የሕይወት ኅብስት
እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ከአምስተኛ ባሕርያተ ነፍስ ፈጥሮ በመንፈስ ቅዱስ አክብሮ ሲያኖረው ለሥጋውም ለነፍሱም ምግብ እንዲያስፈልገው አድርጎ ነው፡፡ ለሥጋውም የሚያስፈልገውም ምግብ ልዩ እንደሆነ ሁሉ የሥጋውና የነፍሱ ባሕርያት የተለያየ ነው፤ ነፍስም እንደ ሥጋ ባሕርያት (ነፋስ፣ እሳት፣ ውኃና መሬት) እንዳላት ሁሉ ምግቧም እንደዚያው ይለያል፡፡ የነፍስ ተፈጥሮዋ ረቂቅ ነው፤ በዚህም ለባዊነት፣ ነባቢነትና ሕያውነትም ባሕርይዋ መሆናቸውን ማወቅና መረዳትም ያስፈልጋል፤ ምግቧም የሕይወት ኅብስት ነው፡፡
ለባዊነት
‹‹ለባዊ›› የሚለው የግእዝ ትርጓሜ ቃል ተመራመረ፣ ወደመረዳት ተጠጋ፣ አጠየቀ፣ ተነተነ የሚል ትርጉም አለው፤ ለነገሮች ማስረገጫና ማብራሪያን መፈለግ፣ ከዘፈቀዳዊነት እምነት ይልቅ ለእውነት ድጋፍን መሻት፣ በጭፍን ከማመን ይልቅ ፍጹም እምነት የነፍስ ለባዊነት መገለጫ ነው። ነፍስ አንድን ነገር ከመቀበሏ ወይም ከማመኗ በፊት ቀድማ መመርመርና መፈተሽ ትችላለች፤ የተነገረን ወይንም የተጻፈን ነገር ብቻም እንደወረደ አትቀበልም፤ ሳትመረምርና ሳትመዝን የምትቀበል ከሆነ ግን ከክብሯ ዝቅ ብላለች ማለት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስም ለሰው ልጅ መንፈስን ሁሉ የመመርመር ኃላፊነትና ግዴታ እንደተሰጠው ይገልጻል። ስለዚህም ነፍስ መንፈስን ሁሉ መመርመር አለባት። ይህ የለባዊት ነፍስ ባሕርይ ነው። ‹‹ወንድሞች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኛ ነቢያት ወደ ዓለም መጥተዋልና፡፡ የእግዚአብሔርን መንፈስና የሐሰትን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ የሚያምን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው›› እንዲል፡፡ (፩ኛ ዮሐ. ፬፥፩-፪)
ነፍስ ለባዊት ናትና እውነትን ከሐሰት፣ በጎን ከክፉ፣ ጽድቅን ከኃጢአት ለይታ ታውቃለች። እንዲያውም እንደ አበው አስተምህሮ ከማንኛውም የመጽሐፍ ሕግ ወይም የቃል ትምህርት በፊት ነፍስ ክፉን ከበጎ የምትለይበት ጊዜ ሕገ ልቡና ይባል ነበረ። የነፍስ ክፉን ከበጎ መለየቷ ብቻውን ግን በቂ አይደለም፤ በጎውን መምረጥና መሥራት ይጠበቅበታል፡፡
ነባቢነት
የነፍስ ነባቢነት ባሕርይ ቃል አውጥቶ ለሌሎች በሚሰማ አንደበት መናገር ነው። መናገር ሲባል ትርጉም ያለው ነገር፣ በሰሚው እዝነ ልቡናና ትኩረት በመያዝ አድማጩ ቦታ ሰጥቶት ምላሽ ሊያደርግበት የሚገባ ሐሳብ ማስተላለፍ ነው። ንግግር ሁሉ እውነት አይሆንምና። ከንግግር ሁሉ እውነትን መርጦ ማውጣት፣ መመርመርና ለጋራ ተግባቦት የሚሆነውን መለየት አስፈላጊ የሚሆነውም ለዚህ ነው። ይህንን ማድረግ ደግሞ የነፍስ ለባዊነት ባሕርይ መገለጫ ነው።
ሕያውነት
የነፍስ ሕያውነት ወይንም ዘለዓለማዊነት ከሞት በኋላ ሕይወት መኖሩን የሚመሰክር ነው፡፡ ነፍስ በባሕርይዋ አትሞትም፡፡ ስትፈጠርም ለዘለዓለም ሕይወት ነበርና፤ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከአራቱ ባሕርያት ሥጋ ከአምስተኛ ባሕርያተ ነፍስ አዋሕዶ ነው፡፡ እናም ከሥጋዊ ሞት በኋላ ነፍስ ሞትን ሳይሆን ዘለዓለማዊ ሐሴትን ታደርጋለች፤ ወደ ገሃነመ እሳት የምትጣል ነፍስ ግን ሕያው ናት አትባልም፡፡ ምክንያቱም ሕያውነት የጽድቅ ሥራ ውጤት ነውና፡፡ ከነፍስ ተፈጥሮ ጋር የሚስማማውን ከሕያዊነቷ ጋር የማይቃረነውን ትመርጥ ዘንድ፣ ምርጫዋንም በተግባር ትገልጥ ዘንድ እውቀትስ ተሰጥቷል።
በአጠቃላይ የነፍስ ባሕርይ በጥንተ ተፈጥሮ ሲገለጽ የፈጣሪን አንድነትና ሦስትነት ወደ ማመን፣ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ወደ ማወቅ፣ መረዳትና መፈጸም እና ለቅዱስ ቊርባን ለመብቃት ያደርሳል፡፡ ይህም ከሞተ ሥጋ በኋላ ሕያው የሚያደርገን የነፍስ ምግባችን ነው፡፡
የሕይወት ኅብስት፤ ቅዱስ ቊርባን
በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በምሥጢረ ቊርባን እንደምንማረውና እንደምንረዳው ቅዱስ ቁርባን የጌታችን መድኃታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋው ክቡር ደሙ ነው፡፡ ጌታችንም በወንጌል በማይታበል አማናዊ ቃሉ እንዲህ በማለት ተናግሯል፤ ‹‹ከሰማይ የወረደ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ከዚህ እንጀራ የሚበላ ለዘለዓለም ይኖራል፤ ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው ይህ እንጀራ ሥጋዬ ነው፡፡›› የምንቀበለው ቅዱስ ቁርባን የሕያው አምላክ የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም ነውና የዘላለም ሕይወት ባለቤት መሆናችንን ያረጋግጣል፡፡ (ዮሐ. ፮፥፶፩)
ምግብና መጠጥ ከሰውነታችን እንደሚዋሐድ ሁሉ ሥጋውንና ደሙን ስንቀበል በእውነት እንደሚዋሐደን ለማስረዳት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ተዋሐጃችሁ እኖራለሁ›› ሲለን ሥጋውና ደሙን በሚበላና በሚጠጣ አደረገው፡፡ ምግብ ለሥጋችን ኃይል እንደሚሆነን ሥጋውና ደሙም ለነፍሳችን መንፈሳዊ ኃይል ይሰጠናል፡፡ በመብልም የጠፋው ዓለም በመብል እንዲድን፣ አዳምና ሄዋን በምግብ ምክንያት ልጅነታቸው እንደተገፈፈባቸው፣ ‹‹አባቶቻችሁስ በምድረ በዳ መና በሉ፥ ሞቱም፡፡ ከእርሱ የበላ ሁሉ እንዳይሞት ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው›› በማለት በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ ልጅነታችንን ሊመልስልን በሚበላና በሚጠጣ አደረገው። (ዮሐ. ፮፥ ፵፱)
በማቴዎስ ወንጌል ላይ እንደተመዘገበው ‹‹ሲበሉም ጌታችን ኢየሱስ ኅብስቱን አንሥቶ፥ ባረከ፤ ቈረሰ፤ ለደቀ መዛሙርቱም ይህ ሥጋዬ ነው “እንኩ ብሉ” ሰጠ፡፡ ጽዋውንም አንሥቶ አመስግኖ ሰጣቸው፡፡ እንዲህም አለ፥ ‹‹ሁላችሁም ከእርሱ ጠጡ፤ ኃጢአትን ለማስተሰረይ፤ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የሐዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው›› በማለት የምሥጢረ ቊርባንን አመሠራረት ጽፎልናል፡፡ አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን ሲቀርቡ የነበሩ መሥዋዕቶችን ሁሉ ምሳሌው አድርጎ በማሳለፍ የራሱን መሥዋዕትነት ካቀረበ በኋላ ቀድሞ የነበሩትን ነፍሳት ብቻ ሳይሆን ከዚያም በኋላ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድርስ የሚመጡትን ሁሉ አንድ ጊዜ ባቀረበው መሥዋዕት የሚያድን ስለሆነ ምሥጢሩ ይፈጸም ዘንድ ከሞቱ አስቀድሞ አስተማረ፡፡ ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ የወልደ እጓላ እመሕያው ክርስቶስን ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም፡፡ ሥጋዬን የበላ ደሜንም የጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው›› በማለት እስከዓለም ፍጻሜ የሰው ልጅ ሌላ መሥዋዕት ሳያስፈልገው በአምላካችን ሥጋና ደም ሕይወት እንደሚያገኝ አስተምሮናል፡፡ (ማቴ. ፳፮፥፳፮)
ከዚህም በላይ የተራበና የተጠማ ሰው ብር፣ ወርቅ ከሚሰጡት ይልቅ መብልና መጠጥ የሰጠውን እንደሚወድ ጌታችንም ፍቅሩን ሲገልጥልን የነፍስ ረሃባችንን ሊያስወግድ ሥጋና ደሙን በምግብና በመጠጥ አደረገው፡፡ መብል በቀላሉ ከሰውነታችን እንደሚዋሐድ እንዲሁም ጌታችንም በቀናች ሃይማኖት በመልካም ምግባር ሆነን ሥጋውን ብንበላ ደሙንም ብንጠጣ ለዘለዓለም ሕያዋን ሆነን በክብር እንደምንኖር ጌታችን ኢየሱስ አስተምሮናል፡፡ ‹‹ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁስ በልተውት እንደሞቱበት ያለ መና አይደለም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ግን ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ ይኖራል›› እንዲል፡፡ (ዮሐ. ፮፥፶፰)
ቅዱስ ቊርባን ከስንዴና ከወይን የሚዘጋጅበት ምክንያት
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ‹‹በልቤ ደስታ ጨመርኩ፤ ከስንዴ ፍሬና ከወይን ከዘይትም ይልቅ በዛ›› በማለት በተናገረው ቃል እንደምንረዳው ከአዝዕርት ስንዴን ከፍራፍሬ ደግሞ ወይንን መምረጡን ነው፡፡ ከዚህ ባሻገርም ስንዴ ስብን ይመስላል፤ ወይን ደግሞ ትኩስ ደምን ይመስላል፤ ስለዚህ በሚመስል ነገር መስጠቱ ነው፡፡ (መዝ. ፬፥፯)
ለቅዱስ ቊርባን መብቃት
ሥጋችንን ለመመገብ ውስጣችን እንደሚያስፈልገው፣ በአእምሮአችንም አስበንና ወስነን እንዲሁም እጃችን ታጥበን ለምግብ እንደምንቀርበው ሁሉ ቅዱስ ቊርባንን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት ያስፈልጋል፡፡
በመጀመሪያም በንስሓ ኃጢአታችንን ማንጻት፤ ቀጥሎም ወደ እግዚአብሔር አምላካችን በመቅረብ እና በእምነት ለቅዱስ ቊርባን መብቃት ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም በልባችን የኃጢአት ሐሳብ እንዳያስገቡ አካለዊ ስሜቶቻችንን ሁሉ መግዛት፣ አካልን መታጠብና አቅም የፈቀደውን ንጽሕና በማከናወን ጽዱ እና ነጭ ልብስ መልበስ፣ ቊርባን በሚቀበሉበት ዋዜማ ዕለት ቀለል ያለ ምግብ መመገብና ለዐሥራ ስምንት ሰዓታት ከምግበ ሥጋ መከልከል፣ በትዳር ለሚኖሩ ከቊርባን በፊት ለሦስት ቀናት ከቊርባን በኋላ ለሦስት ቀናት ከሩካቤ መከልከል፣ ለወንዶች ሕልመ ሌሊት (ዝንየት) ለሴቶች ደግሞ የወር አበባ (ወይም በማንኛውም ምክንያት የሚደማ/የሚፈስ፣ ቊስል) ካጋጠማቸው ደሙ ፈጽሞ እስኪደርቅ፣ቊስሉም እስኪድን መቆየት አለባቸው፡፡ ሴቶች ወንድ ቢወልዱ ዐርባ ቀን ሴት ቢወልዱ ደግሞ ሰማንያ ቀን መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ በሚቆርቡበት ዕለት ቅዳሴ ሲጀመር ጀምሮ ተገኝቶ ማስቀድስ አለባቸው፡፡ (ራእ. ፮፥፲፩)
እግዚአብሔር አምላክ ለቅዱስ ቁርባን የበቃን እንሆን ዘንድ እርዳታው አይለየን፤ አሜን፡፡