ዝክረ ግማደ መስቀሉ
መጋቢት ፱ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
የክብር ባለቤት ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል የተገለጠበትና የተገኘበት መጋቢት ፲ ግማደ መስቀሉን የምንዘክርበት ዕለት ነው። የዚህም የከበረ ዕፀ መስቀል መገለጡና መገኘቱ ሁለት ጊዜ ሆኗል። መጀመሪያ የጻድቁ ንጉሥ የቈስጠንጢኖስ እናት በሆነች በንግሥት ዕሌኒ እጅ ነው።
እርሷ ለእግዚአብሔር ተስላ ነበርና ልጇ ቈስጠንጢኖስ ወደ ክርስቲያን ሃይማኖት ቢገባ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዳ መስቀሉን እስካገኘችው ድረስ ልትፈልግው በኢየሩሳሌም ያሉ ቅዱሳት መካናትንና አብያተ ክርስቲያናትን ልታንፃቸው ነው።
ከዚህ በኃላ ልጇ አምኖ የክርስትና ጥምቀትን በተጠበቀ ጊዜ ዕሌኒ ቅድስት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች፡፡ ከእረሷ ጋርም ብዙ ሠራዊት ነበር፤ ደርሳም ስለ ከበረ መስቀል መረመረች፤ የሚያስረዳት አላገኘችም፤ የአይሁድ ወገን የሆነ አንድ ሽማግሌ ሰው አሥራ በረኃብና በጥማት አስጨነቀችው። በተጨነቀም ጊዜ ለንግሥት ዕሌኒ የጎልጎታን ኮረብታ አስጠርጊ ብሎ ነገራ፤ት እርሷም ይጠርጉ ዘንድ አይሁድን አዘዘቻቸው።
ቤቱን የሚጠርግ ሰው ሁሉ ጥራጊውን በውስጡ የከበረ መስቀል ባለበት በጌታችን መቃብር ላይ እንዲጥል አይሁድ አስቀድመው አዝዘው ነበርና ንግሥት ዕሌኒ እስከ ደረሰችበት ጊዜ ከሁለት መቶ ዓመት በላይ ጥራጊያቸውን ሲጥሉበት ኖሩ፤ ኮረብታም ሆነ። አይሁድም በጠረጉ ጊዜ ሦስት መስቀሎች ተገለጡ፤ የክብር ባለቤት ክርስቶስ የተሰቀለበት የትኛው እንደሆነ አላወቁም። የሞተ ሰውም አግኝተው አመጡ።
አንዱንም መስቀል አምጥተው በሞተው ሰው ላይ አኖሩት፤ አልተነሣም፤ ደግሞ ሌላውን መስቀል አምጥተው በሙቱ ላይ አኖሩ፤ አሁንም አልተነሣም፤ ከዚህም በኃላ ሦስተኛውን መስቀል አምጥተው በሙቱ ላይ አደረጉት፤ ያንጊዜ የሞተው ሰው ተነሣ፤ ዕሌኒም የክርስቶስ መስቀል እንደሆነ ዐውቃ ሰገደችለት፤ የክርስቲያንም ወገኖች ሁሉ ሰገዱለት።
ለልጅዋ የላከችው ‹‹ይህ መስቀል ነው›› የሚል በሌላ መጽሐፍ ይገኛል፤ የቀረው ግን ግንዱ በውስጡ ተተክሎበት የነበረው ከእርሱም እኩሌታውን ከቅንዋቱ ጋራ ወደ ልጅዋ የላከችው ነው።ከዚህም በኃላ ሥርዓታቸውና የሕንፃቸው ነገር በመስከረም ወር በዐሥራ ሰባት ተጽፎ የሚገኝ አብያተ ክርስቲያናትንና የከበሩ ቦታዎችን አነፀች።
ሁለተኛው በሮሙ ንጉሥ በሕርቃል ዘመን የሆነው ሲሆን የፋርስ ሰዎች በግብጽ ሀገር ሳሉ ወደ ሀገራቸው ሊመለሱ ወደዱ። ከሹማምንቶቻቸው አንዱ የጦር መኰንን ተነጥሎ ወደ ኢየሩሳሌም አልፎ ደረሰ፤ ወደ ከበረ መስቀል ቤተ ክርስቲያንም ገባ። መስቀሉም በላዮ በተተከለበት ግንድ ፊት ታላቅ ብርሃን ሲበራ አይቶ ሊያነሣው እጁን ዘረጋ። እሳትም ወጥታ እጁን አቃጠለችው።
ከክርስቲያን በቀር ማንም ሊነካው እንደማይችል የመስቀልን የክብሩን ነገር ሰዎች ነገሩት። ሁለት ዲያቆናትንም ይዞ የከበረ መስቀልን እንዲሸከሙ አዘዛቸው፡፡ ከኢየሩሳሌምም ብዙ ሰዎችን ማርኮ ወደ ሀገሩ ተመለሰ።
የፋርስ ሰዎች ኢየሩሳሌምን እንዳጠፏት ብዙዎች ሰዎችንም እነድ ማረኩና የከበረ የክርስቶስንም መስቀሉን እንደ ወስዱ የሮም ንጉሥ ሕርቃል በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ። ስለርሱም እንዲጾሙ ምእመናንን አዝዞ ወደ ፋርስ ዘምቶ ወጋቸው፤ ብዙዎችንም ገደላቸው፤ የከበረ ዕፀ መስቀልንም እየፈለገ በሀገራቸው ሁሉ ዞረ ግን አላገኘውም።
ያ ዲያቆናቱና መስቀሉን የወሰደ መኰንን ከቦታዎች በቤቱ አንጻር ባለ በአንድ ቦታ ላይ ወስዷቸው ጥልቅ ጉድጓድ እንዲቆፍሩ አዝዞ በዚያ የከበረ መስቀልን አስቀበረ፤ እነዚያንም ዲያቆናት ገደላቸው።
ነገር ግን ያ መኰንን የማረካት የካህናት ወገን የሆነች በእርሱ ቤት የምትኖር አንዲት ብላቴና ነበረች። እርሷም የከበረ መስቀልን ሲያስቀብርና ሁለቱን ዲያቆናት ሲገድላቸው በቤቱ ውስጥ ሁና በመስኮት ትመለከት ነበር፤ ወደ ንጉሥ ሕርቃልም ሂዳ መኰንኑ ያደረገውን ሁሉ ነገረችው።
ይህንንም ንጉሥ ሰምቶ እጅግ ደስ አለው፤ ያቺ ብላቴናም መራችው፤ ከእርሱም ጋራ ብዙ ሠራዊት ሆኖ ኤጲስ ቆጶሳትና ካህናትም ነበሩ። ወደ ቦታውም እስከምታደርሳቸው ያቺን ልጅ ተከተሏት፤ ቅፍረውም የከበረ ዕፀ መስቀልን አገኙት፤ ከዐዘቅቱም አወጡት፤ ንጉሡና ሠራዊቱም ሰገዱለት። በልብሰ መንግሥቱም አጐናጽፈው ታላቅ ክብርንም አከበረው፤ እጅግም ደስ አለው፤ ከሠራዊቱ ጋር። የዚህም መስቀል ሁለተኛ የተገለጠበትና የተገኘበት በዚች ቀን በመጋቢት ዐሥር ነው፡፡ ከዚህ በኃላ ንጉሡ የከበረ ዕፀ መስቀልን ተሸክሞ ወደ ቁስጥንጥንያ ከተማ ወሰደው፡፡
የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመስሉ በረከት ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋር ይኑር፤አሜን፡፡
መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ መጋቢት