የመከሩ መሰብሰቢያ ጊዜው አሁን ነው
አሁን ያለንበት ዘመን ምንም እንኳን የኢ-አማንያንና የመናፍቃን ሴራና ዘመቻ ያየለበት ተልእኮአቸውና ተንኮላቸው የረቀቀበትና በቤተክርስቲያን መስለው ገብተው የሚፈነጩበት እንዲሁም ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ አፉን ከፍቶ እንደ ቀትር እባብ የሚራወጥበት ጊዜ ቢሆንም፤ ኃጢአት በበዛበት የእግዚአብሔር ጸጋ ትበዛለች ነውና ሠራተኛው ያለችውን ጥቂት ዕረፍቱን ለጉባኤ፣ የኮሌጅ ተማሪው እንደ ዕንቁ የተወደደች ጊዜውን ለወንጌል፣ ነጋዴውና ባለሥልጣኑ በገንዘብና በብዙ ሥራ የምትተመን ጊዜውን ለቤተክርስቲያን አገልግሎት የሰጠበትና ለቤተ ክርስቲያንም መልካም አጋጣሚ የተፈጠረበት ነው፡፡
ከሀገር ውጪና በጠረፋማ የሀገሪቱ አካባቢ ኢትዮጵያውያን ባሉበት ሁሉ የቻሉ ቤተክርስቲያን እየተከሉ፣ ያልቻሉ ጉባኤ እየመሠረቱ ይህም ባይሳካ በጽዋ ማኅበር ተሰብስበው በቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ጥላ ሥር ተጠልለው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከትም ደፋ ቀና የሚሉበትም ጊዜ ነው፡፡
አባቶች ከልጆች ጋር ለመሥራት የተነሡበት፣ አህጉረ ስብከት ካህናትን ለማሠልጠንና ሕዝቡን በጉባኤ ለማስተማር የተጉበት፤ በምዕራብ በምሥራቅና በደቡብ የሀገሪቱ ክፍል ከግራኝ ወረራ በኋላ ተረሠቶ የነበረው ሥርዓተ ገዳም በትጉኃን ጳጳሳት ጥረትና በቅዱስ ሲኖዶስ ድጋፍ መስፋፋት የጀመረበት ጊዜም ነው፡፡
የምእመኑ ወደ ቤተክርስቲያን መምጣት መልካም አጋጣሚ ስለፈጠረና ጥቂትም ስለሠራን ነው በርቀት ሆነው ታሪኳንና ቀጥተኝነቷን በዝና ብቻ የሚያውቋትና ወደ እርሷም ለመመለስ ይናፍቋት የነበሩት ወገኖቻችን ወደዚህች ቅድስትና ንጽሕት ወደ ሆነች ቤተክርስቲያን እየተመለሱ በሥርዓቷም ለመገልገልና ለማገልገል እየተፋጠኑ የሚታዩት፡፡
«በአዝመራ ጊዜ ጐበዝ ገበሬ ምርቱን መሰብሰብ ካልቻለ ዝንጀሮ ይጫወትበታል» እንደሚባለው፤ እኛም ቅድስት ቤተክርስቲያንን በመናፈቅና በመፈልግ እየመጡ ያሉትን ወገኖችና ለአገልግሎት የተነሡትን ምእመናን በአግባቡ ካልያዝን የቤተክርስቲያንን ሥርዓትና ሕግን ለማፍለስ የተሰለፉ፤ ገዳማትና አድባራትን ጠፍ ለማድረግ ያሰፈሰፉ፤ የቤተክርስቲያንን ይዞታ ለመንጠቅ የዘመቱ፤ በቤተክርስቲያን ውስጥ ሆነው ቤተክርስቲያናችንን በኑፋቄ መርዝ ለመበከል የታጠቁ፣ ቅርስዋንና ንዋየ ቅድሳቷን በመዝረፍ ለመክበር የቋመጡ የውስጥ አርበኞች ወደ ቤተክርስቲያን እየመጡ ያሉትንና ለአገልግሎት የሚፋጠኑትን ማሰናከላቸው አይቀሬ ነው፡፡
የሕዝቡ ወደ ቤተክርስቲያን መምጣት በራሱ አስደሳችና መልካም አጋጣሚ ቢሆንም ካልሠራንበት፤ አጋጣሚው ብቻውን በጐ ቢሆን ውጤት አያመጣም፡፡ በጐ አጋጣሚዎችን አግኝተው፤ በአጋጣሚዎቹ ተጠቅመው ሳይሠሩ ያለፉ አሉና፡፡ በዘመነ ሐዋርያት ከጌታችን ደቀ መዛሙርት ገጽ በገጽ መማር እየቻሉ አጋጣሚውን ያልተጠቀሙ ነበሩ፡፡
በዚህ ዘመንም ቅድስት ንጽሕት የሆነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ወድደውና ፈቅደው የሚመጡ ወገኖቻችን ተገቢውን የቤተክርስቲያን ትምህርት ተጠንቅቀን ካላስተማርን፣ ገዳማትና አድባራትን ለመርዳት ሲነሡ ተቀናጅተው ውጤት የሚያመጡበትን መንገድ ካልመራናቸው፣ የተዘጉትን በሚያስከፍቱበት ጊዜ በቂ አገልጋይ ካላሠማራንላቸው፤ ጉባኤያትን እያዘጋጁ የመምህራን ያለህ ሲሉ ቦታና ሰው ሳንመርጥ በዕለት ድካምና በሰበብ አስባቡ ሳናመካኝ ካልተገኘንላቸው ተሰባስበው ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ሲነሡ ከመንቀፍ ይልቅ በቤተ ክርስቲያን ደንብና ሥርዓት የሚሠማሩበትን ካልቀየስንላቸው፣ ገዳማትና አድባራትን ለመሳለም በሚዘጋጁበት ጊዜ ተገቢውን አቀባበልና ትምህርት እየሰጠን ከቅዱሱ ቦታ በረከት የሚያገኙበትን ሁኔታ ካላመቻቸንላቸው፣ ከዘፈን መዝሙር መርጠው ሲመጡ ትክክለኛውን ያሬዳዊ መዝሙር ካላቀረብንላቸው፣ ከዘልማድ ጋብቻ ተክሊልን መርጠው ሲመጡ ስለትዳር የሚያስተምሩትንና የሚመክሩትን መምህራን በትክክል ካላገኙ፣ ከዕለት ጉርሱ ከዓመት ልብሱ ቆጥቦ ቅዱሳት መጻሕፍትን ገዝቶ ለማንበብ ሲነሣ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሕይወቱን የሚያንጹለትና የሚገነቡለትን ቅዱሳት መጻሕፍት ካላዘጋጀንለት፣ ጋዜጠኛው አርቲስቱ፣ ነጋዴው ሠራተኛው ተማሪው ወታደሩ፣ ¬ፖለቲከኛው ሹፊሩ ወደ ቤተክርስቲያን ሲመጡ ችግሩን ሊፈቱለት አስቀደመው የተጠሩ ሊቃውንት፣ መምህራን፣ መዘምራን፣ አስተናባሪዎች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አመራሮች፣ ደክመውና ሰልችተው በሥጋዋና ግላዊ ምክንያቶች ተጠላልፈው፤ እርስ በእርሳቸው እየተነቃቀፉ ተቃቅረው እንዳይገኙና ዘመኑን ባርኮና ምቹ አድርጎ የሰጠ እግዚአብሔር እንዳያዝን መንቃት ያስፈልጋል፡፡
ትናንት ሲያስተምሩ፣ ሲዘመሩ፣ ከአጥቢያዎቻቸው ውጪ በየገጠሩ ሰንበት ትምህርት ቤት ሲመሠርቱ፣ በየአጥቢያ ቤተክርስቲያናት ያለ እንቅልፍ ሲያገለግሉ የነበሩ፤ በየገጠሩ ገብተው ሕዝቡን ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ሲቀሰቅሱ፣ የነበሩና ያልተጠመቁትን ለማስጠመቅ የተጉት፣ የሚበሉትና የሚለብሱት፣ የሚያርፉበትና የሚተኙበት ጊዜ አጥተው ለቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ ተሰልፈው የነበሩ ሁሉ፤ ሩጫቸውን የፈጸሙ እንዳይመስላቸው ያልተወረሰ ብዙ መሬት ገና መቅረቱን የሚረዱበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ኢያ. 13.1፡፡
ከኋላ የነበሩት ወደፊት ሲመጡ ከፊት የነበሩት ወደ ኋላ እንዳይሄዱ፣ በጨለማ የነበሩት ወደ ብርሃን ሲመጡ፣ በብርሃን የነበሩት ወደ ጨለማ እንዳይመለሱ፣ ጥቂቶች እያሉ ብዙ የሠሩ እግዚአብሔር ሕዝቡን ሲያበዛላቸው እንዳይደክሙና እንዳይዝሉ የማሰቢያና ብዙ የመሥሪያ አጋጣሚው አሁን ነው፡፡
በዚህ የፍጻሜ ዘመን መጨረሻ ወደ ቤተክርስቲያን እየመጣ ያለውን ሕዝብና ለአገልግሎት እየተጋ ያለውን ምእመን እንደ አመጣጡና እንድ እድሜ ገደቡ ትምህርት በመስጠት በእምነት ልናጸናው፣ በአገልግሎት ልናበረታው ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም መምህራን፣ ካህናት እና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች የየራሳችን ድርሻ አለን፡፡
በአጠቃላይ ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን የመጡና እየመጡ ያሉትን ወገኖቻችንን የምንቀበልበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ጀንበር ሳለ ለሚሮጥ፣ የጋለውን ለሚቀጠቅጥ፣ ቀን ሳለ የብርሃን ሥራ ለሚሠራ፣ ሠላሳ፣ ስድሳና መቶ የሚያፈራበት ዘመን ዛሬ ነው፡፡ እናም እግዚአብሔርን የተጠሙ ነፍሳትን የምናድንበትና በቤተክርስቲያን ሥርዓት እንዲኖሩ የምናደርግበት የመከሩ መሰብሰቢያ ጊዜው አሁን ነውና እንጠቀምበት፡፡