ዝክረ አቡነ ጎርጎርዮስ ሊካሄድ ነው
ሰኔ 09 ቀን 2004 ዓ.ም
በእንዳለ ደምስስ
የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል የማኅበሩን 20ኛ ዓመት ምሥረታ በዓል ምክንያት በማድረግ “ዝክረ አቡነ ጎርጎርዮስ” በሚል ርእስ የጥናትና የውይይት መድረክ ሰኔ 16 ቀን 2004 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም አዲሱ አዳራሽ አዘጋጅቷል፡፡
የጥናትና ምርምር ማእከሉ ም/ዳይሬክተር አቶ ሰይፉ አበበ መርሐ ግብሩን አስመልክቶ እንደገለጹት “የጥናት መድረኩ ዋና ዓላማ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በሕይወት ዘመናቸው ለቤተ ክርስቲያን ያበረከቱትን አገልግሎት፣ የሕይወት ልምዳቸውን፣ ወጣቱን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በአንድ ዓላማ ለማሰለፍ ያደረጉትን ተጋድሎ እንዲሁም ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገት የነበራቸውን ርዕይ የሚዘክር ይሆናል” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ለማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት ጉልህ አስተዋጽኦ የነበራቸው አባት በመሆናቸው ማኅበሩ 20ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን በሚያከብርበት ወቅት ብፁዕነታቸውን መዘከር ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ላይ ለሚገኙ አገልጋዮችና ደቀ መዛሙርቶቻቸው በተለይም ወጣቶችን የሚያተጋ በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት ገልጸዋል፡፡
በጥናት መድረኩ ላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ፣ በዘርፉ የተሰማሩ ተመራማሪዎች፣ ደቀ መዛሙርቶቻቸው ፣ የማኅበረ ቅዱሳን አባላትና ምእመናን ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡