ዕጣ በቤተ ክርስቲያን ትምህርትና ሥርዓት

ታኅሣሥ 1 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ምትኩ አበራ

ዕጣ /እጻ/ የሚለው ቃል ዐፀወ ዕጣ ተጣጣለ /አወጣ/ ከሚለው ግስ የወጣ ሲሆን አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በግእዝ አማርኛ መዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው “አጭርና ቀጭን እንጨት፤ ከመካከለኛ ጣት የሚበልጥ፤” ብለው ይፈቱታል፡፡ ዕጣ እድል ድርሻም ሊባል ይችላል፡፡ የዕጣ አሠራር ከክርስቶስ ልደት በፊት ከኦሪቱ ጊዜ ጀምሮ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ በጥንት ጊዜ ሰዎች ዕጣን በእንጨት፣ ጽሑፍ ባለበት ድንጋይ /ጠጠር/ ይጥሉ ነበር፡፡

 

የዕጣ ሥርዓትን ለሰዎች ያስተዋወቀው ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ “እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፡- ለእነዚህ በየስማቸው ቁጥር ምድሪቱ ርስት ሆና ትከፈላለች… ለሁሉ እንደቁጥራቸው መጠን ርስታቸው ይሰጣቸዋል፡፡ ነገር ግን ምድሪቱ በዕጣ ትከፈላለች፤ በብዙዎችና በጥቂቶች መካከል ርስታቸው በዕጣ ትከፈላለች”፡፡ /ዘኁ.26፥52-56/ ይህንን ትእዛዝ እግዚአብሔር ሲያስተላልፍ ሥርዐተ ዕጣውን የሚመሩትንም ጭምር “….ርስት ትሆናችሁ ዘንድ በዕጣ የምትደርሳችሁን ምድር…. የሚከፍሉላችሁ ሰዎች ስማቸው ይህ ነው፤ ካህኑ አልዓዛርና የነዌ ልጅ ኢያሱ፡፡” በማለት አሳውቋቸዋል፡፡ /ዘኁ.30፥2-16/ በዚህ ዐቢይ ትእዛዝ መሠረት ተሿሚዎቹ በተፈጥሮ ወጣ ገባ፣ ጭንጫና ለም ወዘተ… የሆነችውን ምድር ከሐሜት በጸዳና ከአድልኦ በራቀ መለኮታዊ ሥርዓት ርስቱን አከፋፍለዋል፡፡

 

ከዚህም ውጪ እስራኤላውያን በዕጣ ለእግዚአብሔር የሚሠዋውን ከማይሰዋው ለይተውበታል፤ ዘሌ.16፥8፣ ንጉሣቸውን መርጠውበታል፤ 1ሳሙ.10፥11-21፣ ወንጀለኞችን ለይተውመበታል፤ /ኢያ.7፥18፣ ዮና.1፥7/፣ ለጦር ሥራ ተጠቅመውበታል፤ 1ኛ ዜና.24፥19 መሳ.20፥9-10፣ ንብረት ለመካፈል ተጠቅመውበታል፡፡ ማቴ.27፥35፣ ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ በእግዚአብሔር ትእዛዝና ፈቃድ ሲሠራበት የቆየው ዕጣ ወደ ሐዲስ ኪዳን ዘልቆ ቤተ ክርስቲያን ትጠቀምበት እንደነበር መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

 

ዕጣና ጥቅሙ

በዕጣ መመዘኛዎቹን ተከተለን በአግባቡ መጠቀም ከቻልን በርካታ ጥቅሞች አሉት፡፡ ዕጣ የፈቃደ እግዚአብሔር ማወቂያ መንገድ ሆኖ በሐዋርያትም ዘመን አገልግሎ ነበር፡፡ ሐዋርያት ይሁዳ ረግጧት በሄደው ዕድል ፈንታ ለመተካት የራሳቸውን ዕውቀት ተጠቅመው ሁለት ሰው /ማትያስንና ዮሴፍን/ በእጩነት ካቀረቡ በኋላ፤ የሚፈለገው አንድ ብቻ ነበርና “የሁሉን ልብ የምታውቅ አንተ ጌታ ሆይ ይሁዳ ወደ ገዛ ራሱ ስፍራ ይሄድ ዘንድ በተዋት በዚህች አገልግሎትና ሐዋርያነት ሥፍራን እንዲቀበል የመረጥኸውን ከእነዚህ ከሁለቱ አንዱን ሹመው” ብለው ጸለዩ፡፡ ከዚያም “ዕጣን ተጣጣሉላቸው ዕጣውም ለማትያስ ወደቀና ከዐሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ተቆጠረ” /ግብ.ሐዋ.1፥23-26/ ፈቃደ እግዚአብሔር በዕጣው ላይ ተገለጠ፡፡

 

ዕጣ ዳኛ ሆኖ ያለ አድልኦ ይፈርዳል፤ ሰው ከፈረደው ፍርድ ይልቅ በዕጣ የተገኘን ፍርድ ሰው አክብሮ ያለማጉረምረም ይቀበለዋል፡፡ እስራኤላውያን በኢያሱ አማካይነት ምድረ ርስትን ሲከፋፈሉ በዕጣ ባይሆን ኖሮ መሬት ባላት ወጥ ያልሆነ አቀማመጥ ሳቢያ የሚፈጠረው ጦስ ያስከተለውን ጉዳት እናነብ ነበር፡፡ ያ ሳይሆን የቀረው ግን ርስት የማከፋፈሉ ሥራ በፈቃደ እግዚአብሔር ላይ ተመሥርቶ በዕጣ በመሆኑ ነው፡፡

 

ዕጣ ሐሜትን፣ ጭቅጭቅን፣ አድልዎን ከማስወገዱ በተጨማሪም አስተማማኝና አምላካዊ ውሳኔን አውቆ በእምነት ለመቀበል ያስችላል፡፡ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ ሰቃልያኑ ጭፍሮች ያቺን ሰብአሰገል ለጌታ የሰጡትን ከተግባረ ዕድ ነጻ የሆነች ቅድም፤ ስፍም የሌላትን ወጥ የሆነች ቀሚስ እንዳይቀዷትም እንዳይተውአትም ሳስተው ዕጣ ተጣጣሉ፡፡ “ጭፍሮቹም ኢየሱስን በሰቀሉት ጊዜ ልብሶቹን ወስደው ለእያንዳንዱ ጭፍራ አንድ ክፍል ሆኖ በአራት ከፋፈሉት፤ እጀ ጠባቡን ደግሞ ወሰዱ፡፡ እጀ ጠባቡም ከላይ ጀምሮ ወጥ ሆኖ የተሠራ ነበረ እንጂ የተሰፋ አልነበረም፡፡ ስለዚህ እርስ በእርሳቸው ለማን እንዲሆን በእርሱ ዕጣ እንጣጣልበት እንጂ አንቅደደው ተባባሉ፡፡….” እንደተባለ፡፡ /ዮሐ.19፥23-24/

 

ጭፍሮቹ ነገሮቹን በትንቢቱ /መዝ.24/ መሠረት የፈጸሙት ይሁን እንጂ የዕጣውን አሠራር ባይጠቀሙ ኖሮ ቀሚሷን ሁሉም ከወደዷት ለመውሰድ ሲሞክሩ የሚፈጽሙትን ሌላ የእርስ በእርስ ጠብ ልናነብ እንችል እንደነበር መገመት አያዳግትም፡፡ ስለዚህ ዕጣ አንድ ልብ አንድ አሳብ ለመሆን ይሰጣል፡፡

 

መንፈሳዊ የዕጣ ሥርዓት የሚኖሩት ዋና ዋና መርሖዎች

1.    በዕጣው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመረዳትና ያንንም ለመቀበል ተዘጋጅተን የሚፈጸም በመሆኑ ጸሎት የዕጣ ሥርዓት ቁልፍና ዐቢይ ተግባር ነው፡፡ ብላታ ወልደጊዮርጊስ እንዲህ ይላሉ

 

“አሳብ እንደ አንደበት በከንፈር፣ እንደ ዐይን በቅንድብ፣ እንደዦሮ በጣት አይዘጋም፡፡ አሳብ ረቂቅ ስለሆነ የነፍሳችን እንጂ የሥጋችን ሥራ አይደለም፤ ስለዚህ በግዙፉ ሥጋችን ልናግደው አንችልም፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ትርምስ ውስጣችን ሲያነቃ በቅድሚያ እግዚአብሔርን ሁሉ የሚቻልህ አምላኬ ሆይ የምችለውንና የምሠራውን ብቻ አሳስበኝ የተበተነውንና የሚባክነውን አሳብ ወስንልኝ ብለን እንለምነው፡፡ ከዚህ በኋላ ግን የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት፡፡ ተብሏልና ተገቢውን ጸሎት ካደረጉ በኋላ አሳብን በዕጣ መቁረጥ ተገቢ ነው፡፡ /1ጴጥ.5፥7/ አንዳንድ ጊዜ ሁለት በጎ አሳቦችን ስናወጣና ስናወርድ እንገኛለን፡፡ የሁለቱም አሳቦቻችን ጥቅምና ጉዳት ተካክሎ ሲታየን እግዚአብሔር በማትያስ መመረጥ ጊዜ በሐዋርያት ኅሊና እንዳደረገው መምረጥን ለእሱ እንድንተውለት ሲሻብን ነውና በጸሎት ለምነን በዕጣ መቁረጥ ተገቢ ነው፡፡”

 

2.    ከብዙ ነገሮች አንድን ነገር ለመምረጥ የሚፈጸም ሳይሆን በእኛ አቅም ለምንሻው ግልጽ ዓላማ ግልጽ መስፈርት አውጥተን ከብዙ ጥቂቶችን ከለየን በኋላ የሚያጋጥመንን ማመንታት በእርግጠኝነት ለማለፍ በመሆኑ ከሁለት ወይም ከሦስት ሰዎች ወይም ሁኔታዎች የበለጡ ነገሮችን በዕጣ መለየት ላያስፈልግ ይችላል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በተመረጡ ሰዎች አለማመን ብቃታቸውን መጠራጠር ወ.ዘ.ተ. ስለሚከተል ይህ እንደ መርኅ መያዝ የሚችል ነው፡፡ መጽሐፍም “ዕጣ ክርክርን ትከለክላለች” ይላል፡፡ መክ.18፥18

 

3.    የዕጣ ሥርዓት በራሱ ሁል ጊዜ ከአድልዎ የጸዳ ቢመስልም ከዕጣ ዝግጅትና አወጣጥ ጋር የተያያዙ ሥርዓቶችን በፍጹም ታማኝነትና ግልጽነት መፈጸም ይገባቸዋል፡፡ በዕጣው መካተት ያለባቸው ተመራጮች መካተታቸው፣ ዕጣው በምንም መሥፈርት የተለያየ ያልሆነና አንዱ ከአንዱ መለያ የሌላቸውና ለማንኛችንም ወገኖች ወጥተው ከመገለጣቸው በፊት ሥውር ሊሆኑ ይገባል፡፡ “ዕጣ በጉያ /በስውር/ ይጣላል፤ መደብዋ ሁሉ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” እንዲል፡፡ /ምሳ.16፥3/ የዕጣ አሠራር ከዚህ ሥርዓት ሲወጣ ከባሕር የወጣ ዓሣ ይሆናል፡፡

 

4.    ሲያወጡም ከአድልዎ ነጻ በሆነና ሁሉም በሚያምንባቸው አካላት ሊሆን ይገባል፡፡

ብዙ ጊዜ የተጠቀለለን ዕጣ በሕፃናት ማስወጣት የተለመደ ተግባር ሆኖ ይታያል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ ሰዎች ተንኮል ባልተቀላቀለው ፍቅር እንወድሃለን ሲሉ የሚያከብሩትንና የሚወዱትን እንግዳ በሕፃናት እጅ እቅፍ አበባ በማበርከት ይቀበሉታል፡፡ ዕጣን ማንኛውም ሰው ሊያወጣው ሲችል ሕፃናት የተመረጡበት ምክንያት ግን ለሁላችንም ግልጽ ይመስለናል፡፡ ሕፃናት ንጽሐ ጠባይ ያላደፈባቸው ስለሆኑ እግዚአብሔር በእነሱ ላይ አድሮ በዕጣው አማካኝነት እንዲፈርድልን ከማሰብ የተነሣ ነው፡፡ ክብር ምስጋና ይግባውና ራሱ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ ከቶ ወደ መንግሥተ ሰማያት ትገቡ ዘንድ አትችሉም” /ማቴ.18፥3/ በማለት እንደ ሕፃናቱ ኅዳጌ በቀል፣ የዋሕ፣ ንጹሕና ታማኝ እንድንሆን ይመክረናል፡፡ በየ ዓመቱ ሚያዝያ 3 ቀን በዓለ ዕረፍቱ የሚታሰብለትና በአንድ ወቅት የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የነበረው አባ ሚካኤል በስንክሳር መጽሐፍ የሰፈረው ታሪኩ የዕጣና ሕፃናትና አንድነት ያስረዳናል፡፡

 

አባ ሚካኤል ከታናሽነቱ ጀምሮ በገዳመ አስቄጥስ በአባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን መንኲሶ በተጋድሎ የኖረ አባት ነው፡፡ ከእርሱ በፊት የነበረው ሊቀ ጳጳስ አባ ገብርኤል ሲያርፍ የቅዱስ ማርቆስ መንበር ለ4 ወር ባዶ ሆኖ ቆየ፡፡ ሊቃውንት አባቶች በመንበሩ ላይ የሚተካ ሰው ከየገዳማቱ በመምረጥ ብዙ ከደከሙ በኋላ ሦስት ገዳማውያን አባቶችን በእጩነት አቀረቡ፡፡ ከዛም የሦስቱንም ስም በክርታስ /ወረቀት/ ጽፈው በመሠውያው /ታቦቱ/ ላይ ካኖሩ በኋላ ለሦስት ቀን እየጸለዩና ቅዳሴ እየቀደሱ እግዚአብሔር የወደደውን ያደርግ ዘንድ በመማለድ ቆዩ፡፡ ከሦስቱ ቀናት በኋላ አንድ ታናሽ ብላቴና ጠርተው ከእነዚህ ከሦስቱ ስሞች አንዱን አንሥተህ ስጠን አሉት፡፡ ያም ብላቴና የአባ ሚካኤል ስም ያለበትን ክርታስ አንሥቶ ሰጣቸው፡፡ ሁሉም እግዚአብሔር እንደመረጠው አውቀው ይገባዋል ብለው ሊቀ ጵጵስና ሾሙት፡፡ ይለናል፡፡

 

ዕጣና ውጤቱ

ዕጣ የጣልንበት አሳብ በዕጣው ሲገለጥ ውጤቱ እኛ የጠበቅነውም ያልተቀበልነውም ሊሆን ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ሁል ጊዜም ትክክል መሆኑን ካመንን ምንም ይሁን ምን ውጤቱን መቀበል ግዴታችን ነው፡፡ ለዕጣ የምናቀርበው አሳብ ወይም ሥራ በጎ ከሆነና እንደ ሐዋርያት በጸሎትና በተገቢው ሥርዓት የተደገፈ ሲሆን እግዚአብሔር በዕጣው ውስጥ ተምኔታችንን ይፈጽምልናል፡፡

 

የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ምርጫ እስካሁን ድረስ የዕጣ ሥርዓቱን አልተወም፡፡ የሕዝብ ድምፅ የሚሰጠው ከዕጣ በፊት ነው፡፡ በሐዋርያት ቀኖና እንደተገለጸው ለከፍተኛ የክህነት መዓርግ የሚታጭ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ ይሁንታ ማግኘት አለበት፡፡ በዚሁ መሠረት ለፓትርያርክነት የሚታጩትን ሦስት በሰዎች ለመምረጥ ከአባቶች ጀምሮ ምእመናኑ ሁሉ ድምፅ ይሰጣሉ፡፡ በዚሁ መሠረት ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የወጡት አባቶት ይለያሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ግን የሦስቱም ስም ይጻፍና ሥርዓተ ሲመቱ በሚፈጸምበት ቤተ ክርስቲያን መንበር ላይ ተደርጎ ሁለት ሱባኤ /ለ14 ቀናት/ ሁሉም ሲደልዩ ይሰነብታሉ፡፡ በአሥራ አራተኛው ቀን በዕለተ እሑድ ጸሎተ ቅዳሴው ከተጠናቀቀ በኋላ በዓይነ ስውር ሰው ወይም ለዚሁ በተዘጋጀ ሰው ዕጣው ይወጣል፤ በዕጣው የተመረጠው ሰው ፓትርያርክ ይሆናል፤ ሕዝቡም ይደልዎ ብለው ይቀበሉታል፡፡

 

አሁን በፕትርክና መንበር ላይ ያሉት የእስክንድርያው ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሽኖዳ ሣልሳዊ ከሌሎች ሁለት አባቶች ጋር ለዚህ ታላቅ ሰማያዊ ሥልጣን ሲታጩ የግብፅ ምእመናንም ይሁኑ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሁሉም ማለት ይቻላል አቡነ ሽኖዳ ከምእመናን ጋር ከነበራቸው ሰፊ ግንኙነት አንጻር ፓትርያርክ እንዲሆኑላቸው ቀድመው /ቢመኙም/ በዕጣ የመለየቱ ሥርዓት በግብፅ ቤተ ክርስቲያን የተቀመጠ ግዴታ ስለሆነ ተገቢው ሥርዓተ ጸሎት ደርሶ እግዚአብሔር የወደደውን ያደርግ ዘንድ ዕጣው እንደተጣለ ይታወቃል፡፡

 

በጣም የሚገርመው የሁሉም ምኞት የተሳካና ዕጣው የአቡነ ሽኖዳን ስም ይዞ ብቅ አለ፡፡ እግዚአብሔር በዕጣው ላይ ፈርዶ የልጆቹን የልቡናቸውን መልካም መሻት ፈጸመ፡፡ የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንም ሆነ ሊቃ ጳጳሳቱ የእግዚአብሔርን ምርጫ በምስጋና ተቀበሉት፡፡ ውጤቱ ካሰቡትና ከተመኙት በተቃራኒው እንኳን ቢሆን መቀበል ግን ግዴታቸው ነው፡፡

 

አንዳንድ ሰው ዕጣውን ለመጣል ይቸኩላል እንጂ ለዕጣው አጣጣል ካለመጠንቀቁም ሌላ ውጤቱን በጸጋ መቀበል እያቃተው ይሰነካከላል፡፡ ተገቢውን ሥርዓት ፈጽመን እግዚአብሔር በዕጣው እንዲፈርድ ድርሻ ሰጥተነው ስናበቃ በዕጣ በቆረጥነው አሳብና ተግባር ክፉ ቢያገኘን የእግዚአብሔር ፍርድ መሆኑን አውቀን፣ በጎም ቢያገኘን እሱን አመስግነን በጸጋ መቀበል እንጂ ምኞታችንና የዕጣው ሥርዓት ከመግባታችን በፊት ያስጨንቁን ከነበሩት መንታ አሳቦችና ወደ ዕጣ እንድንገባ ምክንያት ከሆነን ተግባር ይልቅ ይህ ምሬታችን ብርቱ ፈተና ሆኖን ከእግዚአብሔር እቅፍ ሊያወጣን ይችላል፡፡ ስለዚህ ከዚህ የከፋ እንዳያገኘን “ምርሐኒ ፍኖተ እግዝኦ እንተ ባቲ አሐውር” /አቤቱ የምሄድባትን መንገድ አንተ ምራኝ/ እያልን ቆራጥ ልቡናን ከፈጣሪ መለመን አለብን፡፡

 

የማይገባ ዕጣ

በምንኖርባት ዓለም ለሰዎች ልጆች የተፈጠሩትንና የሚሆኑትን ስናስብ ለመልካም እንጂ አንድም ለጥፋት የሆነና የሚሆን የለም፡፡ /ዘፍ.1፥4፣ 16፣ 19፣ 21፣ 25፣ 31/ ሁሉም ለመልካም ቢፈጠርም ቅሉ በአግባቡና በሥርዓቱ ስለማንጠቀምበት አንጻራዊ በሆነ መልኩ መልካሙ መጥፎ፣ ጠቃሚው ጎጂ፣ ለጽድቅ የሆነው ለኀጢአት ሲሆንብንና ስናደርገው ይታያል፡፡ “በጨለማ ለሚኖሩት ብርሃን ወጣላቸው” ተብሎ የተነገረለት ጌታ አይሁድ ባለማወቃቸው ምክንያት “የሚያዩ እንዲታወሩ፤ የማያዩ እንዲያዩ መጥቻለሁ” ብሎ ሲናገር እናነባለን፡፡

 

እንደዚሁም ሥርዓተ ዕጣ ጥቅም እንዳለው ሁሉ ጉዳትም እንዳለው ልናውቅ ያስፈልጋል፡፡ እንዲያውም ዕጣ በተሳሳተ መንገድ እየተፈጸመ በማየታቸው ብቻ አብዝተው የሚናገሩት የዕጣን አላስፈላጊነት ነው፡፡ በጥቅሉ ዕጣ አያስፈልግም ተብሎ መደምደም ባያስኬድም ስለማይገቡ ዕጣዎች ገልጦ ማስረዳት ግን ግድ ነው፡፡

 

ዕጣ አውጭው ጠንቋይ፣ ዕጣው የጠንቋይ ጠጠር ሲሆን ጐጂም ኀጢአትም ነው፡፡ ቀደም ሲል በገጠሩ አሁን አሁን ግን በሚያሳዝን መልኩ በየከተሞቻችን ሰዎች ለትዳር የፈለጉትን አጋር ወደ ጠንቋይ ቤት ተጉዘው “ዕጣ ክፍሌ ማን ነው?” በማለት ለማግኘት ሲሞክሩና ሚስት ወይም ባልሽ ዕጣ ክፍልህ /ሽ/ አይደለም /ችም/ እየተባሉ ትዳራቸውን ፈተው ልጆቻቸውን ሲበትኑ እያስተዋልን ነው፡፡ “ዕጣ”ን ለተቀደሰ ዓላማ እንጂ ለክፋት ለማዋል መሞከርም አደጋው ከፍ ያለ ነው፡፡

 

ሌላው የማይገባ ዕጣ ደግሞ ከክፉ ዓላማ ተነሥተን ክፉንም ለመፈጸም ስንጠቀምበት ነው፡፡ ክፉ ማለትም ሕገ እግዚአብሔር ለሚያስጥሰን ለየትኛው ተግባር ማለታችን ነው፡፡

 

ይህንንም ከንጉሥ አርጤክስስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ከሐማ ውድቀት መማር ይቻላል፡፡ ሐማ መርዶክዮስ ለምን እግሬ ሥር ወድቆ እጅ አልነሳኝም በሚል ከንቱ ስሜት ተነሥቶ በመቶ ሃያ ሰባት ሀገሮች የሚኖሩ አይሁዳውያንን በጅምላ ለማስጨፍጨፍ የትኛው ጊዜና ወቅት ምቹ እንደሆነ ያውቁ ዘንድ በቤተ መንግሥቱ ዕጣ አስጥሎ ነበር፡፡ “ሐማ. በአርጤክስ መንግሥት የነበሩትን አይሁድን ሁሉ ሊያጠፋ ፈለገ፡፡…. ከመጀመሪያው ወር ከኒሳን ጀምሮ በየዕለቱና በየወሩ እስከ ዐሥራ ሁለተኛው ወር እስከ አዳር ድረስ በሐማ ፊት ፉር የተባለውን ዕጣ /በአገራችን እንደጠጠር ጣይ የምንለው ዓይነት ማለት ነው/ ይጥሉ ነበር፡፡” /መጽ.አስ.3፥6-7/ ዳሩ ግን ሥርዓተ ዕጣው ከመነሻው የተበላሸና ዓላማው እግዚአብሔር የማይወደው ስለነበረ ውጤቱ ከፍቶ ሐማን በግንድ ላይ አሰቅሎ ተደመደመ፡፡ ሐማ የቤተ መንግሥቱን አዋቂዎች ሰብስቦ ዕጣ ሲያስጥል የነበረው አይሁድን በጅምላ ለመጨፍጨፍ የሚያስችለውን ጊዜ በመፈለግ መሆኑ ከላይ ተገልጧል፡፡

 

ማጠቃለያ

ዕጣ ውሳኔ ለሚያስፈልገው ለሁሉም ነገር የምንጠቀምበት ሥርዓት አይደለም፡፡ ለታወቀና ግልጽ ለሆነ ነገር ላንጠቀም እንችላለን፡፡ አንጥረን ለለየናቸው በደረጃ እኩል ለሆኑ ለምናመነታባቸው ጉዳዮች ብንጠቀም ተገቢ ነው፡፡ ወይም በሥርዓት ተደንግጎ የሆነውን ደረጃ እኛ ካከናወነው በኋላ ቀሪውን እግዚአብሔር እንዲገባበት ስንሻ ተግባራዊ የምናደርገው ይሆናል፡፡ ወይም ውሳኔያችን ክርክርና ፍቅር ማጣትን የሚያስከትል ከሆነ በዕጣ እናስማማዋለን፡፡ ከላይ በዝርዝር እንዳየነው ዕጣ በፈቃደ እግዚአብሔር ለሰዎች የተሰጠ የዳኝነት ሥርዓትና የመንታ ልብ መቁረጫ መሣሪያ ከሆነ በሃይማኖታዊውም ሆነ በማኅበራዊው ሕይወታችን ለበጎ ዓላማ ብንጠቀምበት መልካም ነው፡፡ የዕጣ ሥርዓት በዓውደ ዓመት ጊዜ የቅርጫን ሥጋ ለመከፋፈልና ለዕቁብ ቤት አንዳንዴም የሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን በየዓውደ ምሕረቱ ከሚጠቀሙበት የገቢ ማስገኛ ባለፈ መልኩ ለተለያዩ የቤተ ክርስቲያን ዓላማዎች በሐዋርያት ዘመን ይደረግ እንደነበረው ከብርቱ ጸሎትና ምልጃ ጋር ቢተገበር መልካም ነው፡፡ በነቢያትና በሐዋርያት የነበረውን ሥርዓትና ለረጅም ዘመንም በሀገራችን የነበረውን ትውፊት ከማስጠበቅ አንጻር በአፈጻጸም ክፍተት ሊኖርባቸው የሚችሉ አሠራሮቻችን ውስጥ ሁሉ ሥራ ላይ እንዲውል ሐዋርያት በሚታሰቡበት በዚህ ወቅት ለመጠቆም እንወዳለን፡፡

 

ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት 17ኛ ዓመት ቁጥር 2 ግንቦት – ሰኔ 2001 ዓ.ም.