“ዝክረ ገብረ እግዚአብሔር” በሚል ርዕስ ጉባኤ ተካሄደ፡፡

ግንቦት 10/2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖአምላክ

m.gerema በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የምክሐ ደናግል ማርያም ወጣቶች መንፈሳዊ ማኅበር (ሰንበት ት/ቤት)  ያዘጋጀውና መ/ር ግርማ ከበደ በዚህች ዓለም ሳለ ያስተማራቸው ልዩ ልዩ ትምህርቶችን አሰባስቦ የያዘው  ሲዲ የተመረቀው ሚያዚያ 27 ቀን 2004 ዓ.ም. ነበር፡፡

 

“ዝክረ ገብረ እግዚአብሔር” በሚል ርእስ በተካሄደው በዚሁ ጉባኤ ላይ መምህር ግርማ ከበደ በዚህ ዓለም ሳለ ያስተማራቸው ትምህርቶችና የሰበካቸው ስብከቶች በአንድነት ተሰባስበው /በMP3 ፎርማት ተዘጋጅተው/ በሲዲ ለምእመናን ተሰራጭተዋል፡፡

 

በደ/አሚን ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የምክሐ ደናግል ማርያም ወጣቶች መንፈሳዊ ማኅበር / ሰንበት ትምህርት ቤት/ ም/ሰብሳቢ ወጣት አበበ ተሻለ ይህን የትምህርት ሲዲ ለማዘጋጀት የታሰበበትን ምክንያት ሲያስረዳ፡- “ጋሽ ግርማ ያስተማራቸውን ትምህርቶችና የሰበካቸውን ስብከቶች ከማሰባሰብ ጀምሮ በየደረጃ የሚሠሩትን ሥራዎች በማጠናቀቅ፣ ሳይገባን፣ በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በጻድቁ አባታችን ተክለ ሃይማኖት ጸሎት ለሃይማኖት ቤተሰቦቹ ስናቀርብ ታላቅ መንፈሳዊ ደስታ ይሰማናል፡፡ይህንን ሲዲ ለማዘጋጀት  ምክንያት የሆነን፡- ምእመናን  በልዩ በልዩ ጊዜያት  በሰ/ት/ቤታችን የሚገኙ የጋሽ ግርማ ትምህርቶችን በማባዛት እንድናሰራጭ ስለጠየቁን፤ በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ረሃበ ነፍስ የተባለው የቀና ሃይማኖትና በጎ ምግባር ማጣት እየተስፋፋ በመምጣቱ የጋሸ ግርማ ስብከቶች እነዚህን ትልልቅ ችግሮች ይቀርፋሉ ብለን በማመናችን ነው፡፡ በሌላ በኩል፡- ጋሽ ግርማ አብዛኛው ሰው በልቡ የሚነሣበትን ጥያቄ በትምህርቱ ከመመለሱ በላይ ፈተናም ያርቅ ነበርና….. እኛ የሰማነውን ሌሎችም ቢሰሙ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ በማመን ልናዘጋጀው ችለናል፤” ብሏል፡፡

 

yo 3ወጣት አበበ በዚሁ ሪፖርቱ ማጠናቀቂያ ላይ ሰንበት ትምህርት ቤቱ በቀጣይ ስለሚፈጽመው አገልግሎት ሲያስተዋወቅ “ከጋሽ ግርማ የተማርንም ሆንን በስም የምናውቀው ድምፁን መስማታችን በራሱ ያስደስተናል በሚል እምነት ለጊዜው ሦስት ሲዲዎችን አዘጋጅተናል፡፡ በቀጣይ ዝግጅታችን “በምሥጢረ ሥላሴ፣ በምሥጢረ ሥጋዌ፣ በምሥጢረ ጥምቀትና በምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን እንዲሁም በሌሎች ተጓዳኝ ርእሶች ያስተማራቸውን ትምህርቶችና የሰበካቸውን ስብከቶች እንድናቀርብ ጸሎታችሁ አይለየን” በማለት ምእመናንን አሳስቧል፡፡

 

በምክሐ ደናግል ማርያም ሰንበት ትምህርት ቤት አባልና የ˝ዝክረ ገብረ እግዚአብሔር” ጉባኤ አስተባባሪ የሆኑት መ/ር ዮሐንስ አየለን “የጋሽ ግርማን ትምህርቶች በመጽሐፍ መልክ ለማዘጋጀት ምን የታሰበ ነገር አለ?” በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፡- “…የጋሽ ግርማን ሕይወት አስመልክቶ ዘጋቢ ፊልም ለመሥራት ቃለ መጠይቅ ያደረግንላቸው ወገኖች ጋሽ ግርማ በመቅረጸ ድምጽ ወምስል ያልተያዙ በርካታ ትምህርቶቹ በማስታወሻ ደብተሮቻቸው እንደሚገኝ ገልጸውልን፣ በመጽሐፍ መልክ አዘጋጅታችሁ ብታወጧቸው በማለት ትውልዱ ይማርባቸው ይመከርባቸው ዘንድ ትምህርቱን የዘገቡባቸውን ማስታወሻ ደብተሮቻቸውን ሰጥተውናል፡፡ ይህንኑ ዐሳብ ኮሚቴው ተቀብሎ የሰንበት ትምህርት ቤታችን ጽሕፈት ቤት በፕሮግራሙ ውስጥ አካቶ ይዞታል፡፡ ለዚህም እንዲረዳ በአሁኑ ወቅት በሲዲ የቀረቡት ሰላሳ ስድስቱም   ትምህርቶች ቃል በቃል ወደ ጽሑፍ ተቀይረዋል፡፡ በቀጣይም  አስፈላጊው ማስተካከያ ተደርጎለት ለመጽሐፍ በሚሆን መልኩ የማዘጋጀት ተግባር ይከናወናል፡፡” ብለውናል፡፡

 

በሌላ በኩል በጋሽ ግርማ ትምህርቶች አማካኝነት ስለሆኑ ድንቅ ነገራት የጠየቅናቸው መ/ር ዮሐንስ፡- “በመቀሌ ቢዝነስ ኮሌጅ ተማሪ የነበረ አንድ ወንድማችን የመምህር ግርማ ከበደን ትምህርት የያዘ አጀንዳ አግኝቶ ወደ ራሱ ማስታወሻ መገልበጥ ይጀምራል፡፡ ሆኖም ይህን ሥራ እያከናወነ ሳለ አንድ ሌሊት ላይ ተኝቶ ሕልም አየ ይኸውም በመሐል ክንዱ ርግብ አርፋ ስትጠረጥረው /በአፏ ስትቧጭረው/ ያያል፡፡ ከሁለት ቀን በኋላ ያ ቦታ ያብጥበታል፡፡ መጻፍም አልቻለም፡፡ በኋላ መቀሌ በዓታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የነበሩ መልአከ ስብሐት አባ አብርሃም ዘንድ ሄደን ልጁ ስላየው ነገርና ስለገጠመው ሁኔታ ስንነግራቸው “መምህሩ (ጋሽ ግርማን ነው) የተጠቀመ ነው፡፡ በትሩፋት በገድል ነው የሚያስተምረው” አሉን፡፡ ከዚህ በኋላ ልጁ ትምህርቱን አቋርጦ ወደ አዲስ አበባ መጣ፡፡ በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ምርመራ ያደረጉለት የጤና ባለሙያዎችም፤ እጁ መቆረጥ እንዳለበት ያለዚያ ለደኅንነቱ አስቸጋሪ እንደሚሆንበት ነገሩት፡፡ በሰማው ነገር እጅግ ተደናግጦና አዝኖ መጥቶ አጫወተን፡፡ መምህራንን ስናማክር ለጻድቁ ተክለሃይማኖት እንዲለምን እንዲሳል ተነገረው፡፡ ልጁም  በደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን መቅደስ መግቢያ ላይ የሚገኘውን የቅዱስ ተክለሃይማኖት ስዕል ሥር ቀርቦ ተማጸነ፡፡ ጸሎቱን አድርሶ የመሬቱን ትቢያ አንስቶ ከታመመበት እጁ ላይ ቀባባው፡፡ ይህ ከሆነ ሦስት ቀን ሳይሞላው እብጠቱ ሙሉ ለሙሉ ጎደለለት፡፡ ይህንኑ ነገር ለመልአከ ስብሐት አብርሃ /የመቀሌ እንዳ ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ/ ነገርናቸው፡፡ እርሳቸውም “ይህ መምህር በገድል በትሩፋት የሚያስተምር ነው፡፡ ስለሆነም የበጎ ነገር ሁሉ ተጻራሪ የሆነ ጠላት ዲያብሎስ ትምህርቱ እንዳይወጣ ሰው እንዳይጠቀም ሲፈታተን ነው፤” አሉን፡፡

 

በሌላ ጊዜም “በይሖዋ ምስክር እምነት ውስጥ የነበረች አንዲት አህት የቤተክርስቲያንን ትምህርት መማር ትፈልጋለችና መጥታችሁ አነጋግሩልን” በሚል ከቤተሰቦቿ ለሰንበት ትምህርት ቤታችን ልጆች መልእክት ይመጣል፡፡ በዚህ ጊዜ ሁለት አባላት ወደ ልጅቱ ቤት ይሄዳሉ፡፡ ነገር ግን ከአንድም ሁለት ጊዜ ወንድሞች ሲሄዱ ለመማር ፈቃደኛ አልነበረችም፡፡ በሌላ ጊዜ ከቤተ ክርስቲያን የማትለይ እህቷ የትምህርት ካሴት ይዛ ወደ ቤቷ ትሄዳለች፡፡ ያንኑ ትምህርትም ከፍታ ልጅቱ ትተኛለች፡፡ በቤታቸው የሚገኘውም የካሴት ማጫወቻ ቴፕ ሰው ካላጠፋው በቀር በራሱ አያቆምም፡፡ በካሴቱ የተቀረጸው ትምህርት ጋሽ ግርማ በዚህ ዓለም ሳለ፡- ˝በእኔ የማይሰናከል ብጹእ ነው” ሲል ጌታችን የተናገረውን ቃል ያስተማረበት ነው፡፡ ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ በይሖዋ ምስክር ቤተ እምነት ውስጥ የነበረችው ልጅ ከእንቅልፏ ነቅታ ታናሽ እኅቷ የከፈተችውን የካሴት ትምህርት መስማት ጀመረች፡፡ ትምህርቱ “ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ መሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡ እናም ትምህርቱ በክኅደት በኑፋቄ የሸፈተ ልቡናዋን ወደ ሃይማኖት መልሰው፡፡ በጧት ተነስታ እናቷንና እኅቷን፡- ˝እነዚያን የቤተ ክርስቲያን ልጆች ማግኘት እፈልጋለሁ ጥሩልኝ” ትላለች፡፡ ልጆቹ ግን ለመከራከር ፈልጋ ነው እንጂ፤ ትምህርቱን በመሻት አይደለም በሚል ለመሄድ አመናቱ፡፡ ነገር ግን በሌላ ጉዳይ ነው የምትፈለጉት ተብለው ሲሄዱ ልጅቱ፡- ˝ይህንን ትምህርት ያስተማረው መምህር ማግኘት መተዋወቅ ከእርሱም መማር እፈልጋለሁ” ትላቸዋለች፡፡ ያን ጊዜ ግን ጋሽ ግርማ በሕይወት አልነበረም፡፡ ከዚህ በኋላ ˝ለካ እኔም በአምላኬ ቃል ተሰናክዬ ፈጣሪዬን ክጄ ኖሬያለሁ” በማለት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በንስሐ ለመመለስ በቅታለች፡፡” እነኚህ ብቻ አይደሉም፡፡ እርሱ ያስተማረውን ትምህርት ሰምተው ንስሐ የገቡ፤ ሥጋ ወደሙ የተቀበሉ፤ ከክህደት ከነፋቄ ወደ ሃይማኖት የተመለሱ በርካቶች ናቸው” በማለት ነግረውናል፡፡

 

የትምህርቱን ሲዲ አዘጋጅቶ ለምእመናን ለማድረስ አንድ ዓመት ከስድስት ወር መውሰዱን የገለጹት መ/ር ዮሐንስ አየለ “በዝክረ ገብረ እግዚአብሔር መርሐ ግብር ላይ የተገኙ አንድ ምእመን የጋሽ ግርማን ኦሪጅናል የትምህርት ካሴቶች እንደሚሰጡን ቃል የገቡልን በመሆኑ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ቀጣዩ ሥራ ከአሁኑ የተሻለ ጥራት ይኖረዋል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

 

“ያመዋል፤ ነገር ግን ደዌ ባልተለየው ጊዜ እንኳ ሲያስተምር /ሲያገለግል/ ፈገግታ አይለየውም፡፡ ገድለ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ሲያነብ ሲያስተምር በእንባ ጭምር ነው፡፡….”  በሚል ስለ ጋሽyo 1 ግርማ ምስክርነታቸውን ለጉባኤው የሰጡት መምህር (ጋሽ) ታዬ አብርሃም ˝ግርማ ምንም ያክል ቢሠራ ‘ይህን ሠራሁ፥ ይህን አደረግሁ’ በማለት አይናገርም፡፡ ውዳሴ ከንቱን አጥብቆ ይጠላል፡፡” በማለት ተናግረዋል፡፡

 

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙ አንዳንድ ምእመናን በሰጡት አስተያየት “ ስለጋሽ ግርማ መታሰቢያ ስንነጋገር፤ እርሱ በፈቃደ እግዚአብሔር ማስተማር የጀመረበት ጉባኤ እንዳይፈታ የየራሳችንን አስተዋጽኦ እናበርክት፡፡”

 

ሌላው አስተያየት ሰጪ ምእመን እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፡- “በሕይወቴ ለውጥ እንዳይ የረዳኝ ጋሽ ግርማ ነው፡፡ ጋሽ ግርማ አሁን ላለው ስብእናዬ ከፈጣሪ በታች መሠረት የሆነኝ እርሱ ነው፡፡ የጋሽ ግርማ ስብከቱ ልዩ ነው፡፡ ስለሰው የሚገደው ሰው ነው፡፡ በእንባ ጭምር የሚያስተምር መምህር ነው፡፡…”

 

በመርሐ ግብሩ ማጠናቀቂያ ላይ የደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ አሚን ሊቀ ጉባኤ ኤርሚያስ ወልደየሱስ  የትምህርት ሲዲውን መርቀው ለምእመናን በይፋ መታደሉን አብስረዋል፡፡

 

በክፍል አንድ ክፍል ሁለትና ክፍል ሦስት ሲዲዎች በአጠቃላይ ሰላሳ ስድስት ትምህርቶች የሚገኙ ሲሆን፤ በክፍል አንድና ሦስት የሃይማኖት ትምህርቶች እንዲሁም በክፍል ሁለት ላይ በልዩ ልዩ ርእሶች መምህር ግርማ የሰበካቸው ስብከቶች ተካተውበታል፡፡