ዘመነ ክረምት ክፍል አራት
ጳጕሜን ፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! በክፍል ሦስት ዝግጅታችን ከነሐሴ ፲ እስከ ፳፰ ቀን (ከማኅበር እስከ አብርሃም) ድረስ ያለው የዘመነ ክረምት ክፍለ ጊዜ ‹‹ዕጕለ ቋዓት፣ ደሰያት፣ ዓይነ ኲሉ›› እንደሚባል፤ ይኸውም የሰውን ልጅ ጨምሮ የሰማይ አዕዋፍ፣ የምድር አራዊትና እንስሳት ሳይቀሩ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርገው በደስታ መኖራቸው፤ በተጨማሪም በዝናም አማካይነት በዙሪያቸው ያለው የውሃ መጠን ከፍ ሲልላቸው ደሴቶች ኹሉ በልምላሜ ማሸብረቃቸው የሚነገርበት ክፍለ ክረምት እንደ ኾነ በማስታዎስ ከሕይወታችን ጋር የሚጣጣም ትምህርት አቅርበን ነበር፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን ደግሞ ቀጣዩን ክፍል ይዘን ቀርበናል፡፡
ከዚያ በፊት ግን ባለፈው ከጠቀስናቸው ትምህርቶች መካከል ‹‹ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ …›› /ሉቃ.፲፪፥፳፪-፴፩/ የሚለው ኃይለ ቃል እንደ እንስሳት ሳትሠሩ እግዚአብሔር ምግብ እንዲሰጣችሁ ለምኑት ማለት ነውን? የሚል ጥያቄ ሊያስነሣ ስለሚችል በመጠኑ ክለሳ አድርገንበት እንለፍ፤ ኃይለ ቃሉን ለማብራራት ያህል የሰው ልጆች ከእንስሳት ከምንለይባቸው ባሕርያት አንደኛው ሠርተን መብላት መቻላችን ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም የታታሪነትንና የሠርቶ ማደርን ጥቅም እንጂ ሳይሠሩ ተቀምጦ መብላትን አላስተማሩንም፡፡ በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የሰው ልጅ እጁ ከሥራ መለየት እንደማይገባው ተጠቅሷል፡፡ ለምሳሌም ጥቂቶቹን እንመልከት፤
በኦሪት ዘፍጥረት እንደ ተጻፈው አባታችን አዳም ከሳተ በኋላ በምድር ጥሮ፣ ግሮ እንዲኖር ተፈርዶበታል፡፡ ይህንንም ‹‹… የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ፡፡ ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ›› ከሚለው ኃይለ ቃል ለመረዳት እንችላለን /ዘፍ.፫፥፲፰-፲፱/፡፡ በተመሳሳይ መልኩ እግዚአብሔር አማላክ አዳምን ከዔደን ገነት ያስወጣው የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድ ነው /ዘፍ.፫፥፳፫/፡፡ ይህም የሰው ልጅ ሠራቶ አዳሪ ፍጥረት መኾኑን የሚያመላክት ነው፡፡
ጠቢቡ ሰሎሞንም ‹‹አንተ ታካች! እስከ መቼ ትተኛለህ? ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሣለህ? ጥቂት ትተኛለህ፤ ጥቂት ታንቀላፋለህ፡፡ ትተኛም ዘንድ ጥቂት እጅህን ታጥፋለህ፡፡ እንግዲህ ድህነትህ እንደ ወንበዴ፣ ችጋርህም ሰይፍ እንደ ታጠቀ ሰው ይመጣብሃል›› በማለት ሰው ሰነፍ ከኾነ (ካልሠራ) ክፉ ድህነት እንደሚመጣበት ተናግሯል /ምሳ.፮፥፱-፲/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ ‹‹ከእናንተ ሊሠራ የማይወድ አይብላ›› በማለት ሥራ የማይወድ ሰው ምግብ መሻት እንደሌለበት አስረድቷል /፪ኛተሰ.፫፥፲/፡፡
ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ስንፍናን የሚያወግዝ፣ ሥራን የሚያበረታታ ኾኖ ሳለ ለምንድን ነው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፡፡ …›› ሲል ያስተማረው ለሚለው የሰው ልጅ ሠራተኛ ፍጥረት ቢኾንም ዝናም አልጥልለት ሲል፤ የዘራበት መሬት ሳያበቅል ሲቀር፤ የወር ደመወዙ ሲዘገይ፤ እኽል የሚሸምትበት ገንዘብ ሲያጣ፤ ወዘተ. በመሳሰሉት ፈተናዎች ውስጥ በኾነ ጊዜ ምን ልበላ፣ ልጠጣ ነው? ልጆቼ እንዴት ሊኾኑብኝ ነው? ዛሬን እንዴት ላልፍ ነው? በሚሉትና በመሳሰሉት የጭንቀትና የተስፋ መቍረጥ ስሜቶች ሳይያዝ የዕለት ጕርሱን፣ የዓመት ልብሱን ይሰጠው ዘንድ የጠፋውን ዝናም ማምጣት፤ የደረቀውን ዘር ማለምለም፤ ባዶ የኾነውን ቤት መሙላት የሚቻለውን እግዚአብሔርን በእምነት ኾኖ በጸሎት ይጠይቀው ለማለት ነው፡፡
ሲጠቃለል የሰው ልጅ ይርበኛል፣ ይጠማኛል ማለቱን ትቶ በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠሩን በማሰብ ዓቅሙ በሚችለው ኹሉ እንዲሠራ፤ የጐደለውን እንዲሞላለት ደግሞ ጸሎቱን ወደ ፈጣሪው እንዲያቀርብ ሲያስረዳ ጌታችን ‹‹ለነፍሳችሁ በምትበሉት፣ ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፡፡ …›› ብሏል፡፡ ስላለፈው ትምህርት ይህንን ያህል ከገለጽን ወደ ዛሬው ዝግጅታችን እናልፋለን፤
በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ከነሐሴ ፳፰ እስከ መስከረም ፩ ቀን (ከአብርሃም እስከ ዮሐንስ) ድረስ ያለው ክፍለ ክረምት ‹‹ጎህ፣ ነግህ፣ ጽባሕ፣ ብርሃን መዓልት›› ይባላል፡፡ በዚህ ክፍለ ክረምት ውስጥ ባሉት ቀናት በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እነዚህን ፍጥረታት የሚመለከቱ የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች ይነገራሉ፤ ይተረጐማሉ፤ ይመሠጠራሉ፡፡
‹‹ጎሕ፣ ነግሕና ጽባሕ›› ንጋት፣ ማለዳ፣ ሌሊቱ ወደ ቀን፤ ጨለማው ወደ ብርሃን የሚሸጋገርበት ክፍለ ጊዜ የሚል ትርጕም አላቸው፡፡ ብርሃን ደግሞ የጨለማ ተቃራኒ፣ የፀሐይ ብርሃን የማይታይበት ክፍለ ዕለት ሲኾን ‹‹ዕለት›› ማለትም በአንድ በኩል የፀሐይ ብርሃን የሚታይበት ጊዜን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከእሑድ እስከ ሰኞ ያሉትን፣ እንደዚሁም ከ፩-፴ የሚገኙ ዕለታትንም ያመላክታል /ዘፍ.፩፥፭-፴፩/፡፡ በአጠቃላይ ‹‹ጎሕ፣ ነግህ፣ ጽባሕ፣ ብርሃን፣ መዓልት›› ኹሉም የግእዝ ቃላት ሲኾኑ ተመሳሳይ ትርጕምና ጠባይዕ ያላቸው ፍጥረታት ናቸው፡፡
ስለ ንጋትና ብርሃን ለመናገር በመጀመሪያ ስለ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት አፈጣጠር ማስታዎስ ያስፈልጋል፡፡ ይኸውም እግዚአብሔር አምላክ በዕለተ ረቡዕ በመጀመሪያው ሰዓተ ሌሊት ‹‹ለይኩን ብርሃን፤ ብርሃን ይኹን›› ባለ ጊዜ ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት ተፈጥረዋል፡፡ የፀሐይ ተፈጥሮዋ ከእሳትና ከነፋስ ሲኾን ጨረቃንና ከዋክብትን ደግሞ ከነፋስና ከውኀ አርግቶ ፈጥሯቸዋል፡፡ ሲፈጥራቸውም ከኹሉም ፀሐይን፤ ከከዋክብት ደግሞ ጨረቃን አስበልጦ ፈጥሯቸዋል፡፡ የፈጠራቸውም እጠቀምባቸዋለሁ ብሎ ሳይኾን ለሰው ልጅና በዚህ ዓለም ለሚገኙ ፍጥረታት እንዲያበሩ ነው፡፡
እነዚህ የብርሃን ምንጮች ልዩ ልዩ ምሳሌያት አሏቸው፤ ጻድቃን ኹልጊዜ በምግባር በሃይማኖት ምሉዓን በመኾናቸው በፀሐይ፤ ኀጥኣን ደግሞ አንድ ጊዜ ሙሉ፣ ሌላ ጊዜ ጐደሎ እየኾኑ ይኖራሉና በጨረቃ ይመሰላሉ፡፡ አካሔዳው በሰማይና በምድር መካከል መኾኑ ምእመናን ጻድቃን በተፈጥሯቸው ምድራውያን ኾነው ሳሉ ሰማያዊውን መንግሥት የመውረሳቸው ምሳሌ ነው፡፡ ሰሌዳቸው ከነፋስ፣ ከእሳትና ከውኀ መኾኑ የመመህራን መንፈሳዊ ቍጣ ምሳሌ ነው፡፡ አንድም እሳት የመለኮት፤ ውኀ የትስብእት፤ ነፋስ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው /ሥነ ፍጥረት አንድምታ ትርጓሜ/፡፡
በሌላ ምሥጢር ስንመለከታቸው ‹‹ጎህ፣ ነግህ፣ ጽባሕ፣ ብርሃን መዓልት›› ወይም ኹሉንም በአጠቃላይ በብርሃን ምንጭነት ወይም በብርሃን ብንሰይማቸው ብርሃን እግዚአብሔር ነው፡፡ እርሱ በጨለማው ዓለም፤ በጨለማው ሕይወታችን፤ በጨለማው ኑሯችን የሕይወትን ወጋገን፣ ንጋት፣ ቀን የሚያወጣ አምላክ ነውና /ዮሐ.፩፥፭-፲/፡፡ ስለዚህ ‹‹እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኀኒቴ ነው፤ የሚያስፈራኝ ማነው?›› በማለት በብርሃን በተባለ በእግዚአብሔር መታመን ያስፈልገናል /መዝ.፳፮፥፩/፡፡ ዳግመኛም የእግዚአብሔር ሕግ ብርሃን ይባላል፡፡ ብርሃን ጨለማን እንደሚያስወግድ ኹሉ የእግዚአብሔር ሕግም ከኀጢአት ባርነት፣ ከሲኦል እሳት ያድናልና፡፡ ‹‹ሕግህ ለእግሬ መብራት፤ ለመንገዴም ብርሃን ነው›› እንዳለ ቅዱስ ዳዊት /መዝ.፻፲፰፥፻፭/፡፡
እንደዚሁም ብርሃን ክርስቲያናዊ ምግባርን ያመለክታል፡፡ ብርሃን ለራሱ በርቶ ለሌሎችም እንዲያበራ ክርስቲያናዊ ምግባርም ከራስ ተርፎ ለሰዎች ኹሉ ደምቆ ይታያልና /ዮሐ.፲፪፥፴፮፤ ፩ኛ ዮሐ.፩፥፯/፡፡ እኛም ‹‹ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃን ተመላለሱ›› ተብሎ እንደ ተጻፈ የጽድቅ ሥራ የማይገኝበት ጊዜ የጨለማ ዘመን ከመምጣቱ በፊት የጽድቅ ሥራ መሥራት በምንችልበት ጊዜ ኹሉ በመልካም ምግባር ጸንተን እንኑር፡፡
ደግሞም መልካም ግብር ያላቸው ምእመናን ብርሃን ተብለው ይጠራሉ፤ ብርሃን በግልጽ ለሰዉ ኹሉ እንደሚታይና እንደሚያበራ መልካም ምግባር ያላቸው ምእመናንም በጽድቅ ሥራቸው ለብዙዎች አርአያ፣ ምሳሌ ይኾናሉና፡፡ ‹‹እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፡፡ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትም›› እንዳለ ጌታችን በወንጌል /ማቴ.፭፥፲፬/፡፡ እንግዲህ ኹላችንም በጨለማ ከሚመሰለው ኀጢአት ወጥተን ወደ ጽድቅ ሕይወት እንመለስና እኛም በርተን ለሌችም ብርሃን እንኹን፡፡ አምላካችን ከኀጢአት ተለይተን፣ ንስሐ ገብተን እንደ ጻድቃኑ ‹‹የዓለም ብርሃን›› ለመባል የበቃን ያድርገን፡፡
በአጠቃላይ ይህ ወቅት ‹‹ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት›› እንደሚባለው ክረምቱ እየቀለለ፤ ዝናሙ እያባራ፤ ማዕበሉ እየቀነሰ፤ ሰማዩ እየጠራ የሚሔድበት የንጋት፣ የወጋገን፣ የብርሃን ጊዜ ነው፡፡ ልክ እንደ ዘመኑ እኛም በልባችን የቋተርነውን የቂም ደመና፤ በአእምሯችን የሣልነውን የክፋት ጨለማ፤ በወገን ላይ ያደረስነውን የዝናምና ማዕበል አድማ በንስሐ ፀሐይ አስወግደን ወደ ብርሃኑ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ፤ ወደ ብርሃኑ ሕገ እግዚአብሔር፤ ወደ ብርሃኑ ምግባረ ሠናይና ወደ ብርሃኑ ክርስትና እንድንመለስ ልዑል እግዚአብሔር ‹‹በሕይወታችሁ ውስጥ ብርሃን ይኹን›› ይበለን፡፡ እርሱ ‹‹ብርሃን ይኹን›› ካለ የኀጢአት ጨለማ በእኛ ላይ ለመሠልጠን የሚችልበት ዓቅም አያገኝምና፡፡
ከአራተኛው ክፍለ ክረምት (ከጎህ፣ ነግህ፣ ጽባሕ፣ ብርሃንና መዓልት) ቀጥሎ የሚገኘው አምስተኛው ክፍል ደግሞ ከመስከረም ፩-፰ ቀን (ከዮሐንስ እስከ ዘካርያስ) ያለው ጊዜ ሲኾን ይኸውም ‹‹ዮሐንስ›› በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ክፍለ ጊዜ የዓዋጅ ነጋሪው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ትምህርት፣ ጥምቀት፣ ምስክርነት፣ አገልግሎት፣ ዜና ሕይወት፣ ክብር፣ ቅድስና፣ ገድልና ዕረፍት፣ እንደዚሁም ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማጥመቅ መመረጡ ከአዲሱ ዓመት ጋር እየተጣጣመ በስፋት የሚዳሰስበት የብሥራት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ሳምንት የቅዱስ ዮሐንስን አገልግሎት የሚመለከቱ ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያን በስፋት ይቀርባሉ፡፡ የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በረከት በኹላችን ላይ ይደር፡፡
ይቆየን፡፡