በአውሮፓ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ጥናት ጉባኤ ተካሔደ
በአውሮፓ ማእከል
ጳጕሜን ፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
በማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል የሙያ አገልግሎት እና አቅም ማጎልበቻ ክፍል አስተባባሪነት ‹‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅርሶች›› በሚል ርእሰ ጉዳይ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጥናት ጉባኤ በስዊድን አገር በሉንድ ዩኒቨርሲቲ ከነሐሴ ፳፯ – ፳፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ተካሔደ፡፡
በጥናት ጉባኤው በታዋቂ ምሁራን በአማርኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች በልዩ ልዩ አርእስት የተዘጋጁ የምርምር ሥራዎች የቀረቡ ሲሆን፣ ከአውሮፓ ሀገራት የመጡ በርካታ ምእመናን እና የስዊድን ዜጎች በተዳሚነት ተሳትፈዋል፡፡
በመጀመሪያው ጉባኤ በለንደን ከተማ የደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት ቀሲስ አባተ ጉበና ‹‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅርስ ጥቅሞች፣ የቤተ ክርስቲያን ደኖች እንደ አገር ብዝኀ ሕይወት ማሳያነት›› በሚል ርእስ ባስተላለፉት መልእክት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በደን ጥበቃ የላቀ አስተዋጽዖ ከማበርከቷ ባሻገር የብዝኀ ሕይወት መገኛ እንደ ሆነችም አስረድተዋል፡፡
በሉንድ ዩኒቨርሲቲ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሳሙኤል ሩቢንሰን፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ ቅርሶች ለክርስትና ታሪክ ያላቸው አስተዋጽዖ›› በሚል ርእስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ በምዕራባውያን ጫና ምክንያት የክርስትና ታሪክ በመጀመሪያ ወደ አውሮፓ መግባቱ፤ በቅኝ ግዛት ዘመን ወደ አፍሪካ እና እስያ መስፋፋቱ በተዛባ መልኩ እንደሚነገር አውስተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ታሪክ በክርስትና ታሪክ ውስጥ የሚያካትቱ አካላትም የኢትዮጵያ ባህል ከሌሎች አገሮች ተገንጥሎ የወጣ እንደ ሆነ እና ለክርስትና ታሪክም አስተዋጽዖ እንደሌለው የማድረግ ዝንባሌ እንደሚታይባቸው ፕሮፌሰሩ አብራርተዋል፡፡ ‹‹በመጀመሪያው ምዕት ዓመት በነበረው የክርስትና አመሠራረት ላይ የኢትዮጵያን አስተዋጽዖ አለማካተት የክርስትናን ታሪክ ጎደሎ እንዲኾን ያደርዋል›› የሚሉት ፕሮፌሰር ሩቢንሰን፣ ክርስትና ከኢየሩሳሌም ወደ አውሮፓ፤ ከዚያም በቅኝ ግዛት ዘመን ወደ አፍሪካ እና እስያ ደረሰ የሚለው አስተሳሰብ ስሕተት መሆኑን በጥናታቸው ጠቁመዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅርሶች ታሪክና ጥበቃ›› በሚል ርእስ ጥናት ያቀረቡት የአርኪዮሎጅ እና አንትሮፖሎጅ ምሁሩ እንግሊዛዊው ፕሮፌሰር ዴቪድ ፊልፕሰን፣ ከዘመነ አክሱም ጀምሮ ያለውን የኢትዮጵያ ቅርሶችን ታሪክ ካስታወሱ በኋላ ስለ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አሠራር፣ ስለሚደረግላቸው ክብካቤና ጥበቃ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በዘራፊዎች ተወስደው በውጭ አገር የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶችን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት እንዳይሳካ የሚያደርጉ ጉዳዮችንም ዳሰዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ ፊሊፕሰን በእንግሊዝ አገር የሚገኙ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ይመለሱ ተብሎ እንቅስቃሴ በሚደረግበት ወቅት ቅርሶችን በማስተዳደር ላይ ያሉት የብሪታንያ ሙዚየም ባለ ሥልጣናት ‹‹ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ቢመለሱ፣ ጥበቃና ክብካቤ የሚያደርግላቸው የለም›› የሚል ምክንያት እንደሚሰጡ በጥናታቸው አውስተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከእንግሊዝ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ቅርሶችም እንዳሉ የጠቆሙት ፕሮፌሰሩ ለአብነትም በ፲፰፻፸፪ ዓ.ም የተመለሰው ክብረ ነገሥት የተባለው መጽሐፍ በአዲስ አበባ ከተማ በመርካቶ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን በጥሩ ክብካቤ እንደሚገኝ ከሰባ ዓመታት በፊት ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ተሞክሮ በመነሣትም ዅሉም ቅርሶቿ ቢመለሱላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሥርዓት እንደምትጠብቃቸው በመጠቆም ፕሮፌሰር ፊሊፕሰን ጥናታዊ ጽሑፋቸውን አጠናቀዋል፡፡
በኖርዌይ አገር የአካባቢያዊ ኬሚስትሪ ምሁሩ ዶክተር ኪዳኔ ፋንታ በበኩላቸው ‹‹የኢትዮጵያ ክርስቲያናዊ ሥዕላት ፊዚኮ – ኬሚካዊ ምርመራ›› በሚል ርእስ ባዘጋጁት ጥናታዊ ጽሑፋቸው ሥዕላቱ የተሠሩበትን ንጥረ ነገር ማወቅ ሥዕላቱን ለመጠበቅና እና እድሳት ለማድረግ ጠቀሜታ እንዳለው አመላክተዋል፡፡ ዘመኑ ያፈራቸውን የረቀቁ የቤተ ሙከራ መሣሪያዎች በመጠቀምና ምርመራ በማድረግ ልዩ ልዩ ሥዕላት፣ የሕንጻ ዓምዶች እና የብራና ጽሑፎች የተዘጋጁበትን ንጥረ ነገር፣ ዘመን እና ቦታ ለመለየትና ለመረዳት እንደሚቻልም በምሳሌ አስረድተዋል፡፡
ሌላኛው ጽሑፍ አቅራቢ የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ተከሥተ ነጋሽ ደግሞ ‹‹ዋሌ ኢየሱስ፣ የአክሱም ዘመን ቤተ ክርስቲያን በዛግዌ ምድር›› በሚል ርእስ ባቀረቡት ጥናት በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ውስጥ የሚገኘውን ጥንታዊ የዋሻ ቤተ ክርስቲያንን አሠራር የሚመለከት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የዋሌ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን አሠራር በአክሱም ዘመን ከታነጹ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ተመሳሳይነት እንዳለውም አስረድተዋል። በቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ የሚኖሩ መነኮሳትና ካህናት ቤተ ክርስቲያኑ ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አስቀድሞ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደ ተመሠረተ ማስረጃዎች መሆናቸውንም ፕሮፌሰር ተከሥተ ነጋሽ አውስተዋል፡፡
ነሐሴ ፳፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ከቅዳሴ በኋላ በሉንድ ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ሁለተኛው የጥናት ጉባኤ የቀጠለ ሲኾን፣ በልዩ ልዩ አርእስት የተዘጋጁ ሦስት ጥናታዊ ጽሑፎች በአማርኛ ቋንቋ ቀርበዋል፡፡ በመጀመሪያ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ቅርሶች ለመጠበቅ፣ ለምእመናን ምን ያኽል ትምህርት ተሰጥቷል?›› በሚል ርእስ የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ እስከ አሁን ድረስ በአደረጉት የሰነድ ምርመራ የቅርሶችን ምንነት እና አጠባበቅ የሚያስረዱ ጽሑፎችን ማግኘት አለማቻላቸውን፤ በቤተ ክርስቲያን የሚሰጡ አብዛኞቹ ትምህርቶችም የቅርስ አያያዝን አለማካተታቸውን አስገንዝበዋል። በዚህ የተነሣም የቤተ ክርስቲያን ቅርሶች የመጥፋት አደጋ እንደ ተጋረጠባቸው ገልጸዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሕንጻዎችን፣ ንዋያተ ቅድሳትን እና መጻሕፍትን ለመጠበቅና ከጥፋት ለመታደግ ይረዳ ዘንድ መሠረታዊ የቅርስ ጥበቃ፣ ክብካቤ እና ጥገናን የሚመለከቱ ሥልጠናዎችን መስጠት አስፈላጊ መሆኑንም ፕሮፌሰር ሽፈራው በጥናታቸው ማጠቃለያ ጠቁመዋል፡፡
በመቀጠል የፊሎሎጅ ምሁሩ ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ ተፈራ ‹‹ጥንታዊ የብራና ላይ ጽሑፎቻችን ዘረፋ፣ የአያያዝ ጉድለትና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች›› በሚል ርእስ የምርምር ሥራቸውን አቅርበዋል፡፡ የብራና ጽሑፎችን ምንነት፣ ዓይነትና ይዘት በመተንተን ጥናታቸውን የጀመሩት ቀሲስ ዶ/ር አምሳሉ፣ በውጭ ሀገራት የሚገኙ በርካታ የኢትዮጵያ ቅርሶች በአብዛኛው በዘረፋ መልክ የተወሰዱ፤ የተወሰኑት ደግሞ ነገሥታቱ ለመሪዎች በስጦታ መልክ ያበረከቷቸው መሆናቸውን አውስተዋል፡፡ እንደ ቀሲስ ዶ/ር አምሳሉ ማብራሪያ በአጠቃላይ 6,245 የብራና መጻሕፍት በልዩ ልዩ መንገድ ከኢትዮጵያ የተወሰዱ ሲሆን፣ አብዛኞቹም በእንግሊዝ፣ በጀርመን፣ በጣልያን እና ቫቲካን አገሮች ይገኛሉ፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም ጥቂት የብራና ጽሑፎች በልዩ ልዩ ጊዜያት ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን አስታውሰው እርሳቸው ተሳትፎ ያደረጉበትን ከአሜሪካው ሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም የተመለሰውን የገድለ ሰራባሞን እና ሌሎችም ቅርሶችን በማስረጃነት ጠቅሰዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን፣ መንግሥት እና እያንዳንዱ ግለሰብ ቅርሶችን የመጠበቅ ሓላፊነት እንዳለበት በማሳሰብ ቀሲስ ዶ/ር አምሳሉ ጥናታቸውን አጠቃለዋል፡፡
በጥናት ጉባኤው ማጠናቀቂያ ዕለትም ከጥናት አቅራቢዎች መካከል ፕሮፌሰር ዴቪድ ፊልፕሰን ‹‹በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል ይህን ዐውደ ጥናት በማዘጋጀቱ በቤተ ክርስቲያኒቱ ዙሪያ የሚሠሩ ምርምሮችን ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን ልጆች ጋር ለመወያየት እድል ፈጥሮልኛል›› በማለት አስተያየት ከሰጡ በኋላ ዐውደ ጥናቱን ያዘጋጀውን ማኅበረ ቅዱሳንን አመስግነዋል፡፡ ሌሎች ጥናት አቅራቢዎችና ተሳታፊዎችም በጉባኤው እንደ ተደሰቱ ገልጸው ወደፊትም ይኽን ዓይነቱ የጥናት ጉባኤ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም ለዚህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ መሳካት አስተዋጽዖ ላደረጉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ለሉንድ ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ሰበካ ጉባኤ፣ ለሉንድ ዩኒቨርሲቲ፣ ለፕሮፌሰር ሳሙኤል ሩቢንሰን፣ ጥናታዊ ጽሑፍ ላቀረቡና መልእክት ላስተላለፉ ምሁራን፣ ለተጋባዥ እንግዶች እና በጉባኤው ለተሳተፉ ምእመናን የዐውደ ጥናት ዝግጅት ኮሚቴው ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ በኮሚቴው፤ ዲያቆን ዓለምነው ሽፈራው ደግሞ በአውሮፓ ማእከል ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡