“የሚሰማኝ ግን በተስፋ ይኖራል” (ምሳ.፩፥፴፫)

ዲያቆን ዮሐንስ ተመስገን

ሚያዚያ ፳፮ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

በብዙ ኅብረ አምሳል አምላካችን እግዚአብሔር የሰውን ልጅ አስተምሯል። ነቢያቱን በብዙ ቋንቋና ምሳሌ አናግሯል። የሰው ልጅ በልቡናው መርምሮ የተወደደ ሕይወት መኖር ሲሳነው በሊቀ ነቢያት ሙሴ በኩል ሕገ ኦሪትን ሰጥቶታል። በሕገ ልቡና “እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን” እንደሚል ቀደምት አበው የተጻፈ ነገር ሳይኖር እንደ እግዚአብሔር አሳብ መኖር ችለዋል። (ሮሜ.፰፥፳፰) እንደ አሳቡ መኖር ላልቻሉት ደሞ ጽሕፈቱን እያዩ በንጽሕና እንዲኖሩ ኦሪት ተጽፋ በሙሴ በኩል ተሰጠች። በኋላም ራሱ ጌታችን ሰው ሁኖ ፻፳ ቤተሰብ መርጦ በቃልና በገቢር አስተምሯል። ይህን ትምህርትም ወንጌላውያን ጽፈው ደጉሰው እንዲያስቀምጡት የጌታችን ፈቃድ ሁኖ ለትውልድ ተላልፏል።

እናት የምትወደው ሕፃን ልጇ ካጥር ወጥቶ በመኪና ተገጭቶ እንዳይሞት አጥር ዘግታ እንድትከለክለው ልዑል አምላካችንም ሕግን የሰጠን ስለሚወደን ነው፤ ባለማወቅ ስተን ከመንግሥቱ እንዳንለይ ስለሚያስብልን ነው። “የሚሰማኝ ግን በተስፋ ይኖራል፤ ከክፉም ያርፋል” ተብሎ በተደጋጋሚ የሚነገረው በነቢያትና በሐዋርያት በኩል የተነገረውን ሰምተን በተስፋ እንድንኖርና ከክፉ እንድናርፍ ለማሳሰብ ነው። (ምሳ.፩፥፴፫)

የምንሰማው ማንን ነው?

፩. እግዚአብሔርን

ዓለም ሳይፈጠር የነበረ፣ ዛሬም ያለ፣ ወደ ፊትም ለዘለዓለም የሚኖር አምላካችን እግዚአብሔር ቃሉ የማይለወጥ፣ የማይቀየር፣ የማይተካ እና የማያልፍ ነውና በነቢያቱ፣ በሐዋርያቱ፣ በቅዱሳን አባቶቻችን ላይ አድሮ እንዳስተማረን ሁሉ አሁን ያስተምረናልና፡፡

፪.የቅዱሳንን ሕይወት

የቅዱሳን የተጋድሎ ሕይወት ለእኛ አስተማሪ ነው፡፡ በጸሎትና በጾም ያሳለፉት ዘመናት ያስተምሩናል፤ እንዲሁም ትጋታቸውን ተምሳሌት አድርገን ከመንፈሳዊ ሕይወታቸው እየተማርን ልንኖር ያስፈልገናል፡፡

፫.መጻሕፍትን

ቅዱሳት መጻሕፍት የእግዚአብሔር አምላካችን ድንቅ ሥራዎች የተጻፈባቸው፣ የቅዱሳን ገድል የተጻፈባቸው፣ የጻድቃንን ሰማዕታት ምስክርነት የተመዘገበባቸው ናቸው፡፡ እነርሱም ሲነበቡ ይገባናል፡፡

፬.ቅዱሳት መካናትን

የእግዚአብሔር አምላክ ቅዱስ ቃል የሚነገርባቸው፣ ጸሎት የሚደረግባቸውና የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ የሚፈተትባቸው ቅዱሳት መካናት ታላቅ ትምህርት ቤታችን ናቸው፡፡

ልዑል አምላካችን እግዚአብሔር ለሚሰሙት በቅዱሳኑ ሕይወት፣ በሚነበቡ መጻሕፍትና ገቢረ ተአምራት በሚፈጸምባቸው ቅዱሳት ገዳማትና አድባራት በሚኖሩት ሕጉንና ትእዛዙን በጠበቁ አባቶች ላይ እያደረ ይናገራል። ድውይ እየፈወሰ፣ ሽባ እየተረተረ፣ ሙት እያስነሣ፣ ለምጽ እያነጻ፣ ዕውር እያበራ ይኖራል። በነቢያትና በሐዋርያት ላይ እያደረ ለሚሰሙት ቃላቸውን ቃሉ አድርጎ ይናገርባቸዋል። ይህ ሁሉ ግን ሰምተው በተስፋ እንዲኖሩ ነው።

ከክፉ ማረፍ የተባለውስ ምንድን ነው ብሎ ለሚጠይቅ የሰይጣን ፍላጻ፣ የሲኦል እስራት የዲያብሎስ ግዛት ሳያገኘው ነፍሱ በገነት፣ ከሕልቀተ ዓለም በኋላም በመንግሥተ ሰማይ በዕረፍት መኖር ነው። ዳዊት “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም። በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፤ በዕረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል” እንዳለ። (መዝ.፳፫፥፪)

የተወደዳችሁ የልዑል እግዚአብሔር ቤተሰቦች የምንሰማውን መምረጥ እንዲገባ እጽፍላችኋለሁ። ዘመኑ የተለያዩ መረጃዎች እንዲሁ እንደዋዛ ተደበላልቀው የሚለቀቁበት ነው። በጥቅስ የታጀቡ ነፍስን ግን የሚገድሉ ገዳይ ንግግሮችና ጽሑፎች ሜኒስትሪም ሚዲያውን ተቆጣጥረውታል። በዩቱዩቦችና በመካነ ድሮች በየቀኑ የሚለቀቁ አሰቃቂ የደም ፖለቲካ ንግድ፣ የምንዝርና ትውዝፍት ጌጥ፣ የአጥማቂዎች ማወናበጃ ምስሎችና ቪድዮዎች ሞልተውታል። ቅዱሳት ሥዕላትን ይዘው፣ ነጠላ አጣፍተው፣ ማተብ እያሳዩ የሚናገሩ ሁሉ ተስፋውን ለማሳየት፣ ከክፉ ለማሳረፍ ብቻ እንዳይመስላችሁ፤ በዚህ ምለው እየተገዘቱ የሚያወናብዱ ብዙዎች ናቸውና መጠንቀቅ ያሻል። “በስሜ ብዙዎች ይመጣሉ መባሉ ለዚህ ነው፤ (ማቴ.፳፬፥፭) የተባለውም ይፈጸም ዘንድ በስሙ ይመጣሉና ራስን መጠበቅ አስፈላጊ ነው።

ዘመናችን ተናጋሪ እንጂ አድማጭ የጠፋበት መሆኑም “በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ” እንዲሉ መልካምና ክፉን ለመለየት አስቸጋሪ እየሆነ ነው። ታላቁ መጽሐፋችን ግን እንዲህ ይላል “የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቍጣም የዘገየ ይሁን” (ያዕ.፩፥፲፱)። ለመስማት የፈጠነ ይሁን ማለቱ ዓለምና በዓለም ያለውን አለመሆኑን ሲያሳይ በሌላ ስፍራ “መስማትም የእግዚአብሔርን ቃል ነው ይላል። (ሮሜ ፲፥፲፯) የምንሰማው ቃለ እግዚአብሔርን መሆኑን ሲያሳይ ነው።

በመጨረሻም ልብን የሚያሳርፈውን፣ በመንግሥተ እግዚአብሔር ለመኖር ተስፋ ያለውን፣ ከክፉ የሚጠብቀውን ቃለ እግዚአብሔርን መስማትና በተስፋ መኖር ይገባል እንጂ ከምላስ ተወርውሮ ነፍስን የሚቆራርጥ የክፉዎችን የአንደበት ጦርን አይደለም። እንዲህ ያሉ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ የመንደር ወሬወችን ፊት መንሣት፣ ጆሮ መንፈግ አስፈላጊ መሆኑን እየነገርኳችሁ ጽሑፌን አጠቃልላለሁ።

ቃሉን ሰምተን በተስፋ ለመኖር፣ የሰማነውን በገቢር ገልጠን መንግሥቱን ለመውረስ ያብቃን። አሜን!