ዐቢይ ጾም
መምህር አብርሃም በዕውቀቱ
የካቲት ፲፰ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
‹‹ዐቢይ›› የተባለው የዓለማት ፈጣሪ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአርአያነት ጾሞ የመሠረተው ጾም ስለሆነ ነው፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ካሉት ሰባት የአዋጅ አጽዋማት ረጅሙ (፶፭ ቀን ያለው) ስለሆነ ደግሞ ‹‹ሁዳዴ›› ይባላል፡፡ ኢትዮጵያዊው የዜማና የቅዱሳት መጻሕፍት ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በዐቢይ ጾም ውስጥ የሚገኙትን ስምንት ሣምንታት ለትምህርት፣ ለአዘክሮና ለምስጋና በሚመች መልኩ ልዩ ስያሜዎች ሰጥቷቸዋል፡፡ ስለሆነም በእያንዳንዱ ሳምንት (ሰንበት) የሚነበቡ፣ የሚተረጎሙ፣ የሚዘከሩ፣ የሚዘመሩ ልዩ ልዩ መጽሐፍ ቅዱሣዊ ኩነቶችና አስተምህሮዎች አሉ፡፡
ፍጹም ሰው፣ ፍጹም የባሕርይ አምላክ ከሆነ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሰማያዊ ዕውቀት የባሕርዩ የሆነ፡ ሰማያዊ ሀብትን ሰማያዊ ዕውቀትን ገንዘብ ያደረገ ምድራዊ መምህር የለም፡፡ ሰማያዊ ሀብትን ሰማያዊ ዕውቀትን ገንዘብ ያደረገ ከሰማይ የወረደው ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ከምድራዊያን መምህራን በራሱ ወደ ሰማይ ወጥቶ ተመልሶ ወርዶ ያየውን የሚያስተምር የለም፡፡ እርሱ ከሰማይ የመጣው ግን ሰማያዊ ምሥጢርን ለማስተማር (ለመግለጥ) የራሱ ባሕርይ (የባሕርዩ) ነው፡፡
ከጌታችን በቀር በኅልውና ያየውን የሚገልጥ በሰማይ ሆኖ በህልውና ያየውን በህልውና የሰማውን መጥቶ የሚያስተምር ምድራዊ መምህር የለም፡፡ በሰማይ ሆኖ በህልውና ያየውን በህልውና የሰማውን የራሱን ምሥጢር ያስተማረ እርሱ ብቻ ነው፡፡ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው፡፡
ከጌታችን በቀር ሰማያዊ የለም፡፡ ሰማይ የልዕልና ስፍራ፣ የእግዚአብሔር ዙፋን ነው፡፡ በዚያ ዙፋን የተቀመጠ፣ ሰውንም ለማዳን ከዙፋኑ የወረደ እርሱ ብቻ ነው፡፡ ሌላ በዚያ ዙፋን የተቀመጠ ከዚያ ዙፋንም የወረደ የለም፡፡ ሰውን ለማዳን ከዙፋኑ የወረደው በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው፡፡
ከጌታችን በቀር በራሱ ፈቃድ ከሰማይ የወረደ የለም፡፡ ፍጡራን (መላእክትና ሰዎች) ወደ ሰማይ ቢወጡም ቢወርዱም በራሳቸው ፈቃድ አይደለም፡፡ በራሱ ፈቃድ በአባቱ ፈቃድ ከሰማይ የወረደ ወደ ሰማይም የወጣ እርሱ ብቻ ነው፡፡ በራሱ ፈቃድ ከሰማይ የወረደው በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው፡፡
ከጌታችን በቀር በባሕርይው መለወጥ የሌለበት፣ አንድ ባሕርይ የሆነ፣ ይህንንም በራሱ ፈቃድ የወሰነ የለም፡፡ ከሰማይ የወረደው ወደ ሰማይ የወጣውም አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው፡፡ ከሰማይ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆኖ ወርዶ ሁለት ባሕርይ ሁለት አካል ሆኖ ወደ ሰማይ የወጣ አይደለም፡፡ ልክ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆኖ እንደወረደ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆኖ ወጣ ማለት ነው፡፡ አንድ ባሕርይ ሆኖ ወርዶ አንድ ባሕርይ ሆኖ ወደ ሰማይ የወጣው በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው፡፡
ዘወረደ በተባለችው የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሰንበት ወልደ እግዚአብሔር ስለ ድኅነታችን መውረዱን እያሰብን ስናመሰግን የመውረዱንም ምክንያት በሚገባ ከመረዳት ጋር ሊሆን ይገባል፡፡ ጌታችን ከሰማይ የወረደው፣ ከድንግል ማርያም የተወለደው፣ በዚህ ምድር ላይ እንደ ሰው ተመላልሶ ያስተማረው ስለ ሁለት ምክንያት ነው፡፡ አንደኛው ለቤዛነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለአርአያነት ነው፡፡
ለቤዛነት፡– በእርሱ የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው፣ የሰው ልጅ ዳግመኛ እንዳይጠፋ፣ እርሱ ስለእኛ ተሰቅሎ ቤዛ ሊሆነን፣ ዓለም በልጁ ቤዛነት እንዲድን እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ስለወደደ ለቤዛነት ከሰማይ ወረደ፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት ‹‹እግዚአብሔር ለዘላለም ንጉሥ ነው፤ በምድር መካከልም መድኃኒትን አደረገ፤›› (መዝ.፸፫፥፲፪) እንዳለ ‹‹እግዚአብሔር አንድያ ልጁን በዓለም እንዲፈርድ አልላከውም፡፡ መድኃኒት ሆኖ እንዲያድነን እንጂ፡፡ ስለዚህ በእርሱ የሚያምን አይፈረድበትም፤ በእርሱ ያላመነ ግን በአንዱ የእግዚአብሔር ልጅ ስላላመነ ተፈርዶበታል›› እንደተባለ በስሙ አምነን ቤዛ ይሆነን ዘንድ ወረደ፣ ተወለደ፡፡
ለአርአያነት፡– ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለሙ ሁሉ ሊያበራ፣ ብርሀን የሆነውን ሕገ ወንጌልን ሊሠራልን ወረደ፡፡ የሰውንም ልቡና በወንጌል ሊያበራ ወረደ፡፡ ሕግን የሰራ እርሱ የሰራውን ሕግ እየተገበረ አርአያ ሆኖ ሊያስተምረን ወረደ፡፡ ነገር ግን ‹‹ክፉ የሚያደርግ ብርሀንን ይጠላል፤ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሀን አይመጣም›› እንደተባለ ክፉ የሚያደርጉ በብርሃን ክርስቶስ አያምኑም፤ አርአያ ሆኖ የፈጸመውን ሕግም አይፈጽሙም፤ ብርሀንን ለማጥፋት ይጥራሉ እንጂ፡፡ ክፉ የሚያደርጉ (የጨለማ ሥራ የሚሠሩ) ወደ ጨለማ ይሄዳሉ፡፡ በአንፃሩ ‹‹እውነትን የሚያደርግ ወደ ብርሀን ይመጣል፡፡ ሥራውም በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደሆነ እንዲገለጥ ወደ ብርሃን ይመጣል›› እንደተባለ መልካም የሚያደርጉ በእርሱ ያምናሉ፡፡ መልካም የሚያደርጉ የብርሀን ልጆች ወደ ብርሃን ክርስቶስ ይመጣሉ፤ በቅዱስ ስሙ ያምናሉ፤ አርአያነቱንም ይከተላሉ፡፡
ክፉዎች አይሁድ ጌታን የሰቀሉት የጨለማ ሥራቸው እንዳይገለጥ ነበር፡፡ ዛሬም አንዲሁ ነው፡፡ የጨለማ ሥራቸው እንዳይገለጥ የሚፈልጉ ነውረኞች እውነተኞችን ሲያሳድዱ ይኖራሉ፡፡ የሕይወት ባለቤት፣ የብርሃን አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአርአያነትና ለቤዛነት ከመጣ ከእኛ የሚጠበቀው በፍጹም ፍቅር በተሞላ የአባትና የልጅ ፍርሃት ሆነን ለእርሱ መገዛት ነው፡፡