የለንደን ደ/ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን እንደገና ተከፍታ አገልግሎት መስጠት ጀመረች
ታኅሣሥ 25 ቀን 2006 ዓ.ም.
ከUK ቀጠና ማዕከል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትን እና ምእመናንን ባሳዘነ ሁኔታ ከዘጠኝ ወራት በላይ ተዘግታ የቆየችው የለንደን ርእሰ አድባራት ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን እሁድ ታኅሣስ ፳ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ እንጦንስ በተገኙበት በይፋ እንደገና ተከፍታ አገልግሎት መስጠት ጀመረች።
ደብሩ እስካሁን በእንግሊዝ መንግሥት የሚታወቅበትን የእምነት እና የበጎ አድራጎት ተቋማት (Charity) ምዝገባ ወደ “ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ” (Company Limited by Guarantee) ምዝገባ ለመቀየር በተነሱ ሰዎች እና ይህ ምዝገባ ከቤተ ክርስቲያናችን ቃለ አዋዲ ጋር ስለማይስማማ፣ ኃላፊነቱንም በጥቂት ሰዎች እጅ ብቻ የሚያስገባና እነርሱም የሚኖርባቸውን ተጠያቂነት ስለሚቀንስ ለቤተ ክርስቲያን አይስማማም በማለት በተቃወሙ ወገኖች መካከል ልዩነት በመፈጠሩ እና ይህም አለመግባባት ተጠንክሮ መጋቢት ፩ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም. ካህናት ጸሎተ ኪዳን አድርሰው ቅዳሴ ለመግባት እየተዘጋጁ በነበረበት ሰዓት ላይ በተነሳ ረብሻ ቤተ ክርስቲያኒቱ መዘጋቷ ይታወሳል።
ቅዱስ ሲኖዶስም ከሀገረ ስብከቱ በቀረበለት ጥያቄ መሠረት ብፁዕ አቡነ ገብርኤልንና ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስን በሚያዝያ ወር ወደ ለንደን በላከበት ወቅት ምንም እንኳን አብዛኛው የደብሩ ካህናት፣ የሰ/ት/ቤት ወጣቶች እና ምእመናን በቃለ አዋዲ እና በቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ እንደሚመሩ ቢያረጋግጡም (ከዚህ ቀደም የደብሩ አስተዳደር በሀገረ ስብከቱ ስር አልነበረም)፣ ጥቂት ካህናት እና የተወሰኑ ምእመናን ባለመስማማታቸው ሊቃነ ጳጳሳቱ ከአንድ ወር ቆይታ በኋላ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ /ርክበ ካህናት/ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል።
በወርሀ ጥቅምት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ፣ በወቅቱ ከአኀት አብያተ ክርስቲያናት ጋር ለመወያየት ወደ እንግሊዝ መጥተው ከነበሩት ከብፁዕ አቡነ ገብርኤል እና ከብፁዕ አቡነ ያዕቆብ ጋር በመሆን ቤተ ክርስቲያኒቱ ተከፍታ አገልግሎት መስጠት እንድትጀምር ለማድረግ ቢሞክሩም መከፈቷን የሚቃወሙ ሰዎች በር ላይ ረብሻ በማስነሳታቸው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ከፖሊስ ጋር በመነጋገር እና ለህዝቡ ደህንነት በመስጋት ለሌላ ጊዜ እንዲሸጋገር አድርገው ነበር።
ቤተ ክርስቲያኒቱ ከዘጠኝ ወራት በላይ በእንዲህ ያለ ሁኔታ አገልግሎት መስጠት ሳትችል ብትቆይም፣ አሁን ያለው የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ከሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ እና ከሀገሪቱ የበጎ አድራጎት ተቋማት ኮሚሽን/Charity Commission/ ባገኘው ማረጋገጫና ድጋፍ መሠረት አለመግባባቱ የተፈጠረው እና ድርድሩም መቀጠል ያለበት በአምልኮተ እግዚአብሔር ላይ ሳይሆን በሌላው ጉዳይ ላይ መሆኑን በመግለጽ ቤተ ክርስቲያኒቱም በምትከፈትበት ጊዜ ችግር እንዳይፈጠር የአካባቢውን ፖሊስ እርዳታ በመጠየቅ ታኅሣስ ፳ ቀን የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ አእላፍ ተወልደ ገብሩ፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ጽዮን አባ ግርማ ከበደ፣ የደብሩ ሊቃውንት እና ካህናት፣ መዘምራን እና ምእመናን በተገኙበት በይፋ አገልግሎት መስጠቷን ቀጥላለች።
ብፁዕ አቡነ እንጦንስ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ በቦታው በመገኘት ሥርዓተ ጸሎቱን ሲመሩ እና ቡራኬ ሲሰጡ የቆዩ ሲሆን ባስተላለፉት ቃለ ምእዳንም የሰው ጠላቱ ዲያብሎስ ብቻ መሆኑን እና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚወዱንን ብቻ ሳይሆን የሚጠሉንንም እንድናፈቅር እንዳዘዘን በማስተማር ማንም በማንም ላይ ቂም እንዳይይዝ አባታዊ ምክር ሰጥተዋል፡፡ ለህዝቡም ጸሎተ ንስሐ ከደገሙ በኋላ ሦስት ጊዜ “ይቅር ለመድኃኔዓለም!!!” በማስባል እርስ በርስ አስታርቀዋል። በቀጣይም ተቋርጦ የነበረው አገልግሎት እንደሚቀጥል፣ ሀገረ ስብከቱ ከሰበካ ጉባኤው ጋር በመሆን አለመግባባቱን በውይይት እና በክርስቲያናዊ ፍቅር ለመፍታት እና አዲስ የሰበካ አስተዳደር ጉባኤ ለማስመረጥ እንደሚጥር ገልጸዋል።
በቤተ ክርስቲያኒቱ የተገኙ ሊቃውንት፣ ካህናት እና ምእመናን ከእንባ ጭምር በመጸለይ እና በመዘመር አምላካቸውን ያመሰገኑ ሲሆን፤ መርሐ ግብሩ በእግዚአብሔር ቸርነት ከቀኑ 7፡30 በሰላም ተጠናቋል።