን የሰው ልጅ የፈጠረውን አምላክ ዙፋኑን በመሻት “አምላክ ልሁን” በማለት በድሎ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ ገነትን የመሰለች ቦታ ተነጠቀ፤ ከጸጋው ተጎሳቁሎ ተባሮ ወጣ። ከውድቀቱም የተነሣ አዳም እጅግ በጣም አዝኖ በንስሓ በሱባኤ እግዚአብሔር አምላክን ዘወትር ይለምነው ነበር፡፡

እግዚአብሔር አምላክም ለአዳም “አትዘን፤ እነሆ ትዛዜን አፍርሰህ ከወጣህበት ገነት መልሼ እንድትገባ አደርጋለው” ብሎ በገባለት ቃልኪዳን መሠረት ንስሓውን ተቀብሎ ከአምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን በኋላ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ተዋሕዶ ተወልዶ በመስቀል በከፈለው ካሳ ከኃጢአት ባርነት ነጻ አውጥቶናል፤ (መጽሐፈ ቀሌምንጦስ ፪÷፳፩) ይህም የመጀመሪያውን ተነሣሂ አዳምንና የንስሓን ታላቅነት ያሳየናል። በንስሓ ኃጢአት ካልሠሩ ጻድቃን ጋር ይተካከሏል፤ በቅዱስ ወንጌል በዐሥራ አንደኛ ሰዓትም የገቡ ጠዋት ከገቡት ጋር እኩል እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ዲናር እንደተቀበሉ እንደተጻፈው ማለት ነው።

እንግዲህ ንስሓ ገብተን፣ የኃጢአትን ሥርየት አግኝተን፣ ከሰውና ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀን በጽድቅ ጎዳና ለመራመድና በደኅንነት ጸጋ ለመኖር እንድንችል ቢያንስ ሦስት ነገሮችን መፈጸም አለብን።

የመጀመሪያው የንስሓ ኀዘን ወይም እውነተኛና ልባዊ የሆነ ጸጸት ሲሆን ይህም ስለ ክፉ ሥራችን ነው፤ ስለ መተላለፋችን የምንጸጸትበትና በደላችንን የምናምንበት ነው። መበደላችንንና መተላለፋችንን ሳናምንና ጥፋተኝነታችንን ሳንቀበል ወደ ሚቀጥለው የንስሓ ሥርዓት ልንደርስ አንችልም።

ሁለተኛው ኑዛዜ ሲሆን የበደልነውን በደልና ክፉ ሥራችንን ሁሉ ካህኑን ምስክር አድርገን በእግዚአብሔር ዳኝነት ፊት የምንናዘዝበትና ራሳችንን ጥፋተኛ አድርገን የምንቀርብበት መንገድ ነው።

ሦስተኛው ደግሞ ስለ ኃጢአታችን የሚሰጠንን የንስሓ ቅጣት የሚመለከት ሲሆን የሚሰጠንን ቀኖና (ሥርዓት) መፈጸምና ከዚህ በኋላ በካህኑ በኩል የምናገኘው የፍትሐት (ከኃጢአት እሥራት የመፈታት) ጸጋ ነው። እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ይቅር እንደሚለንና ምሕረትን እንደምንቀበል ማመናችን የተሰጠንን ቀኖና በመንፈሳዊ ታማኝነትና በእምነት በመፈጸማችን ይታወቃል።

ምእመናን በንስሓ አባታችን ዘንድ የንስሓ ልጆች እንደመሆናችን ከላይ የተመለከትናቸውን ሦስቱን ነገሮች በአግባቡ ልንፈጽምና በሥርዓቱ ልንመላለስ ይገባል፤ እንዲሁም አንድ ሕፃን በአባቱ ፊት እንደማያፍርና እንደማይሽኮረመም ይልቅስ የሚፈልገውን ሁሉ በግልጽ እንዲናገር እኛም ለአባታችን (አበ ነፍስ) በደላችንን በእምነትና በነጻነት መናገር መቻል አለብን። ነገር ግን ንስሓችንን በግልጽ ባንናገር ብንደብቅ እንደ ሐናንያና እንደ ሰጲራ እግዚአብሔርን መዋሸት ይሆንብናል፤ ስለዚህ ሳንደብቅ ሳናስቀር መናዘዝ መቻል አለብን፤ እንዲሁም፦

  • የተሰጠውን ቀኖና በአግባቡ መፈጸም አለብን፤ ተነሣሒውም የተማረ እንደሆነ ቄሱ ንስሓውን ቢያሳንስለት የንስሓዬን ልክ እኔ አውቀዋለሁ ብሎ አይጨምር። ቄሱ ከሰጠኝ ጥቂት ቢሆን እኔ ምን ዕዳዬ አይበል። የኃጢአቴን ብዛት እኔ አውቀዋለሁ ጨምርልኝ አይበል፤ ወደ እግዚአብሔር ንስሓዬን ሳላደርስ አትግደለኝ እያለ ያመለክት እንጂ።
  • ንስሓ ሲገቡ ቄስ ያዘዘውን ማድረግ ይገባል፤ ቄስ ካዘዘው ግን መውጣት አይገባም። አስቀድሞ ሲናገር ምክንያት አለመስጠት፣ ከኃጢአት አለመክፈል (አለማስቀረት)፣ የሰጠውን ማድረስ ከሰጠው አለማስቀረት አለመጨመር ይገባል።
  • በጊዜው ሁሉ ያጋጠመውን ሥጋዊም ይሁን መንፈሳዊ ችግር ለንስሓ አባት ማካፈልና መፍትሔ ማግኘት ይገባል።
  • ስለ ሠራው ኃጢአት ንስሓ ለመግባት ነገ ዛሬ ያለማለት መብትም ኃላፊነትም አለበት ‹‹ተቆጡ አትበድሉም ፀሐይ ሳይጠልቅም ቁጣችሁን አብርዱ ለሰይጣንም መንገድን አትስጡት›› ተብሎአልና። (ኤፌ.፬፥፳፯)
  • የንስሓ አባቱን ክብር የመጠበቅ ይህም ማለት ሲመጣ መነሣት ሲሄድ የመሸኘት ነው። የንስሓ ልጅ ይህንና የመሰለውን በተግባር የመፈጸም ኃላፊነት አለበት። ‹‹ለመምህራኖቻችሁ ታዘዙ፤ ተገዙላቸው፤ ስለ እናንተ በግዚአብሔር ፊት ምላሽ የሚሰጡ እንደ መሆናቸው ይህን ሳያዝኑ ደስ ብሎአቸው ያደርጉት ዘንድ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉና›› እንደተባለ መምህረ ንስሓው ለእርሱ ነፍስ የሚጨነቀውን ያህል ልጁም ስለ መምህረ ንስሓው የሚያስብ ሊሆን ይገባል። (ዕብ.፲፫፥፲፯)

በዚህም መሠረት አንድ ምእመን ንስሓውን “እግዚአብሔርን በደልኩ፤ አሳዘንኩት” በሚል ጽኑ በሆነ ኀዘንና ቁጭት ለካህን (ለንስሓ አባት) ይነግረዋል፤ መምህረ ንስሓውም የተነሳሒውን አቅም መዝኖ የጾም፣ የጸሎት፣ የስግደት፣ የምጽዋት ቅጣት ይሰጠዋል። ለዚህም ጊዜ ይወሰንለታል። የቀኖና ጊዜውን ከጨረሰ በኋላ ተነሳሒው ወደ መምህረ ንስሓው ተመልሶ እንደ ትእዛዙ መፈጸሙን ይነግረዋል። ቄሱም ፍትሐት ሰጥቶ ሥጋውን ደሙን አቀብሎ ከምእመናን ጋር እንዲቀላቀል ይፈቅድለታል። (ኅብረ ሥርዓት ዘቤተ ክርስቲያን ኦርቶዶክሳዊት በመምህር አብርሃም አረጋ፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታየ፣ መጽሐፈ ምዕዳን በርእሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን፣ ዓምደ ሃይማኖት)

ሥርዓተ ቅዱስ ቊርባንና ልንጠነቀቅባቸው የሚገቡ ነገሮች

ቊርባን “ቀረበ፣ ቄረበ” ከሚሉ የግእዝ ግሶች የወጣ ሲሆን “መቅረብ መስጠት፣ መንፈሳዊ አምኃ፣ ስለት፣ መዋዕት፣ መባእ፣ ለአምላክ የሚቀርብ የሚሰጥ ገንዘብ” ማለት ነው። (ኅብረ ሥርዓት ዘቤተ ክርስቲያን ኦርቶዶክሳዊት በመምህር አብርሃም አረጋ ገጽ ፷፰) እና የጌታ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙም ጌታ ለምእመናን የሰጠው ስለሆነ፣ ወልደ እግዚአብሔር ሰው በሆነ ጊዜ ወዶ በአቀረበልን በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ ቁርባንነት እኛ ሁላችን እንከብር ዘንድ ለሚያምኑ ሁሉ መንጻት፣ ሥርየተ ኃጢአት፣ ክብር፣ ሕይወት የሚገኝበትን አንዲት መሥዋዕት ለዘለዓለም የማትሻር የማትለወጥ አድርጎ ሠርቶ የሰጠን የወንጌል መሥዋዕት ነውና ቁርባን ተብሏል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ “ይህ ሙሴ የሰጣችሁ እንጀራ አይደለም፤ ይህ ከሰማይ የወረደ ኅብስት ከእግዚአብሔር የተገኘ ነው። እኔም የምሰጣችሁ ኅብስት ሥጋዬ ነው፤ በእኔ የሚያምን አይራብም፤ አይጠማም፤ አባቶቻችሁ በምድረ በዳ እንጀራ በሉና ሞቱ፤ ከዚህ ኅብስት የሚበላ ግን ለዘለዓለም ይኖራል እንጂ አይሞትም፤ ከሰማይ የወረደ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ለዘለዓለም ሕይወት የምሰጠው ምግብ ሥጋዬ ነውና በእውነት እነግራችኋለሁ፤ የወልደ ዕጓለ እመሕያውን ሥጋውን ከአልበላችሁ ደሙንም ከአልጠጣችሁ የዘለዓለም ሕይወት የላችሁም” እንዳለው ቅዱስ ቁርባን የዘለዓለም ሕይወትን የሚሰጠን አማናዊ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነው። (የሐ.፮÷፳፯-፶፰)

ለቅዱስ ቊርባን የምናደርገው ዝግጅት

የሚቆርቡ ሰዎች በቅዱስ ጋብቻ ሥርዓት የሚኖሩ ከሆነ ከመቁረባቸው በፊት ፫ ቀናት ከቊርባን በኋላ ፪ ቀናት ከሩካቤ ሥጋ መከልከል ይገባቸዋል፤ ወንዶችም ዝንየት (ርስሐት) ካገኛቸው በዚያ ቀን አይቆርቡም፤ ከአንድ ዕለት በኋላ ታጥበው ነጽተው ይቀበላሉ። ማንኛውም ሰው ሊቆርብ በተዘጋጀበት ቀን ዕንቅፋት ቢያገኘው ማለትም ነስር፣ ትውኪያ (አንቃር)፣ ብስና ማንኛውም የአካል መድማት መቁሰል ወደ አፍ የሚገባ እንደ ትንኝ ዝምብ ይህን የመሰለ ሁሉ ቢያጋጥመው በዚያው ዕለት መቁረብ አይገባውም። ከክርስቲያን ወገን ማንም ሰው የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ተቀብሎ ትንሣኤ ዘለሕይወትን ሊወርስ ቢወድ ልቡን ከቂም ከበቀል ሰውነቱን ከበደል ንጹሕ አድርጎ መቀበል አለበት።

ከላይ ስለ ንስሓ በተመለከትነው ክፍል እንዳየነው ሁሉም ምእመን ኃጢአቱን አምኖ፣ አዝኖ ለካህን መናዘዝና ቀኖናውን መፈጸም መቻል አለበት፤ በዚህ መልኩ ካልሆነ ዲያቆኑ በሥርዓተ ቅዳሴ “…እግዚአብሔርን እንዳሳዘነው በእርሱም ላይ እንደ ተነሣሣ ይወቅ ይረዳ…” እንደሚለው እግዚአብሔርን እናሳዝናለን፤ እግዚአብሔር ካዘነብን ደሞ መቀበላችን ለበረከት መሆኑ ቀርቶ ለመርገምና ገሃነመ እሳትን ለመቀበል ይሆንብናል ማለት ነው።

ሌላኛው ሥጋ ወደሙን ለመቀበል በቅድሚያ ፲፰ ሰዓት መጾም ግዴታ ነው፤ ለ፲፰ ሰዓት ጹመን አፋችን ምሬት ሲሰማው መሆን አለበት ቁርባን የምንቀበለው። (ፍት.መን ፲፫፤ ረስጠብ ፵፮) በእነዚህ ነገሮች ራሱን ያበቃና ያዘጋጀ ሰው ቅዳሴ ከመጀመሩ በፊት ንጹሕ ነጭ ልብስ ለብሶ አስቀድሞ ተገኝቶ ሥርዓተ ቅዳሴውን በተመስጦ ኅሊና በአንቃዕድዎ ልቡና ሆኖ መከታተል ማስቀደስ ይገባል፤ ቅዳሴው እያለቀ የመቁረቢያ ሰዓት ሲደርስም ከመቀበል አስቀድሞ “አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ርኩስ ከሆነች ከቤቴ ጠፈር በታች ትገባ ዘንድ የሚገባህ አይደለም። እኔ በዚህ ዓለም አሳዝኜሃለውና በፊትህም ክፉ ሥራ ሠርቻለውና፣ በአርያህና በአምሳልህ የፈጠርከው ነፍሴንና ሥጋዬን ትእዛዝህን በማፍረስ አሳድፌያለሁና፣ በጎ ሥራ ምንም ምን የለኝምና፣ ነገር ግን ስለ መፍጠርህና እኔን ለማዳን ሰው ስለመሆንህ፣ ስለ ክቡር መስቀልህም ማሕዊ ስለሚሆን ሞትህም፣ በሦስተኛው ቀን ስለመነሣትህ፣ ጌታዬ ፈጥሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከበደልና ከመርገም ሁሉ ከርኩሰትም ሁሉ ታነጻኝ ዘንድ እለምንሃለሁ፤ እማልድሃለሁም። የቅድስናህንም ምጢር በተቀብልሁት ጊዜ ለወቀሳና ለመፈራረጃ አይሁንብኝ፤ ማረኝ፤ ይቅርም በለኝ እንጂ። የዓለም ሕይወት ሆይ በእርሱ የኃአቴን ሥርየት የነፍሴንም ሕይወት እንጂ። በሁለት ወገን ድንግል በምትሆን በወለደችህ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም በመጥምቁ በዮሐንስ አማላጅነት ክቡራን በሚሆኑ በመላእክት፣ በሰማዕታት ለበጎ ነገር በሚጋደሉ በጻድቃን ሁሉ ጸሎት እስከ ዘለለሙ ድረስ አሜን!” እያለ በፍርሃት በንስሓ ልቡና መጸለይ ይገባል። (ቅዳሴ ሐዋርያት)

በቅዱስ ቊርባን ጊዜም አስቀድሞ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳት ይቀበላሉ፤ ቀጥሎ በቁምስና መዓርግ ያሉ መነኮሳት፣ ቀጥሎ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት ይቀበላሉ፤ ቀጥሎ ወንዶች በአርባ ቀን የሚጠመቁ ሕፃናት ከሁሉ አስቀድመው ይቀበሉ፤ የዕለት ሹማምንት ናቸውና በንጽሐ ጠባይዕ መላእክትን ይመስላሉና። ከእነዚህ ቀጥሎ ከአርባ ቀን በኋላ እስከ ስድስት፣ ሰባት ዓመት ያሉት ሕፃናት ትንሾቹ በፊት እየሆኑ እንደ የዕድሜያቸው ይቀበሉ፤ ከዚያ ቀጥለው /ክህነት የሌላቸው/ በድንግልና ኑረው የመነኮሱ ደናግል ይቀበሉ፤ ከዚያ ቀጥለው ሃያ፣ ሃያ ሁለት ዓመት የሆናቸው ደናግል ይቀበሉ፤ ከዚያ ቀጥለው በሹመት ያሉ ናቸውና ንፍቀ ዲያቆናት፣ አናጉንስጢሳውያን፣ መዘምራን ይቀበላሉ፤ ከዚያ ቀጥለው የንስሓ ሕዝባውያን በየመዓርጋቸው ይቀበላሉ።

በሴቶችም በኩል ከሁሉ አስቀድሞ የተጠመቁ የሰማንያ ቀን ሕፃናት ይቀበላሉ፤ የዕለት ሹማምንት ናቸውና በንጽሐ ጠባይዕ መላእክትን ይመስላሉና፤ ከእነዚያ ቀጥሎ ከሰማንያ ቀን እስከ ስድስት፣ ሰባት ዓመት ያሉ ሕፃናት እንደ የዕድሜያቸው ሕፃናቱ አስቀድመው ታላላቆች ቀጥለው ይቀበላሉ፤ ከዚያ ቀጥለው ዐሥራ ሁለት፣ ዐሥራ አምስት የሆናቸው ደናግል ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው የቀሳውስት ሚስቶች ይቀበላሉ፤ ከእነዚያ ቀጥለው በሕግ ኑረው የመነኮሱ እናቶች ይቀበላሉ፤ ከእነዚያ ቀጥለው የዲያቆናት ሚስቶች ይቀበላሉ፤ ከእነዚያ ቀጥለው በንሰሓ ተመልሰው የመነኮሱ መነኮሳት እና መነኮሳይያት ይቀበላሉ፤ ከእነዚያ በኋላ የንፍቀ ዲያቆናት፣ የአናጉንስጢሳውያን፣ የመዘምራን ሚስቶች ይቀበላሉ፤ ከእነዚያ ቀጥለው በሕግ ጸንተው ያሉ ሕጋውያን እናቶች ይቀበላሉ፤ ከእነዚያ ቀጥለው የንስሓ ሕዝባውያን ሚስቶች በየመዓርጋቸው ይቀበላሉ።

ቅዱስ ቊርባንን ስንቀበል፦

ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ስንቀበል በፍርሃት ሆነን ቸርነቱን እየተማጸንን “ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ይህ ምሥጢርህ በእኔ በደል አይሁንብኝ ሥጋዬንና ነፍሴን ለማንጻት ይሁንልኝ እንጂ” እያልን ወይም “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ሥሉስ ዘኢይትነገር…” የሚለውን ጸሎት (ምስጋና) በቃል ይዘን መጸለይ ማመስገን ይገባል፤ (ቅዳሴ ሐዋርያት) ቅዱስ ሥጋውን ሲቀበል አንድ ጊዜ ክቡር ደሙን ሲቀበል ሁለት ጊዜ “አሜን” ማለት ይገባል።

ቅዱስ ቊርባንን ከተቀበልን በኋላ፦

ቅዱስ ቊርባንን ከተቀበልን በኋላ እንዲህ ብለን እንጸልያለን፤ ‹‹ሰውን ለማዳን ሰው ከሆነ ከአምላካዊ ምሥጢር በተቀበልሁ በእኔ በአንደበቴ ምስጋናህን በልቡናዬ ሐሤትን በሰውነቴ ደስታን ምላ፡፡›› ቀጥሎም የቅዳሴ ጸበልን ለመጠጣት ከቆምንበት ተመልሰን ድርገት እስኪመለስ መጠበቅ ይገባል፤ በአፍ ውስጥ ትንኝና የመሳሰሉት ተሐዋስያን እንዳይገቡ አፍን በመሐረብ መሸፈን ይገባል፤ ከሠርሆተ ሕዝብ አስቀድሞ (ከስንብት በፊት) ቅዱስ ቊርባንን የተቀበሉ በሌላ ጸሪቀ መበለት አፋቸውን አያድፉ፤ ቅዳሴ ጠበሉም ከአፋቸው አይንጠብ፤(ፍት.መን አን ፲፫ ፥ ፭፻፳፯)፤ ከቤተ መቅደስ ሳይጋፉ በቀስታ ወጥቶ በደጀ ሰላም ጸሪቀ መበለት  ቀምሶ አፍን ማደፍ ይገባል። በዚህ ዕለት ብዙ ማውራት፣ ጸብና ክርክር ካለበት ቦታ መሄድ፣ ወደ ፍርድ ቤት መሄድ መሟገት፣ አብዝቶ መመገብ መጠጣት፣ ዘፈን ጫጫታ ወዳለበት መዝናኛ ቦታዎች መሄድ፣ ከልብስ መራቆት (ሲቆርቡ የለበሱትን ማውለቅ)፣ ጥፍርን መቁረጥ፣ ምራቅን እንትፍ ማለት፣ ፀጉርን መላጨት፣ በውኃ ልብስን ማጠብ፣ ሰውነትንም መታጠብ፣ ብዙ መንገድ መሄድ፣ ብዙ ሥራ መሥራት፣ ተራክቦ መፈጸም (ለሁለት ቀን) በፍጹም የተከለከለ ነው።

የተቀበልነው ቅዱስ ሥጋው ክቡር ደሙ ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሐደው የአምላክ ሥጋና ደም ነውና ፈጽመን በፈሪሃ እግዚአብሔር ልናከብረውና ልንጠነቀቅ ይገባል፤ በዚህ መልኩ ሥርዓቱን ጠብቀን ስንቀበል ሥርየተ ነፍስን ፈውሰ ሥጋን ያሰጣል፤ ልቡናን ያበራል፤ ለበጎ ምግባር ያተጋል፤ ረድኤተ እግዚአብሔርን ያቀርባል። (ሥርዓተ ቅዳሴ፣ ቅዳሴ ሐዋርያት፣ ኅብረ ሥርዓት ዘቤተ ክርስቲያን ኦርቶዶክሳዊት በመምህር አብርሃም አረጋ፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታየ)

ቆየን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!