የሊቀ ማእምራን ወመጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት ባይነሳኝ አጭር የሕይወት ታሪክ

003

ነሐሴ ፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

 

በኢሳይያስ ቦጋለ

የተወደዳችሁ የዝግጅታችን ተከታታዮች! የሊቀ ማእምራን ወመጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት ባይነሳኝን ዜና ዕረፍት ባስነበብንበት ዕለት ሐምሌ ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በገባነው ቃል መሠረት የሊቁን ሙሉ የሕይወት ታሪክ በአጭሩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤

ሊቀ ማእምራን ወመጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት ባይነሳኝ ከአባታቸው ከአቶ ባይነሳኝ ላቀውና ከእናታቸው ከወ/ሮ በፍታ ተሾመ በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት በላስታ /ሙያጃ ወረዳ ልዩ ስሙ ዐሥራ ሁለት ተኹላ ደብረ ዘመዶ መዝገብ ዓምባ ማርያም በተባለው አካባቢ ሐምሌ ፳፩ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ የመዝገብ ዓምባ ማርያም የቅዳሴ መምህር ከነበሩት ባሕታዊ አባ ኃይለ ማርያም ከፊደል ጀምሮ ንባብ፣ ሰዓታት፣ ቅዳሴ ከተማሩ በኋላ በ፲፱፻፵፪ ዓ.ም የወሎ ክፍለ ሀገር ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ከብፁዕ አቡነ ገብርኤል ቀዳማዊ መዓርገ ዲቁና ተቀብለው በመዝገብ ዓምባ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከአንድ ዓመት በላይ በዲቁና አገልግለዋል፡፡

ከዚያም ትምህርታቸውን በመቀጠል በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ወፍጫት መድኀኔ ዓለም ከመምህር መኰንን ሊበን እና ቀጋዎች ገብረ መንፈስ ቅዱስ ከመምህር በጽሐ ቅኔ ከነአገባቡ ጠንቅቀው በመማር አስመስክረዋል፡፡ የቅኔ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በመቄት ወረዳ ገረገራ ጊዮርጊስ ከድጓው መምህሩ መ/ር አበባው አዳነ ድጓና ፀዋትወ ዜማ፤ ዱዳ ኪዳነ ምሕረት ከየኔታ ጌራ ወርቅ አቋቋም፤ በግምጃ ቤት መካነ ነገሥት ማርያም ከመምህር ክፍሌ ይመር የሐዲሳትን እና የሊቃውንትን ትርጓሜ ጠንቅቀው በመማር አስመስክረዋል፡፡

መጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት በመጋቤ ሐዲስ ክፍሌ ይመር፣ በንጉሡና በባለሥልጣናቱ ተመርጠው በወር ፶ ብር እየተከፈላቸው በግምጃ ቤት መካነ ነገሥት የሐዲሳት ትርጓሜ ቤት ከ፲፱፻፷፭-፲፱፻፸ ዓ.ም ድረስ ምክትል መምህር ኾነው ሲያስተምሩ ቆይተዋል፡፡ ከዚያ በኋላ በወቅቱ የጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ቀዳማዊ ትእዛዝ አሁን ‹‹ሐዋርያው ጳውሎስ የሕፃናት መርጃ ማእከል›› በመባል በሚታወቀው ጉባኤ ቤት ከሚያዝያ ወር ፲፱፻፸ ዓ.ም ጀምሮ የሐዲሳት ትርጓሜ መምህር ኾነው ለአንድ ዓመት ያህል አስተምረዋል፡፡

ሊቀ ማእምራን ወልደ ሰንበት መጋቤ ሐዲስ ክፍሌ ይመር ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩም ‹‹መጋቤ ሐዲስ›› በሚል መዓርግ የጎንደር ግምጃ ቤት መካነ ነገሥት ማርያም የመጻሕፍት ትርጓሜ ምስክር ጉባኤ ቤት የትርጓሜ መጻሕፍት መምህር ኾነው ተመድበዋል፡፡ በመምህርነት ከተመደቡበት ከ፲፱፻፸ ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ትርጓሜ መጻሕፍትን በማስተማር በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር በልሉ ልዩ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ የሚገኙ በርካታ የቤተ ክርስቲያን መምህራንን አፍርተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ብፁዕ አቡነ ያሬድ እና ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ ይጠቀሳሉ፡፡

መጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት በ፲፱፻፹፭ ዓ.ም ለጉባኤ ወደ አዲስ አበባ በሔዱበት ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ‹‹እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ በተሻለ ደመወዝ እንመድብዎ›› የሚል ጥያቄ አቅርበውላቸው እንደ ነበርና እርሳቸው ግን ‹‹መካነ ነገሥት ጉባኤ ቤትን እንዳለቅ አደራ አለብኝ›› በማለት ወደ በዓታቸው እንደ ተመለሱ በወቅቱ የነበሩ አባቶች ይናገራሉ፡፡

ሊቀ ማእምራን በቃል ካስተማሩት ትምህርተ ወንጌል ባሻገር የማኅሌተ ጽጌን ዚቅ፤ የሊቃውንት አባቶችን ታሪክ፣ እንደዚሁም የመካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን ታሪክ አዘጋጅተው በማሳተም ለንባብ ያበቁ ሲኾን ‹‹የአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን (ፍሬምናጦስ) እና የአብርሃ ወአጽብሃ ነገሥታት ታሪክ›› ደግሞ ያልታተሙ መጻሕፍቶቻቸው ናቸው፡፡

መጋቤ ሐዲስ ከመምህርነት ሙያቸው በተጨማሪ በብፁዕ አቡነ እንድርያስ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አማካይነት ‹‹ሊቀ ማእምራን›› በሚል መዓርግ ተሰይመው የመካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪነት ኾነው ተሹመው ከ፲፱፻፺፯ ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ድረስ ካህናቱንና ሕዝበ ክርስቲያኑን በቅንነት፣ በትሕትና እና በአባታዊ ሥነ ምግባር ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ ከዚሁ ኹሉ ጋርም ወጣቶችን በቤተ ክርስቲያን እየሰበሰቡ በማስተማርና መምህራንን በመመደብ በየቦታው የሰንበት ት/ቤት አገልግሎት እንዲጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክተዋል፡፡

በአጠቃላይ ሊቀ ማእምራን ወመጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት ባይነሳኝ በጠባይዓቸው ዝምተኛ፣ ትዕግሥተኛና ባሕታዊ፤ ከቃለ እግዚአብሔር በስተቀር ሌላ ክፉ ቃል ከአንደበታቸው የማይወጣ፤ ከተማሪነታቸው ጀምሮ እስከ መምህርነታው ድረስ ከማንም ጋር ተቀያይመው የማያውቁና ከቂም በቀል የራቁ፤ ቀንም ሌሊትም ለአገር ሰላም፣ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገትና ለምእመናን አንድነት የሚጸልዩ፤ ከዓለማዊ ኑሮና ከውዳሴ ከንቱ የተለዩ፤ ከዚሁ ኹሉ ጋርም እንግዶችን መቀበል የሚወዱ፤ ከደመወዛቸውና ከዕለት ጕርሳቸው ቀንሰው ለተቸገሩ የሚሰጡ ርኅሩኅ፣ ደግና ታላቅ አባት ነበሩ፡፡

በመጨረሻም እኒህ ታላቅ ሊቅ ባደረባቸው ሥጋዊ ሕመም በልዩ ልዩ የሕክምና ተቋማት ሲረዱ ቆይተው ሊሻላቸው ባለመቻሉ በጉባኤ ቤታቸው እንዳሉ ሐምሌ ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በተወለዱ በ፹ ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ሥርዓተ ቀብራቸውም የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ የሀገረ ስብከቱና የየወረዳ ቤተ ክህነት ሓላፊዎችና ሠራተኞች፣ ባልንጀሮቻቸው፣ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ደቀ መዛርታቸውና የመንፈስ ልጆቻቸው፣ ማኅበረ ካህናትና በርካታ ምእመናን በተገኙበት በተማሩባትና ወንበር ተክለው፣ ጉባኤ ዘርግተው ትርጓሜ መሕፍትን በማስተማር በርካታ ሊቃውንትን ባፈሩባት በግምጃ ቤት መካነ ነገሥት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሐምሌ ፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ተፈጽሟል፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን የእኒህን አባት በረከት በኹላችንም ያሳድርብን፤ እንደ እርሳቸው ያሉ ሊቃውንትንም አያሳጣን እያልን ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለመንፈስ ልጆቻቸው መጽናናትን እንመኛለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር::