ዐቢይ ጾም
ዲያቆን ፍቅረሚካኤል ዘየደ
የካቲት ፳፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
ዐቢይ ማለት ታላቅ የከበረ ማለት ሲሆን ዐቢይ ጾም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ በገዳመ ቆሮንቶስ ዐርባ መዓልትና ዐርባ ሌሊት ከቆመ ሳያርፍ ከዘረጋ ሳያጥፍ በትኅርምት የጾመው ታላቅ ጾም ነው፡፡ በተለይም የዲያብሎስን ሦስቱን ፈተናዎች ውድቅ ያደረገበት፤ በፍቅረ ንዋይ የመጣውን በጸሊዐ ንዋይ በትዕቢት የመጣውን በትሕትና በስስት የመጣውን በቸርነት ድል ያደረገበትም ነው፡፡ (ማቴ. ፬፥፩)
በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን እኛም ጾሙን አምላክ ወልደ አምላክን አብነት አድርገን ፈቃደ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍስ አስገዝተን እንጾመዋለን፡፡ ይህ ጾም ብዙ ስያሜዎች አሉት፤ ጾመ ሁዳዴ ይባላል፤ በጥንት ዘመን ገባሮች ለባለርስቱ የሚያርሱት መሬት ሁዳድ (እርሻ) ይባል እንደነበር ዐቢይ ጾምም ሕግን የሠራ ክርስቶስ ስለጾመው ምእመናንም ይህን በማሰብ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ የሚጾሙት በመሆኑ ስያሜውን አግኝቷል፡፡
አንድም የቀድሶተ ገዳም ጾም ይባላል፡፡ ነቢዩ ኤልያስ እና መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ሌሎችም አበው የኖሩትን የብሕትውና ኑሮ ጌታችን ለባሕታውያን እና ለመነኰሳት ባርኮ ስለሰጠ ከከተማ ርቆ ከሰው ተለይቶ በገዳም ከአራዊት ጋር ኑሮ ፀብአ አጋንንትን ድምጸ አራዊትን ታግሠው ለሚኖሩ ዛሬ ላሉት መነኰሳት አብነት ይሆን ዘንድ ጾሙን በምድረ በዳ በገዳም ቆሮንቶስ አድርጎታል፡፡
ንጹሐ ባሕርይ የሆነው አምላካችን ጾሙን የጾመው ‹እቀደስ፣ እከብር፣ እነጻ› ብሎ ሳይሆን ክብር ምስጋና ይግባውና ሁሉን ማድረግ ሲችል መምህረ ትሕትና በመሆኑ አርአያውን ሊተውልን ራሱን ዝቅ አደረገ፡፡ እኛንም ወደ እርሱ በፍቅር ይስበን ዘንድ አስቀድሞ ወደእኛ መጣ፡፡ መጥቶም ረኀባችንን ተርቦ፣ ድካማችንን ደክሞ፣ ፈተናችንንም ተፈትኖ ድል ያደረገበት ጾም ነው፡፡
ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው ለዐቢይ ጾም ሰንበታት የተለየ መዝሙር ሠርቶላቸዋል፡፡ ሰንበታቱም በመዝሙሩ ስም ዘወረደ፣ ቅድስት፣ ምኵራብ፣ መጻጒዕ፣ ደብረ ዘይት፣ ገብርኄር፣ ኒቆዲሞስ እና ሆሳዕና በመባል ይጠራሉ፡፡ የበረከት እና የዕረፍት ዕለታት በመሆናቸው ከሥጋ ሐሳብ እና ሥራ ተለይተን በእግዚአብሔር ቃል በጸሎትና በዝማሬ ተግተን ለእግዚአብሔር ምስጋና የምናቀርብባቸው ሳምንታት ናቸው፡፡
በዐቢይ ጾም ተድላ እና ደስታ ማድረግ አይገባም፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያን የጥሉላት ምግብ (ወተት ሥጋ እንቁላል) እንደሚተው ሁሉ ከሥጋዊ ነገርም መጠበቅ መጠንቀቅም ይገባዋል፡፡ ቅዱስ ያሬድ በዜማው ‹‹ይጹም ዓይን፤ ይጹም ልሳን፤ ዕዝንኒ ይጹም እምሰሚዐ ኅሱም በተፋቅሮ ንንበር በሰላም ዓይን ክፉ ነገርን ከማየት፣ አንደበት መጥፎ ነገር ከመናገር፣ ጆሮም ክፉ ነገርን ከመስማት ይጹም ይከልከል፤ እርስ በርስ በመዋደድ በሰላም እንኑር›› በማለት ጾሙን በፍቅር በአንድነት መጾም ክፉ ነገርን ከማየት፣ ከመስማት፣ ከመናገርም መከልከል እንዳለብን አስተምሮናል፡፡ ዳግመኛም ስለጾም በተናረበት ሌላኛው ክፍል፤ ‹‹ጾም ትፌውስ ቊስለ ነፍስ ወታጸምም ኵሎ ዘሥጋ ፍትወታተ ትሜህሮሙ ጽሙና ለወራዙት፤ ጾም የነፍስን ቁስል ታድናለች፤ የሥጋ ፍትወታትንም ታስታግሣለች (ታቀዘቅዛለች)፡፡ ለወጣቶችም አርምሞን ጽሙናን ታስተምራለች›› ብሏል፡፡ ይህ ወቅት በደላችንን እያሰብን፣ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሲል የተቀበለውን መከራ በዓይነ ልቡናችን እየሳልን፣ በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደትና ምጽዋት ከፈቲው ከሰይጣን ጾር ለመጠበቅ ብርቱ ተጋድሎ የምናደርግበት ነው፡፡ ይልቁኑም የኃጢአታችንን ሥርየት የምናገኝበትን ዘለዓለማዊውን ሕይወት የምንወርስበትን የጌታችንና የአምላካችንን የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የምንቀበልበት ታላቅ ሱባዔ ነው፡፡ (ጾመ ድጓ እና ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ)
ዘወረደ
የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ እሑድ ዘወረደ ይባላል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ከሰማይ እንደወረደ እንዲሁም አዳምንና ልጆቹን ከሞት ለማዳን መምጣቱን የሚያመለክት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የሰው ዘርን አዳምን ለማዳን ከሰማይ መውረዱንና በመስቀል መሰቀሉንም ያወሳል፡፡
ሊቁ ቅዱስ ያሬድም ስለ ዐቢይ ጾም የመጀመሪያው እሑድ በጾመ ድጓው ድርሰቱ ሲገልጽ ‹‹ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ ወሚመ ኢያእመሩ እግዚአ ኵሉ ዘያሐዩ በቃሉ፤ አዳምን ለማዳን ከሰማይ የወረደውን አምላክ አይሁድ ሰቀሉት፤ የሰማይ ሥልጣን ያለው የሁሉ ጌታ እንደሆነም ምንም አላወቁም›› ማለት ነው፡፡
የመጀመሪያው ሳምንት ‹‹ጾመ ሕርቃል›› ተብሎም ይጠራል፡፡ በባይዛንታይኑ ንጉሥ በሕርቃል ስም ተሰይሟልና፡፡ የዚህም ምክንያቱ በእርሱ ዘመነ መንግሥት ፋርሶች ኢየሩሳሌምን በመውረር የጌታችንን መስቀል ወሰዱ፡፡ ንጉሡም ወደ ፋርስ ሄደ መስቀሉን ለማስመለስ ሊዋጋቸው ተነሣ፤ የሀገሩ ሕዝብም ‹‹አንተ ጠላታችንን አጥፋልን፤ መስቀሉን አስመልስልን እንጂ የአንድ ሰው ዕድሜ ቢበዛ ሰባ፣ ሰማንያ ዓመት ነው፡፡ ጾሙን አምስት አምስት ቀን ተከፋፍለን እኛ እንጾምልሃለን›› ብለው ጾመውለታል፡፡ ንጉሡም በጦርነቱ ድል አድጎ መስቀሉን ወደ ኢየሩሳሌም አስመልሶታል፡፡
በዚህም መሠረት የዚህን ዋጋ የተገነዘቡት ሁሉ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያለማቋረጥ ጾመውታል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጾም እንዲሁ ‹‹ጾመ ሕርቃል›› እያለች ታውጃለች፡፡
ነቢዩ ኢዩኤል ‹‹ቀድሱ ጾመ ወስብኩ ምሕላ…፤ ጾምን ያዙ፤ አጽኑ፡፡ ምሕላንም ዐውጁ፡፡ ሸማግሌዎቹን ከፈጣሪያችን ቤት ሰብስባችሁ በአንድነት ሆናችሁ ወደ እግዚአብሔር ጩኹ(ለምኑ)›› በማለት የጾምን ታላቅነት ተናገሯል፤ ይህን ጾም የምንጾመው ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጹሞ እንድንጾም አርአያነቱን እንድናይ የሠራልን የጾም ሥርዓት ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህም ጾሙን በአንድነት በፍቅር ሆነን ስለ ኃጢአታችን ሥርየት፣ ስለሀገራችን ሰላም፣ ስለሰማይ ጠል፣ ስለምድር በረከት፣ ስለ ሰው ልጆች ሁሉ ፍቅር፣ ስለሚራቡትና ስለሚጠሙት፣ ስለተሰደዱትና በጽኑ አገዛዝ በጭንቅ ስለአሉት ሁሉ፣ በጽኑ ደዌ በአልጋ ቊራኛ ስለተያዙት ወደ እግዚአብሔር ልንጮኽ፣ በምሕላም ወደ ቤቱ ልናሳስብ ይገባል፡፡ (ኢዩ. ፲፪፥፲፭-፲፮)
የጾምን አስፈላጊነት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹በምትጾሙበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትኹኑ፤ ስለ ጽድቅ የሚራቡ የሚጠሙ ንዑዳን ክብራን ናቸው›› ብሎ በተናገረው ቃል እንረዳለን፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ወኩኑ ላእካነ ለእግዚአብሔር በጾም ወበንጽሕ፤ በጾምና በንጽሕና ተወስናችሁ እግዚአብሔርን አገልግሉ›› ብሏል፡፡ (፪ቆሮ.፮፥፬-፮)
ቅዱሳን ሐዋርያት ከጌታችን ሞትና ትንሣኤ እንዲሁም ዕርገት በኋላ ጾመው የጾምን ሕግም መሥረተውልናልና እንደ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደዚሁ እኛም በተገቢው ሥርዓት ልንጾመው ይገባል፡፡ (ማቴ.፭፥፮-፲፮)
አምላካችን እግዚአብሔር ጾሙን በሰላም አስጀምሮ ያስጨርሰን፤ አሜን፡፡
ይቆየን
ምንጭ፡- ‹‹ጾምና ምጽዋት›› በዲያቆን ቃኘው ወልዴ