‹‹የሚራሩ ብፁዓን ናቸው›› (ማቴ.፭፥፯)
መምህር ዐቢይ ሙሉቀን
መጋቢት ፲፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
መራራት ማለት ምሕረት ማድረግ፣ ቸርነት፣ ለተጨነቀ ወይም ለተቸገረ ማዘንና ርዳታን መስጠት፣ ይቅር ማለት፣ ማዘን፣ ወዘተ ሲሆን ምሕረት ሥጋዊና ምሕረት መንፈሳዊ ተብሎ በሁለት ሊከፈል ይችላል።
ሀ. ምሕረት ሥጋዊ፡- ርኅሩኅነት፣ ቆርሶ ማጉረስ፣ቀዶ ማልበስ፣ ቢበደሉ ይቅርታ ቢበድሉ ማሩኝታ ነው፡፡ ‹‹ብፁዕ ዘይሌቡ ላዕለ ነዳይ ወምስኪን እምዕለት እኪት ያድኅኖ እግዚአብሔር፤ ለድሃና ለምስኪን የሚያስብ ብፁዕ ነው እግዚአብሔር ከክፉ ቀን ያድነዋል›› በማለት ልበ አምላክ ዳዊት እንደተናገረው ለተቸገረ ማብላት ማጠጣት፣ ድኆችን ማሰብ ያስፈልጋል። እግዚአብሔር በባለጸጋዎች ላይ አድሮ ይሰጣል፤ በነዳያን ላይ አድሮ ይቀበላል። ‹‹ዘየዐሢ ተወካፊ፤ የሚሰጥ የሚቀበል›› ተብሎ በትምህርተ ኅቡኣት እንደተጻፈ። ስለዚህ ማንኛውም ሰው ለተቸገረ ሲሰጥ ለእግዚአብሔር እንዳደረገው አምኖ መስጠት አለበት፡፡ (መዝ.፵፥፩)
ንጉሠ ሰማያት ወምድር ኢየሱስ ክርስቶስ በዳግም ምጽአቱ ለወዳጆቹ የሚናገረው ቃል ‹‹እናንተ የአባቴ ቡሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ትወርሱ ዘንድ ኑ። ተርቤ አብልታችሁኛልና ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና… ያንጊዜም ጻድቃን … አቤቱ መቸ ተርበህ አይተንህ አበላንህ መቼስ ተጠምተህ አይተንህ አጠጣንህ›› ይሉታል ንጉሡም መልሶ እንዲህ ይላቸዋል። እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ ከአመኑ ከእነዚህ ከታናናሾቹ ወንድሞቼ ለአንዱ የአደረጋችሁትን ሁሉ ለእኔ አደረጋችሁት” የሚል ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነቱን መልካም ተግባር ሁሉም ሊያከናውነው ያስፈልጋል። ሰው ሁሉ እንዲህ ሲያደርግና ሲሠራ ብፁዕ ይባላል። (ማቴ. ፳፭፥፴፬-፵)
በአሁኑ ወቅት በትግራይ፣ በማይካድራና በመተከል ከየቤታቸው ተፈናቅለው፣ በሜዳ ላይ በድንኳን የተቀመጡ፣ የጎዳና ተዳዳሪ የሆኑ፣ በነበረው ችግር ሀብት ንብረታቸው ወድሞባቸው፣ የሚበሉት የሚጠጡት ያጡ ወገኖቻችን እየተሠቃዩ የሚገኙ ወገኖቻችን ብዙ ናቸው። ለእነዚህ ወገኖቻችን ሁሉ ልንደርስላቸው ይገባል። ለእንደነዚህ ያሉት ወገኖቻችን መድረስ ብፁዕ ያስብላልና።
ለ. ምሕረት መንፈሳዊ፡- አንድ ሰው ክፉው ምግባር መልካም ምግባር መስሎት ይዞት ሲኖር መክሮ አስተምህሮ መመለስ ምሕረት መንፈሳዊ ይባላል። ዛሬ ወጣቱ በአንዳንድ አካባቢ በጫት፣ በሲጋራ፣ በመጠጥ ሱስ ተይዞ፣ በዝሙት፣ በስርቆት፣ በብዙ አስከፊ ምግባራት ተጠምዶ ይገኛል። በአንዳንድ አካባቢ ደግሞ ከቃለ እግዚአብሔር ርቆ፣ መማር እየፈለገ ግን የሚያስተምረው አጥቶ፣ የሚያስተምር ቢገኝም በሀገሪቱ አለመረጋጋት በአግባቡ ተቀምጦ መማር የማይችልበት ሁኔታ ላይ በመገኘቱ እየተቸገረ ሳይወድ በግድ ወደማይሆን ሁኔታ እየገባ ይገኛል። ስለዚህ እንደነዚህ ያሉ ወገኖችን ከክፉ ሕይወት መመለስ ምሕረት መንፈሳዊ ይባላል። በአርአያ እግዚአብሔር የተፈጠረ ሰው እንደዚህ ባልሆነ ሕይወት ተጠምዶ ማየት እጅግ አሰቃቂ ነው። ‹‹ኃጢአተኛውን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ራሱን ከሞት እንዳደነ፥ ብዙ ኃጢአቱንም እንደ አስተሰረየ ይወቅ›› እንዲል። (ያዕ. ፭፥፳)
በሌላም መንገድ አንድ ሰው ክህደቱን (ምንፍቅናውን) ትክክለኛ ሃይማኖት መስሎት ይዞት ሲኖር መክሮ አስተምህሮ ወደ ትክክለኛው ሃይማኖት መመለስ ነው። ዛሬ ዛሬ በተለይም ወጣቱ ፍልስፍናን ከሃይማኖት፣ ሳይንስን ከሃይማኖት፣ ሞራልን ከሃይማኖት፣ መለየት ተስኖት የሳይንስ፣ ዕውቀት የለው፣ የፍልስፍና ዕውቀት የለው፣ የሥነ ምግባር ዕውቀት የለው ፣ የሃይማኖት ዕውቀት በተለይም የውጪ ጠላት በፈጠረበት የዘረኝነት መንፈስ ተለክፎ ሁሉ ተደበላልቆበት ተቀምጧል። ስለዚህ በእንደዚህ ዓይነት መምታታት ያለን ሰው መክሮ አስተምህሮ ወደ ትክክለኛው ሃይማኖት መመለስ ምሕረት መንፈሳዊ ይባላል፡፡ በቅዱስ ወንጌልም የተጻፈውና ብፁዕ የሚያስብለው ተግባር ይህ ነው። ዓለም እየጠፋ ነው፤ የተዘራብን የዘረኝነት መንፈስ፣ ሀገራችን ያለችበት የፖለቲካ ሁኔታ እርስ በእርስ መተሳሰብን አንዱ ለሌላው መራራትን የሚገፋፋ አይደለም።
አሁን ያለንበት ወቅት ከሃይማኖት ይልቅ ለዘር ቅድሚያ የተሰጠበት፣ ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ የፖለቲካ ፓርቲ ይበልጥብኛል የሚባልበት ዘመን ሆኗል። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ እንደ ፖለቲከኛ እንጂ እንደ ክርስትና ስለማይጠቅም የሚጠቅመውንና የማይጠቅመውን፣ የሚጎዳውንና የማይጎዳውን መለየት ያስፈልጋል። በክርስትና ዘር፣ ጎሣ፣ ቀለም፣ ብሔር ወዘተ የሚባሉ ጉዳዮች ቦታ የላቸውም። በአርባ በሰማንያ ቀናችን ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና ስንቀበል የአንድ አባትና የአንዲት እናት ልጆች ሆነናል።
ሰዎች በደረሰው ችግር ከቤታቸው ተፈናቅለው፣ ሕፃናቱ እናት አባቶቻቸው ሙተውባቸው፣ አረጋውያኑ ጧሪ ቀባሪ አጥተው በባዶ ቦታ ወድቀው በረኃብ አለንጋ እየተገረፉ ይገኛሉ። ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ ‹‹ኀየሱ ቅቱላን በሰይፍ እምቅቱላን በረኃብ ፤ በሰይፍ የሞቱት በረኃብ ከሞቱት የተሻሉ ሆኑ›› በማለት እንደተናገረው ምንም እንኳን ለጊዜው ባለመሞታቸው ቢደሰቱም አሁን ረኃቡን መቋቋም አልችል ሲሉ በሞቱት ሰዎች እየቀኑ ያሉበት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። ስለዚህ በእንደዚህ ዓይነት ችግር ላይ ላሉት መራራት ብፁዕ ያስብላልና ልንራራላቸውና ልንደርስላቸው ይገባል። (ሰቆ.ኤር.፬፥፱)
ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስም ‹‹መልካም መሥራትን ተማሩ፤ ፍርድን ፈልጉ፤ የተገፋውን አድኑ፤ ለድሃ አደጉ ፍረዱለት፤ ስለመበለቲቱም ተሟገቱ›› በማለት ፍርድ ለተጓደለበት የሚገባውን ፍርድ እንዲያገኝ ማድረግ፣ ለተበደለው ማገዝ፣ የተገፋውን መርዳት፣ በችግር ላይ ያለውን መንከባከብ፣ በአጠቃላይ መልካም መሥራት እንደሚያስፈልግ አስረድቷል። (ኢሳ.፩፥፲፯)
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ርኅራኄ እንደሚያስፈልግና እርስ በእርሳችንም መተጋገዝ እንደሚያስፈልግ በስፋት አስረድቷል። ለማሳያ ያህል ለኤፌሶን ምእመናን በላከው መልእክቱ ‹‹እርስ በእርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፤ እግዚአብሔርም በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ›› በማለት ምን እንደሚያስፈልገንና የሚያስፈልገንን ጉዳይ ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን ይህንም አብነት ልናደርገው የሚገባንን የእግዚአብሔርንም ፍቅር በመጥቀስ አስረዳን። (ኤፌ.፬፥፴፩)
ወንጌላዊውና የጌታ ወዳጅ (ፍቁረ እግዚእ) እየተባለ የሚጠራው ዮሐንስ በመልእክቱ ‹‹በዚህም ፍቅርን አወቅነው እርሱ ራሱን ስለእኛ አሳልፎ ሰጥቷልና፤ እኛም ስለባልንጀሮቻችን ራሳችንን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባናል። የዚህ ዓለም ንብረት ያለው ወንድሙንም ተቸግሮ አይቶ ምጽዋትን የሚከለክለው የእግዚአብሔር ፍቅር እንዴት በእርሱ ላይ ይኖራል?›› በማለት ዘለዓለማዊ ሕይወትን ለማግኘት በዚህ ዓለም ስንኖር ምን ማድረግ እንዳለብን አስረድቷል። (፩ ዮሐ. ፫፥፲፮-፲፯)
ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ ‹‹የሁሉም ፍጻሜ የባልንጀራችሁን መከራ እየተቀበላችሁ አንድ ልብ ትሆኑ ዘንድ ነው፤ እንደ ወንድሞችም ተዋደዱ፤ ርኅሩኆችና ትሑታንም ሁኑ፤ ክፉ ላደረገባችሁ ክፉ አትመልሱ፤ የሰደባችሁንም አትስደቡ፤ ጠላታችሁንም መርቁ፤ በረከትን ትወርሱ ዘንድ ለዚህ ተጠርታችኋልና›› በማለት አንዱ ለሌላው መራራት እንዳለበት፣ ለሚወደው ብቻ ሳይሆን ክፉ ላደረገበትም ሳይቀር መልካም ማድረግ እንደሚኖርበት በዚህም በረከትን ሊወርስ እንደሚችል አስተምሯል። (፩ጴጥ.፫፥፰-፲)
የሰዎች ችግር የሚበላ የሚጠጣ ብቻ ላይሆን ይችላል። የሥነ ልቡና መጎዳት፣ ከቃለ እግዚአብሔር መለየት፣ ከቤተ ክርስቲያን መራቅ ወዘተ ሁሉ ያለበት ነው። በዚህ ሁሉ ከጎናቸው በመገኘት ከቃለ እግዚአብሔር በመራቅ የቃለ እግዚአብሔር ጥማት ያለበትን በቃለ እግዚአብሔር ማርካት፣ የሥነ ልቡና ጉዳት የደረሰበትን ማጽናናትና ማረጋጋት ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል የተናገረውን በድጓው እንዲህ ሲል ጠቅሶት እናገኛለን። ‹‹ቦአ ኢየሱስ ምኵራበ አይሁድ ወመሀረ ቃለ ሃይማኖት ወይቤሎሙ ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕት፤ ኢየሱስ ከአይሁድ ምኩራብ ገባ፤ የሃይማኖትን ቃል አስተማረ፤ ከመሥዋዕት ይልቅ ምጽዋትን እመርጣለሁ አላቸው›› እንዲል። (ጾመ ድጓ ዘምኵራብ)
ይህ ሁሉ የሚያስረዳን እግዚአብሔር አምላካችን በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረው ፍጥረት በረኃብ እየተሠቃየ ማየት አግባብ እንዳልሆነ ይልቁንም መራራት እንዳለብን፣ ከተረፈን ሳይሆን ካለን ከፍለን እንድንሰጥ ነው። እግዚአብሔር በረኃብና በጥም እየተሠቃዩ የሚገኙ ወገኖቻችንን በቸርነቱ ይጎብኝልን፤ አሜን።