«በህልምም ተረድቶ ወደገሊላ ሀገር ሄደ፤……. ናዝሬት ወደምትባልም ከተማ መጥቶ ኖረ»

ሕዳር 6 ቀን እመቤታችን ጌታን ይዛ ከግብጽ /ከስደት/ ወደ ኢየሩሳሌም መመለሷ ይታሰባል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቀጥሎ ካለው የማቴዎስ ወንጌል ምንባብ በመነሳት ይህንን አስመልክቶ በማቴዎስ ወንጌል ትርጓሜው ላይ ያስተማረውን ትምህርት እናቀርባለን፡፡
«ሄሮድስም ከሞተ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በህልም ታይቶ የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሳ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ አለው፡፡ ዮሴፍም ተነስቶ ሕፃኑንና እናቱን በመያዝ ወደ እስራኤል ምድር ተመለሰ፤ ነገር ግን አርኬላዎስ በአባቱ ፈንታ በይሁዳ መንገሱን በሰማ ጊዜ ወደዚያ መሄድ ፈራ፤ በህልምም ተረድቶ ወደገሊላ ሀገር ሄደ፤ በነቢያት ናዝራዊ ይባላል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ» /ማቴ. 2-19-23/፡፡

ዮሴፍ የሕፃናቱ ገዳይ መሞቱን ሰምቶ ከስደት ተመልሶ ወደ ሀገሩ ተመልሶ መጣ፡፡ ነገር ግን ገና እግሩ ሀገሩን እንደረገጠ በድጋሚ የቀደመውን አደጋ ቅሪት /ተረፍ/ አገኘ፤ የክፉው ገዢ ልጅ ንጉስ ሆኗል፡፡

ሄሮድስ በንጉስነት የሚመራትን ሀገር /እስራኤልን/ ለሦስት ከፋፍሎ ሦስቱ ልጆቹ በእርሱ ስር ሆነው በሀገረ ገዢነት እንዲመሯት አድርጎ ነበር፡፡ እርሱ ከሞተ በኋላ ቆይተው እነዚህ ልጆቹ መንግስቱን ለሦስት ተካፍለውታል፡፡ የበላይ ንጉስም አልነበረም፡፡ አሁን ግን ሄሮድስ ገና መሞቱ ስለሆነ መንግስቱ ገና አልተከፋፈለምና ልጁ አርኬላዎስ ለጥቂቱ ለጊዜው መንግስቱን ተቀብሎ ንጉስ ሆነ፡፡

ዮሴፍ በአርኬላዎስ ምክንያት ይሁዳ መቀመጥ ከፈራ /ቤተልሔም የምትገኘው በይሁዳ ነው/ በወንድሙ በሄሮድስ አንቲጳስ ምክንያት ናዝሬት መቀመጥን ለምን አልፈራም? /ናዝሬት የምትገኘው የሄሮድስ አርኬላዎስ ወንድም ሄሮድስ በአንቲጳስ በሚገዛት በገሊላ ነው/ ይህ በቂ ምክንያት አይሆንም?

ቦታውን በመቀየር ጉዳዩ እንዲሸፈን፣ እንዲረሳ ለማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም ጥቃቱ / ግድያው/ ሙሉ በሙሉ የተካሄደው «በቤተልሔምና በአውራጃዋ» ነው /ማቴ. 2-6/፡፡ ስለዚህ ግድያው ከተፈፀመ በኋላ ወጣቱ አርኬላዎስ የሚያስበው ሁሉም እንደተፈፀመ እና እርሱም /ጌታም/ ከብዙዎቹ ሕፃናት ጋር አብሮ እንደተገደለ ነው፡፡

ስለዚህ ዮሴፍ ወደ ናዝሬት መጣ፡፡ በአንድ በኩል አደጋውን ለማስቀረት፤ በሌላ በኩል ደግሞ በቀድሞ /native/ ቦታው ለመኖር፡፡ ተጨማሪ ድፍረት እንዲሆነውም በጉዳዩ ላይ ከመልአኩ ምክር ተሰጠው፡፡ «በህልምም ተረድቶ ወደ ገሊላ ሀገር ሄደ»

ታዲያ ቅዱስ ሉቃስ ወደ ናዝሬት የሄዱት እንዲህ ባለ መልኩ ነው ለምን አላለም? ምክንያቱም ከጌታችን ልደት በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሄዱ ከነገረን በኋላ እንዲህ ይላል፡፡ «በዚያም በእግዚአብሔር ሕግ የተጻፈውን ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ ወደ ገሊላ ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ » /ሉቃ. 2-39/ ወደ ናዝሬት የሄዱት ከግብጽ ሲመለሱ መሆኑን አይነግረንምን?

ቅዱስ ሉቃስ እየተናገረ ያለው ወደ ግብጽ ከመውረዳቸው በፊት ካለው ጊዜ ነው፡፡ ምንም ነገር ከህጉ ውጭ እንዳይፈጸም ከጌታችን ልደት በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው ሕጉ የሚያዘውን ሁሉ ፈጽመዋል፡፡

«እንደ ሙሴ ህግ የመንጻታቸው /ማለትም 40 ቀን/ በተፈጸመ ጊዜ በጌታ ሕግ የበኩር ልጅ ወንድ ልጅ ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይባላል ተብሎ እንደተጻፈ፣ በጌታ ፊት ሊያቆሙት በጌታም ሕግ ሁለት ዋልያ ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች እንደተባለ መስዋዕት ሊያቀርቡ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት» /ሉቃ.2-21-24/ «ሁሉንም እንደህጋቸው ከፈፀሙ በኋላ ወደ ገሊላ ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ፡፡ /ሉቃ.1-39/ ጌታ «ኦሪትና ነቢያትን ልፈጽማቸው እንጂ ልሽራቸው አልመጣሁም» /ማቴ.5-17/ እዳለው፡፡ ይህ ከመደረጉ /ሕጉ ከመፈጸሙ/ በፊት ወደ ግብጽ እንዲወርዱ አልሆነም፡፡ ይህ እስኪሆን ተጠበቀ ከዚያ ወደ ናዝሬት ሄዱ፤ ከዚያ በኋላ ወደ ግብጽ እንዲወርዱ፡፡

ግብጽ ደርሰው ከመጡ በኋላ ግን ቅዱስ ማቴዎስ እንደተናገረ መልአኩ ወደ ናዝሬት እንዲወርዱ ያዘቸዋል፡፡ መጀመሪያ ወደ ናዝሬት የሄዱት ግን ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው ሳይሆን ቅዱስ ሉቃስ እንዳለው የመኖሪያ ቦታቸው /ከተማቸው/ ስለነበረ ነው፡፡ ምክንያቱም ወደ ቤተልሔም የሄዱት ለሕዝብ ቆጠራው እንጂ እዚያ ለመቆየት አይደለም፡፡ ስለዚህ ቤተልሔም የሄዱበትን ምክንያት ሲፈጽሙ ወደ ናዝሬት ተመለሱ፡፡

ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ወደ ናዝሬት የሄዱበትን ሌላም ምክንያት ይነግረናል፤ ትንቢት፡፡ «በነቢያት ልጄ ናዝራዊ ይባላል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ» /ማቴ.2-23/

ይህንን የተናገረው የትኛው ነቢይ ነው» አትጓጉ አትጨነቁም፡፡ ምክንያቱም ከትንቢት ጽሑፎች ብዙዎች ጠፍተው ነበርና፡፡ ይህንንም በመጽሐፈ ዜና መዋዕል ከተመዘገበው ታሪክ ማወቅ እንችላለን፡፡
«የቀረው ፊተኛውና ኋለኛው የሰሎሞን ነገር በነቢዩ በናታን ታሪክ በአኪያ ትንቢት ስለ ናባጥም ልጆች ስለ ኢዮርብዓም ባየው በባለ ራእዩ በኢዩኤል ራእይ የተጻፈ አይደለምን?» እነዚህ ሁሉ ተጽፈዋል የተባሉት ትንቢቶች ግን ዛሬ በእኛ ዘንድ አልደረሱም፡፡

ምክንያቱም አይሁድ ስለ መጻሕፍቱ ቸልተኛ ስለነበሩና በተደጋጋሚ ከአምልኮተ እግዚአብሔር ይወጡ ስለነበር አንዳንዶቹ ጠፍተው ነበር፡፡ ሌሎቹንም ራሳቸው አቃጥለዋቸው ቀዳደዋቸው ነበር፡፡ ሁለተኛው መቃጠላቸው እንደተፈፀመ ነቢዩ ኤርምያስ በትንቢት መጽሐፍ ይነግናል፤

«ንጉሱም /ሴዴቅያስም/ ክርታሱን /የነቢዩ የኤርምያስን ትንቢት የያዘ/ያወጣ ዘንድ ይሁዳን ላከ፤ እርሱም ከጸሐፊው ከኤሊሳማ ክፍል ወሰደው፡፡ ይሁዳም በንጉሱ አጠገብ በቆሙት አለቆች ሁሉ ፊት አነበበው፡፡ ንጉስም በክረምት በሚቀመጥበት ቤት ተቀምጦ ነበር፤ ከፊቱም እሳት ይነድድ ነበር፡፡ ይሁዳም ሦስትና አራት ዐምድ በአነበበ ቁጥር ንጉሱ በብርዕ መቁረጫ ቀደደው፡፡ ክርታሱንም በምድር ውስጥ ባለው እሳት ፈጽሞ እስኪቃጠል ድረስ በምድጃ ውስጥ ወደ አለው እሳት ጣለው፡፡» /ኤር.30-23/

የመጀመሪያውን /መጥፋታቸውን/ በተመለከተ ደግሞ የመጽሐፈ ነገሥት ፀሐፊ የኦሪት ዘዳግም መጽሐፍ አንድ ቦታ ተቀብሮ ተደብቆ ቆይቶ በችግር መገኘቱን ይነግረናል፡፡ «ታላቁ ካህን ኬልቅያስ ፀሐፊውን ሳፋንን የጠፋውን «የሕጉን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ቤት አግኝቻለሁ» አለው»፡፡ /2ኛ ነገ.12-8/

ምንም ቀኝ ገዥ ባልነበረበት ጊዜ መጽሐፎቻቸው መጠበቅ እንዲህ ከከበዳቸው በግዞት ስር በነበሩባቸው ዘመናትማ የበለጠ ጥፋት ይኖራል፡፡

አንድ ነቢይ ይህንን ትንቢት በእርግጠኝነት እንደተናገረው ለማወቅ ግን ሐዋርያቱ በተለያየ ቦታ እርሱን ናዝራዊ ብለው መጥራታቸው ማስረጃ ነው፡፡

«ጴጥሮስም «ወርቅና ብር የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ እነሆ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነስተህ ሂድ» አለው» /ሐዋ.3-6/

«እንግዲህ እናንተ ሁላችሁ የእስራኤልም ወገን ሁሉ በናዝሬቱ በኢየሱስ ስም ይህ ሰው እንደዳነና በፊታችሁ በእውነት እንደቆመ እወቁ» /ሐዋ.4-10/

ታዲያ ይህ ስለ ቤተልሔም የተነገረው ትንቢት ላይ ጥላ ማጥላት አይሆንምን? ሊባል ይችላል፡፡ ምክንያቱም ነቢዩ ሚኪያስ ክርስቶስ /መሲሕ/ ከቤተልሔም እንዲወጣ ተናግሯል፡፡ በፍጹም ምክንያቱም መጀመሪያ ነቢዩ ያለው «በቤተልሔም ይኖራል» ሳይሆን ከቤተልሔም ይወጣል» ነው፡፡
ጌታችን በናዝሬት መኖሩ ናዝራዊም መባሉ የሚያስተምረን ታላቅ ነገር አለ፡፡ ይህች ቦታ /ናዝሬት/ በጣም ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣት ቦታ ነበረች፡፡ ለምሳሌ ናትናኤል «በውኑ ከናዝሬት ደግ ሰው ይወጣልን?» ብሎ ጠይቋል /ዮሐ. 1/ እንዲሁም የናዝሬት ከተማ ብቻ ሳትሆን አጠቃላይ የገሊላ አውራጃ የተናቀ ነበር፡፡ ስለዚህም ነው ፈሪሳውያኑ «ከገሊላ ነቢይ እንደማይነሳ መርምርና እይ» /ዮሐ. 6-52/ ያሉት፡፡ እርሱ ግን ከእነዚህ ቦታዎች ወጣ መባልን አያፍርበትም ደቀ መዛሙርቱንም የመረጠው ከገሊላ ነው፡፡ ይህም ጽድቅን ገንዘብ ካደረግን /ከሰራን/ አፍአዊ /ውጫዊ/ የሆነ የክብርና የሞገስ ምንጭ እንደማያስፈልገን ለማሳየት ነው፡፡ በዚሁ ምክንያት ለራሱ ቤት እንኳን እንዲኖረው አልፈለገም፤ «የሰው ልጅ ግን አንገቱን የሚያስገባበት የለውም» ብሏል፤ ሄሮድስም በእርሱ ላይ ሴራ ሲጎነጉንበት ተሰዷል፤ ልደቱ በከብቶች በረት ሲሆን የተኛውም በግርግም ነው፤ እናቱ እንድትሆን የመረጠውም በዚህ ምድር መስፈርት ዝቅ ያለችውን ትንሽ ብላቴና ነው፤ ይህ ሁሉ እንዲህ ያሉ ነገሮችን እንደ መዋረድ እንዳንቆጥርና እያስተማረንና ራሳችንን ለመልካም ምግባር ብቻ እንድንሰጥ ግድ እያለን ነው፡፡

ስለዚህ በእነዚሁ ሁሉ ነገሮች «እኔ ለዓለሙ ሁሉ ባይተዋር እንድትሆኑ ሳዛችሁ እናንተ በተቃራኒው በሀገራችሁ፤ በወንዛችሁ በዘራችሁ፣ በአባቶቻችሁ የምትኮሩት ለምንድን ነው?» እያለን ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ምንም ምግባር ሳይኖራቸው በአባቶቻቸው ይመኩ የነበሩትን እንዲህ ብሏቸዋል «አብርሃም አባት አለን በማለት የምትድኑ አይምስላችሁ» /ማቴ.3-9/ ቅዱስ ጳውሎስም እንዲህ ይላል «ከእስራኤል የተወለደ ሁሉ እስራኤላዊ አይደለም፤ ከአብርሃም ዘርም ስለሆኑ ሁሉም ልጆች አይደሉም» /ሮሜ. 8-6-8/

እስኪ ንገሩኝ የሳሙኤል ልጆች እነርሱ የአባታቸውን የመልካም ምግባር ሕይወት ወራሾች ሳይሆኑ፤ በአባታቸው መልካምነት /ታላቅነት/ ምን ተጠቀሙ? የሙሴስ ልጆች የእርሱን ፍጹምነት ሳይደግሙ በእርሱ መልካምነት ብቻ ምን ተጠቀሙ? እነርሱ /የሙሴ ልጆች/ መንግስቱን አልወረሱም፤ ነገር ግን መሪ የነበረው ሙሴ አባታቸው ሁኖ ሳለ መንግስቱ የተላለፈው በምግባሩ የሙሴ ልጅ ለሆነው ለሌላው /ለኢያሱ/ ነው፡፡

ጢሞቲዎስስ የተወለደው ከግሪካዊ አባት መሆኑ /ዕብራዊ አለመሆኑ/ ምን ጎዳው) ወይም የኖህ ልጅ /ከነአን/ ባርያ ሆነ እንጂ በአባቱ መልካም ምግባር ምን ተጠቀመ? ኤሳውስ ቢሆን የያቆብ ልጅ አልነበረምን? አባቱስ በእርሱ ጎን አልነበረምን? አዎ አባቱ እርሱ በረከቱን እንዲቀበል ፈልጎ ነበር፤ እርሱ ለዚህ ብሎ አባቱ ያዘዘውን ሁሉ አድርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን ክፉ ስለነበረ እነዚህ ሁሉ ነገሮች አልጠቀሙትም፤ ቀድሞ የተወለደ  ቢሆንም፤ አባቱም በዚህ ረገድ ያሉትን ነገሮች ለማድረግ ከእርሱ ጋር ቢሆንም ፣ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስላልነበር፣ ሁሉን ነገር አጣ፡፡

ስለ ሰዎች ብቻ ለምን እናገራለሁ አይሁድ የእግዚአብሔር ሕዝቦች /ልጆች/ ነበሩ፤ በዚህ ታላቅ ልደት ግን ምንም አልተጠቀሙም፡፡ እንግዲህ አንድ ሰው የእግዚአብሔር ልጅ ሁኖ ለዚህ የተከበረ ልደት የሚገባ መልካምነት ከሌላው የበለጠ የሚቀጣ ከሆነ ለምን የቅርብ እና የሩቅ አባቶቻችሁን እና አያቶቻችሁን ትቆጥራላችሁ»

ይህ የሚሆነው በብሉይ ኪዳን ብቻ ሳይሆን በሐዲስ ኪዳንም ነው፡፡ ያመኑና የተጠመቁ ሰዎች የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው፤ ነገር ግን ከእነዚህ መካከል ወደ እግዚአብሔር መንግስት የማይገቡ አሉ፡፡ እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጅ መሆን እንኳን ያለ ምግባር ብቻውን የማይጠቅም ከሆነ፤ እንዴት ከሰዎች መወለድ ሊጠቅም ሊያኩራራ ይችላል? ስለዚህ ከታላላቅ ሰዎች በመወለድ በሃብት፣ በዘር፣ በሀገር ራሳችንን አናኩራራ፤ ይልቁንም እንዲህ የሚያደርጉትን እንገስጻቸው፡፡ በድሕነትና /ድሀ በመሆንና/ እነዚህን ነገሮች በማጣትም አንዘን፤ እነዚህ ነገሮች በእግዚአብሔር መንግስት አይጠቅሙንምና፤ ይልቁንም የመልካም ምግባር ባለሀብቶች ለመሆን እንጣር፤ . . . .

ምንጭ /Saint Jhon Chrysostome, homily 9 on the Gospel of St. Mathew/

ወስብሐት ለእግዚአብሔር