ዐውደ ርእዩ በሺሕ በሚቈጠሩ ምእመናን እየተጐበኘ ነው፡፡
ሰኔ ፳፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ በሚል መሪ ቃል የአዳማ ማእከል በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ መልካም ፈቃድ በአዳማ ከተማ በደብረ ናዝሬት ኢየሱስ ደብር ያዘጋጀው ዐውደ ርእይ ከሰኔ ፲፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ጀምሮ በሺሕ በሚቈጠሩ የናዝሬት (የአዳማ) ከተማና የአካባቢው ምእመናን እየተጐበኘ ይገኛል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝ፣ ምክትል ዋና ጸሐፊው አቶ ሰይፈ ዓለማየሁ እና የኅትመትና ኤሌክሮኒክስ ሚድያ ዋና ክፍል ምክትል ሓላፊ አቶ አክሊሉ ለገሠ ሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በአዳማ ከተማ በደብረ ናዝሬት ኢየሱስ በመገኘት የአዳማ ማእከል ያዘጋጀውን ዐውደ ርእይ የጐብኙ ሲኾን፣ ዝግጅት ክፍላችንም በዕለቱ በቦታው በመገኘት ይህንን ዘገባ አጠናቅሯል፡፡
አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝ የዐውደ ርእዩን ዓላማ ለዝግጅት ክፍላችን ሲገልጹ ማኅበረ ቅዱሳን ይህንን ዐውደ ርእይ ያዘጋጀው ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ዕውቀት የበለጸጉና ዕውቀታቸውንም በተግባር መለወጥ የሚችሉ፤ ከውጪ ኾነው የሚመለከቱና የሚተቹ ሳይኾኑ የቤተ ክርስቲያኗ አገልግሎት የኔ ነው የሚሉና ክርስትናን በሕይወት የሚኖሩ ምእመናንን ለማፍራትና የድርሻቸውንም እንዲወጡ ለማስገንዘብ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ ሰይፈ ዓለማየሁ በበኩላቸው ይህ ዐውደ ርእይ በየማእከላቱ እንዲታይ ማኅበሩ አቅጣጫ መስጠቱንና የአምቦ ማእከል በቀዳሚነት ዐውደ ርእዩን ማስጐብኘቱን ገልጸው፣ *እንደ አዳማ ማእከል ኹሉ ሌሎች ማእከላትም ይህንን ተሞክሮ በመውሰድ በ፳፻፱ ዓ.ም የአገልግሎት ዘመን የዕቅዳቸው አካል በማድረግ ይህንን ዐውደ ርእይ ለምእመናን ማስጐብኘት ይጠበቅባቸዋል* ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አቶ ሰይፈ አያይዘውም የአዳማ ከተማና የአካባቢው ምእመናን ዐውደ ርእዩን እየጐበኙ የሚገኙት ያለምንም ክፍያ መኾኑን ጠቅሰው *ማኅበራችን የተቋቋመው ለአገልግሎት እንጂ ለትርፍ አይደለምና በኪሳራም ቢኾን ሕዝበ ክርስቲያኑን ማስተማር ይገባናል፡፡ ምእመናኑ በገንዘብ ምክንያት የቤተ ከርስቲያን አስተምህሮ ሊያመልጣቸው ስለማይገባ፤ ደግሞም የዐውደ ርእዩ ዓላማ ማስተማር እንጂ ገንዘብ መሰብሰብ ስላልኾነ ዐውደ ርእዩ በነጻ እንዲታይ አድርገናል ሲሉ ዐውደ ርእዩ ያለ ክፍያ እንዲታይ የተደረገበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡
የአዳማ ማእከል ሰብሳቢ መምህር ጌትነት ዐሥራትም የዐውደ ርእዩ ዓላማ ምእመናን የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በማወቅና የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ችግሮች በመገንዘብ የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማነሣሣት መኾኑን ገልጸው ቦታውን ከመፍቀድ ጀምሮ ለዐውደ ርእዩ መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ ለሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ለመጋቤ ትፍሥሕት ሙሉጌታ ቸርነት፣ ለየመምሪያ ሓላፊዎች፣ ለደብረ ናዝሬት ኢየሱስ እና ደብረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ካቴድራል አስተዳዳሪ ሊቀ ጉባኤ አባ ተክለ ሃይማኖት ወልዱ፣ ለደብሩ ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤትና አገልጋይ ካህናት፣ ለሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ እንደዚሁም ለመንፈሳውያን ማኅበራትና ለበጎ አድራጊ ምእመናን ማእከሉንና የዐውደ ርእይ ዝግጅት ኰሚቴውን ወክለው ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ዐውደ ርእዩ በትዕይንት ገላጮች ብቻ ሳይኾን በድምፅ ወምስል በታገዙ መረጃዎች እንደሚቀርብ፤ እንደዚሁም የአብነት መምህራንና ደቀ መዛሙርቱ ሥርዓተ ትምህርት፣ የዋናው ማእከልና የአዳማ ማእከል ሥራዎች የትዕይንቱ አካላት እንደ ኾኑ የገለጹት የዐውደ ርእይ ዝግጅት ኰሚቴው ሰብሳቢ መምህር ኃይለ ኢየሱስ ከበረ ደግሞ በአባቶች ጸሎት ከተከፈተበት ዕለት ጀምሮ እስከ ሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ድረስ ከአምስት ሺሕ በላይ ምእመናን እንደ ጐበኙት ጠቅሰው በቀን በአማካይ እስከ ስምንት መቶ የሚደርሱ ጐብኚዎች መታደማቸውን አስታውቀዋል፡፡
ዝግጅት ክፍላችን ካነጋገራቸው ከትዕይንት ገላጮች መካከል አቶ ፍሬ ሰንበት ተክለ ሚካኤል የተባሉ ወንድም ሃይማኖታዊ ድርሻቸውን ለመወጣትና እርሳቸው የሚያውቁትን ለሌሎች ለማካፈል በማሰብ በትዕይንት ገላጭነት በማገልገል ላይ እንደሚገኙ ነግረውናል፡፡
በዐውደ ርእዩ ከታደሙ ምእመናን መካከልም አንዳንዶቹ በዐውደ ርእዩ ብዙ ቁም ነገር መጨበጣቸውን ጠቅሰው በአንጻሩ ግን በተለይ በጠረፋማ አካባቢዎች በባዕድ አምልኮ ውስጥ የሚኖሩ ወገኖች ለመጠመቅ እየፈለጉ ነገር ግን በሰባክያንና በካህናት እጥረት ምክንያት የቤተ ክርስቲያን አባላት ሳይኾኑ በመቅረታቸው ማዘናቸውን ገልጸውልናል፡፡
ሌሎቹ ደግሞ ዐውደ ርእዩ ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ይበልጥ እንድንወዳትና የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ችግሮችንም እንድንገነዘብ አድርጎናል፤ ከዚህ በኋላ የሚጠበቅብንን ኹሉ ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡ አክለውም ይህንን ዐውደ ርእይ እስከ ማእከል ድረስ እንዲታይ በማድረጉ ማኅበረ ቅዱሳንን አመስግነዋል፡፡
በመጨረሻም የአዳማ ማእከልና የዐውደ ርእዩ ዝግጅት ኰሚቴው አባላት ከኹሉም በላይ በአገልግሎታቸው ኹሉ ላልተለያቸው ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ካቀረቡ በኋላ ዐውደ ርእዩ ሰኔ ፳፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ገልጸው አሁንም ምእመናኑ መጐብኘታቸውን እንዲቀጥሉ ሲሉ መንፈሳዊ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡