የማያልቀው ሀብት

ሐምሌ ፲፯፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ነጭ አይሉት ጥቁር፣ አመዳማም አይደል ቀለሙ ይለያል፡፡ብዙዎች ስለ መልኩ መናገር ያዳግታቸውና ዝምታን ይመርጣሉ፤አያሌዎች ደግሞ በተፈጥሮው ተማርከው ውበቱን ያደንቃሉ፤ መግለጽ ግን ያቅታቸዋል፡፡ ጌታው ከፈጠረለት አፍላጋት ሲወጣ እንደ ወይን ሆኖ ሲፈስ፣ ከገነት ከወጣ እንዲህ መልኩ መቀየሩን ያውቅ ይሆን?

ጥርት ባለው ምንጭ ኮለል እያለ ሲወርድ፣ በጅረቱም ሲፈስ ለሚያየው ወደ ሩቅ ሀገር የሚጓዝ መንገደኛ ይመስላል፡፡ ተትሮ ወደ እርሻው እንደሚገሠግሥ ገበሬ ወይም የንግድ ቤቱን በነግህ መክፈት እንዳለበት ነጋዴ ወዳሰበበት ስፍራ በፍጥነት ይነጉዳል፡፡ ግንድና ሥር ካልገደበው፣ ይዞም ካላስቀረው ማንስ ላስቁምህ ቢል እንዴት ይቻለዋል? እንዲያውም አፈር ሰብስቦና ግንድ ይዞ ይዞራል፡፡

በምድር ላይ ሲጓዝ በኅብረ ቀለማቷ አሸብርቆ ላየው እጅጉን አስደናቂ ነው! ሰማያዊ መሬት ላይ በሰማያዊ፣ አረንጓዴ ልምላሜ ላይ ሲደርስ በአረንጓዴ ውበት ይደምቃል፡፡ ዕጣ ፈንታው ሆነናም ተልእኮውን ሳይተው መሬትን ይከባታል፤ አጥግቦም ያጠጣታል፤ ፍሬ ትሰጥ ዘንድ ያረሰርሳታል።

በነፋስ እንቅስቃሴና ውሽንፍር ጊዜ አቤት ምንኛ ያምራል! ድምጹን እያንሾዋሸወ፣ አካሉን እያማታ፣ ወደ ላይና ወደ ታች ሲል ማየት “በእውን ነው ወይስ በሕልም” ያሰኛል! የእርሱ ድንቅ ፍጥረት ለማን ያልሆነ አለ? ያለ እርሱስ ማን ሊኖር ይችላል? ከአካላችን ብቻም ሳይሆን ከቤታችን አልያም ከኑሮአችን ከጠፋ እንዴት ሕይወት ይኖረናል?

ጥማችንን አርክቶ፣ ምግባችንን አዘጋጅቶ፣ አካላችንና ልብሳችንን አጥቦ የሚያኖረንን የማያልቀው ሀብታችንን እንዴት እንገልጸዋለን? ውለታውንስ በምን እንከፍለዋለን? “ግዮን ሆይ፥ ውለታህ ብዙ ነው፤ አንተን የፈጠረም ምስጉን ነው” ብንለውስ ያንሰው ይሆን?

ግዮን ከእናት ሀገራችን ገነት ወጥቶና ከኤፌሶን፣ ከጤግሮስና ከኤፍራጥስ ተለይቶ ወደ ምድር ሲፈስ ለእኛ ፍጹም ደስታችን በመሆኑ “ግዮን ሆይ፥ እንኳንም መጣህልን!” እንለዋለን፤ በእርሱ እንኖራለንና፤ ሕይወታችን ሙሉና ዝግጁ ሆኖልና፤ በገንዛባችን ሳይሆን በተፈጥሮአችን የተሰጠን የማያልቅ ሀብታችን ነውና፡፡

ግዮን መጠጥና፣ መብል ሆኖ፣ ዕፅዋትን፣ አዝርዕትንና ፍራፍሬን የሚያሳድግ ብቻም ሳይሆን በምሽት ለሚጨልም መጠለያችን መብራት ነው፡፡ አምላክ በሰጣቸው ጥበብ ታግዘው ጠበብት በመብራት ማመንጨት ሥራቸው ቤታችን ይበራልናል፤ ለኑሮአችንም እንዳስፈላጊነቱ የምንጠቀምበትን ሁሉ ያገኘነው በግዮን በወንዝ በመሆኑ የማያልቅ ሀብታችን ነው፡፡

የማያልቀው ሀብት እውነትም ውለታው ብዙ ነው! ቅዱሱ አባት አቡነ ዘርዐ ብሩክ ከጠላት ወረራ ባመለጡ ጊዜ አደራ ብለው የሰጡትን ዳዊትና ወንጌል እንዲሁም ሌሎች ሰባት ቅዱሳት መጻሕፍትን በአስደናቂ ተአምር አንድም የውኃ ጠብታ ሳይኖርበት መመለሱ ሲደንቃቸው “በውስጥሽ ታላቅ ድኅነት ይደረግብሽ” ብለው ባረኩ፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ ሲመለሱም “ግዮን ሆይ መጻሕፍቴን ግሺ /መልሺልኝ/”” ሲሉ አደራን የመለሰው ግዮንም አባታችንንና ዘሩፋኤል የተባለውን ደቀ መዝሙራቸውን ብቻ ሳይሆን እኛንም እጅግ አስደንቆናል!

ግዮን አቡነ ዘርዐ ብሩክ በባረኩት ጊዜ መካኖችን አስወልዷል፤ ደውዮችንም ፈውሷል፤ ስሙንም “ዐባይ” አሉት፡፡ አባታችን በሴት አምሳል ውዲቱን ዐባይ እንደ ጠሯት እኛም “እናታችን ዐባይ” እያልን ብንጠራትስ እንችል ይሆን? መጋቢያችን፣ መኖሪያችንና መጠለያችን ናትና፡፡

ዐባይ ሕይወታችን ብቻም ሳትሆን ጌጣችን ሆናለች፤ የከበሩ ዕንቁዎች፣ ውድ የሆኑ ማዕድኖችና አንጸባራቂ የአልማዝ ጌጦች ይገኙባታልና፡፡ ያመረና የተዋበ ቤታችንን የምንሠራባት፣ ግቢያችንንና አትክልት ስፍራችንን የምናስውብባት፣ ተክለ ሰውነታችንንና ልብሳችንን የምናስጌጥባት ዐባይ የማያልቅ ሀብት ናት፡፡
ዐባይ ሆይ፥ የሀገራችን የማያልቅ ሀብት ነሽ! ፈጣሪ በአስደናቂ ጥበቡ ቢፈጥርሽ ተልእኮሽን ሳትረሺ ኢትዮጵያን ታጠጫለሽ፡፡ ምድራችን ስትረሰርስም ዕፅዋቱን፣ አዝርዕቱን፣ ማዕድኑን የከበሩ ድንጋዮችን እንዲሁም ልዩ ልዩ ጌጦችን ትሰጪናለሽና የማያልቅ ሀብታችን ነሽ!

አንቺን የፈጠረ አምላክ ይክበር! ይመስገን!

ምንጭ፡- ወንጌል ትርጓሜ፣ ገድለ አቡነ ዘርዐ ብሩክ