ዘመነ ዕርገት

ሰኔ ፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ዕርገት በግእዝ ቋንቋ ማረግ፣ ከታች ወደ ላይ መውጣት ማለት ሲኾን የጌታችን ትንሣኤ በተከበረ በዐርባኛው ቀን የሚውለው ዐቢይ በዓልም ዕርገት ይባላል /ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ገጽ ፯፻፷/፡፡

እንደምናስታውሰው ባለፈው ሐሙስ (ሰኔ ፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም) ከጌታችን ከመድኀኒታችን ኢየሱስ ዐበይት በዓላት መካከል አንዱ የኾነው በዓለ ዕርገት በቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት ተከብሯል፡፡ ከጌታችን የዕርገት በዓል ጀምሮ (ከዐርባኛው ቀን) እስከ ጰራቅሊጦስ ዋዜማ (ዐርባ ዘጠነኛው ቀን) ድረስ ያለው ወቅት ዘመነ ዕርገት ይባላል፡፡

በዓለ ዕርገት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለዐርባ ቀናት በግልጽም በስውርም ለቅዱሳን ሐዋርያትና ለቅዱሳት አንስት መጽሐፈ ኪዳንን፣ ትርጓሜ መጻሕፍትን፣ ምሥጢራትን፣ ሕግጋትንና ቀኖናተ ቤተ ክርስቲያንን ሲያስተምር ቆይቶ ወደ ቀደመ ዙፋኑ ወደ ሰማይ ማረጉን የምንዘክርበት ታላቅ የደስታ ቀን ነው፡፡

መጽሐፈ ስንክሳር በዓለ ዕርገት የክብር ባለቤት ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ በነሣው ሥጋ ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ወዳለው የአንድነት አኗኗሩ ወደ ሰማይ ያረገበት ዕለት መኾኑን ጠቅሶ፣ በዚህች ቀን ያን ጊዜ በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ ወጣ፤ በነፋሳትም ክንፎች ላይ ኹኖ ወጣ /መዝ.፲፯፥፲/ የሚለው የዳዊት ትንቢት መፈጸሙን ያትታል፡፡

በተጨማሪም ሌሊት በራእይ አየሁ፤ እነሆም እንደ ሰው ልጅ የሚመስል በሰማይ ደመና መጣ፤ በዘመናትም ወደ ሸመገለው ደረሰ፡፡ ወደ ፊቱም አቀረቡት፡፡ ወገኖችና አሕዛብ፣ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ኹሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር፣ መንግሥትም ተሰጠው፡፡ ግዛቱም የማያልፍ የዘለዓለም ግዛት፤ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው፤ /ዳን.፯፥፲፫-፲፬/ የሚለው የነቢዩ ዳንኤል ትንቢት በጌታችን ዕርገት መፈጸሙን ይናገራል /ስንክሳር፣ ግንቦት ፰ ቀን/፡፡

ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ዐርባ ስድስተኛውን መዝሙረ ዳዊት በተረጐመበት አንቀጹ ድል መንሳት ባለበት የነጋሪት ድምፅ እግዚአብሔር ዐረገ አለ እንጂ መላእክት አሳረጉት አላለም፡፡ በፊቱ መንገድ የሚመራው አልፈለገም፡፡ በዚያው ጎዳና እርሱ ዐረገ እንጂ፤ በማለት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላካዊ ሥልጣኑ ወደ ሰማይ ማረጉን ተናግሯል፡፡

በተመሳሳይ ምሥጢርም የጌታችንን ዕርገት ከነቢዩ ኤልያስ ዕርገት ጋር በማነጻጸር ነቢዩ ኤልያስ በመላእክት ርዳታ ወደ ሰማይ መወሰዱን /፪ኛነገ.፪፥፩-፲፫/፤ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የመላእክት ፈጣሪ ነውና በእነርሱ ርዳታ ሳይኾን በገዛ ሥልጣኑ ማረጉን ያስረዳል /ሐዋ.፩፥፱-፲፪/፡፡

ሊቁ በተጨማሪም ሕማም የሚስማማው ግዙፍ ሥጋን ተዋሕዶ ሳለ ከስቅለቱ አስቀድሞ በባሕር ላይ ከሔደ፣ ዛሬ ነፋስን ከፍሎ ሲያርግ ቢታይ ማንም ማን አይጠራጠር፡፡ ሥጋው አልተለወጠምና፤ በማለት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞቱና ከትንሣኤው አስቀድሞ በውኀ ላይ እንደተራመደ ኹሉ፣ በለበሰው ሥጋ ወደ ሰማይ ማረግም እንደሚቻለው አስረድቷል /ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ፣ ከፍል ፲፫፣ ምዕ.፷፯፥፲፪-፲፭/፡፡

በበዓለ ዕርገት ሊቃውንቱ ሌሊት በማኅሌት፣ በዝማሬ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ያድራሉ፡፡ ሥርዓተ ማኅሌቱ እንዳበቃ የሚሰበከው የነግህ ምስባክም፡- ዘምሩ ለእግዚአብሔር ዘዐርገ ውስተ ሰማይ ሰማይ ዘመንገለ ጽባሕ ናሁ ይሁብ ቃሎ ቃለ ኃይል /መዝ.፷፯፥፴፫/ የሚለው የዳዊት መዝሙር ሲኾን ቀጥተኛ ትርጕሙም በምሥራቅ በኩል ወደ ሰማየ ሰማያት ለወጣ (ላረገ) ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ የኀይል የኾነውን ቃሉን እነሆ ይሰጣል የሚል ኾኖ ምሥጢሩም ነፍሳትን ይዞ ከሲኦል ወደ ገነት ለወጣ፤ አንድም በደብረ ዘይት በኩል ላረገ ለእግዚአብሔር ምስጋና አቅርቡ ማለት ነው፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ጌታችን ባረገ በዐሥረኛው ቀን የኀይል ቃል የተባለ መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት መላኩን፤ እንደዚሁም ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሔድ እንዳያችሁት፣ እንዲሁ ይመጣል፤ ተብሎ እንደ ተጻፈ /ሐዋ.፩፥፲፩/፣ ጌታችን ዳግም እንደሚመጣ፤ እኛም ይህንን የጌታችንን የማዳን ሥራ እያደነቅን ለእርሱ ምስጋና፣ ዝማሬ ማቅረብ እንደሚገባን ያስረዳል፡፡

የነግህ ወንጌል (ከቅዳሴ በፊት የሚነበበው) ደግሞ የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፬ ቍጥር ፵፭ እስከ መጨረሻው ድረስ ያለው ኃይለ ቃል ሲኾን፣ ኃይለ ቃሉም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት እንደሚወርድ፣ የሰውን ልጅ ለማዳን ሲል መከራ እንደሚቀበል፣ እንደሚሞት፣ ከሙታን ተለይቶ እንደሚነሣ፣ ወደ ሰማይ እንደሚያርግና ዳግም እንደሚመጣ በነቢያት የተነገረው ትንቢት መፈጸሙንና ለዚህም ቅዱሳን ሐዋርያት ምስክሮች መኾናቸውን ማለትም በመላው ዓለም እየዞሩ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ እንደሚሰብኩና በሰማዕትነት እንደሚያልፉ፤ እንደዚሁም ሰማያዊ ሀብትንና ዕውቀትን እስኪያገኙ ድረስ በኢየሩሳሌም እንዲቆዩ መታዘዛቸውን ያስረዳል /ትርጓሜ ወንጌል/፡፡

ይህ ምሥጢር ለጊዜው ሐዋርያትን የሚመለከት ይኹን እንጂ ፍጻሜው ግን ኹላችንም ቅዱሳት መጻሕፍት የተናገሩትን ቃል አብነት አድርገን የእግዚአብሔርን ሰው መኾንና የማዳኑን ሥራ አምነን፣ ሌሎችንም በማሳመን በሃይማኖታችን ጸንተን መኖር እንደሚገባን፤ እግዚአብሔር አምላካችን ኃይሉን፣ ጸጋውን፣ ረድኤቱን እንዲያሳድርብንም ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን መለየት እንደሌለብን የሚያስገነዝብ መልእክት አለው፡፡

በዕለተ ዕርገት በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም ከቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ዕብራውያን ፩፥፩ እስከ ፍጻሜው ድረስ፤ ከሌሎች መልእክታት ደግሞ ፩ኛ ጴጥሮስ ፫፥፲፰-ፍጻሜየሐዋርያት ሥራ ፩፥፩-፲፪ ሲኾኑ፣ ምስባኩም ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ የሚለው ኾኖ /መዝ.፵፮፥፭-፮/፣ መልእክቱም በዕልልታና በመለከት ድምፅ ላረገ ለአምላካችን፣ ለጌታችንና ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና አቅርቡ ማለት ነው፡፡

ወንጌሉ ደግሞ፣ ማርቆስ ፲፮፥፲፬ እስከ ፍጻሜ ድረስ ሲኾን ቃሉም በነግህ ከተነበበው የወንጌል ክፍል ቃል ተመሳሳይነት አለው፡፡ ቅዳሴውም ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ ሲኾን ይኸውም ከሦስቱ አካላት አንዱ የኾነውን የእግዚአብሔር ወልድን (የኢየሱስ ክርስቶስን) ዘለዓለማዊነት የሚያስረዳ፤ ሥጋዌዉን፣ ሕማሙን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤዉን፣ ዕርገቱንና ዳግም ምጽአቱንም የሚናገር በመኾኑ በዘመነ ትንሣኤ፣ በዘመነ ዕርገትና በበዓለ ሃምሳ ይቀደሳል፡፡

ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በቅዳሴዉ መጀመሪያ ላይ ሀልዎተ እግዚአብሔርንና ምሥጢረ ሥላሴን መሠረት በማድረግ ለእግዚአብሔር ምስጋና ካቀረበ በኋላ፣ ቍጥር ፴፩ ላይ ደግሞ ወበ፵ ዕለት አመ የዐርግ ሰማየ አዘዞሙ እንዘ ይብል ጽንሑ ተስፋሁ ለአብ፤ ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በዐርባኛው ቀን በብርሃን፣ በሥልጣን፣ በይባቤ ወደ ሰማይ በሚያርግበት ጊዜ አብ የሚሰድላችሁ መንፈስ ቅዱስን እስክትቀበሉ ድረስ ከዚህ ቆዩ ብሎ አዘዛቸው፤ በማለት መጽሐፍ ቅዱሳዊ በኾነ ቋንቋ የጌታችንን ወደ ሰማይ ማረግና ለሐዋርያት የሰጠውን አምላካዊ ትእዛዝ ይናገራል /ሉቃ.፳፬፥፵፱/፡፡

በዘመነ ዕርገት ውስጥ በሚገኘው እሑድ (ሰንበት) ሌሊት ሊቃውንቱ የሚያደርሱት መዝሙርም በሰንበት ዐርገ ሐመረ የሚል ሲኾን ይኸውም ጌታችን በሰንበት ወደ ታንኳ በመውጣት ባሕርንና ነፋሳትን እንደ ገሠፀ፤ ሐዋርያቱንም ጥርጥር ወደ ልቡናችሁ አይግባ፤ አትጠራጠሩ እንዳላቸው፤ እንደዚሁም ወንጌልን ይሰብኩ፣ ያስተምሩ ዘንድ በመላው ዓለም እንደሚልካቸው፤ በሰማያዊ መንግሥቱ ይኖሩ ዘንድም ዳግመኛ መጥቶ እንደሚወስዳቸው የሚያስገነዝብ መልእክት አለው /ሉቃ.፰፥፳፪-፳፬፤ ዮሐ.፲፬፥፪፤ ፳፥፳፩/፡፡

በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ ምንባባትም በዕለተ ዕርገት (ሐሙስ) ከተነበቡት ጋር ተቀራራቢነት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ናቸው፡፡ ለማስታወስ ያህልም ከጳውሎስ መልእክት ሮሜ ፲፥፩ እስከ ፍጻሜው፤ ከሌሎች መልእክታት ፩ኛ ጴጥሮስ ፫፥፲፭ እስከ ፍጻሜው ድረስ ይነበባሉ፡፡ የሐዋርያት ሥራ፣ ምስባኩና ቅዳሴው ከሐሙስ ዕለቱ (ከዕርገት) ጋር አንድ ዓይነት ሲኾን ወንጌሉም ሐሙስ ጠዋት (በነግህ) የተነበበው ሉቃ.፳፥፵፭ እስከ ፍጻሜው ድረስ ያለው ኃይለ ቃል ነው፡፡

በዘመነ ዕርገት ከቅዳሴ በኋላ ከሚቀርቡ ዝማሬያት መካከል ዐርገ ሰማያተ በዐምደ ደመና የሚለው አንደኛው ሲኾን፣ ይህ ዝማሬ ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷ ነፍስ የነሣ (የተዋሐደ)፤ ለእስራኤላውያን በሲና በረኀ መና ያወረደ፤ ሶስናን ከረበናት እጅ ያዳነ፤ ሰንበትን ለሰው ልጆች ዕረፍት የሠራ፤ የክርስትና ሃይማኖትን ያቀና (የመሠረተ)፤ ከሰማይ የወረደው የሕይወት እንጀራ፤ በባሕርዩ ምስጋና የሚገባው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደመና ተጭኖ ወደ ሰማይ ማረጉን የሚያስረዳ ሰፊ ምሥጢር አለው፡፡

በአጠቃላይ በዘመነ ዕርገት በማኅሌት፣ በቅዳሴ፣ በመሥዋዕት ጊዜ በቤተ ክርስቲያን የሚሰጡ ትምህርታት፣ የሚቀርቡ መዝሙራትና የሚነበቡ መጻሕፍት የእግዚአብሔርን ሰው መኾን፣ ተአምራቱን፣ ሕማሙን፣ ሞቱን፣ ነፍሳትን ከሲኦል ማውጣቱን፣ ትንሣኤውን፣ ለሐዋርያትና ለቅዱሳት አንስት መግለጡን፣ በተለይ ደግሞ ዕርገቱን፣ ዳግም ምጽአቱንና ምእመናን በእርሱ አምነው የሚያገኙትን ድኅነት፣ ጸጋና በረከት፣ እንደዚሁም ስለ መንግሥተ ሰማያት የሚያስረዳ ይዘት አላቸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ምርኮን (የነፍሳትን ወደ ገነት መማረክ) የሚያትቱ ትምህርቶች የሚሰጡትም በዚህ በዘመነ ዕርገት ወቅት ሲኾን፣ ይኸውም በሰይጣን ባርነት ተይዘው የኖሩ ነፍሳት ነጻ የወጡት በኢየሱስ ክርስቶስ አምላካዊ ሥልጣን በመኾኑ ነው፡፡ ምርኮን ማረከህ፤ ወደ ሰማይም ወጣህ፡፡ ስጦታህንም ለሰዎች ሰጠህ፡፡ ያድሩ ዘንድ ይክዱ ነበርና እንዳለ ቅዱስ ዳዊት /መዝ.፷፯፥፲፰/፡፡ ይህም ጌታችን ነፍሳትን ይዞ ከሲኦል ወደ ገነት መውጣቱንና ለምእመናን የሥላሴ ልጅነትን እንደሰጠ የሚያስረዳ ሲኾን፣ ያድሩ ዘንድ ይክዱ ነበር ሲልም በክህደት ይኖሩ የነበሩ ኹሉ ጌታችን በሰጠው ልጅነት ተጠርተው፣ አምነውና በሃይማኖት ጸንተው መኖራቸውን ሲያመለክት ነው፡፡

ከላይ እንደ ተመለከትነው ዘመነ ዕርገት ወደ ላይ የመውጣት፣ የማረግ፣ ከፍ ከፍ የማለትና የማደግ ወቅት ነው፡፡ እኛም በሞት ከመወሰዳችን በፊት ለመንግሥቱ የሚያበቃ ሥራ ያስፈልገናልና ሕሊናችን በጽድቅ ሥራ እንዲያርግ (ከፍ ከፍ እንዲል) ዘወትር በጾም፣ በጸሎት መትጋት ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም ዕርገት ሲባል በአካል ማረግን ወይም ወደ ሰማይ መውጣትን ብቻ ሳይኾን፣ በአስተሳሰብና በምግባር መለወጥን፣ በአእምሮ መጎልመስንም ያመለክታልና፡፡

በሞቱ ሕይወታችንን ለመለሰልን፤ በትንሣኤው ትንሣኤያችንን፣ በዕርገቱ ክብራችንን ለገለጠልን ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ለዘለዓለሙ ክብር ምስጋና ይደረሰው፡፡ ዜና ብሥራቱን፣ ፅንሰቱን፣ ልደቱን፣ ዕድገቱን፣ ስደቱን፣ ተአምራቱን፣ ሕማሙን፣ ሞቱንና ትንሣኤውን በሰማንበት ዕዝነ ልቡናችን፣ ባየንበት ዓይነ ሕሊናችን ዕርገቱንም እንድንሰማና እንድናይ ዕድሜ ለንስሐ ሰጥቶ እስከ ዛሬ ድረስ እንደ ጠበቀን ኹሉ፣ ዳግም ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜም እናንተ ቡሩካን ወደ እኔ ኑ የሚለውን የሕይወት ቃል እንዲያሰማን ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡-

መጽሐፍ ቅዱስ፣ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፤ አዲስ አበባ፣ ፳፻ ዓ.ም፡፡

መዝሙረ ዳዊት ንባቡና ትርጓሜው፣ ተስፋ ገብረ ሥላሴ፤ አዲስ አበባ፣ ፲፱፻፹፪ ዓ.ም፡፡

ማኅቶተ ዘመን፣ መ/ር በሙሉ አስፋው፣ ገጽ ፻፺፩-፻፺፬፤ አዲስ አበባ፣ ፳፻፩ ዓ.ም፡፡

ዝማሬ ወመዋሥዕት፣ ትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት፤ አዲስ አበባ፣ ፲፱፻፹፱ ዓ.ም፡፡