ወርኃ ጳጉሜን
ነሐሴ ፳፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
የሰው ልጅ እግዚአብሔር አምላኩ ባደለው ሥጦታ ‹ጊዜ› በሕይወት ዘመኑ በበጎ ምግባር እንዲኖርና በጸሎት በጾም እንዲተጋ በዓመታት፣ በወራት እና በቀናት ምልልስ በሚያገኘው ዕድል ዘወትር ፈጣሪውን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሊሠራ እንዲገባ የጊዜ ጭማሪ ተደረገለት፡፡ ይህችም የጭማሮ ጊዜ እስከ ዕድሜው(ዘመኑ) መጨረሻ ከኃጢአት በሙሉ ይነጻ እንዲሁም ጸጋ በረከትን ያገኝ ዘንድ የቀናት ምርቃት ሆነችለት፤ ‹የጳጉሜን ወር› (ወርኃ ጳጉሜን) ተብላም ተሰየመች፡፡
ወርኃ ጳጉሜን እንደሌሎቹ ወራት ፴ ቀናት ሳይሆን በአራት ዓመት አንዴ ማለትም በዘመነ ዮሐንስ ስድስት ቀናት ሲኖራት በዘመነ ማርቆስ፣ በዘመነ ሉቃስና በዘመነ በማቴዎስ ደግሞ አምስት ቀናት ብቻ ይኖራታል፤ ነገር ግን የዓመቱ ዐሥራ ሦስተኛ ወር ተደርጋ ትቆጠራለች፡፡
ጳጉሜ የሚለው ስያሜ ‹‹ኤፓጉሜኔ›› ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም ‹‹ጭማሪ›› ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ መዝገበ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገብ ቃላት፤ ገጽ ፱፻፭)
ወርኃ ጳጉሜን ካሳለፍነው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት፣ ከዘመነ ክረምት ወደ ጸደይ መሸጋገሪያ በመሆኗ የዓለም ፍጻሜ መታሰቢያ ተደርጋም ትታሰባለች፡፡ ዳግም ምጽአት ከምድራዊ ሕይወት ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት መሸጋገሪያ ናትና፡፡ ጳጉሜን የክረምት ማብቂያ እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም እንዲሁም የዚህ ዓለም ኑሮ ማብቂያ ናት፡፡ ወርኃ ጳጉሜን አዲሱን ዓመት ለመቀበል የዝግጅት ጊዜ እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም ጻድቃን አዲሲቷን ምድር (መንግሥተ ሰማያትን) ለመውረስ የበቁትን ‹‹እናንተ በ የአባቴ ብሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ›› የሚባሉባት ዕለት ናት፡፡ በዚህም የተነሣ ብዙ ምእመናን በወርኃ ጳጉሜን በጾምና በጸሎት ይተጋሉ፡፡ የጳጉሜ ጾም ከሌሎቹ የዓመቱ አጽዋማታችን መካከልና የዓመቱ መደምደሚያ ጾማችን በመሆኗ ብዙዎች በዚህ ወቅት ሱባኤ ይገባሉ፡፡ (ማቴ.፳፭፥፴፬)
ከዚህም ጋር ተያይዞ በቅዱስ ሩፋኤል ዓመታዊ በዓል በጳጉሜን ሦስት ሰማያት የሚከፈቱበት (ርኅዎተ ሰማይ) በመሆኑ በዚህች በተከበረችው ዕለት ምእመናን ጸሎታቸው ያርግላቸው ዘንድ ከምን ጊዜውም በበለጠ ተግተው ይጸልያሉ፡፡ በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን የእኛም ጸሎታችንን በምልጃቸው የሚያሳርጉልን ቅዱሳን መላእክትም መሥዋዕቱን የሚያሳርጉበትና የአምላካችንን ምሕረት ቸርነት ለሰው ልጆች የሚያወርዱበት ዕለት ነው፡፡
ከፈቃድ አጽዋማት መካከል አንዱ የሆነውም ‹ጾመ ዮዲት (የዮዲት ጾም)› በዚህ በጳጉሜን ወር የምንጾመው ነው፡፡ ዮዲት በናቡከደነጾር ዘመነ መንግሥት ትኖር የነበረች ስትሆን በንጽሕና ተጠብቃ፣ በጸሎትና በሕገ እግዚአብሔር የምትኖር ሴት ነበረች፡፡ የፋርስ ንጉሥ ናቡከደነጾር በሠራዊቱ ተመክቶ ጠላት አጥፋ ድንበር አስፋ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበልህ ያላመነውን እያሳመንህ ና ብሎ ለጦር አበጋዙ ሆሎፎርኒስ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ እርሱም እንደታዘዘው በኃይላቸው የታመኑ ፲፪ ሺህ እግረኞችንና በፈረስ የተቀመጡ ፲፪ ሺህ ጦረኞችን እየመራ ዘምቶ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበለ ያላመነውን እያሳመነ ብዙ ሀገሮችን እያጠፋ ሲሄድ ከአይሁድ ከተማ ደረሰ፤ በዚህም ብዙ ጥፋት በመድረሱ የእስራኤል ልጆች አለቀሱ፡፡ በዚያን ጊዜ ንጉሡ ሥልጣኑን መከታ በማድረግ የእግዚአብሔርን ሕዝብ በግድ እያስገደደ እጅ መንሻ ይቀበል ነበር፡፡ የመንግሥቱን ትእዛዝ ያልተቀበለውንም እየገደለ፣ ጭፍሮቹ ኃያልነቱንና ገናናነቱን በአዋጅ በጦር አዛዦች ጭምር እያሳወጀ፣ በርካታ የጦር ሠራዊቶችን አሰልፎ ከአይሁድ ከተማ ገባ፡፡ በዚያም ነዋሪዎችን በማስፈራራት የመንግሥቱን ትእዛዝ ያልተቀበሉትን ሁሉ እያሳደደ ስላስጨነቃቸው ማቅ ለብሰው፣ አመድ ነስንሰውና ድንጋይ ተንተርሰው ወደ ፈጣሪያቸው በመጮህ መለመን ጀመሩ። በጭካኔ የተሞላው የጦር አበጋዙ ሆሎፎርኒስም ይበልጥ እጅግ እንዲሠቃዩ ውኃ የሚቀዱበትን ስፍራ ተቆጣጠረው፤ በግዴታ ማርኮም እጅ እንዲሰጡ እንዳደረጋቸው በመጽሐፈ ዮዲት ላይ ተጽፏል፡፡ በአካባቢው ይኖር የነበረ ዖዝያን የተባለ አንድ ሰው የአባቶቻቸው አምላክ ጸሎታቸውን እንዲሰማቸው ለአምስት ቀናት በትዕግሥት ይጾሙና ይጸልዩ ዘንድ ሕዝቡን መከራቸው፤ እነርሱም በትዕግሥት ሊጠብቁ ተስማሙ፡፡ (ዮዲ. ፪፥፪-፳፰፣፬፥፲፫)
ሕዝበ እስራኤል የናቡከደነጾርን ጦር ተዋግተው ለመርታት ካልሆነ ግን እጅ ለመስጠት ተመካከሩ። ነገር ግን ዮዲት እግዚአብሔርን የምትፈራ ብቸኛዋ ሴት እርሷ ነበረችና ምክክራቸውን ስትሰማ ለምን «እግዚአብሔር ያድነናል አትሉም» ብላ ገሠጸቻቸው፡፡ ማቅ በመልበስ፣ አመድ በመነስነስና ድንጋይ በመንተራስም ሱባኤ ገባች። በሦስተኛው ቀንም እግዚአብሔር አምላክ ሕዝቧን የምታድንበትን ጥበብ ገለጸላት፤ ዮዲትም እግዚአብሔር የሰጣትን ውበት ተጠቅማ ሕዝቧን ከጥፋት የምትታደግበትን ጥበብ ተረዳች። (ዮዲ. ፱፥፲፫)
በአልባሳትም ተሸልማ፣ ሽቱ ተቀብታና ተውባ የጠላት ሠራዊት ወዳሉበት የጦር ሰፈር በድፍረት ተጓዘች፡፡ ሠራዊቱም ውበቷን አይተው እጅግ በመደነቅ «ይህችስ ለአለቃችን ትገባለች» ተባብለው ከጦር መሪያቸው ዘንድ ወሰዷት። ዮዲትም ቀድማ ከጠላቷ ማምለጫ መንገድ አዘጋጅታ ስለነበር የሠራዊቱ አለቃ ወደ ነበረበት ሥፍራ ከገባች በኋላ «ክቡር ጌታዬ ሆይ ርስት ተወስዶብኛል፤ እንድትመልስልኝ አስቀድሜ ደጅ ልጠና መጥቻለውና ርዳኝ፤ ትብብርህ አይለየኝ» ብላ ጠየቀችው፡፡ የሠራዊቶቹ አዛዥም በዝሙት መንፈስ ታውሮ ስለነበር የጠየቀችውን እንደሚፈጽምላት ነገራት። ዮዲትም ባማረ ድንካን አስቀመጣት፤ በእግዚአብሔር ረዳትነትም ጥበቧንም ተጠቅማ ማምለጫዋን አዘጋጀች፡፡ (ዮዲ. ፲፥፳፫፣፲፩፥፳፫)
ዮዲትም ለቀናት በድንኳኑ ከተቀመጠች በኃላ የሠራዊቱ አበጋዝ የምሳ ግብዣ አዘጋጅቶ ከጎኑ አስቀመጣት፤ ከበሉና ከጠጡ በኋላም ሁሉን ሰው አስወጥቶ እልፍኙን በመዝጋት ከእርሷ ጋር ብቻውን ቀረ፤ ነገር ግን እንቅልፍ ጣለው፡፡ በዚያን ጊዜም ዮዲት ወደ አምላኳ በመጸለይ ፈጣሪዋ እንዲረዳት ለመነች። ከዚህ በኋላ የሠራዊቱን አለቃ ከራስጌው ሰይፉን በማንሣት አንገቱን ቀላችው፤ በድኑንም ከመሬት ጣለችው። የሆሎፎርኒስን ሞት ሠራዊቱ በሰሙ ጊዜም በያሉበት ተበተኑ። እስራኤላውያንም ከሞት ተርፈው በእግዚአብሔር ኃይል ድል አደረጉ፤ በደስታም ፈጣሪያቸውን አመሰገኑ። (ዮዲ. ፲፪፥፪፣፲፫፥፳)
ዮዲት ጠላቷን ለማጥፋት የቻለችው በጾምና በጸሎት በመትጋት እንዲሁም በእግዚአብሔር አምላክም ኃይልና ብርታት ነው፡፡ ስለዚህ እኛም ሰዎች ጥንተ ጠላቶታችንን ለማሸነፍ በወርኃ ጳጉሜን ፈጣሪያችንን በጾም በጾሎት ተግተን ልንማጸነው በፈቃድ እንጾማለን፡፡
ጠንካራዋ ሴት ዮዲት ጠላቶቿን ድል ያደረገችው ሱባኤ በመግባት በጸሎትና በጾም በመትጋት በመሆኑ ይህንን ታሳቢ በማድረግ እንደ እርሷ ሱባኤ ገብተን፣ ማቅ ለብሰን፣ አመድ ነስንሰንና ድንጋይ ተንተርሰን አብዝተን ልንጾምና ልንጸልይ ይገባል፡፡ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ሰላም፣ ፍቅርና አንድነትን አሳጥቶ፣ እርስ በርስ አጣልቶ እንዲሁም ከክብራችን አዋርዶ ወደ ዘለዓለማዊ እሳት ሊጥለን ዘወትር ይቃጣልና ሳንታክት መጸለይና መጾም ይገባናል፡፡
ወርኃ ጳጉሜን በመልካም ሥነ ምግባር ታንጸን በሃይማኖት ጸንተን፣ ለዘመነ ማርቆስ እንድንደርስ አምላካችን እግዚአብሔር ይርዳን፤ አሜን።