የመናፍቃን ቅሠጣ በቤተክርስቲያን
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጥንታዊትና ታሪካዊት ነች፡፡ አስተምህሮዋና መሠረተ እምነቷ ከአማናዊው መምህር ኢየሱስ ክርስቶስ የተገኘ በመሆኑ አማናዊትና ርትዕት ናት፡፡ ከቤተክርስቲያን ታሪክ በቀጥታ መረዳት እንደሚቻለው ቤተክርስቲያኗ «ወርቃማ» ተብለው የሚጠሩ ዘመናትን ያሳለፈች ስትሆን በዚያው መጠን እጅግ ፈታኝ የሆኑ የመከራ ጊዜያትንም አሳልፋለች፤አሁንም እያሳለፈች ትገኛለች፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሁሉም የራሱን እምነት በሰላም ማራመድ ሲገባው በተቃራኒው ፀረ ኦርቶዶክስ ዘመቻ በሁለት ግንባር በመካሔድ ላይ ይገኛል፡፡
የፀረ ክርስትናው ቡድን ውድመትና የሐሳውያን መናፍስት የቅሠጣ ዘመቻ፤በሰባክያነ ወንጌል እጥረትና በአባቶች ቸልተኝነት አብያተ ክርስቲያን እየተዘጉ ናቸው፤ምእመናንንም በነጣቂ ተኲላዎች እየተበሉ ነው፡፡ ለውጡን ተከትሎ የሚነሣ ፀረ ክርስትና ቡድን በሚወስደው ኢ-ክርስቲያናዊ እርምጃ ምክንያት የአምልኮተ እግዚአብሔር መፈጸሚያ የሆኑት አብያተ ክርስቲያን ሲደፈሩና ሲወድሙ፤ በአገልጋዮቿ ካህናትና በተከታዮቿ ምእመናንም ላይ እስከ ኅልፈተ ሕይወት ጉዳት ሲደርስ፤ሌላ አቅም ባይኖራትም የተከታይ አቅም እያላት «ዝም በሉ የእኔን እግር ነው የሚበላው» እንደተባለው ዐይነት ነገር የደረሰባትን ጉዳትና ችግር ሁሉ በትዕግሥት፤በአርምሞና በጽሞና ማሳለፍ ይቻላል (ዜና ቤተክርስቲያን ርእሰ አንቀጽ፤ ጥቅምት እና ኅዳር ፳፻፲፩ ዓ.ም.)
እነዚህ ፈታኝ ወቅቶች ኢትዮጵያዊያን ሕዝባዊ ጠባይን የተላበሰ የአኗኗር ዘይቤ እንዲከተሉ ከማድረጉም በላይ የተለያዩ እምነቶች ወደ አገሪቱ እንዲገቡ መንገድን አመቻችተዋል፡፡ ቤተክርስቲያኗም ከውስጥና ከውጭ በተነሱባት ፈተናዎች ምክንያት «ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርቴ አድርጓቸው» (ማቴ.፳፥፲፱ ) «ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ» (ማር.፲፮፥፲፭) «አባቴ እንደላከኝ እናንተንም እልካችኋለሁ» (ዮሐ.፳፥፳፩) ተብሎ በወንጌል የታዘዘውን ለዓለም ለማዳረስ በምታደርገው አገልግሎት ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች እንቅፋት ሆነውባት አገልግሎቷን በሚፈለገው መጠን መፈጸም እንዳትችል አድርጓታል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የኅብረተሰቡን ችግር ምክንያት በማድረግ የተለያዩ እምነቶች አብዛኛውን የገጠርና ጠረፋማ ኀብረተሰብ የተሳሳተ አስተምህሮን በማስተማርና በጥቅም በመደለል ፍጹም ከቤተክርስቲያኗ ሲያርቁት መመልከት የተለመደ እየሆነ መጥቷል፡፡ ለዚህም በቂ ማስረጃ የሚሆኑን ለሦስት ተከታታይ ጊዜያት የተካሄዱት የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤቶች ምስክሮች ናቸው፡፡
ይህ የሌሎች ቤተ እምነት ተጽኖ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በቂ አለመሆንና የምእመናን የግንዛቤ ማነስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ለሦስት ተከታታይ ወቅቶች በተካሄደው የሕዝብና ቤት ቆጠራ መሠረት ቊጥራቸው እየቀነስ መጥቷል፡፡ ይህም በአኃዝ ሲሰላ (በ፲፱፻፸፮ ዓ.ም፤60.02% በ፲፱፻፹፮ ዓ.ም፤ 50.6% እና በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም፤43.5%) ይሆናል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የአጽራረ ቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ የሚገታና ምእመናንን በቤተክርስቲያን እንዲጸኑ ሊያደርግ የሚችል ሥራ መሥራት ካልተቻለ አሁንም ብዙ ምእመናንን ከቤተክርስቲያን በረት ይልቅ ወደ ሌሎች ቤተ እምነቶች የመኮብለል እድላቸውን ሊያሰፋው እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡ ስብከተ ወንጌል የቤተክርስቲያናችን የጀርባ አጥንት ነውና የግራኝ አሕመድ ጊዜ እንደገና እንዳያገረሽ፤ቤተክርስቲያናችን ዘመቻ ፊልጶስን ልታውጅ ይገባታል፡፡
ምንጭ፡ዐውደ ርእይ፤ ስለ ወንጌል እተጋለሁ! መጽሔት ከሰኔ ፲፬ እስከ ፲፮/፳፻፲፩ ዓ.ም.