ዕረፍተ ዘአበዊነ አብርሃም፣ይስሐቅ ወያዕቆብ
ነሐሴ ፳፮ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
የአባቶቻችን የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብን መታሰቢያቸውን እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አባቶቻችን አዘውናል፤ ከእርሳቸው ዘለዓለም የሚኖር ርስትን ተቀብለናልና፡፡ የእነዚህንም አባቶች ገድላቸውን እንዘክር ዘንድ ተገቢ ነው፡፡
ቅዱስ አብርሃም
ከሁሉ ነገር አስቀድሞ እግዚአብሔር አብርሃምን ጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ከሀገርህ ወጥተህ ከዘመድህ ከአባትህ ወገን ተለይተህ እኔ ወደ ማሳያህ ምድር ሂድ። ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ፤ ስምህንም ከፍ ከፍ አደረገዋለሁ፤ የተባረክህም ትሆናለህ፤ የሚአብሩህንም አከብራቸዋለሁ፡፡ የዚህ ዓለም አሕዛብ ሁሉ በአንተ ይከብራሉ፡፡” አብርሃምም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሄደ፡፡ የወንድሙን ልጅ ሎጥንና ሚስቱ ሣራንም ከርሱ ጋር ወሰደ፡፡ አብርሃምም ከካራን በወጣ ጊዜ ዕድሜው ሰባ አምስት ዘመናት ሆኖት ነበር፡፡ በካራንም ያጠራቀሙትን ገንዘባቸውን ሁሉ ይዘው ወደ ከነዓን ምድር ደረሰ፡፡ አብርሃምም ያቺን ሀገር ረጅም ዕንጨት እስከ አለበት እስከ ሴኬም ድረስ ዞራት፡፡ የከነዓን ሰዎች ግን የዚያን ጊዜ በዚያች ሀገር ነበሩ፡፡ እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተገልጦለት “ይህችን ሀገር ለልጆችህ እሰጣታለሁ” አለው፡፡ አብርሃምም በዚያ ለተገለጠለት ለእግዚአብሔር ምሥዋዕትን አዘጋጀ፡፡
ከዚያም ወደ ምሥራቅ ወደ ቤቴል ሄደ፤ በቤቴልም በጋይ በኩል በስተምራብ ድንኳኑ ተከለና በዚያ ተቀመጠ፡፡ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ የእግዚአብሔር ስም ጠራ፡፡ አብርሃምም ከዚያ ተነሥቶ ሄደ፤ በዚያም ሊኖር ወደ አዜብ ተጓዘ፤ በሀገሩም ራብ በጸና ጊዜ በዚያ ሊኖር ወደ ግብጽ ወረደ፡፡
አብርሃምም ወደ ግብጽ ይገባ ዘንድ በቀረበ ጊዜ ሚስቱን ሣራን እንዲህ አላት፤ “አንቺ መልከ መልካም ሴት እንደሆንሽ አውቃለሁ፡፡ የግብጽም ሰዎች ካዩሽ ሚስቱ ናት ብለው ይገድሉኛል፡፡ አንቺንም በሕይወት ያኖሩሻል፡፡ እንግዲህ ስለ አንቺ ይራሩልኝ ዘንድ በአንቺ ዘመንም ነፍሴ ትድን ዘንድ እኔ እኅቱ ነኝ በያወቸው፡፡” አብርሃም ወደ ግብጽ በደረሰ ጊዜ እንዲህ ሆነ፤ የግብጽ ሰዎች ሚስቱን እጅግ መልከ መልካም እንደሆነች አዩአት፤ የፈራዖን ሹማምንቶችም አይተው ወደ ፈራዖን ወሰዷት፤ ወደ ቤቱም አገቧት፡፡ ስለ እርሷም ለአብርሃም በጎ ነገርን አደረጉለት፡፡ ሴቶችና ወንዶች አገልጋዮች፣ ላሞችንና በጎችን፣ በቅሎዎችንና ግመሎችን፣ አህዮችንም አገኘ፡፡ እግዚአብሔርም በአብርሃም ሚስት በሣራ ምክንያት ፈርዖንና ቤተሰቡንም ጽኑ ሥቃይን አሠቃያቸው፡፡ ፈርዖንም አብርሃምንና ጠርቶ በእኔ ያደረከው ይህ ነገር ምንድን ነው? ሚስት መሆናን ያልነገርከኝ? ለምንስ እኅቴ ናት አልከኝ? ሚስት ልትሆነኝ ወስጃት ነበር፡፡ አሁንም ሚስትህ ያቻት፤ ይዛሃት ሂድ” አለው፡፡ ፈርዖንም አብርሃምንም ሚስቱን ሣራን ከጓዛቸው ሁሉ ጋር እንዲሸኟቸው ብላቴኖቹን አዘዘ፡፡
ከዚህመ በኋላ ለአብርሃም ዘጠና ዘጠኝ ዓመት በሆነው ጊዜ እግዚአብሔር ለአብርሃም ተገለጠለት፤ እንዲህም አለው፡፡ በፊትህ የሄዱኩ ፈጣሪህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ በፊቴ በጎ ነገርን አድርግ፤ ንጹሕም ሁን፡፡ በእኔና በአንተ መካከል ኪዳኔን አጸናለሁ፤ ፈጽሜም አበዛሃለሁ፤ ለብዙ አሕዛብ አባት ትሆናለህ፡፡ እንግዲህ ስምህ አብራም አይባልም፡፡ አብርሃም እንጂ፤ እጅግም አበዛለሁ፤ አሕዛብ ነገሥታትም ከአንተ እንዲወለዱ አደርጋለሁ፡፡
አብርሃም በቀትር ጊዜ በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በወይራ ዛፍ አጠገብ ተገለጠለት፡፡ ዓይኖቹንም አቅንቶ በተመለከተ ጊዜ እነሆ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቁመው ነበር፡፡ አይቶም ከድንኳኑ በር ሊቀበላቸው ሮጠ፡፡ በምድር ላይም ሰገደ፤ እንዲህም አለ፤ “አቤቱ በፊትህ ባለሟልነትን አግኝቼ ከሆነ ባሪያህን አትለፈው፤ ውኃ አምጥተን እግራችሁን እንጠባችሁ፤ ከጥላው ዕረፉ፤ እንጀራም እናምጣላችሁና ብሉ፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ አሰባችሁት ትሄዳላችሁ፡፡” እነርሱም እንዳልክ እንዲሁ አድርግ አሉት፡፡
አብርሃምም ወደ ሚስቱ ወደ ሣራ ሩጦ ወደ ድንኳኑ ከገባ በኋላ እንዲህ አላት፤ “ቶሎ በዩ! ሦስቱን መሥፈሪያ ዱቄት አቡክተሽ አንድ ዳቦ ጋግሪ፤ አብርሃምም ሁለት ላሞች ወዳሉበት ሮጠ፤ አንድ የሰባ ወይፈን ወሰደና ለብላቴናው ሰጠው፤ እርሱም ፈጥኖ አዘጋጀው፡፡ ማርና እርጎ ያዘጋጀውንም ሥጋ አምጥቶ ያሳልፍላቸው ነበር፡፡ እርሱም “ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?” አለው፡፡ አብርሃምም “እነሆ በድንኳን ውስጥ አለች” ብሎም መለሰ፡፡” በተመለስኩ ጊዜ የዛሬ ዓመት እንደዛሬው ወዳንተ እመጣለሁ፤ ሣራም ወንድ ልጅን ታገኛለች” አለው፡፡ ሣራም በድንኳኑ ደጃፍ በስተኋላው ቁማ ሳለች ይህን ሰማች፡፡ አብርሃምና ሣራ ግን ፈጽመው አርጅተው ዘመናቸው አልፎ ነበር፡፡ ሣራንም የሴቶች ልማድ ትቷት ነበር፡፡ እርሷም ለብቻዋ ሳቀች፤ በልቧ እንዲህ ብላለችና “እስከ ዛሬ ገና ነኝን? ጌታዬም አርጅቷል፡፡” እግዚአብሔርም አበርሃምን እንዲህ አለው፤ “ሣራን ለብቻዋ ምን አሳቃት? እስከ ዛሬ ገና ነኝን? በእውነቱስ እወልዳለሁን? ጌታዬም አርጅቷል፤ እኔም እነሆ አርጅቻለሁ” አለች፡፡ በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? በቀጠርኩህ ዓመት ወደ አንተ በተመለስኩ ጊዜ ሣራ በሰባተኛ ወሯ ልጅን ታገኛለች፡፡ የዚህም አባት ተጋድሎው፣ ትሩፋቱ፣ ርኅራኄው፣ ጽድቁም ብዙ ነው፡፡ ሁልጊዜ እንግዳ ካላገኘ በቀርና በማዕዱ አብሮት ካልተቀመጠ አይበላም ነበር፡፡ ስለዚህም ልዩ ሦስትን አካላት በማዕዱ እንዲቀመጡ የተገባው ሆነ፡፡
አብርሃምም ከዚያ ተነሥቶ ወደ አዜብ ምድር ሄደ፤ በሱሬና በቃደሴ መካከልም ኖረ፤ በጌራራም ተቀመጠ፤ አብርሃምም “ሚስቱ ሣራን እኅቴ ናት” አላቸው፤ አቤሜሌክ ልኮ ሣራን ወሰዳት፡፡ በዚያች ሌሊት አቤሜሌክ ተኝቶ ሳለ እግዚአብሔር ወደ አቤሜሌክ ገባ፡፡ በሕልም እንዲም አለው፤ እርሷ የጎልማሳ ሚስት ናትና ስለዚህ ስለወሰድካት ሴት እነሆ አንተ ትሞታለህ፡፡” አቤሜሌክ ግን አልነካትም ነበር፤ አቤሜሌክም እንዲህ አለ፤ “በውኑ ያላወቀ ሰውን ታጠፋለህን? እርሱ እኅቴ ናት አለኝ፡፡ እርሷም ወንድሜ ነው አለችኝ፡፡” ይህንም ሥራ በንጹሕ ልቤ በንጹሕ እጄ አደረግሁት፤ እግዚአብሔርም በሕልም እንዲህ አለው፡፡ “እኔም በየዋህነትህ እንዳደረግከው አውቄዋለሁና ራራሁልህ፤ ኃጢአትም እንዳትሠራ ጠበቅኩህሁ፤ ስለዚህም እንድትቀርባት አልተውኩህም፡፡ አሁንም ለዚያ ሰው ሚስቱን መልስለት፤ ነቢይ ነውና ስለ አንተ ይጸልይልህ፤ አንተም ትድናለህ፤ ባትመልስለት ግን አንተ ሞትን እንድታሞትን ያንተ የሆነው ሁሉ እንዲጠፋ ዕወቅ፡፡ አቤሜሌክም አብርሃምን ጠርቶ ይህ በእኔና በመንግሥቴ ላይ ያደረገከው ምንድን ነው? ማንም የማይሠራው ታላቅ ኃጢአት ነው፡፡ ይህንንስ ያደረግህ ምን አይተህ ነው? አለው፡፡” አብርሃምም እንዲህ አለ፤ “ምናልባት በዚህ ቦታ እግዚአብሔርን መፍራት የለምና ስለ ሚስቱ ይገድለኛል ብዬ ነው፡፡ ዳግመኛም በእውነት ከእናቴ ያይደለች ከአባቴ ወገን የሆነች እኅቴ ናት፡፡ ሚስቱም ሆነችኝ፤ እግዚአብሔርንም ከአባቴ ቤተ ባወጣኝ ጊዜ ይህንን በጎ ሥራ አድርጊልኝ፤ በገባንበትም ቦታ ሁሉ ወንድም ነው ብዬ አልኋት፡፡” አቤሜሌክም ሽህ ምዝምዝ ብርን፣ ሴቶችና ወንዶች አገልጋዩችን፣ ላሞችና በጎችንም አምጥተው ለአብርሃም ሰጠው፤ ሚስቱ ሣራንም መለሰለት፡፡
አብርሃምም ወደ እግዚአብሔር ለመነ፤ እግዚአብሔርም አቤሜሌክን ፈወሰው፤ ልጆችንም ሁሉም ወለዱ፤ ስለ አብርሃም ሚስት ስለ ሣራ እግዚአብሔርም ማኅፀንን ሁሉ በአፍኣ በውስጥ ዘግቶ ነበርና፡፡ ከዚህም በኋላ በጎ ተጋድሎውን ፈጽሞ እግዚአብሔርንም አገልግሎ በመቶ ሰባ አምስት ዕድሜው ወደ ወደደው እግዚአብሔር ሄደ፡፡
ቅዱስ ይስሐቅ
ዳግመኛም የአባቶች አለቃ ለሆነ አብርሃም ልጅ ለይስሐቅ የዕረፍቱን መታሰቢያ እንድናደርግ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን መምህራን አባቶቻችን አዘውናል፡፡ ይህ ጻድቅ ይስሐቅም በልዑል አምላክ ብሥራት ተወለደ፡፡ ይህንንም ንጹሕ ይስሐቅን እግዚአብሔርን ለልጁ ክርስቶስ ምሳሌው አደረገው፡፡ አብርሃምን እንዲህ ብሎታልና፤ “የምትወደውና ልጅህን ይስሐቅን ከአንተ ጋር ውሰደውና ወደ ላይኛው ተራራ ሂድ፤ እኔ ወደ እምነግርህ ወደ አንዱ ተራራ ላይ አውጥተህ በዚያ ሠዋው፡፡” አብርሃምም በጥዋት ተነሥቶ አህያውን ጫነ፤ ልጁ ይስሐቅና ሁለቱ ብላቴኖቹንም ወሰደ፤ ለመሥዋዕትም ዕንጨትን ፈልጦ አሸክሞ ሄደ፡፡ በሦስተኛው ቀን እግዚአብሔር ወዳለው ወደዚያ ቦታ ደረሰ፡፡ አብርሃምም በዓይኑ ቃኘ፤ ቦታውንም ከሩቅ አየ፡፡ አብርሃምም ብላቴናዎቹን “እናንተ አህያውን ይዛችሁ ከዚህ ቆዩ፤ እኔና ልጄ ግን ወደ ተራራ እንደሄዳለን፤ ሰግደንም ወደእናነተ እንመለሳለን” አላቸው፡፡ አብርሃምም መሥዋዕት የሚቃጠልበትን ዕንጨት አምጥቶ ለልጁ ለይስሐቅ አሸክመው፤ እርሱም ወቅለምቱንና እሳቱን በእጁ ያዘ፤ ሁለቱንም በአንድነት ሄዱ፤ ይስሐቅም አባቱ አብርሃምን “አባ” አለው፡፡ እርሱም “ልጄ ምነው?” አለው፤ “እነሆ እሳትና ዕንጨት አለ፤ መሥዋዕት የሚሆነው በጉ ወዴት ነው?” አለው፡፡ አብርሃምም “መሥዋዕት የሚሆነውን በግ እግዚአብሔር ያዘጃጋጃል” አለው፤ አብረውም ሄደው እግዚአብሔር ወደለው ወደዚያ ቦታ ደረሱ፤ አብርሃምም በዚያ መሠዊያን ሠራ፤ ዕንጨቱን ደረደረ፡፡ ልጁ ይስሐቅንም አሥሮ ጠልፎ በመሠዊያው በዕንጨቱ ላይ በልቡ አስተኛው፤ አብርሃምም ልጁን ያርደው ዘንድ እጁን ዘርግቶ ወቅለምቱን አነሣ፡፡ በዚያን ጊዜም እግዚአብሔር አብርሃምን “አብርሃም አብርሃም” ብሎ ጠራው፤ እርሱም “አቤት” አለ፡፡ “በልጅህ ላይ እጅህን አትዘርጋ፤ ምንም ምን አታደርግበት፤ አንተ እግዚአብሔርን እንደምትፈራው አሁን አወቅሁ፤ ለምትወደው ለልጅህ አልራራህለትምና” አለው፡፡
አብርሃምም በተመለከተ ጊዜ ቀንድና ቀንዱ በዕፅ ሳቤቅ የተያዘ አንድ በግ አየ፤ አብርሃምም ሄደና ወስዶ በልጁ ይስሐቅ ፈንታ ሠዋው፡፡ ይህም ንጹሕ ይስሐቅ ጎልማሳ ሲሆን አባቱ ሊሠዋው በአቀረበው ጊዜ እግዚአብሔር በበግ እስከ አዳነው ድረስ ለአባቱ በመግዛት ለመታረድ አንገቱን ዘርግቶ ሰጠ፡፡ እርሱም በአባቱ በአብርሃም ኅሊና ፍጹም መሥዋዕት ሆነ፡፡ ከዚህም በኋላ ይስሐቅን መቸገርና ስደት አግኝቶታል፡፡ በአባቱ በአብርሃም ዘመን ከሆነው ሌላ በሀገር ረኃብ ሁኖ ነበርና የፍልስጥኤም ንጉሥ አቤሜሌክ ወዳለበት ወደ ጌራራ ይስሐቅ ሄደ፤ በዚያ ተቀመጠ፡፡
የሀገር ሰዎችም ይስሐቅን የሚስቱን የርብቃን ነገር ጠየቁት፤ እርሱም “እኅቴ ናት” አላቸው፤ ሚስቱ ርብቃ መልከ መልካም ስለነበረች የዚያች ሀገር ሰዎች እንዳይገድሉት “ሚስቴ ናት” ብሎ መናገርን ፈርቷልና፡፡ በዚያም ብዙ ዘመን ኖረ፤ አቤሜሌክም በመስኮት በተመለከተ ጊዜ ይስሐቅን ከርብቃ ጋር ሲጫወት አየው፡፡ አቤሜሌክም ይስሐቅን ጠርቶ “እኅቴ ናት አልኸኝ እንጂ እነሆ ሚስትህ ናት” አለው፤ ይስሐቅም በርሷ ምክንያት ይገድሉኛል ብዬ ነው” አለው፡፡ አቤሜሌክም “ይህ ያደረክብኝ ነገር ምንድን ነው? ከዘመዶቹ የሚሆን አንድ ሰው ከሚስትህ ጋር ሊተኛ ጥቂት ቀርቶት ነበር፤ ባለማወቅም ኃጢአትን ልታመጣብኝ ነበር፡፡” ንጉሡም “የዚህን ሰው ሚስቱን የነካ ሁሉ ፍርድ ይሙት” ብሎ ሕዝቡን አዛዘቸው፡፡ ይስሐቅም በዚያች ምድር ዘርን ዘራ፤ መቶ ዕጽፍ ሆነለት፤ እግዚአብሔርም ባረከው፤ ከፍ ከፍም አለ፤ እጅግም ገነነ፡፡ ወንድና ሴት ባርያዎችን፣ ላምን በግን አብዝቶ ገዛ፤ የፍልስጥኤም ሰዎችም ቀኑበት፡፡ በአባቱም ዘመን የአብርሃም ብላቴናዎች የቆፎሩአቸው ጉድጓዶች የፍልስጥኤም ሰዎች ደፈኑዋቸው፤ አፈርንም መሏቸው፡፡ አቤሜሌክም ይስሐቅን ፈጽመህ በርትተህብናልና ከእኛ ተለይተህ ሂድ” አለው፡፡ ይስሐቅም ከዚያ ተነሥቶ በጌራራ ሸከቆ ሰፍሮ በዚያ ተቀመጠ፡፡ የአባቱ አገልጋዮች የቆሩዋቸውንና አባቱ አብርሃምም ከሞተ በኋላ የፍልስጥኤም ሰዎች የደፈኗቸውን የውኃ ጉድጓዶች እንደገና ቆፈራቸው፤ አብረሃም እንደጠራቸው ጠራቸው፡፡ የይስሐቅም አገልጋዮች በጌራራ ቆላ ጉድጓድ ቆፍራው የሚጣፍጥ የውኃ ምንጭ አገኙ፤ ይስሐቅም እረኞችና የጌራራ እረኞች “ይህ ውኃ የእኛ ነው፤ የእኛ ነው” በማለት ተጣሉ፡፡ ያችንም የውኃ ጉድጓድ የዓመፅ ጉድጓድ ቆፈረ፤ በእርሷም ምክንያት ተጣሉ፤ ስሟንም “ጠብ” ብሎ ጠራት፡፡ ከዚያም ተጉዞ ሄዶ፤ ሌላ ጉድጓድን ቆፈረ፤ በእርሷ ምክንያት ግን አልተጣሉትም፤ ስሙንም “ሰፊ” አለው፡፡ “ዛሬ እግዚአብሔር አሰፋልን በምድርም አበዛን” ሲል ነው፡፡
ከዚህም በኋላ ሁለት ልጆችን ኤሳውንና ያዕቆብን ወለደ፡፡ ይስሐቅም አሳውን ጽኑዕ ኃይለኛ ስለሆነ ይወደዋል፡፡ ይስሐቅም አርጅቶ ዓይኖቹ ፈዘው የማያይ ከሆነ በኋላ እንዲህ ሆነ፡፡ ታላቁ ልጁ ኤሳውን ጠርቶ “እነሆ አረጀሁ፤ የምሞትበትን ቀን አላውቅም፡፡ ማደኛ መሣሪያህን የፍላፃ መንደፊያ ይዘህ ወደ በረሃ ውጣ፡፡ ሳልሞት ነፍሴ እንድትመርቅህ እበላ ዘንድ እንደምወደው አድርገህ አምጣልኝ” አለው፡፡ ርብቃም ታናሹ ልጁ ያዕቆብን እንዲህ አላቸው፡፡ “እነሆ አባትህ ወንድምህ ኤሳውን ሳልሞት በእግዚአብሔር ፊት እንድመርቅህ ከአደንከው አዘጋጅተህ የምበላውን አምጣልኝ ሲለው ሰምቼዋለሁ፡፡ አሁንም ልጄ ሆይ በማዝህ ነገር እሺ በለኝ፡፡ ወደ በጎቻችንም ሂደህ ያማሩ ሁለት ጠቦቶችን አምጣልኝና አባትህን እንደሚወደው አዘጋጃቸው ዘንድ ሳይሞት በልቶ እንዲመርቅህ ወስደህ ለአባትህ እንድትሰጠው” አለችው፡፡ ያዕቆብም እናቱ ርብቃን እንዲህ አላት፤ “እነሆ ወንድሜ ኤሳው ጠጉራም ነው፤ እኔ ግን አይደለሁም፤ ምንአልባት አባቴ ቢዳስሰኝ በፊቱ እንደምዘብትበት እሆናለሁና ምርቃን ያይደለ በላዬ መናገርምን አመጣለሁ፡፡” እናቱም “ልጄ ሆይ መርገምህ በእኔ ይሁን፤ ቃሌን ብቻ ሰማኝ፤ ሂድና የምልህን አምጣልኝ” አለችው፤ ሂዶም ለእናቱ አመጣላትና አባቱ እንደሚወደው አድርጋ መብሉን አዘጋጀች፡፡
ርብቃም ከእርሷ ዘንድ የነበረውን ያማረውን የታላቅ ልጇ የኤሳውን ልብስ አምጥታ ለታናሽ ልጅዋ ለያዕቆብ አለበሰችው፡፡ ያንንም የሁለቱን ጠቦቶች ለምድ በትክሻውና በአንገቱ ላይ አደረገች፤ ያንን ያዘጋችውን እንጀራና ጣፋጭ መብልን ለያዕቆብ በእጁ ሰጠችው፡፡ ወደ አባቱ ገብቶም “አባቴ ሆይ” አለው፡፡ አባቱም “እነሆኝ ልጄ ሆይ አንተ ማነህ?” አለው፡፡ ያዕቆብም እኔ የበኩር ልጅህ ኤሳው ነኝ፤ ያልኸኝን አዘጋጅቻለሁ፤ ተነሥና ተቀመጥ፤ ከአደንኩልህም ብላና ነፍስህ ትመርቀኝ ዘንድ” አለው፡፡ ይስሐቅም “ልጄ ቅረበኝ፤ ልዳሥሥህ፤ አንተ ኤሳው እንደሆንክ ወይም እንዳልሆንክ” አለው፡፡ በቀረበም ጊዜ ዳሠሠው፤ “ቃልህ የያዕቆብ እጆችህ ግን የኤሳው ናቸው” አለው፡፡ “ልጄ አድነህ ያመጣህልኝን በልቼ ነፍሴ ትመርቅህ ዘንድ አምጣልኝ” አለው፡፡ አቅርቦለት በላ፤ ወይንም አመጣለትና ጠጣ፡፡ ይስሐቅም “ልጄ ቅረበኝና ሳመኝ” አለው፤ ቀርቦም ሳመው፤ ሽታው እግዚአብሔር እንደባረከው እንደ ዱር አበባ ሽታ ነው” አለ፡፡ እንዲሁም ብሎ መረቀው፤ ከሰማይ ጠል ከምድር ስብ ይስጥህ፤ ስንዴህን፣ ወይንህንና ዘይትህን ያብዛልህ፡፡ አሕዛብም ይገልዙልህ፤ አለቆችም ይስገዱልህ፤ ለወንድሞችህም ጌታ ሁን፤ የአባትህም ልጆች ይስገዱልህ፤ አንተን የሚመርቅህ የተረገመ ይሁን፤” ይህም በእግዚአብሔር ፈቃድ ሆነ፡፡ ይህም አባት ይስሐቅ ወደ መቶ ሰማንያ ዘመን በደረሰ ጊዜ እንዲህ ብሎ ተናገረ፤ “ከዚህም በኋላ መልአክ ወደ ሰማይ ወሰደኝ፤ አባቴ አብርሃምን አየሁትና ሰገድኩለት፤ እርሱም ሳመኝ፤ ንጹሐን ሁሉ ስለ አባቴ ተሰበሰቡና ወደ ውስጠኛው የአብ መጋራጃ ከበውኝ ከእኔ ጋራ ሄዱ፤ እኔም ወድቄ ከአባቴ ጋር ሰገድኩ፡፡ የሚያመሰግኑ መላእክት ሁሉ “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ” ተብሎ የሚመሰገን አሸናፊ እግዚአብሔር ምስጋናው በሰማይና በምድር የመላ እያለ ጮኹ፡፡ አባቴ አብርሃምን እኔ በቦታዬ ልዩ ነኝ፤ ሰው ሁሉ ልጁን በወዳጄ ይስሐቅ ስም ቢሰይም በቤቱ ውስጥ በረከቴ ለዘለዓለም ይኖራል፡፡ የብሩክ ወገን የሆንክ አንተ ብሩክ አብርሃም ሆይ መምጣትህ መልካም ነው፡፡ አሁንም በወዳጄ በልጅህ ይስሐቅ ስም የሚለምን ሁሉ በረከቴ በቤቴ ውስጥ ለዘለዓለም እንዲኖር ቃል ኪዳኔን አጸናታለሁ፤ ትሩፋቱን፣ ቅንነቱን፣ ገድሉን የሚጽፍ ካለ ወይም በስሙ የተራበ የሚያጠግብና በመታሰቢያው ቀን የተራቆተ የሚያለብስ እኔ የሚያልፈውን መንግሥት እሰጠዋለሁ” አለው፡፡
አብርሃምም እንዲህ አለ፤ “አቤቱ ዓለሙን ሁሉ የያዝክ አብ ሆይ፥ ቃል ኪዳኑን፣ ገድሉን ይጽፍ ዘንድ ካልታቸለው ቸርነትህ ትገናኘው፤ አንተ ቸሪ መሐሪ ነህና እንጀራ የሌለው ችግረኛ ቢሆንም፡፡” ጌታም እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ “በወዳጄ በይስሐቅ በመታሰቢያው ዕለት ከሌሊት ጀምሮ በጸሎት ይትጋ፤ አይተኛም፤ እኔም መንግሥቴን ከሚወርሱ ጋራ ከበረከቱ እሰጠዋለሁ፡፡” አባቴ አብርሃምም ሁለተኛ እንዲሀ አለ፤ “በሽተኛ ድውይ ከሆነ ቸርነትህ ታግኘው፡፡” ጌታም እንዲህ አለ፤ “ጥቂት ዕጣን ያግባ፤ ዕጣንን ካላገኘ የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ፈልጎ በልጅህ በወዳጄ በይስሐቅ መታሰቢያው ቀን ያንብበው፡፡ ማንበብም የማያውቅ ከሆነ ወደሚያነብለት ሄዶ እርሷን አስነብቦ ይስማ፡፡ ከእነዚህም ይህን ማድረግ ካልቻለ ወደ ቤቱ ገብቶ ደጁን ይዝጋ፤ እንደጸለየ መቶ ስግደቶችን ይስገድ፤ እኔም የሰማይ የመንግሥት ልጅ አደርገዋለሁ፡፡ ለቁርባን የሚሆነውንና መብራቱን ያገባ እኔ ያልኩትን ሁሉ የሚያደረግ እርሱ የመንግሥተ ሰማያትን ርስት ይቀበላል፡፡ ቃል ኪዳኑንና ገድሉን ትሩፋቱን ለመጻፍ ልቡን ያበረታውን እኔ ስሙን በሕይወት መጽሐፍ እጽፋለሁ፤ በሽህ ዓመት ውስጥ ምሳ ላይም ይገኛል፡፡ እግዚአብሔርም ይህን ብዙ ነገርን በተናገረ ጊዜ ያዕቆብ አይቶ በመደንገጥ ነፍሱ ተመሠጠች፡፡ ይስሐቅም ያዕቆብን አንሥቶ “ልጄ ሆይ ዝም በል፤ አትደንግጥ” ብሎ ጠቀሰው፡፡ ከዚህም በኋላ ሳመውና በሰላም ዐረፈ፤ ከኤሞር ልጆች በገዛው እናቱ ሣራ በተቀበረችበት በአብርሃም መቃብር ተቀበረ፡፡
ቅዱስ ያዕቆብ
እግዚአብሔር አምላክ “እስራኤል” ብሎ ስም ያወጣለትን የአባቶች አለቃ የሆነ የያዕቆብን የዕረፍቱን መታሰቢያ እናደረግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አባቶቻችን አዘዙን፡፡ ይህም ቅዱስ በበጎ ሥራ ሁሉ በመራራት፣ በቅንነት፣ በትሕትና በለጋስነት የአባቶቹን የአብርሃምንና የይስሐቅን መንገድ የተከተከ ሆነ፡፡ ወንድሙ ኤሳውም ብኵርናውን ስለወሰደበት አብዝቶ ስለጠላው ሊገድለው ይፈልግ ነበር፡፡ ስለዚህም አባቱና እናቱ ርብቃ ያዕቆብን ወደ ርብቃ ወንድም ወደ ላባ ሰደዱት፡፡ እየተጓዙም ሳለ በአደረበት በረሃ ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርሱ መሰላል የእግዚአብሔርም መላእከት በውስጡ ሲወርዱ ሲወጡ በሕልሙ አየ፡፡ እንዲህም አለ፤ “ይህ የሰማይ ደጅ ነው፤ ከዚህም የእግዚአብሔር ቤት ይሠራል፡፡ በሶሪያ ምድር ወደሚኖር ወደ እናቱ ወንድም ወደ ላባ በደረሰ ጊዜ ሁለቱን ልጆቹን ልያንና ራሔልን አጋበው፡፡ በዚያም የላባን በጎች እየጠበቀ ሃያ አንድ ዓመት ያህል ኖረ፡፡ ላባም “የምሰጥህ ምንድን ነው?” አለው፡፡ ያዕቆብም “ምንም የምትሰጠኝ የለም፡፡ አሁን ወደ ፊት የምነግርህን ነገር ካደረግህልኝ ዳግመኛ በጎችህን ፈጽሜ እጠብቃለሁ፡፡ አሁን በጎችህ በፊት ይለፉና ከበጎችህ ሁሉ ጠጉራቸው ነጨጭ የሆኑትንና መልካቸው ዝንጉርጉር የሆነውንም ስለ ዋጋዬ ለይልኝ” አለው፡፡ ዓይነቱን ዝንጉርጉር ያልሆነውና መልኩ ነጭ ያልሆነው ሁሉ ግን ላንተ ይሁን” አለው፤ ላባም እንዳልክ ይሁን አለ፡፡
በዚያችም ቀን ነጩንም ቀዩንም ዝንጉርጉር መልኩ ዳንግሌ የሆነውንም የፍየሉንም አውራ ለይቶ ለልጆቹ ሰጠ፡፡ በእነርሱምና በያዕቆብ መካከል ሦስት ቀን የሚያስኬድ ጎዳና ርቀው ሄዱ፡፡ ያዕቆብ ግን የቀሩትን የላባን በጎች ይጠብቅ ነበር፡፡ ያዕቆብም የልምጭ በትርንና ታላቅ የሎሚ በትርን ወስዶ ቅርፍቱን ልጦ ጣለው፤ ያዕቆብ የላጣቸው በትሮች ነጫጭ ሁነው ታዬ፡፡ እነዚያንም በትሮች በጎች ከሚጠጡበት ገንዳ ላይ ጣላቸው፡፡ በጎች ውኃ ሊጠጡ በመጡ ጊዜ እነዚያ በትሮች በፊታቸው ሁነው ይታዩ ዘንድ፤ መጥተውም በጠጡ ጊዜ እነዚያን በትሮች አስመስለው ፀንሰው ነጩንና ሐመደ ክቦውን ዝንጉርጉርን ወለዱ፡፡ ያዕቆብም አውራ አውራቹን በጎች ለየ፤ አውራ አውራውን ከለየ በኋላ አንስት እንስቶቹን በጎች ለይቶ ዝንጉርጉር ሐመደ፡፡ ክቦና ነጭ በሆኑ አውራጃዎች ፊት አቆማቸው፤ የራሱንም በጎች ለያቸው እንጂ ከላባ በጎች ጋራ አልቀላቀላቸውም፡፡
ያዕቆብም እጅግ ፈጽሞ ባለጸጋ ሆነ፤ ወንዶችንና ሴቶችን አገልጋዮችን ገዛ፤ ብዙ ከብት ላሞችን፣ በጎችን፣ ግመሎችንን፣ አህያዎችንም ገዛ፡፡ ያዕቆብም ወደ ሀገሩ በተመለሰ ጊዜ እስከ ንጋት ድረስ አንድ ሰው ሲታገለው አደረ፡፡ ከእርሱም ጋር ሲታገል እንዳልቻለው ባየ ጊዜ እርም የሚሆንበት ሹልዳውን ያዘው፤ “ኅህ ቀድዷልና ልቀቀኝ” አለው፡፡ “ስምህ ማን ይባላል?” ቢለው “ስሜ ያዕቆብ ነው” አለው፤ “እንግዲህ ስምህ ያዕቆብ አይባል፤ እስራኤል ይባል እንጂ” አለው፤ “ከእግዚአብሔርና ከሰው ጋር መታገልን ችለሃልና፡፡”
ከዚህ በኋለ ስለ ልጁ ዮሴፍ ብዙ ኀዘን አገኘው፤ ወንድሞቹ ወደ ግብጽ ሸጠውታልና በጠየቃቸው ጊዜ “ክፉ አውሬ በልቶታል” አሉት፤ ከልቅሶውም ብዛት የተነሣ ዓይኖቹ ታወሩ፡፡ ከዚያም ረኃብ ሆነ፤ በግብጽ ሀገር እህል የሚሸጥ መሆኑን ያዕቆብ ሰማ፤ ሥንዴ ይሸምቱ ዘንድ ልጆቹን ላካቸውና ወደ ዮሴፍ ደረሱ፤ ንጉሥ ሆኖም አግኝተውት ሰገዱለት፡፡ ወንድማቸው እንደሆነም አላወቅትም፤ እርሱ ግን አውቋቸዋል፡፡ ሥንዴውንም ሰጥቶ አሰናበታቸው፤ ሁለተኛም በተመለሱ ጊዜ ራሱን ገለጠላቸውና “ወደዚህ ስለሸጣችሁኝ አትፍሩ እመግባችሁ ዘንድ በፊታችሁ እግዚአብሔር ለሕይወት ልኮኛልና” አላቸው፡፡ አሁንም ፈጥናችሁ ሂዱና ለአባቴ ንገሩት፤ ልጅህ ዮሴፍ እንዲህ ይላል በሉት፤ “ለግብጽ ሀገር ሁሉ እግዚአብሔር ጌታ አድርጎኛል፤ ፈጥነህ ና፤ በዚያ ልኑር አትበል፤” ስለዚህም እስራኤል ወደ ግብጽ ሀገር ከቤተሰቡ ሁሉ፣ ከጓዙና ከገንዘቡ ጋር ወርዶ በዚያ የሚኖር ሆነ፡፡ ዕረፍቱም በቀረበ ጊዜ ልጆቹን ጠርቶ እያንዳንዳቸውን መረቃቸው፤ ትንቢትንም ተናገረላቸው፤ የዮሴፍንም ልጆች ኤፍሬምና ምናሴን እጆቹን አመሳቅሎ ባረካቸው፤ መረቃቸውም፤ ከዚህም በኃላ በሰላምና በፍቅር ዐረፈ፡፡
የቅዱሳን አባቶቻችን የአብርሃም፣ የይስሐቅ እና የያዕቆብ በረከታቸው ይደረብን፤ አሜን፡፡
ከመጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ነሐሴ