“ወበ እንተዝ ኢየኃፍር እግዚአብሔር ከመ ይትበሃል አምላኮሙ”
(ክፍል 2)
ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም.
በቀሲስ ይግዛው መኰንን
4. ሰማያዊውን ሕይወት ናፋቂዎች ስለሆኑ
ክቡር ዳዊት âበቤትህ የሚኖሩ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው፤ ለዓለምና ለዘለዓለምም ያመሰግኑሃል፡፡ አቤቱ እርዳታው ከአንተ ዘንድ የሆነለት በልቡም የላይኛውን መንገድ የሚያስብ ሰው ምስጉን ነው፡፡â በማለት ሰማያዊውን መናፈቅ እንደሚያስመሰግን በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ተናገረ፡፡ መዝ. 83፥4
ቅዱስ ጳውሎስም የሚጠበቅበትን አገልግሎት ካከናወነ በኋላ âልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፤ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤â በማለት ምድራዊ ያይደለ ሰማያዊ ሕይወት ምን ያህል እንደሚናፈቅ ገልጿል፡፡ ፊል.1፥23 ለዚህ ነው ቅዱሳን በሥጋ የምኞት ፈረስ እንዲጋልቡ፥ በኃጢአት ባሕር እንዲዋኙ፥ በክፉ አሳብ ጀልባ እንዲቀዝፉ የሚፈታተናቸውን ርኩስ መንፈስ በመልካም ሥራቸው በመቃወም ድል የሚያደርጉት፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ âለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ፡፡â በማለት የአሁኑን ችግርና ፈተና ከሚመጣው ጋር በማመዛዘን የተናገረው፡፡ ሮሜ.8፥18
ቅዱስ ኤፍሬምም በውዳሴ ማርያም ጸሎቱ âሰማዕታት በእውነት የዚህን ዓለም ጣዕም ናቁ፤ ስለ እግዚአብሔርም ሲሉ ደማቸውን አፈሰሱ፤ ስለመንግሥተ ሰማያትም ሲሉ መራራ ሞትን ታገሡ፡፡â በማለት የዚህን ዓለም መከራ መታገሥ ሰማያዊውን ክብር በማስታወስና የሚገኘውን ዋጋ በማመን እንደሆነ ገልጿል፡፡ /የሐሙስ ውዳሴ ማርያም/ ለዚህም ነው ሰማእታት እሳቱን ስለቱን፣ ጻድቃን ግርማ ሌሊቱን፥ ጽምፀ አራዊቱን፣ ጸብአ አጋንንቱን ታግሰው ሥጋቸውን ለነፍሳቸው አስገዝተው የኖሩበት ዐቢይ ምሥጢር፡፡
ሰማዕታት የሚታሰሩበትን ገመድ፣ የሚሰቀሉበትን ግንድ ይዘው ወደ ሞት ሲነዱ ጻድቃንም አስኬማቸውን ደፍተው፣ ደበሎአቸውን ለብሰው፣ ከምግበ ሥጋ ተለይተው ርሃቡን ጥሙን ችለው ሲኖሩ ደስ ይላቸዋል፡፡ ምክንያቱም ከፈጣሪያቸው እንደሚያገኙ ያውቃሉና ነው፡፡ መሬት ፊቷን ወደ ፀሐይ ስታዞር ብርሃን እንደምታገኝ፣ ፊቷን ስትመልስ ደግሞ ጨለማ እንደሚሆን ሳይንሱ ይነግረናል፡፡ የሰው ልጅም ፊቱን ወደ እግዚአብሔር ካዞረ ብርሃን ይሆንለታል፤ ፊቱን ከፈጣሪው ካዞረ ግን ይጨልምበታል፡፡ ኑሮው፣ ትዳሩ፣ መንገዱ ሁሉ የተሳካ እንዲሆን፣ የውስጥ ሰላምን እንዲያገኝ፣ በሚያገኘው ተደስቶ እንዲኖር፣ ሰላም፣ ጤና በረከት ከቤቱ እንዳይርቁ፣ አሸሼ ገዳሜ በሉ፣ አይዟአችሁ ጨፍሩ የሚለውን የጥንት ጠላት የአጋንንት ስብከት በመልካም ሥራ በዝማሬ በማኅሌት በሰዓታት በቅዳሴ፣ በኪዳን ተጠምዶመቃወም ያስፈልጋል፡፡
የዘወትር ስብከት âሥጋችሁ በነፍሳችሁ ላይ ትንገሥâ የሚል ስለሆነ እኛ ግን ነፍሳችንን በሥጋችን ላይ ልናነግሣት እንደ አባቶቻችን ቅዱስን ሰማያዊውን ናፋቂዎች ልንሆን ያስፈልጋል፡፡ âድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘለዓለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንፃ እንዳለን እናውቃለንና፡፡ በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና፣ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም፡፡â እንዲል፡፡ 2ቆሮ.5፥1
5. ለሌላው አሳቢዎች በመሆናቸው
ለሌላው ማሰብ፥ ለሌላው መጨነቅ፥ ከሚደሰቱ ጋር መደሰት፥ ከሚያዝኑ ጋር ማዘን፥ ችግር የወደቀባቸውን ሰዎች የችግራቸው ተካፋይ መሆን ፈጣሪን መምሰል ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ âበአንድ አሳብ ተስማሙ፣ አንድ ፍቅር፣ አንድም ልብ፣ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤ ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቁጠር፤ እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፡፡ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ፡፡
በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን፡፡â በማለት ከራስ ይልቅ ለሌላው ማሰብን እንድናስቀድም ያስተምረናል፡፡ ፊልጰ.2፥1 ታላቁ ሊቅም በሰቆቃወ ድንግል ላይ âኢየሱስ ስዱድ ተስፋሆሙ ለስዱዳን፡፡ ኢየሱስ ግፉዕ ምስካዮሙ ለግፉዓን፡፡ እግዚአብሔር ማኅደር ዘአልቦ ከመ ነዳያን..â በማለት የጌታችን መሰደድ የተሰደደውን የሰውን ልጅ ለመመለስ እንደሆነ፤ ጌታችን ያለ በደሉ የተገፋው የተገፋ የሰውን ልጅ ሊያድን እንደሆነ፤ እግዚአብሔር ተስፋ፣ ላጡ ተስፋ ማረፊያ ቤት ለሌላቸው ማረፊያ እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ይህንን ስለሚያውቁ ቅዱሳን ከራሳቸው በላይ ለሌላው ያስባሉ፡፡
âይህንን ኀጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍ እባክህ ደምስሰኝ አለ፡፡â የሚለውን የታላቁን ሰው የሙሴን ልመና ስንመለከት ምን ያህል ለሌላው ማሰብ እንደሚገባ እንማራለን ዘፀ.32፥32 ዛሬ ቢሆን ምናልባት ሌላውን ደምስሰህ እኔን ጻፍ ሳይባል ይቀራል ትላላችሁ፡፡ ቅዱሳን ግን እንደፈጣሪያቸው ለሌላው አሳቢወች በመሆናቸው âእግዚአብሔር አያፍርባቸውምâ ተባለ፡፡
ዛሬም ሰው ለድሃ እጁን ሲዘረጋ እግዚአብሔር ደግሞ የምሕረት እጁን ይዘረጋለታል፡፡ የወደቀ ባልንጀራውን ሲያነሣ እግዚአብሔር እርሱን ከወደቀበት ያነሣዋል፡፡ የተጨነቀውን ሲያጽናና፥ የተጨቆነውን ነጻ ሲያወጣ ተስፋ ለቆረጠው ሲደርስለት በእውነት ዋጋው አይጠፋበትም፡፡ ለዚህ ነው ክቡር ዳዊት âለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው፤ እግዚአብሔር ይጠብቀዋል፤ ሕያውም ያደርገዋል፡፡â በማለት ያስተማረን፡፡ መዝ. 40፥1 ስለዚህ በዘመናችን ያለውን የወገንተኝነት፥ የትዕቢትና የሥጋዊነትን አስተሳሰብና አመለካከት በወንጌል መሣሪያነት አፈራርሶና ንዶ ለራስ ነጻ በመውጣት ለሌላውም መትረፍ ያስፈልጋል፡፡ ከነዚህ ክፉ ተግባራት ካልተለየን ገና ዛሬም በጨለማ ውስጥ ስላለን እንጠንቀቅ፡፡
âልጄ ድሃውን ምጽዋቱን አትከልክለው ከሚለምንህ ከድሃውም ዓይኖችህን አትመልስ፡፡ የተራበች ሰውነትን አታሳዝን ያዘነ ሰውንም አታበሳጭ፡፡ ያዘነ ልቡናን አታስደንግጥ፣ የሚለምንህን ሰው አልፈኸው አትሂድ፡፡ የሚገዛልህ ቤተ ሰብህን አትቆጣ፤ ከድሃም ፊትህን አትመልስ፡፡â ካለ በኋላ ቀጥሎ âከሚለምንህ ሰው ፊትህን አትመልስ፤ በልቡናው አዝኖ ቢረግምህ ፈጣሪው ልመናውን ይሰማዋልና፡፡â
በማለት ምስካየ ኅዙናን፣ ረዳኤ ምንዱባን የሆነ እግዚአብሔር የድሃውን ኀዘን ሰምቶ እንደሚበቀል ይነግረናል፡፡ ሲራ.4፥2 ስለዚህ የነዚህ ቅዱሳን ልጆች የሆን እኛ ፍትሕ ተጓድሎባቸው የሚሰማቸው አጥተው የሚገባቸውን፣ ተነፍገው፣ መከበር ሲገባቸው ተዋርደው ከሰው በታች ሆነው ለሚቆዝሙ ወገኖች ፈጥነን ልንደርስላቸው ይገባል፡፡ âሳትሞት ለባልንጀራህ በጎ ነገርን አድርግ፡፡â ተብለን ተመክረናልና፡፡ ሲራ.14፥13
6. ለመከራ ራሳቸውን ያዘጋጁ በመሆናቸው
ከላይ እንዳየነው እምነታቸው በማዕበል ቢመታ የማይፈርስ እውነተኛ እምነት ስለሆነ ለመከራ አይበገሩም፡፡ ከእሳቱ ከሰይፉ ከመከራው በስተጀርባ የሚወርድላቸው አክሊለ ሕይወት ስለሚታያቸው ወደሞት ሲነዱ ደስ እያላቸው ይሄዳሉ፡፡ ራሳቸውን ለሞት ራሳቸውን ለስቅላት፣ ራሳቸውን ለእንግልት አዘጋጅተው በሃይማኖት ስለሚኖሩ፣ ፈጣሪ ያዝንላቸዋል፡፡ ደስ ይሰኝባቸዋልም፡፡ ያለ መከራ ዋጋ እንደማይገኝም ስለሚያውቁ âአቤቱ ቅጣኝ ነገር ግን እንዳታዋርደኝ በመጠን ይሁን እንጂ በቁጣ አይሁን፡፡â እያሉ ድሎትን ሳይሆን መከራ ሥጋን ይለምናሉ፡፡ ኤር.1፥24 ሥጋ ሲጎሰም ለነፍስ እንደሚገዛ ይረዳሉ፡፡
âከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል መከራ ወይስ ጭንቀት ወይስ ስደት፣ ወይስ ረሃብ ወይስ ራቁትነት፣ ወይስ ፍርሃት፣ ወይስ ሰይፍ ነውን âስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፣ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጥረንâ ተብሎ እንደተጻፈ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ግን በወደድን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን፡፡ ሞት ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ ግዛትም ፍጥረትም ቢሆን፣ በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ፡፡â የሚለው የቅዱስ ጳውሎስም ትምህርት የሚያስተምረው ራስን ለመከራ ማዘጋጀትን ነው፡፡ ሮሜ.8፥35
ገበሬ ብርዱን፣ ዝናቡን፣ ፀሐዩን ታግሦ እሾሁን ነቅሎ መሬቱን አለምልሞ ተክል የሚተክለውና ከበቀለም በኋላ የሚኮተኩተው የሚያርመው ፍግ እያስታቀፈ የሚንከባከበው ውኃ እያጠጣ፣ ፀረ ተባይ መድኀኒት እየረጨ ከተባይ የሚጠብቀው፣ ቅጥር ምሶለት፣ አጥር አጥሮለት ከእንስሳት የሚያስጠብቀው በአጠቃላይ ብዙ የሚደክምለት መልካም ፍሬን ለማግኘት ነው፡፡ እንዲህ ከለፋ በኋላ አመርቂ ውጤት ቢያገኝ በልፋቱ ይደሰታል፡፡ በሚቀጥለውም ከመጀመሪያው የበለጠ እንክብካቤ ያደርግለታል፡፡ ካልሆነ ግን ያዝናል፡፡ ተክሉ ፍሬ አልባ ቢሆን ወይም ደግሞ ጣፋጭ ፍሬን እየጠበቀ መራራ ፍሬን ቢያፈራ ከማዘንም አልፎ እንዲቆረጥ ያደርገዋል፡፡ ዮሐ.15፥5፣ ማቴ.21፥18
ሰውም የእግዚአብሔር ተክል ነው፡፡ በቃለ እግዚአብሔር በምክረ ካህን ተኮትኩቶ በረድኤተ እግዚአብሔር አጥርነት ተጠብቆ የሚኖር የእግዚአብሔር የእጁ ሥራ ነው፡፡ ታዲያ ይህንን ስለሚያውቁ ቅዱሳን መልካም ፍሬን አፍርተው በመገኘታቸው እግዚአብሔር ተደስቶባቸዋል፡፡
ፍሬአቸው መራራ የሆኑ ተክሎች /ሰዎች/ ጨለማን ተገን አድርገው ሰው አየን አላየን ብለው ኀጢአትን የሚፈጽሙትን ያህል በእግዚአብሔር ቤት የተተከሉ፣ ፍሬአቸው ያማረ ቅዱሳን ጨለማው ሳይከለክላቸው ጽድቅን ሲሠሩበት ያድራሉ፡፡ በዓለም ላይ ለ5 ሺሕ 5 መቶ ዘመናት ኀጢአት በዓለም ላይ ነግሦ ይኑርም እንጂ በዚህ ኀጢአት በነገሠበት ዘመን ጽድቅን ሲሠሩ የኖሩ አባቶችና እናቶች ነበሩ፡፡ ዛሬም ኀጢአት በዓለማችን ላይ ጠፍንጎ ይዞ እያስጨነቀን እንዳለ ብንረዳም የነዚህ የቅዱሳን አበው በረከት ያደረባቸው በየገዳማቱ ወድቀው ለጽድቅ ራሳቸውን ሲያስገዙ እንመለከታለን፡፡
ማጠቃለያ
አንድን መንፈሳዊ ሥራ መጀመር ብቻውን የጽድቅ ምልክት አይደለም፡፡ ከላይ ያየናቸው የቅዱሳን ሕይወት ጽድቃቸው ከሰውም አልፎ በእግዚአብሔር የተመሰከረላቸው ከመጀመሪያው ይልቅ መጨረሻቸው በማማሩ ነው፡፡ ጀምረው ያቋረጡማ የሚነገርላቸው ማቋረጣቸው እንጂ ጽድቃቸው አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው ሳጥናኤል የመላእክት አለቃ ነበር፡፡ አርዮስ ካህን፣ ይሁዳ ከሐዋርያቱ ጋር ተቆጥሮ የነበረ፣ ዴማስ ከአርድዕተ ክርስቶስ ከነ ሉቃስ ጋር ተደምሮ የነበረ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ታዲያ እነዚህ ሰዎች የጀመሩትን መንፈሳዊ አገልግሎት ችላ ማለታቸው ከሰማይ ወደ ምድር፣ ከክብር ወደ ውርደት፣ ከሹመት ወደ ሽረት፣ ከማግኘት ወደ ማጣት ተወረወሩ እንጂ ምን ጠቀማቸው? በትናንት ማንነት ብቻ ድኅነት አይገኝም፡፡ ዛሬ የማያሳፍር ሥራን መሥራት እንጂ፡፡
ትናንት ዘመነኞች፣ ቅንጦተኞች፣ ኩሩዎች፣ የነበሩ ነገሥታት ወመኳንንት ዛሬ የት አሉ? በሀብታቸው የሚኩራሩ፣ በሥልጣናቸው የሚንጠራሩ፣ ፊታቸውን ከፈጣሪ ያዞሩ ሁሉ ጊዜ አልፎባቸው ገንዘባቸው፣ ሥልጣናቸው፣ ወገናቸው አላድናቸው ብሎ በጸጸት አለንጋ ከመገረፍ ውጪ ምንም አላገኙም፡፡ ስለዚህ ከዚህ መማር የዘመኑ ትውልድ ድርሻ ነው፡፡ በሃይማኖት ቁመው ከተጠቀሙት በሃይማኖት የመቆምን ጥቅም፣ ወድቀው ከተጎዱት የመውደቅን አስከፊነትና ጉዳት መማር እንችላለን፡፡
ስለዚህ ቆም ብለን ራሳችንን እንመርምር፡፡ በየመሥሪያ ቤታችን የምንሠራው ሥራ ሰውንና እግዚአብሔርን የሚያስደስት ነው ወይስ የሚያሳዝን፣ በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ በተለይ በሐዲስ ኪዳን âከአሁን በኋላ ባሮች አልላችሁም፣ ልጆች ብያችኋለሁ፡፡â በማለት ያቀረበውን ፍጹምም የወደደውን የሰው ልጅ እንዴት እያየነው ነው? እውነት የምንሠራው ሥራ አሳፋሪ ነው ወይስ የሚያስደስትና የሚያስከብር? የሚለውን ጠይቀን ለራሳችን ምላሽ ልንሰጥ ያስፈልጋል፡፡ ያለ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ መልካምን ማድረግም አይቻልምና ለመልካም ሥራ እንዲያነሣሣን ኃይሉን ብርታቱንም እንዲሰጠን መልካም ፈቃዱ ይሁንልን፡፡