ዐውደ ርእዩ በኢንድያናፖሊስ ከተማ ቀረበ
በዝግጅት ክፍሉ
ነሐሴ ፲፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
‹‹ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ›› በሚል ርእስ በማኅበረ ቅዱሳን የተዘጋጀው ልዩ ዐውደ ርእይ በአሜሪካ አገር በኢንዲያናፖሊስ ከተማ ለምእመናን ቀረበ፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን አሜሪካ ማእከል ኢንዲያና ግንኙነት ጣቢያ አዘጋጅነት ሐምሌ ፳፱ እና ፴ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም የቀረበው ይህ ልዩ ዐውደ ርእይ በጸሎተ ወንጌል ተባርኮ በወጣቶች እና ሕፃናት ዘማርያን ያሬዳዊ መዝሙሮች ከቀረቡ በኋላ ከኢንዲያና እና አጎራባች ግዛቶች በመጡ ከሦስት መቶ ስልሳ በላይ በሚኾኑ ካህናትና ምእመናን እንደ ተጐበኘ የአሜሪካ ማእከል አስታውቋል፡፡
እንደ ማእከሉ ማብራሪያ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ ሐዋርያዊ አገልግሎቷ፣ ተጋድሎዋ፣ ያጋጠሟት ችግሮች እና ችግሮቿን ከመፍታት አንጻር የምእመናን ድርሻ እንደዚሁም የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት በቤተ ክርስቲያን የሚሉ ጉዳዮች በዐውደ ርእዩ የተካተቱ የትዕይንት ክፍሎች ሲኾኑ፣ ትዕይንቶቹም በአማርኛ፣ ትግርኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች ተተርጕመው ለወጣቶች እና ሕፃናት በሚመጥን መልኩ ቀርበዋል፡፡
መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ኃይለ ማርያም የኢንዲያናፖሊስ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ እና መልአከ ኃይል ቀሲስ ፍቅረ ኢየሱስ የኬንታኪ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ካህን ከሌሎች አባቶች ጋር በዐውደ ርእዩ ተገኝተው ከምእመናን ለሚነሡ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት የአባትነት ድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡
የዐውደ ርእዩ ትዕይንቶች ወደ ትግርኛ ቋንቋ ተተርጕመው ለምእመናን እንዲቀርቡ በማድረግ በኢንዲያናፖሊስ ከተማ የሚኖሩ ትግርኛ ቋንቋ መናገር የሚችሉ ካህናት እና ምእመናን ድርሻ የላቀ እንደ ነበርም በማእከሉ ሪፖርት ተጠቅሷል፡፡
በአጠቃላይ የዐውደ ርእዩ ዝግጅት ላይ የኢንዲያናፖሊስ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ፣ የሰንበት ት/ቤቱ አባላት፣ የአጥቢያው ምእመናን፣ የኢንዲያና ግንኙነት ጣቢያ እና የቺካጎ ንዑስ ማእከል አባላት በገላጭነት፣ በአስተባባሪነት እና በልዩ ልዩ የአገልግሎት ዘርፎች ከፍተኛ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡
በመጨረሻም የዝግጅት ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር በላይነህ ደስታ ለዝግጅቱ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ላደረጉ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ስፖንሰር (ድጋፍ) በማድረግ ለተባበሩ የግል ድርጅቶች እና ለበጎ አድራጊ ምእመናን ምስጋና ካቀረቡ በኋለ ዐውደ ርእዩ በአባቶች ጸሎት ተፈጽሟል፡፡