ክብረ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
ጥቅምት ፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
በምድረ በዳ እንደመላእክት የኖሩትና በዝቋላ ተራራ ባለው ባሕር ውስጥ ፻ (መቶ) ዓመት ተዘቅዝቀው ለኢትዮጵያ ሰዎች ምሕረትን የለመኑት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቃል ኪዳን የተቀበሉበት ዕለት በሀገራችን ኢትዮጵያ በድምቀት ይከበራል፡፡
አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሀገራቸው ንሂሳ ግብጽ ነው፡፡ አባታቸው ስምዖን እናታቸው አቅሌስያ ይባላሉ፡፡ ልጅ አጥተው ፴ (ሠላሳ) ዘመን ሲያዝኑ ኖረዋል፡፡ አንድ ቀን አቅሌሲያ ቤተ እግዚአብሔር ገብታ ከሥዕለ ሥላሴ ሥር ወድቃ ስትማጸን ክብሩ ከሰማይ ከፍታ የሚበጥ ልጅ እንኪ ተቀበይ የሚል ድምጽ ሰማች፡፡ ‹‹ሥልጣኑ ከሰማይ ከፍታ ከፍ የሚል ንጽሕናው ከሚካኤል ከገብርኤል የሚተካከል ክህነቱ እንደ መልከጼዴቅ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ እንደ ነቢይ ኤልያስ የሆነ ልጅ እንቺ ተቀበይ›› አላት፡፡ አቅሌስያም በመጋቢት ፳፱ ቀን ፀንሳ በታኅሣሥ ፳፱ ቀን ደም ግባቱ እጅግ የሚያምር ወንድ ልጅ እንደወለደች መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በሰው አምሳል መጥቶ ‹‹የዚህ ልጅሽ ስሙ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ይሁን›› አላት፡፡ ወዲያውም ሕፃኑ ተነሥቶ ከእናቱ ጭን ወርዶ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ሦስት ጊዜ ሰገደ፡፡ ዳግመኛም ‹‹ከጨለማ ወደ ብርሃን ለአወጣኸኝ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን›› አለ፡፡
ከዚህም በኋላ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ መጋቢት ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ተፀንሰው ታኀሣሥ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ተወለዱ፡፡ አባታችን ዓይን በገለጹ ጊዜ ከሚታይ ነገር ላይ እንዲያርፍ እርሳቸውም በተወለዱ ጊዜ ተነሥተው «ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ ዘዓውፃእከኒ እምጽልመት ውስተ ብረሃን» ብለው አመስግነዋል። ቅዱስ አባታችን ለአምላካቸው ሰግዶ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ካመሰገነ በኋላ እናታቸው አላቀፈቻችውም፤ ጡትም አልጠቡም፡፡
ሦስት ዓመት ሲሞላቸው እግዚአብሔር አምላክ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን እንዲህ ብሎ አዘዘው፡- ‹‹ሕፃኑን ከእናቱ ክንድ ተቀበል፣ ብዙ ገዳማውያን ወዳሉበት ገዳም ውሰድና ከበራቸው አስቀምጠው፤ አበ ምኔቱንም ሕፃኑን ከበር አንሥተህ ካንተ ዘንድ አኑረው፤ ስለ ልብሱ ስለ ምግቡ አታስብ፤ ሕፃኑ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ነውና ምግቡም መንፈሳዊ ነው፡፡ ይኸውም ከእግዚአብሔር የሚወጣ ቃል ነው፤ ሰው በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር ዕወቅ በለው›› በማለት አዘዘው፡፡ ብርሃናዊው መልአክ የራማው ልዑል ቅዱስ ገብርኤልም እንደታዘዘው ከሰማይ ወርዶ ሕፃኑን ከእናቱ ክንድ ወስዶ በክንፎቹ አቅፎ ስሞ እስከ ሰባቱ ሰማይ አውጥቶ በሥሉቅ ቅዱስ ፊት አቅርቦት አስባረከው፡፡ እግዚአብሔርም መልአኩን ‹‹ወደ እናቴ ወደ ማርያም ውሰደውና ትባርከው›› አለውና ወስዶት እመቤታችንም ባረከችው፡፡
ዳግመኛም ከአዳም ጀምሮ ሄሮድስ በግፍ እስካስፈጃቸው ሕፃናት ያሉት ሁሉም ቅዱሳን ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት፣ ደናግልና መነኮሳት ሁሉም እንዲባርኩት አደረገው መልሶ ከእግዚአብሔር ፊት አቆመው፡፡ መድኅን ጌታም ሕፃን ገብረ መንፈስ ቅዱስን ‹‹በመንግሥቴ ከእኔ ጋር ትነግሣለህና ደስ ይበልህ፣ በርታ የሚደርስብህን ሁሉ ታገሥ ብዙ ነፍሳት በአንተ ምክንያት ይድናሉ፤ ሰላሜ ከአንተ ጋር ይሆናል›› አለው፡፡ ከዚህም በኋላ መልአኩ አባ ዘመደ ብርሃን ወዳለበት ገዳም አወረደውና ሕፃኑን ከበር ላይ አስቀምጦ እርሱ ወደ ውስጥ ገብቶ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉን ነገረው፡፡ አባ ዘመደ ብርሃንም ሕፃኑን አስገብቶ በእንክብካቤ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሁሉ እያስተማረ አሳደገው፡፡ ሕፃኑም ትምህርቱን በጨረሰ ጊዜ ዲቁና ተቀብሎ እንደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ጸጋንና ሞገስን የተመላ ሆነ፡፡ ፍጹም የእግዚአብሔር ጸጋ አድሮበታልና ሥራው ሁሉ በዕውቀት የተመላና የተቃና ሆነ፡፡ አባ ዘመድ ብርሃንም በሕፃኑ ላይ ያደረበትን ጸጋ እያየ እጅግ ደስ ይለው ስለነበር እንደ ቅዱስ እንጦንስ አስኬማን ሰጠው፡፡ ከዚህም በኋላ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቅስናን ተቀበሉና በጾም በጸሎት ተጠምደው በታላቅ ተጋድሎ መኖር ጀመሩ፡፡ እንደ ሐዋርያትም የተአምራትና የፈውስ ሀብት ተሰጣቸውና ድውያንን የሚፈውሱ፣ ሙታንን የሚያነሡ፣ አጋንንትን የሚያወጡ ሆኑ፡፡
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ዳግመኛ ተገልጦላቸው ወደ ሰማይ አሳረጋቸውና ከእግዚአብሔር ፊት አቆማቸው፡፡ ያን ጊዜም ጌታችን ክቡራን የሆኑ እጆቹን ዘርግቶ ከባረካቸው በኋላ ‹‹በጸሎትህ ከሲኦል የምታወጣቸው ብዙ ነፍሳት አሉ፤ ድውያንንም ትፈውሳለህ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ከሰው ተለይተህ ወደ ጫካ ገብተህ ከአንበሶችና ከነብሮች ጋር ኑር›› አላቸው፡፡ አባታችንም ጌታችንን ‹‹የሰጠኸኝ እነዚህ አንበሶችና ነብሮች ምን ይመገባሉ?›› አሉት፡፡ ጌታችንም ‹‹የረገጥከውን መሬት ይልሳሉ በዚያም ይጠግባሉ፡፡ ወደ እኔም እስክትመጣ ድረስ ይኸው ምግብ ይሆናቸዋል›› አላቸው፡፡ ቅዱሳን መላእክትም ይህንን በሰሙ ጊዜ ደስ አላቸው፡፡ ጌታችንም መልአኩን ወደ ቀደመ ቦታቸው ይመልሳቸው ዘንድ አዘዘው፡፡ ከዚህ በኋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ከራሳቸው እስከ እግራቸው ድረስ ጠጉር በቀለላቸው፡፡ የጠጉራቸውም ርዝመቱ አንድ ክንድ ከስንዝር ነው፡፡ አባታችንም በታላቅ ተጋድሎ ሲኖሩ በጸጋ ላይ ጸጋ ተጨመረላቸው፡፡ ከዕለታት በአንደዋ ቀን የፈወሳቸው ሕሙማን ብዛታቸው እልፍ ሆነ፡፡ የሀገሩ ሰዎችም ሥራቸውን ስላወቁባቸው አዘኑ፡፡ ‹‹ውዳሴ ከንቱ እንዳይሆንብኝ ተነሥቼ ሰው ወደማያውቀኝ አገር እሄዳለሁ›› ብለው ተነሥተው ሄዱ፡፡ ሕዝቡም አባታችን እንደተሰወሩ ባወቁ ጊዜ በኀዘን አለቀሱ፡፡
ከዚህም በኋላ አባታችን ወደ ጫካ ገብተው ብቻቸውን የበጋውን ሐሩር የክረምቱን ቁር ታግሠው ምንም ልብስ ሳይለብሱ ራቁታቸውን ሆነው በተጋድሎ ኖሩ፡፡ ከጽኑው ተጋድሎአቸውና ከጫካው ቅዝቃዜ የተነሣ ሰውነታቸው አልቆ ከአጥንታቸው ጋር ተጣበቀ፡፡ ፍራፍሬም ሆነ ምንም ነገር አይመገቡም፤ ውኃም ፈጽሞ አይጠጡም ነበር፡፡ አባታችን በምድረ በዳ እንደሰው ሳይሆን እንደመላእክት ኖሩ፡፡ ቅዱሳን መልእክትም ዘወትር ይጎበኟቸው ነበር፤ ስለምግባቸውም ሰማያዊ ኅብስት አምጥተው ይሰጧቸዋል፡፡ ነገር ግን አባታችን ያንን ኅብስት አይመገቡትም፤ ይልቁንም ጽዋውን ባሸቱት ጊዜ እንዲሁ ይጠግባሉ፤ ይረካሉ፡፡
አባታችን በተወለዱበትም ቤት አልኖሩምና እናት አባታቸው የሥጋ ዘመዶቻቸውም አላወቋቸውም፡፡ በበረሃ ብቻቸውን ኖሩ እንጂ፡፡ ነገር ግን ሰማያውያን ሁሉ ወዳጆቻቸው ሆኑ፤ እመቤታችን ወዳጄ ትላቸዋለች፡፡ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ወገናችን ይሏቸዋል፡፡ መላእክትም ወዳጃችን እያሉ በክንፋቸው ያቅፏቸዋል፡፡ የአባታችን መዓዛቸው ጫካውን ይሞላው ነበር፡፡ በመንፈስ ቅዱስም ኃይል ወደፈለጉት ቦታ በፍጥነት እንደወፍ ይበራሉ፡፡ ስለተሰጣቸውም ጸጋ የበረሃ እንስሳት (አንበሳና ነብር) ሁሉ ያገለግሏቸዋል፡፡ አባታችን ሁልጊዜ እንዲህ ይሉ ነበር፡- ‹‹የሚጣፍጥ ምግብን መውደድ ኃጢአትን ያመጣል፣ ሞትን ያስከትላል፡፡ ክንፍ ያላቸው የሰማይ ወፎች እንኳን በመብል ምክንያት ይጠመዳሉ፣ ምግብ በመሻት ከምድር ላይ ይወድቃሉ በወጥመድም ይያዛሉ፡፡ የሰው ልጅም ምግብን በመውደድ በኃጢአት ይወድቃልና እኔስ ለሰውነቴ ምግብ መጠጥን አልፈልግም፤ ልብስም አልሻም ዕራቁቴን ከእናቴ ማኅፀን እንደወጣሁ እንዲሁ ዕረቁቴን ወደ መቃብር እመለሳለሁ እንጂ፡፡ ከዚህ ከኃላፊው ዓለም በሞት በተለየሁ ጊዜ መብል መጠጥንና ልብስን ማን ያስከትልልኛል?›› አሉ፡፡ ዳግመኛም ‹‹ሰው ሊደርስ በማይችልበት በረሃ እኖራለሁ፣ ነጣቂ ተኩላዎችና አራዊቶች ባሉበት እነርሱ እንዲበሉኝ ሥጋዬን እጥላለሁ፤ ዳዊት በመዝሙር ‹‹የጻድቃን ሥጋቸው ለዱር አራዊት ነው›› እንዳለ እኔ ክፉ አውሬዎች፣ ተናዳፊ እባቦችና ዘንዶዎች ወዳሉበት እገባለሁ ምግብም እሆናቸው ዘንድ እወዳለሁ›› በማለት አባታችን ራሳቸውን ለሞት አሳልፈው ይሰጡ ነበር ነገር ግን አራዊቱ ሁሉ እየሰገዱላቸው ይገዙላቸው ከእግራቸውም በታች ይተኙ ነበር፡፡ እንደሚታዘዝ ደቀ መዝሙርም ይታዙላቸው ነበር፤ ለጸሎትም በሚቆሙበት ጊዜ አብረዋቸው ይቆማሉ፡፡ በፊታቸውም ይጫወታሉ፡፡ በአንደኛው ዕለት አባታችን ጸሎታቸውን እንደጨረሱ ሰማይ ተከፍቶ የእሳት ድንኳን ተገልጦ አርባእቱ እንስሳ የእግዚአብሔርን ዙፋን ተሸክመው ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይ ማዕጠንት ይዘው፣ ቅዱሳን መላእክትና አለቆቻቸው በየነገዳቸው በዙሪያው ቆመው ጌታችን ለአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በአንድነት በሦስትነት እንዳለ ተገለጠላቸው፡፡ አባታችንም ይህንን ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተውና ደንግጠው መሬት ላይ ወደቁ፡፡ ጌታችንም ካጸናቸውና ካበረታቸው በኋላ ‹‹ዮሐንስ ቀለምሲስ እኔን እንዳየኝ አንተም እኔን ማየት የምትችልበትን ኃይል እሰጥሃለሁ፤ ወዳጄ ሆይ ምን ትሻለህ? የምትጠይቀኝስ ነገር ምንድነው? ልይህ ብለህ በለመንከኝ ጊዜ ተገልጥኩልህ፡፡ ሰማንያ ዓመት በጫካ ኖርክ፤ በረሃዎችን ዞርክ፤ ከአንበሶችና ነብሮች ከአራዊትም ጋር መኖርን አልፈራህም፤ ጨክነህ እስከ ሞት ድረስ ታገሥህ፡፡ የመረጥኩህ ወዳጄ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሆይ! ምን አደርግልህ ዘንድ ትወዳለህ?›› አላቸው፡፡ አባታችንም ይህንን ቃል ከጌታችን ሲሰሙ ‹‹አምላኬ ሆይ ይህን ልታደርግልኝ አይገባኝም፡፡ በፊትህስ ሞገስን ካገኘሁ የገቦታን ሰዎች ማርልኝ፤ እነርሱ ኃጥአን ናቸውና አንተ ንስሓን ለማይሹ ጻድቃን አልመጣህምና ኃጥአንን ወደ ንስሓ ልትመልስ ነው እንጂ›› አሉት፡፡ ዳግመኛም ‹‹አቤቱ እንደ ክረምት ውኃ እንባቸውን እያፈሰሱ ጥርሳቸውን እያፋጩ በደይን የሚኖሩትን አስባቸው፤ ሰይጣን አስቷቸዋልና፤ በማወቅ ባለማወቅ በሠሩት ማራቸው፤ ይቅር በላቸው›› እያሉ ለመኑት፡፡ ጌታችንም ‹‹ወዳጄ ሆይ የለመንከኝን አልከለክልህም፣ እንደቸርነቴም ስምህን የጠሩትን መታሰቢያህን ያደረጉትን ኃጥአንን ምሬልሃለሁ፤ የለመንከኝንም ሁሉ አደርግልህ ዘንድ ቃል ኪዳንን ሰጥቼሃለሁ›› አላቸው፡፡ አባታችንም እጅግ ደስ ብሏቸው በግንባራቸው መሬት ላይ ወድቀው ጌታችንን ሲያመሰግኑት ቅዱሳን መላአክትና ሰማያውያን ቅዱሳን ሁሉም አብረው ተደስተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡
አባታችንም ይህንን ቃልኪዳን ሲቀበሉ ዕድሜአቸው ፫፻ (ሦስት መቶ) ዓመት ነበር፡፡ ጌታችንም የመላእክት አለቆችን ‹‹ስለ ወዳጄ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ምልጃ ወደ ገሃነም ሂዱና የኃጥአንን ነፍስ አውጡ፤ ከእስራታቸውም ፍቱአቸው›› አላቸውና እነርሱም የገቦታ ሰዎችን ሦስት ሺህ ነፍሳት ከደይን አውጥተው ወደ ገነት አገቧቸው፡፡ ዳግመኛም እግዚአብሔር አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ‹‹እንደ አንተ ካሉት ሰዎች በቀር በዓለም ያሉ ሰዎች እንዳያውቁህ አደርጋለሁ፤ መላእክት ይጎበኙሃል እንጂ ከካህናት፣ ከመነኮሳት፣ ከምእመናንም ወገን ቢሆን ምንም ያለ ፈቃድህ አያይህም፡፡ ወደጄ ሆይ እንደ ወደድህም እኔን አባቴንና መንፈስ ቅዱስን በሦስትነቴ አየኸኝ፡፡ አሁንም ወደ ኢትዮጵያ ሂድ፤ በዚያም ከደይን የምታወጣቸው ነፍሳት አሉ›› አላቸው፡፡ አባታችንም ‹‹አምላኬ ሆይ ወደዚያች አገር ማን ያደርሰኛል?›› አሉት፡፡ እግዚአብሔርም ‹‹እኔ በሥልጣኔ አደርስሃለሁ›› ካላቸው በኋላ ከእርሳቸው ተሰወረ፡፡
አባታችንም የገቦታ ሰዎች ምሕረትን ሲያገኙ አይተው እጅግ ተደሰቱ፡፡ በሌላም ጊዜ አባታችን አራት ሺህ እልፍ እየሰገዱ፣ ፫፻ (ሦስት መቶ) ጊዜ የቀኝ ፫፻ (ሦስት መቶ) ጊዜ ደግሞ የግራ ፊታቸውን በድንጋይ እየመቱ፣ መዝሙረ ዳዊትን እየደገሙ፣ ፲፭ቱን መኅልየ ነቢያት፣ መኅልየ ሰለምንንና ውዳሴ ማርያም እየጸለዩ ለኃጥአን ምሕረትን ሲለምኑ ዕንባቸው እንደ ውኃ ይፈስ ነበር፡፡ ጌታችንም ‹‹በተወለድሁባት፣ በተጠመቅሁባትና ከሞት በተነሣሁባት ዕለት እልፍ እልፍ ነፍሳትን እምርልሃለሁ›› አላቸው፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን ስድሳ አንበሶችና ስድሳ ነብሮች እየተከተሏቸው ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ መጡ፡፡ ብርሃናዊው መልአክ ቅዱስ ገብርኤልም ከእነዚሁ ተከታዮቻቸው ጋር በነፋስ ሠረገላ ጭኖ ምድረ ከብድ አደረሳቸው፡፡ ዳግመኛም ‹‹ደብር ቅዱስ›› ወደሚባለው ወደ ዝቋላ ወሰዳቸው፡፡ አባታችንም በውኃው ዳር ቆመው ምሥራቁን፣ ምዕራቡን፣ ሰሜኑን፣ ደቡቡን በመለከቱ ጊዜ የኢትዮጵያ ሰዎች ኃጢአታቸው በፊታቸው የተገለጠ ሆነ፡፡ ሰው የገዛ ፊቱን በመሥታወት እንደሚያይ የኃጥአንም ሥራቸው በአባታችን ፊት እንዲሁ የተገለጠ ነውና፡፡ አባታችንም የኢትዮጵያን ሰዎች ኃጢአታቸውን በግልጽ በተመለከቱ ጊዜ ተወርውረው ወደ ባሕሩ በመግባት ተዘቅዝቀው መጸለይ ጀመሩ፡፡ ‹‹ከባሕር እንዳልወጣ፣ በእግሬም እንዳልቆም በሕያው ስምህ ምያለሁ›› ብለው ዐርባ መዓልት ዐርባ ሌሊት ቆዩ፡፡ በ፵ኛ ቀናቸው የታዘዘ መልአክ መጥቶ ‹‹ስምህን የጠራ መታሰቢያህን ያደረገውን እምርልሃለሁ ብሎሃል›› አላቸው፡፡ አባታችንም መልአኩን ‹‹መላ ኢትዮጵያን ካልማረ ከዚህ ባሕር አልወጣም›› አሉት፡፡ መልአኩም ከእሳቸው ተለይቶ ከሄደ በኋላ አባታችን በዚያ ባሕር ውስጥ መቶ ዓመት ተዘቅዝቀው ሲጸልዩ ኖሩ፡፡ አባታችንም በባሕሩ ውስጥ ተዘቅዝቀው መቶ ዓመት ሲጸልዩ ከኖሩ በኋላ ደማቸው ፈሶ አለቀና ውኃው ደም መሰለ፡፡ ሥጋቸውም አልቆ አጥንቶቻው እንደበረዶ ሆኑ፡፡ ሰባት ሺህ እልፍ ሦስት መቶ የሚሆኑ አጋንንትም ከአራቱም አቅጣጫ እየመጡ ሰውነታቸውን በፍላፃዎቻቸው ይወጓቸው ነበር፡፡
ጌታችን መጥቶ ከባሕሩ ዳር በመቆም ‹‹ወዳጄ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሆይ! መላ ኢትዮጵያን ምሬልሃለሁና ተነሥ ከባሕሩ ውጣ›› አላቸው፡፡ አባታችንም አጥንታቸው እንደመርፌ ቀዳዳ ተበሳስቶ ፈጽመው ደክመው ነበርና ጌታችን በክቡራን እጆቹ ሁለንተናቸውን ቢዳስሳቸው እንደቀድሞው ደህና ሆኑ፡፡ ጌታችንም ከባረካቸው በኋላ ወደ ምድረ ከብድ እንዲሄዱ ነገራቸው፡፡ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ምድረ ከብድ እንደደረሱ እንደ ዓምድ ተተክለው ሰባት ዓመት ቆመው ጸለዩ፡፡ በዚህም ጊዜ ሰይጣን በቁራ ተመስሎ መጥቶ ሁለት ዐይኖቻቸውን አንቁሮ አጠፋቸው ነገር ግን አባታችን ጸሎታቸውን ሳያቋርጡ ሁለት ሳምንት በጸሎት ቆዩ፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል መጥተው በዐይኖቻቸው ላይ እፍ ብለው ብርሃናቸውን ከመለሱላቸው በኋላ አባታችንን ‹‹ከሰማይ ፍጹም ኃይል ይሰጥሃልና ጠላቶችህን ትበቀል ዘንድ ወደ ዝቋላ ሂድ›› ብለዋቸው ዐረጉ፡፡
አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስም እንደታዘዙት ወደ ዝቋላ እየሄዱ ሳለ በመንገድ ላይ ከዛፍ ሥር ያረፉ ሦስት ሽማግሌዎችን አገኙ፡፡ አባታችንም ባዩአቸው ጊዜ ለመሰወር ቢያስቡም ሽማግሌዎቹ ግን ይመጡ ዘንድ ጠሯቸውና ‹‹በእግዚአብሔር ዙፋን ተማጽነናል ሦስታችንንም በጀርባህ አዝለህ አንድ አንድ ምዕራፍ ሸኘን›› አሏቸው፡፡ አባታችንም ሽማግሌዎቹን በቀረቧቸው ሰዓት ሽበት የከበባቸው የደከሙ ሽማግሌዎች ሆነው አገኟቸው፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን አንደኛውን ሽማግሌ አዝለው ከአንድ ምዕራፍ አደረሷቸው፡፡ ያም ሽማግሌ ‹‹ከዚህ አሳርፈኝ፣ አንተ ደክመሃል የማትበላ የማትጠጣ ነህና›› አሏቸው፡፡ አባታችንም ‹‹አባ የት ያውቁኛል?›› አሏቸው፡፡ ሽማግሌውም ‹‹አሁን ደግሞ ሄደህ ጓደኞቼን አምጣልኝ›› አሏቸው፡፡ አባታችንም የቀሩት ሁለቱ ሽማግሌዎች ካሉበት ደርሰው ሁለቱንም በየተራ እያዘሉ የመጀመሪያውን ካደረሱበት ቦታ አደረሷቸው፡፡ ከዚህም በኋላ እነዚያን ሽማግሌዎች ‹‹አባቶቼ ሆይ! ከየት ነው የመጣችሁት?›› አሏቸው፡፡ ሦስቱም ሰዎች ተነሥተው ቆሙና ለአባታችን በአንድነት በሦስትነት ተገለጡላቸው፡፡ አንድ ሲሆኑ ሦስት ሦስት ሲሆኑ አንድ ሆኑ፡፡ ሥሉስ ቅዱስ ለአብርሃም በመምሬ አድባር ሥር በአንድነት በሦስትነት እንደተገለጡለት ሁሉ አሁንም ለአባታችን ለገብረ መንፈስ ቅዱስ በአንድነት በሦስትነት ተገለጡላቸው፡፡ በጀርባቸውም አዘሏቸው፡፡ የእግዚአብሔርንም ክብር ስላዩ አባታችን ፊታቸው እንደፀሐይ አበራ፡፡ ቅዱሳን መላእክት ወርደው እንደሻሽ ተነጥፈው ሲያመሰግኑ ሰማይና ምድር ተነዋውጠው ተራሮች ኮረብቶች ዓለቶች ተሰነጣጠቁ፡፡ በዚያችም ሰዓት ታላቅ ፍርሃት ሆነ፡፡ አባታችንም ዙሪያቸውን በከበባቸው በምሥጢራት ጎርፍ ተውጠው ተንቀጥቅጠው በግንባራቸው ወደቁና እንደ በድን ሆኑ፡፡ በራእይ ውስጥም ሆነው እነዚያ ሽማግሌዎች አባታችንን እስከ ሰባተኛው ሰማይ እንዳደረሷቸው ተመለከቱ፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ሐዋርያትን እንደ ቅዱስ ጴጥሮስን እንደቀሰቀሳቸው አባታችንንም ቀሰቀሳቸውና ‹‹ወደ ዝቋላ ውረድ መቶ ዓመት ሙሉ አጥንትህን ሥጋህን እየነደፉ የተዋጉህን አጋንንት ታጠፋቸው ዘንድ፡፡ እነሆ እኔ እንደወሰድኩህ ባለማወቃቸው በትዕቢት ላይ ናቸውና ‹‹በባሕር ውስጥ አለ›› ይሉሃል፡፡ ሰባቱ ሊቃነ መላእክት ይረዱሃል፤ መባርቅትም በፊት በኋላ ይከተሉሃል›› አላቸው፡፡ ያንጊዜም አባታችን በመብረቅ ላይ ሆነው እነዚያ አጋንንት ወዳሉበት ወረዱ፡፡ አጋንንቱንም ደመናት ከበቡአቸው፣ መላእክትም በእሳት ሰይፍ መተሩአቸው፣ በመብረቅ አጨዷቸው፤ አመድ ሆነው በነፋስ በተኗቸው፡፡ የእነዚያም አጋንንት ቁጥራቸው ሰባ ሺህ እልፍ ከአንድ ሺህ ነበር፡፡ ሁሉም በአንድ ጊዜ አልቀዋልና ከእነርሱ ሸሽቶ ያመለጠም አልነበረም፡፡ ሰባቱ ሊቃነ መላእክትም ወደ ሰማይ ዐረጉ፡፡ አባታችንም አንበሶችና ነብሮች፣ ድብና ዘንዶ ወዳሉበት ምድረ ከብድ ተመለሱ፡፡
አባታችንም ወደ ምድረ ከብድ ከተመለሱ በኋላ መንፈስ ቅዱስ የጠራቸው ሦስት ቅዱሳን ሁሉም በየአንበሶቻቸው ላይ ተቀምጠው ወደ ምድረ ከብድ መጡ፡፡ እነዚህም ቅዱሳን የዋልድባው አቡነ ሳሙኤል፣ የአዘሎው አቡነ አንበስ እና ከላዕላይ ግብፅ ተነሥቶ የመጣው አቡነ ብንያም ናቸው፡፡ ነገር ግን አባታችን እነዚህን ቅዱሳን ስለተሰወሯቸው ቅዱሳኑ እስከ ሰባት ቀን ድረስ በምህላ ሰነበቱ፡፡ የአባታችን የሚያስፈሩ አንበሶች ወጥተው የቅዱሳኑን አንበሶቻቸውን ገድለው ደማቸውን አፍስሰው ሥጋቸውን በሉ፡፡ ሦስቱም ቅዱሳን በዚህ ፈጽመው ደንግጠው ሳለ አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስ ፷ ነብሮችንና ፷ አንበሶችን አስከትለው ተገለጡላቸውና ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን የእግዚአብሔር ቅዱሳኑ አትፍሩ›› አሏቸው፡፡ ቅዱሳኑም ‹‹አባታችን ሆይ! ጸሎትህ ቅድስት እንደሆነች ባወቅን ጊዜ በእግዚአብሔር ፈቃድ እንባረክ ዘንድ ወደ አንተ መጣን፡፡ ነገር ግን ባላገኘንህ ጊዜ እስከ ሰባት ቀን አለቀስን›› አሏቸው፡፡ ዳግመኛም ‹‹የእርስዎም አንበሶች መጥተው አንበሶቻችንን በሉብን›› አሏቸው፡፡ አባታችንም አንበሶቻውን ‹‹እስከ ዕለተ ሞቴ ድረስ በእግሬ ከረገጥኩት ምድር በቀር እግዚአብሔር ያላዘዛችሁን ለምን በላችሁ? አሁንም የበላችሁትን ትፉ›› አሏቸው፡፡ እነዚያም አንበሶች አፋቸውን ከፈቱና የበሉትን የአንበሶቹን ሥጋቸውን አጥንታቸውን ከደም ጋር ተፉ፤ በሆዳቸውም የቀረ የለም፡፡ አባታችንም ወዲያው ወደ ምሥራቅ ዞረው እግዚአብሔር ካመሰገኑ በኋላ ‹‹አቤቱ አልዓዛርን ያስነሣኸው አንተ ነህና አሁንም እነዚህን አናብስት ከሞት አስነሣቸው፤ ለባሮችህም የድካማቸውን ማረፊያ ይሆኑላቸው ዘንድ የሰጠሃቸውን አትከልክላቸው…›› እያሉ ጸለዩ፡፡ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ብለው ጸሎታቸውን ከጨረሱ በኋላ የአንበሶቹን ሥጋቸውን በመስቀል ምልክት ባርከው ‹‹በጌታዬ በፈጣሪዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ተነሡ›› አሏቸው፡፡ አንበሶቹም እንደ ዐይን ጥቅሻ ፈጥነው ተነሡና እንደቀድሞው ሆኑ፡፡ ለአባታችንም እጅ ነሥተውና ሰግደው የእግሩን ትቢያ ላሱ፡፡ አባታችንም ወደጌቶቻቸው መለሳቸው፡፡
እነዚህም ሦስቱ ቅዱሳን በአባታችን ላይ አድሮ ድንቅ ነገርን የሚሠራ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ የዋልድባው አቡነ ሳሙኤልም አባታችንን ‹‹አባት ሆይ በዚህች ቀን ድንቅ ሥራን አየን፤ አርአያህ የእግዚአብሔርን መልአክ አርአያ ይመስላል፤ ቅድስናህ ፍጹም ነው፤ የጸሎትህ ኃይል ሙታንን ያስነሣል፤ የተበሉ አንበሶችን ከአንበሶች ሆድ አወጣህ›› አሏቸው፡፡ ዳግመኛም አባታችን ስለ ቅዱሳኑ ምግብ ወደ እግዚአብሔር በጸለዩ ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ፋኑኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ በእጁ ሦስት ኅብስትና ሦስት ጽዋ ይዞ መጣ፡፡ አባታችንም ሦስቱን ቅዱሳን ‹‹እግዚአብሔር የሰጣችሁን ይህንን ኅብስትና ጽዋ ንሡ ብሉ ጠጡ›› አሏቸው፡፡ ቅዱሳኑም ሥራቸውን እያደነቁ በልተው ጠጥተው ጠገቡ፡፡ በማግሥቱም አባታችን ቅዱሳኑን ‹‹በሰላም ሂዱ›› ብለው መርቀው ሸኟቸውና የእግዚአብሔር ሥራ እያደነቁ ወደየበዓታቸው ተመልሰው ሄዱ፡፡
ከዚህም በኋላ ለአባታችን ጌታችን ተገልጦ ብዙ ምሥጢራትን ከነገራቸው በኋላ ወደ አረማውያን አገር ሄደው እንዲያስተምሩና የሚደርስባቸውንም መከራጭምር ነገራቸው፡፡ አባታችንም ክርስቶስን ፈጽመው ወደማያውቁት ዐረብ አገራት ሄዱ፡፡ የዐረብ ንጉሥም ብዙ ሠራዊቱን አስከትሎ ብዙ ጣዖታን አሶዞ ሲጓዝ አገኙት፡፡ በጣዖታቱ ውስጥ አድረው የነበሩ አጋንንትም አባታችንን ባዩ ጊዜ ወጥተው ሸሹ፣ጣዖታቱም ከምድር ላይ ወድቀው ተሰባበሩ፡፡ የዐረቡም ንጉሥ ‹‹አንተ ፀጉር ልብሱ ምንድነህ? ሰው ነህን?›› አላቸው፡፡ አባታችንም ‹‹አዎ እኔ ሰው ነኝ ያውም የጌታዬ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ›› አሉት፡፡ ንጉሡም መልሶ ‹‹በዚያ አይሁድ በሰቀሉት ታምናለህን?›› አላቸው፡፡ አባታችንም ‹‹አዎን እኔ በእርሱ አምናለሁ፤ አላፍርም፤ ስለእኔ የተሰቀለውን በሰው ፊት አምነዋለሁ፡፡ ስለእኔ ብቻ አይደለም ንጉሥ ሆይ ስለ አንተና ካንተ ጋር ስላሉትም ነው እንጂ፡፡ በእርሱ እመኑ የዘላለምን ሕይወት ታገኙ ዘንድ አላችሁ›› አሉት፡፡ ንጉሡም ይህንን በሰማ ጊዜ በጣም ተቆጥቶ ሠራዊቱን ሁሉ ጠርቶ በቶሎ እሳት እንዲያነዱ አዘዛቸው፡፡ የእቶን እሳቱንም ካነደዱ በኋላ ‹‹በሉ ይህንን የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ነኝ የሚለውን ፀጉረ ለባሹን አንስታችሁ ከእሳቱ ውስጥ ጨምሩት›› አላቸው፡፡ አባታችንም ንጉሡና መኳንንቱ ሠራዊቱ ሁሉ እያየአቸው ከእቶኑ እሳት ውስጥ ገቡ፡፡ ነገር ግን እሳቱ እንደ ወንዝ ውኃ ሆነ፡፡ የንጉሡም ሠራዊት ይህንን ከመለከቱ በኋላ ግማሾቹ ‹‹በዚህ ሰው አምላክ አምነናል›› አሉ፡፡ ንጉሡም ፸፯ አዛዦቹን በማዘዝ ‹‹አምነናል›› ያሉትን ሰዎች ራስ ራሶቻቸውን በሰይፍ አስቆረጣቸው፡፡
ቁጥራቸውም ዐርባ እልፍ ነበር፡፡ ንጉሡም ሰይፉን መዝዞ የአባታችንን ራስ ሊቆርጥ ተወርውሮ ወደ አባታችን ሲሄድ ወዲያው ጽኑ የመብረቅ ነጎድጓድና ንውጽውጽታ ሆነ፡፡ ጌታችንም ወደ አባታችን ዘንድ መጣ፡፡ መብረቁም በአንድ ጊዜ ንጉሡንና ሠራዊቶቹን ሁሉ አጠፋቸው፡፡ የሞቱም ሰዎች ቁጥራቸው አራት መቶ ሺህ ሆነ፡፡ አንድስ እንኳን ሳይቀር ሁሉም አለቁ፡፡አባታችንም በመብረቅ የሞቱን ሰዎች ባዩ ጊዜ ውስጣቸው በሀዘን አለቀሰ፤ ነፍሶቻቸውን የጽልመት መላእክት ወደ ገሀነመ እሳት ሲያወርዷቸው ተመልክተዋልና፡፡ በዚህም ጊዜ አባታችን ጌታችንን ‹‹እነዚህም ሰዎች ማርልኝ›› አሉት፡፡ ዳግመኛም ‹‹ሰው ስሕተተኛ ነው፣ አንተ ግን መሐሪ ይቅር ባይ ነህና በእኔ ምክንያት በእነዚህ ሰዎቸ አትፍረድባቸው… ›› እያሉ በለመኑት ጊዜ ጌታችን ተሰወረባቸውና ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ አባታችንም ወዲያው አጠገባቸው ካለው ገደል እግራቸውን በገመድ አሥረው ቁልቁል ተዘቅዝቀው ተሰቀሉ፡፡ ሰይጣንም መጥቶ ያችን ገመድ በቆረጣት ጊዜ አባታችን በገደሉ ሲወድቁ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል እንደ ዐይን ጥቅሻ መጥቶ አባታችንን አቅፎ ያዛቸውና ‹‹በእግርህ ላቁምህ/ ወይስ በራስህ ላቆምህ ትወዳለህ/›› አላቸው፡፡ አባታችንም ገብረ መንፈስ ቅዱስም መልአኩን ‹‹ተወኝ በራሴ ልቁም›› አሉትና መልአኩም በዚያው ትቷቸው ዐረገ፡፡ አባታችንም በጥርሳቸው ድንጋይ ነክሰው እስከ ፴ ዓመት ተዘቅዝቀው ሲጸልዩ ኖሩ፡፡ ናላቸው ሁሉ ፈሶ አለቀ፤ አንጀታቸውም ፈሰሰ፤ እንደ ዕንጨትም ቅርፊት ሆኑ፡፡ ከ፴ ዓመትም በኋላ ጌታችን ሰባቱን ሊቃነ መላአክትና እናቱን ቅድስት ድንግል ማርያን አስከትሎ ወደ አባታችን መጣና ሦስት ጊዜ በስማቸው ጠርቶ ‹‹እነዚያን ከሐዲዎች ምሬልሃለሁ›› አላቸው፡፡ አባታችንም ነክሰውት የነበረውን ድንጋይ በጣሉት ጊዜ ጥርሶቻቸው አብረው ተነቅለው ወደቁ፡፡ ጌታችንም በከቡራን እጆቹ ቢዳስሳቸው ሰውነታቸው ታደሰችላቸው፡፡ አባታችንም ጌታችንን ‹‹ምሬልሃለሁ ካልከኝና ከማርክልኝስ ነፍሳቸውን ከሥጋቸው ጋር አዋሕድልኝ›› አሉት፡፡ ጌታችንም አባታችንን ‹‹እንዳልክ እንደወደድክ ይሁንልህ እኔ ሙታንን ልታስነሣ ሥልጣን የሰጠሁህ አይደለምን አሁንም ወደሞቱት ሰዎች ሂድና አማትብባቸው›› አላቸውና ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ ያንጊዜም አባታችን ወደ ሞቱት ሰዎች ሄደው በላያቸው ከጸለዩ በኋላ ‹‹እናንት ሁላችሁ በጌታዬ በፈጣሪዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ተነሡ›› ቢሏቸው ሙታኑም ወዲያው አፈፍ ብለው ተነሥተው በአባታችን ፊት ቆሙ፡፡ አባታችንም ሃይማኖትን አስተምረው አጥምቀው ክርስቲያን አደረጓቸው፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን ከእነርሱ ተለይተው በመብረቅ ተጭነው ወደ ምድረ ከብድ ተመለሱ፡፡ ዳግመኛም አባታችን እነዚያን ሰዎች ይጎበኟቸው ዘንድ ወደ ዐረብ ሀገር ሄዱ፡፡
እነዚያ ከሞት አስነሥተው ክርስቲያን ያደረጓቸው ሰዎችም ሃይማኖታቸውን ጥምቀታቸውን አጽንነተው ቤተ ክርስቲያን ሠርተው በጽድቅ ሕይወት እየኖሩ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ሆነው ‹‹አምላከ ገብረ መንፈስ ቅዱስ›› እያሉ ሲያመሰግኑ ተመለከቷቸው፡፡ አባታችንም ይህንን አይተው ስለሰዎቹ መዳን ደስ ተሰኝተው ተመልሰው ወደ ምድረ ከብድ መጡ፡፡ ነገር ግን አባታችን ሄደውሄደው እንደጎበኟቸው ሰዎቹ አላወቁም ነበር፡፡ እነዚያም ክርስቲያኖች እስከዛሬ ድረስ አሉ፡፡
አባታችን ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በኢትዮጵያ ፪፻፷፪ (ሁለት መቶ ስድሳ ሁለት) ዓመት ኖረው በ፭፻፷፪ (አምስት መቶ ስድሳ ሁለት) ዓመታቸው በተስፋቸው ያመነውን በኪዳናቸው የተማጸነ ጌታ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ሊምርላቸው ተስፋቸውን ተቀብለው በዕለተ እሑድ ዐርፈዋል፡፡ መላእክት በአክናፈ እሳት ኢየሩሳሌም ወስደው በየማነ ምስዋዕ ቀብረዋቸዋል፡፡
የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፤ በጸሎታቸው ይማረን!
ምንጭ፡ – ገድለ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ ተስፋ ገብረ ሥላሴ ፲፱፻፺፪ ዓ.ም
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክብር አሜን